ድንች ከሌሎች የሰብሎች አኳያ ሲነፃፀር በአነስተኛ ይዞታ በአጭር ጊዜና በውስን ሀብት ከፍተኛ ምርት በመስጠት በቤተሰብ ደረጃ የምግብና የሥነ ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው የሰብል ምርት ነው፡፡
በተለይ አነስተኛ ይዞታ ላላቸው አርሶ አደሮች በግብርናው ዘርፍ የሥራ ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ያላት ተስማሚ ሥነ ምኅዳር ድንችን ለምግብና ሥነ ምግብ ዋስትና እንዲሁም ለምግብ ኢንዱስትሪ ግብዓት ከማዋል አኳያ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ለምግብና ሥነ ምግብ ዋስትና እንዲሁም ለምግብ ኢንዱስትሪ ግብዓት በመሆን የሚሰጠውን ጠቀሜታ መሠረት በማድረግ በድንች ልማት፣ ሳይንስና በንግድ ሥራ መስክ አስተዋጽኦ ለማበርከት ዘርፈ ብዙ ተቋማት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
ከእነዚህ ተቋማት መካከል መስከረም 10 ቀን 2015 ዓ.ም. የተመሠረተው የአይርሽ ድንች ምርምርና ልማት ማኅበር ተጠቃሽ ነው፡፡
የማኅበሩ መመሥረት በዋናነት በድንች ላይ የሚሠሩ የመንግሥት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ምርምር ተቋማት በማቀናጀት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ ግብ መያዙን በምሥረታው ወቅት ተገልጿል፡፡
በሆለታ የግብርና ምርምር ማዕከል የድንች ተመራማሪ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት የአይርሽ የድንች ምርምርና ልማት ማኅበር ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ገብረ መድኅን ገብረ ጊዮርጊስ፣ ሰብሉ ለአገሪቱ የምግብ ዋስትና የሚሰጠውን ጠቀሜታ በመገንዘብ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ለመሥራት ማኅበሩ መመሥረቱን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ለድንች ምርት የተሰጠው ቦታ አናሳ መሆኑን ገልጸው፣ ማኅበሩ የተለያዩ ተቋማትን በማስተባበር ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ ማቀዳቸውን ተናግረዋል፡፡
ማኅበሩ በድንች ላይ ከሚያደርገው ምርምር በተጨማሪ በአገሪቷ የሚገኙ ከፍተኛ ባለሙያዎችና ማዕከላት የምርመር ውጤቶችን ወደ ተጠቃሚዎች የማድረስ ዓላማ ማንገቡን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡
እነዚህን ተቋማት በማስተባበር በድንች ምርት በዓለም 43ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘውን ኢትዮጵያ ከትልልቆቹ ተርታ ለማሠለፍ ማቀዳቸውን ተናግረዋል፡፡
በዓመት ከ700 እስከ 800 ሺሕ ሔክታር በድንች በኢትዮጵያ ይመረታል ተብሎ የሚታሰብ ቢሆንም የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታቲክስ መረጃ ደግሞ ከ300 ሺሕ እንደማይበልጥ የሚገልጽ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ያስረዳሉ፡፡
እነዚህን መረጃዎች በማሰባሰብ ትክክለኛ ዓመታዊ የምርት መጠኑን በማስቀመጥ፣ መንግሥት የድንች ምርታማነትን ለማስፋፋት የሚያስችል በቂ መረጃ እንዲያገኝ ማኅበሩ የሚሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሔክታር 140 ኩንታል ድንች እንደሚገኝ የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ነገር ግን ምርምርና የተለያዩ ድጋፎች ከታከለበት በአንድ ሔክታር እስከ 400 መቶ ኩንታል ማግኘት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
ይህንን የምርምርና የጥራት ውጤት ወደ አርሶ አደሩ እንዴት ማስፋፋት ይችላል የሚለው ጉዳይ ላይ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ሰፊ ሥራዎች እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፣ በሽታዎችን የሚቋቋም በምርምር የተገኙ የድንች ዝርያዎችን ጎበዝ አርሶ አደሮች ካገኙ በአንድ ሔክታር እስከ 400 ኩንታል ሊመረት እንደሚችል፣ ነገር ግን በአገሪቱ አሁን ያለው የድንች ምርት በበሽታና በምርጥ ዘር እጥረት ሳቢያ ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የመንግሥት ለድንች ምርት የሰጠው ትኩረት እንደሌሎች ሰብሎች አይደለም ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ ምርቱ ዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰጠው ደረጃ ለማድረስ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
የድንች ምርት በአገር ደረጃ ለኢንዱስትሪያል ግብዓት ከመሆን አኳያ ብዙ ክፍተቶች እንዳሉት፣ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ የድንች ዝርያዎችን ለማምረት ምርምር መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከስንዴና ከሩዝ ቀጥሎ ድንች ሦስተኛ የምግብ ሰብል መሆኑን የገለጹት አቶ ገብረ መድኅን፣ ነገር ግን በኢትዮጵያ የተሰጠው ቦታ ዝቅተኛ መሆኑን የሚያመላክቱ ዓመታዊ ሪፖርቶች ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የአይርሽ ድንች ምርምርና ልማት ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋው መኩሪያ በበኩላቸው፣ ድንች ኢትዮጵያውያን ለምግብነት ከሚመርጧቸው ሰብሎች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ድንች ለምግብነት የሚውል፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓትና የሥራ ዕድል ፈጠራ የሚያስገኝ ምርት በመሆኑ፣ መንግሥት ለምርቱ ትኩረት እንዲሰጥ ግፊት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
ማኅበሩን የመሠረቱ ድርጅቶች ዘጠኝ መሆናቸውን፣ እነዚህም ግብርና ሚኒስቴር፣ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ አማራ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትና ሌሎችም አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡
የማኅበሩ ዓላማ በአገር ደረጃ ድንች ስትራቴጂክ ኮሙዲቲ ሆኖ ትኩረት እንዲሰጠውና በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማትን በፋይናንስና በዕውቀት ለማገዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ምርቱ አሁን ካለበት የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖረው ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ፈንድ በማፈላለግ፣ ድጋፍ በመስጠት፣ ከውጭ የተሻሉ የምርምር ዕውቀቶች እንዲመጡ በማድረግ የምርምር ተቋማቱ ባሉባቸው ክፍተቶች እንዲሞሉ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በግብርና ሚኒሰቴር የእርሻና ሆርቲ ካልቸር ዘርፍ የሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ አብዱልሰመል አብዱ እንደተናገሩት፣ መንግሥት የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ ይገኛል፡፡
መንግሥት ከሚያደርጋቸው ጥረቶች መካከል በርካታ ምርት ሊሰጡ የሚችሉ ሰብሎችን በዝናብና በመስኖ የማልማት ስትራቴጂ አዘጋጅቶ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የአይርሽ ድንች ማምረትና ማልማትም አንደኛውና ዋንኛው ትኩረት የተሰጠው ሰብል መሆኑን አማካሪው ገልጸው፣ ድንች በትንሽ ሔክታር ላይ ትልቅ ምርት ሊያስገኝ የሚችል በመሆኑ ትኩረት ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡
በገጠርና በከተማ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ለዕለት ምግባቸው የሚያገለግል ሰብል መሆኑን፣ መንግሥትም ለዚህ ሰብል ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
መንግሥት በርካታ ሥራዎች እየሠራ በመሆኑ ሁሉንም ሥራ በመንግሥት መሥራት ስለማይችል፣ በድንች ዝርያ ከሚሠሩ የልማት አገሮችን በማሰባሰብ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከእነዚህ ተቋማት መካከል የአይርሽ ድንች ምርምርና ልማት ማኅበር አንድ መሆኑን፣ መንግሥት የድንች ምርትና ምርታማነትን ለማስፋፋት እያደረገ ያለውን ጥረት ሊያግዝ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡