- እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል
ዕድሳቱ ከሁለት ዓመታት በላይ የፈጀው የአዲስ አበባ ስታዲየም በመጀመርያ ምዕራፍ የተደረገው የሳር ተከላ እንደገና እንዲከናወን መወሰኑ ተሰማ፡፡
ከዓመት በፊት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ፍሬንድስ ኢንጂነሪንግ ጋር የሳር ተከላውን ጨምሮ የስታዲየሙን ክፍል ዕድሳት ለማጠናቀቅ መስማማታቸውን ተገልጾ ነበር፡፡
በምዕራፍ አንድ ግንባታ የመልበሻ ክፍል፣ የመጫወቻ ሜዳ ሳር ተከላ፣ ቪአይፒና የሚዲያ ክፍሎችን ጨምሮ በ39 ሚሊዮን ብር ወጪ ለማጠናቀቅ ከስምምነት መድረሱ ተጠቁሟል፡፡
በዚህም መሠረት ሚኒስቴሩ የሳር ተከላ በአፍሪካ አብዛኛው አገሮች የሚጠቀሙት ዓይነት መሆኑ መግለጹ ይታወሳል፡፡
ሆኖም የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የስታዲየሙ የሳር ተከላ ጥራቱ የተጠበቀ አለመሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ከወራት በፊት ሚኒስቴሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳ የስታዲየሙ ዕድሳት አብዛኛው መጠናቀቁን ገልጸው፣ ለ2016 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ማስተናገድ እንደሚችል አስታውቀው ነበር፡፡
በአንፃሩ የስታዲየሙ ዕድሳት ባለመጠናቀቁና በተለይ የመጫወቻ ሜዳው ሳር በተፈለገው ደረጃ ላይ አለመገኘቱ የሊጉ ውድድር ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መዞሩ ተገልጿል፡፡
ዕድሳቱን ለማከናወን ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር ውል ያሰረው ተቋራጩ ሚኒስቴሩ የተለያዩ የሳር ዓይነቶች እንዲቀርቡለት ጠይቋል፡፡
‹‹የሳር ተከላውን ከማድረጋችን አስቀድሞ ያሉትን የሳር ዓይነቶች ለምርጫ አቅርበናል፡፡ ሆኖም ሚኒስቴሩ በቂ በጀት እንደሌለው ጠቅሶ፣ የአገር ውስጥ ሳር እንዲተከል ተመርጧል፤›› በማለት የፍሬንድስ ኢንጂነሪንግ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ቤቴልሔም አያሌው (ዶ/ር) ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
እንደ ባለሙያዋ አስተያየት ከሆነ ተቋራጩ ከአገር ውስጥ ባሻገር የተለያዩ የውጭ አገር የሳር ዓይነቶች ቢኖሩትም፣ ሁሉንም አማራጮች አቅርቧል፡፡
እንደ ሪፖርተር ምንጮች ከሆነ ከሳር ተከላው አስቀድሞ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መተከል ስላለበት የሳር ዓይነትና በካፍ ተቀባይነት ሊያስገኝ በሚችል መልኩ መሆን እንዳለበት ምክረ ሐሳብ ሲያቀርብ ነበር፡፡
በአንፃሩ ሚኒስቴሩ ቀድሞ ከነበረው የሳር ዓይነት የበለጠ ለማሻሻልና የካፍ መሥፈርትን ያሟላ ሆኖ እንዲተከል እየሠራ መሆኑን አንስቷል፡፡
‹‹የስታዲየሙ እድሳት እየተገባደደ ነው፡፡ አብዛኛው እድሳት ተጠናቋል፡፡ ሆኖም የመጫወቻ ሜዳው ሳር ደረጃውን የጠበቀና የተሻለ ለማድረግ እየሠራን እንገኛለን፤›› ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ደኤታ መስፍን ቸርነት (አምባሳደር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በዚህም መሠረት የሳር ተከላውን ለማከናወን የተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ተቋራጮች እየተሳተፉ እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፣ በቅርቡ ጨረታውን ያሸነፉት ይለያሉ ተብሏል፡፡
እንደ ሪፖርተር ምንጮች ከሆነ የሳር ተከላውን ለማድረግ የቱርክና የፈረንሣይ ተቋራጮች ስታዲየሙን ጎብኝተዋል፡፡
በአንፃሩ የታቀደው የሳር ተከላ ሰው ሠራሽ ሊሆን እንደሚችል የተጠቆመ ሲሆን፣ ይህም በካፍ ተቀባይነት የማግኘቱ ነገር አሁንም አጠራጣሪ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
እድሳቱ ተጠናቆ የዘንድሮን የፕሪሚየር ሊግ፣ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ፣ የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ፣ እንዲሁም የብሔራዊ ቡድኑ የማጣሪያ ጨዋታ ያስተናግዳል ተብሎ ነበር፡፡
ሆኖም ዕድሳቱ ባለመጠናቀቁ ምክንያት በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ እየተካፈለ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታውን በግብፅ ሜዳ ለማድረግ ተገዷል፡፡
በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች እየተዘዋወረ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታውን ሲያከናውን የሰነበተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ ዘንድሮም ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ሊገጥመው እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታ ሒደት በእንጥልጥል መቅረቱ ችግሩን ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› አድርጎታል፡፡
ከቻይናው ተቋራጭ ጋር ውሉን ያቋረጠው ሚኒስቴሩ ጨረታ ማውጣቱንና ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ተቋራጮች እየተሳተፉ መሆኑንና በቅርቡም ተቋሞቹን ለይቶ እንደሚያሳውቅ ገልጿል፡፡
ግንባታውን የጀመረው የቻይናው ኮንስትራክሽን ዲዛይን ኮርፖሬሸን ፕሮጀክቱን አስረክቦ እንዲወጣ መታዘዙ ይታወሳል፡፡