- ምንድነው እንደዚህ መስጦ የያዘህ ጉዳይ?
- መጡ እንዴ ክቡር ሚኒስትር፣ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያወጣውን መግለጫ እያነበብኩ ነው፡፡
- ግን እኮ ፊትህ ላይ የመገረም ስሜት ይነበባል፡፡
- አዎ፣ መግለጫው ላይ የተመለከትኳቸው አንዳንድ ነጥቦች ትንሽ አስገርመውኝ ነው፡፡
- እንዴት? የትኛው ነጥብ ነው ያስገረመህ?
- ለምሳሌ እዚህ ጋ የፓርቲው አባላት የጋራ አመለካከት እንዲይዙ በማድረግ ውጤት መመዝገቡን አረጋግጧል ይላል፡፡
- አዎ፣ ምኑ ነው የገረመህ?
- አሁን ግጭት በሚካሄድበት ክልል የፓርቲ አመራሩ የጎራ መደበላለቅ ለግጭቱ ምክንያት ነው ሲባል ነበር ብዬ ነው።
- እሱ እንዳለ ሆኖ ማለቴ ነው።
- እንደዚያ ከሆነ ጥሩ፣ ግን ደግሞ ዝቅ ብሎ በፓርቲው የአመራር ዲሲፕሊን መሻሻሉና የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም መጎልበቱ ተረጋግጧል ይላል።
- አዎ፣ ልክ ነው፡፡
- በቅርቡ ግን አንድ ከንቲባና ሌሎች ከፍተኛ የፓርቲ አመራሮች በማዳበሪያ ዝርፊያ ተጠርጥረው ዕርምጃ እንደተወሰደባቸው ተነግሮ ነበር።
- እሱ እንዳለ ሆኖ፡፡
- እንዳለ ሆኖ ሲሉ ምን ለማለት ነው?
- ችግሩ አለ ለማለት ነው ወይም…
- እ?
- ወይም ደግሞ ተገምግሟል ማለቴ ነው፡፡
- ግን አይጋጭም?
- አይጋጭም። ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት ህፀፆች እንዳይደገሙ አቅጣጫ ተቀምጧል።
- የምን አቅጣጫ?
- እንዲህ ዓይነት ችግሮችን ለመፍታት በቀጣይ የአመራር አቅም ግንባታ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል።
- ወደ መጨረሻ አካባቢ ደግሞ፣ በግብርና መስክ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተሠራው ሥራ ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል ይላል።
- አዎ፣ ልክ ነው።
- ግን በበርካታ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች አርሶ አደሩ የግብርና ሥራውን ማከናወን እንዳልቻለ ይታወቃል።
- እሱ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው።
- የአፈር ማዳበሪያም በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ማድረስ እንዳልተቻለና ይህም ከቅሬታ አልፎ አርሶ አደሩን አስቆጥቷል፣ በአንዳንድ አካባቢዎችም የተቃውሞ ሠልፍ ወጥቷል።
- እሱ እንዳለ ሆኖ።
- እንደዚያ ነው?
- አዎ፣ ችግሩ ተገምግሟል ቢሆንም የተገኘውን ስኬት የሚያደበዝዝ ሆኖ አላገኘነውም።
- እዚህ ጋ ደግሞ እንዲህ ይላል…
- ምን ይላል?
- በኢትዮጵያ ታምርት መርሐ ግብር የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች የነበሩባቸው ችግሮች ተፈትተው የማምረት አቅማቸው እንዲያድግ ተደርጓል ይላል።
- ልክ ነው።
- በዚህም ምክንያት በርካታ ባለሀብቶች ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲሰማሩ ማድረግ እንደተቻለና ምርትና ምርታማነት እንዳደገ ይገልጻል።
- ልክ ነው።
- ግን እኮ አብዛኞቹ ኢንዱስትሪዎች የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንዳልቻሉ እየገለጹ ነው።
- እሱ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው።
- በተደረገው ጥረት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካት ረገድ ትልቅ ስኬት ተመዝግቧል ይላል።
- አዎ፣ በዚህ ረገድ ትልቅ ስኬት ነው የተመዘገበው።
- እንዴት?
- ምን እንዴት አለው?
- አሁንም የምግብ ዘይት ከጂቡቲ እያስገባን አይደለም እንዴ? ስኳርስ ቢሆን ከውጭ አይደለም የሚገባው?
- እሱ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው።
- ታዲያ በአገር ውስጥ ተተኩ የተባሉት ምን ዓይነት ምርቶች ናቸው?
- ለምሳሌ አንድ ሁለት መጥቀስ እችላለሁ።
- ችግር የለም፣ እንድም ቢሆን ይበቃል።
- ለምሳሌ ዩኒፎርምን መጥቀስ ይቻላል።
- የምን ዩኒፎርም?
- የፀጥታ አካላት!
- Advertisment -
- Advertisment -