Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የውጭ ባንኮች ከገቡ ያጠፉናል የሚለው አስተሳሰብ አገራችንን ተባብረን እናጥፋ ማለት ነው›› ቆስጠንጢኖስ በርኸ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በርካታ ጫናዎች እንዳሉበት በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት ቁልፍ ችግር በመሆን ቀጥሏል፡፡ ኢኮኖሚው ያሉበትን ችግሮች ለመፍታት በመንግሥት እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎች ቢኖሩም፣ እምብዛም ውጤታቸው አይታይም ወይም ጊዜ የሚወስዱ ናቸው የሚል አመለካከት የሚያንፀባርቁ ወገኖች አሉ፡፡ ኢኮኖሚውን ለመታደግና እንደ ዋጋ ንረት ያሉ ሥር የሰደዱ ችግሮችን ለመቅረፍ መንግሥት እየወሰዳቸው ባሉ ዕርምጃዎች፣ እንዲሁም በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ዳዊት ታዬ የኢኮኖሚ ባለሙያውን ቆስጠንጢኖስ በርኸ (ዶ/ር) አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ በዋጋ ንረት ሳቢያ የሚታዩ ችግሮች ተባብሰዋል፡፡ በአገራዊ ኢኮኖሚው ላይም የራሱ የሆነ ጫና እያሳደረ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እርስዎ እንዴት ይገመግሙታል?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- ኢኮኖሚው በተለይ ከዋጋ ግሽበት አንፃር ስናየው ጥሩ አይደለም፡፡ ከ30 በመቶ በላይ የዋጋ ንረት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ አኃዝ አሁን ትንሽ ዝቅ ያለ ቢመስልም፣ የዋጋ ንረቱ በእርግጥም ኢኮኖሚው ላይ ጫና አሳርፏል፡፡ በአብዛኛው አገር ጤነኛ የዋጋ ንረት ነው ተብሎ የሚታመነው ሁለት በመቶ አካባቢ ሲሆን ነው፡፡ የዋጋ ንረት ሁለት በመቶ መሆን ኢንቨስትመንትን ያፈጥናል ተብሎ ይታመናል፡፡ ከዚህ በላይ ሲሆን ግን አስቸጋሪ ነው፡፡ በአንድ አገር ኢኮኖሚ ውስጥ አቅርቦትና ፍላጎት ካልተመጣጠነ የዋጋ ንረት እያደገ ይመጣል፡፡ በሌላ ኢኮኖሚውን በአጠቃላይ ስንመለከተው ግን በተለይ ከአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት (ጂዲፒ) አንፃር ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለው ማለት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) አኳያ ኢኮኖሚው ዕድገት አሳይቷል ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- ኢኮኖሚው ከጂዲፒ አንፃር ሲታይ ጥሩ ነው የሚባለው ብዙ አገሮች የማይደርሱበት የዕድገት ምጣኔ አለ፡፡ የዓለም ባንክና የዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እንደ  መሰከሩለት ከስድስት በመቶ በላይ እያደገ ነው ያለው፡፡ ነገር ግን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሒዩማን ዴቨሎፕመንት ኢንዲኬተር ሪፖርት ሲመዘን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ደረጃ ዝቅተኛ ነው፡፡ የጂዲፒ ምዘና የኢኮኖሚውን ጤንነት ከሕዝቡ አኳያ ሲታይ አይተረጉመውም በሚል፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሒዩማን ዴቨሎፕመንት ኢንዲኬተር በሚባል እየተዘጋጀ የሚያወጣው ነው፡፡ በዚህ ሪፖርት መሠረት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሲታይ ደግሞ ጥሩ አይደለም፡፡ የሒዩማን ዴቨሎፕመንት ኢንዲኬተር ሪፖርት ኢኮኖሚው በከፍተኛ ሁኔታ ውጥረት ውስጥ መሆኑን ያሳያል፡፡ በሒዩማን ዴቨሎፕመንት ኢንዲኬተር መሥፈርት መሠረት ኢኮኖሚው በትምህርት፣ በጤና፣ ሰዎች በሚኖሩበት አኗኗርና በሚኖሩት ዕድሜ ልክ የሚቆጠር ነው፡፡ ስለዚህ የሒዩማን ዴቨሎፕመንት ኢንዲኬተር ሪፖርት መሠረት ደረጃችን በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ባለበት፣ በየአካባቢው ከፍተኛ አለመግባባት በሚታየበት ሁኔታ ኢኮኖሚው ችግር ውስጥ መውደቁ አይቀርም፡፡ በተለይ የሰላም ዕጦቱ ሰዎች ተረጋግተው እንዳያመርቱ በማድረጉ ተፅዕኖው ጎልቶ እንዲታይ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ኢኮኖሚው ከጂዲፒ አንፃር ጥሩ ሲሆን፣ ከሰዎች ልማት ቀመር አንፃር ስናየው ግን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- አስቸጋሪ ያሉትን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወደ ትክክለኛው መስመር ለማስገባትና ለማስተካከል ምን ዓይነት መፍትሔ ያስፈልገዋል ይላሉ? መንግሥትስ እየሄደበት ያለው አቅጣጫ እንዴት ይመዘናል?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- መንግሥት የአሥር ዓመት ዕቅድ አውጥቷል፡፡ በቅርቡ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረቱን ለመቀነስ እያደረገ ያለው ጥረትም አለ፡፡ በብሔራዊ ባንክ ከተወሰደው የገንዘብ ፖሊሲ አንፃር አንዱ ዕርምጃ ባንኮች የሚሰጡትን ብድር መቀነስ ነው፡፡ የሞኒታሪ ፖሊሲውንም እየሠራበት ነው፡፡ ሞኒታሪ ፖሊሲው ገንዘብ በከፍተኛ ሁኔታ ኢኮኖሚ ውስጥ በሚዘዋወርበት ጊዜ ሰው እጅ ስለሚገባ፣ በትንሹ በሚመረቱ ቁሳቁሶች ላይ ውድድር ስለሚኖር ገንዘብ ያላቸው ሰዎች እነዚህን ዕቃዎች በመግዛት ዕቃው እንዲወደድ ያደርጉታል፡፡ አሁን ላለው የዋጋ ንረትም አንዱ ምክንያት ይኸው በመሆኑ ይህንን ለመቀነስ የተወሰደ ዕርምጃ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ የሚበደረውን ገንዘብ መቀነስና ባንኮች ለሕዝቡ የሚያበድሩትን ገንዘብ መግታትን ነው እንደ አማራጭ አድርጎ የተመለከተው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ የፖሊሲ ዕርምጃ መፍትሔ ያመጣል ይላሉ?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- ይህ የፖሊሲ ዕርምጃ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ነገር ግን የፖሊሲ ዕርምጃው በደንብ ከተሠራበት ውጤት ሊያመጣ ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሪፖርት ላይ ያላየሁት ነገር አለ፡፡ ከውጭ ምንዛሪ አንፃር ሲታይ የብር ዋጋ በጣም እያሽቆለቆለ መጥቷል፡፡ በዓመት 20 ቢሊዮን ዶላር የደረሰው ከውጭ የሚመጡ ዕቃዎች ዋጋ በብር ሲመነዘር በጣም እየተወደደ ነው፡፡ የምግብ ዘይት፣ ስኳርና የመሳሰሉት ከውጭ ይመጣሉ፡፡ ስለዚህ የብር ዋጋ እያሽቆለቆለ መምጣት ዋጋ እንዲወደድ ስለሚያደርግ ሕዝቡን ይጎዳዋል፡፡ እነዚህን ኅብረተሰቡ በየቀኑ የሚፈልጋቸውን ምርቶች ዋጋቸው እንዳይወደድ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ አንዱ ጉዳይ መንግሥት ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት ወደ ውይይት መድረክ የሚኬድበትን መንገድ መፍጠር አለበት፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ መንግሥት የጥቁር ገበያ ኢኮኖሚን ማጥፋት ወይም መቆጣጠር መቻል አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ኢኮኖሚው ከጥቁር ገበያው ጋር እየተያያዘ ነው የሚል አመለካከት ጎልቶ እየተሰማ ነወ፡፡ ጥቁር ገበያን ለማጥፋት ሊወሰዱ የሚገባቸው ዕርምጃዎች ያስፈልጋሉ የሚል ግፊትም አለ፡፡ ጥቁር ገበያን እንዴት ማጥፋት ይቻላል?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ– ይቻላል፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት መንግሥት በሦስት ዓመት ውስጥ የብር ዋጋ እንዲንሳፈፍ እናደርጋለን የሚል ዕቅድ ነበረው፡፡ ይህንን ማለቱ በሌሎች አገሮች እንደሚደረገው የውጭ ምንዛሪ ዋጋን በገበያ ዋጋ እንዲተመን ለማድረግ ነበር፡፡ የምንዛሪ ዋጋውን በትክክለኛው የገበያ ዋጋ ማስተናገድ ቢቻል፣ ሰዎች ዶላርን በሕጋዊ መንገድ ለማምጣትና ዕቃን በሕጋዊ መንግድ ለማስገባት የሚችሉበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡ አሁን እየተሠራበት ያለው ግን ከዚህ ውጪ በመሆኑ ክፍተት ይፈጥራል፡፡ ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ የሚባል ድርጅት ባወጣው ሪፖርት ደግሞ፣ በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ኢትዮጵያ ከ1.5 ቢሊዮን እስከ 3.5 ቢሊዮን ዶላር ታጣለች ይላል፡፡ ይህ የሚሆነው የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ከውጭ ለማምጣት ከዚህ በዶላር መልክ በማውጣት ነው፡፡ ይህንን ዶላር እንዴት ነው የሚያገኙት ከተባለ ደግሞ አንዱ መንገድ እዚህ ከተማ ውስጥ በጥቁር ገበያ በመጠቀም ነው፡፡ ሁለተኛ ገንዘቡን የሚያገኙት ደግሞ መንግሥት በማያውቀው በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጪ ከሚላክ ምርት ነው፡፡ ለምሳሌ ብዙ ጊዜ የሚጠቀሰው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የቀንድ ከብቶች እየተነዱ መውጣት ነው፡፡ ይህ ሕገወጥ የቀንድ ከብት የወጪ ንግድ የመንግሥት ገቢ ላይ አይታይም፡፡ ወርቅና ቡናም በተመሳሳይ በሕገወጥ መንገድ ይወጣሉ፡፡ ከእነዚህ ሕገወጥ ንግዶች የሚገኘው ገንዘብ ነው እንደገና ወደ ጥቁር ገበያው የሚመላለሰው፡፡ ይህ የኮንትሮባንድ ንግድና የገንዘብ ዝውውር አንደኛ ጥቁር ገበያውን ይመግበዋል፡፡ ሁለተኛ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በብዛት ይገባሉ፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያለውን ሕገወጥነትና ጥቁር ገበያው እያስከተለ ያለውን ጉዳት አይቶ ምንዛሪውን በገበያ ዋጋ መሠረት ማስተናገድ ይመረጣል፡፡

      በቅርቡ እንኳን አዲሱ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ሥልጣን በያዙ ማግሥት ከወሰኗቸው ውሳኔዎች አንዱ፣ የውጭ ምንዛሪ በገበያ ዋጋ ይወስን ማለታቸው ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ ሌሎች ኢኮኖሚያቸውን እያሳደጉ ነው የሚባሉት እነ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳና የመሳሰሉት አገሮች ሁሉም የውጭ ምንዛሪዎቻቸውን የሚያስተናግዱት በገበያ ዋጋ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አማራጭ ከጠፋና የዋጋ ግሽበትን ለማጥፋት እንደ አርጀንቲና ያሉ አገሮች ገንዘባቸውን አጥፍተው በዶላር ለመሥራት እየሞከሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ አገር የራሱን ገንዘብ አጥፍቶ በዶላር በመጠቀሙ የዋጋ ንረቱን ለመከላከል ይጠቅመዋል? ኢኮኖሚውን ይደግፋል?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- እንዲህ ያለው ዕርምጃቸው አጠቃላይ የዋጋ ንረቱን በአንድ ጊዜ ያጠፋዋል የሚል ሐሳብ አለ፡፡ ነገር ግን ከዚህ በፊት እነ ኢኳዶርና ቮሊቪያ የመሳሰሉ አገሮች ይህንን ሞክረውት ተግዳሮቶች እንደገጠማቸው ይነገራል፡፡ በአጠቃላይ የአገራችን የዋጋ ግሽበትን ለማስተካከልና የጥቁር ገበያውን ጫና ለማቃለል በዋናነት የውጭ ንግድ መጨመር ነው፡፡ ለምሳሌ አሥራ አንዱ የስኳር ፋብሪካዎች በዕቅዳቸው ልክ ሥራ ቢጀምሩ ኖሮ ከውጭ የሚመጣውን ስኳር በማስቀረት ከምናወጣው 500 ሚሊዮን ዶላር ባሻገር፣ የስኳር ምርቱን ወደ ውጭ ልከን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ይቻል ነበር፡፡ እንደ እነዚህ ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ለምን ሳይተገበሩ ቀሩ የሚለው ጥያቄም መልስ ያስፈልገዋል፡፡ በአጠቃላይ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ሊወሰዱ የሚገባቸው የተለያዩ ዕርምጃዎች አሉ፡፡ በአጠቃላይ ግን አገሪቱ በከፍተኛ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ነች፡፡ ትልልቅ ግድቦችን፣ መንገዶችንና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ገንብታለች፡፡ ትልልቅ ግንባታዎችን ለማከናወን አገሪቱ ከፍተኛ ዕዳ ውስጥ ገብታ ነው የሠራችው፡፡ አሁንም ዕዳውን እየከፈልን ነው፡፡ ስለዚህ የአገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ሪፖርት ላይ እንዲህ ያለውን ጉዳይ በደንብ አድርገው ጽፈውታል፡፡

ሪፖርተር፡- ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ያወጣው የገንዘብ ፖሊሲ በዋናነት የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ነው የሚል ነው፡፡ በዚህ የፖሊሲ ዕርምጃው ተፈጻሚ ይሆናሉ ብሎ ካወጣቸው ድንጋጌዎች መካከል የባንኮች የብድር ምጣኔ ከ14 በመቶ በላይ መሆን የለበትም የሚል ነው፡፡ ከሰሞኑ እየተሰማ ያለው ደግሞ ባንኮቹ የብድር ምጣኔያቸው ላይ ገደብ በመጣሉ ከዚህ የሚያጡትን ጥቅም ለማካካስ እነሱም የብድር ወለድ ምጣኔያቸውን እየጨመሩ ነው፡፡ ይህ የወለድ ምጣኔ ዕድገት መልሶ የዋጋ ንረቱን አያባብስም?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- በቅርብ የተቋቋሙት ባንኮች ካላበደሩ ሥራ መሥራት አይችሉም፡፡ እነዚህ ባንኮች ለብሔራዊ ባንክ አቤት ስለማለታቸው ሰምቻለሁ፡፡ ነገር ግን ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩልህ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲውን ነው የሚመለከተው፡፡ በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ ገንዘብ በሚሠራጭበት ጊዜ ምርትና አገልግሎቶች እኩል አይሆኑም፡፡ ገንዘቡ ይበዛና ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ደግሞ ለጥቂት ዕቃዎች ሲወዳደሩ ዋጋ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ የነጋዴው ፍላጎት ደግሞ ዋጋ መጨመር ነው፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፍሰቱን በመቀነስ የዋጋ ግሽበቱ ወደ ላይ እየናረ እንዳይሄድ ለመሞከር ነው፡፡ ለዚህ ነው የባንኮች የብድር ምጣኔ ዕድገት በ14 በመቶ ይገደብ ያለው፡፡ በዚህ ፖሊሲ ላይ ሌላው ውሳኔ ባንኮች ከብሔራዊ ባንክ የሚወስዱትን ብድር ወለድ ወደ 18 በመቶ ከፍ ያደረገበትም ምክንያት የገንዘብ ሥርጭትን ይቀንሳል በሚል ነው፡፡ የመንግሥት ወጪዎችን መቀነስ እንዳለበት ነው፡፡ ለምሳሌ ምናልባት የካፒታል ፕሮጀክቶችን ወደኋላ ገፋ ሊያደርጋቸው የሚችል ከሆነ ይህንን ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ እንደ ህዳሴ ግድብ ያሉትን ሊያቆም አይችልም፡፡ ሌሎቹን ትልልቅ የሚባሉ የካፒታል ፕሮጀክቶች እንዲቀንሱ ማድረግ ወጪውን ሊቀንስ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ጥያቄዬ ባንኮች የብድር ወለድ መጠናቸውን መጨመራቸው የዋጋ ንረቱን አያባብስም ወይ?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ዋናው የተፈለገበት ምክንያት የገንዘብ እንቅስቃሴን ለመቀነስ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ባንኮች የብድር ወለዳቸውን በጨመሩ ቁጥር የሚበደረው ሰው እያነሰ ይሄዳል፡፡ ይኼ እኮ በእኛ አገር ብቻ የሚደረግ አይደለም፡፡ በአሜሪካ እኮ ወለድ ጨምረው፣ ጨምረው የዋጋ ንረቱን ከዘጠኝ በመቶ ወደ ሦስት በመቶ አውርደውታል፡፡ ፌዴራል ሪዘርቩ በየጊዜው እየተሰበሰበ የብድር ወለዱን መጠን እስከ 5.25 በመቶ አድርሰውት ነበር፡፡ ይህም ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው የገንዘብ ዝውውር መቀነስ ሰዎች እንዳይበደሩ ማድረግ ነው፡፡ ይህም ኢኮኖሚውን ይገታል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢኮኖሚው እንዴት ይገታል?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- ኢኮኖሚው ቢገታ ይሻላል፡፡ ግን ኢኮኖሚውን ይዞ ሊጠፋ የሚችል ነገር ከሚኖር ተብሎ ነው እንዲህ ዓይነት ፖሊሲ የሚወጣው፡፡ የዋጋ ንረቱ እየጨመረ ከወጣ ለኢኮኖሚው በጣም አስቸጋሪና አዳጋች ስለሚሆን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲና ተያያዥ ዕርምጃዎች ትክክል ናቸው ማለት ነው?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- የብሔራዊ ባንክ ሥራው እኮ ይኼ ነው፡፡ የገንዘብ ፖሊሲ ማውጣትና የገንዘብ ፍሰትን መቆጣጠር ነው፡፡ አንደኛ በኢኮኖሚ ውስጥ ያለው የገንዘብ ፍሰት እንዲጨምር ወይም እንዲቀነስ፣ ሁለተኛ ወለድ ከፍና ዝቅ እንዲል ማድረግ ሥራው ነው፡፡ ባንኮች ከብሔራዊ ባንክ የሚበደሩበትን ወለድና ባንኮች ለግለሰቦችና ለኩባንያዎች የሚያበድሩት ብድር ወለድ መወሰንና የመሳሰሉት በብሔራዊ ባንክ ደረጃ የሚደረጉ ነገሮች ናቸው፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ ባንክ የራሱን ኃላፊነት ለመወጣት ነው ይህንን ሥራ የሚሠራው፡፡ የገንዘብ ፍሰቱ እንዲቀንስ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ ተግዳሮት ተደርጎ ለዓመታት ሲጠቀስ የቆየው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው፡፡ እጥረቱ አሁን የበለጠ ተባብሷል፡፡ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ኢኮኖሚው መጎዳቱ ይታመናል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ምን ዓይነት ዕርምጃ ቢወሰድ መፍትሔ ይምጣል ብለው ያምናሉ?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- ዋነኛው መፍትሔ የወጪ ንግድ ገቢን ማሳደግ ነው፡፡ እስካሁን ከነበሩ ሁኔታዎች አንፃር ስታየው የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትን ለመሸፈን የሚያስችሉ ዕድሎች ነበሩ፡፡ አገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ የውጭ ምንዛሪ ታገኝ ነበር፡፡ ከዳያስፖራው በርከት ያለ ገንዘብ ይመጣ ነበር፡፡ ወደ አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ በየዓመቱ በዕርዳታ መልክ ምዕራብያውያኑ ይሰጡ ነበር፡፡ ከዳያስፖራው ይገኝ የነበረውም የውጭ ምንዛሪ ወደ አምስት ቢሊዮን ዶላር ይደርስ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በብድርና በኢንቨስትመንት የሚመጣ የውጭ ምንዛሪ አለ፡፡ አሁን በዕርዳታ የሚመጣው ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም፣ ነገር ግን ቀንሷል፡፡ አሁን ከዳያስፖራው የሚመጣውም ወደ አራት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነው፡፡ ስለዚህ እጥረቱ አለ፣ እንዲያውም አንዳንድ የውጭ ምንዛሪ ምንጮች መነቀሳቸው ይታወቃል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ የቀነሰው እንደገና እንዲጨምር፣ እንዲሁም ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማግኘት ምን ዓይነት ዕርምጃ ያስፈልጋል? በተለይ ከፖሊሲ አኳያ ምን ዓይነት አማራጭ አዋጭ ሊሆን ይችላል?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- የዛሬ 22 ዓመት ገማ እኔ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በምሠራበት ወቅት፣ ሱዳን እንዲህ ያለ ችግር ውስጥ ስለነበረች አንድ ቡድን ይዤ ሄጄ ነበር፡፡ ሱዳን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ዳያስፖራ አላት፡፡ ሐኪሞችና ነርሶች ናቸው፡፡ በዓረብ አገሮች የማኔጅመንት ሥራ የሚሠሩ እነሱ ናቸው፡፡ ስለዚህ በርከት ያለ ገንዘብ ወደ አገራቸው ይልካሉ፡፡ የሱዳን ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛራ ዋጋን ቋሚ (ፊክሲድ ሬት) ሲያደርግ ከውጭ ይመጣ የነበረው የዳያስፖራው ገንዘብ ነጠፈ፡፡ ሲነጥፍ ምን እናድርግ ብለው በመምከር የውጭ ምንዛሪ ተመኑን በተለያየ ጉዳይ ለይተው እንዲመነዘር የሚያስችል አሠራር ዘረጉ፡፡ ለዚህም ወደ አምስት ሌቭል (ደረጃ) የምንዛሪ ዓይነት ነበር እንዲኖር ነበር ስምምነት ላይ የደረስነው፡፡ በወቅቱ የውጭ ምንዛሪ ገበያቸውን እንዲያሳድጉ ይረዳቸዋል ብለን ካስቀመጥናቸው የመፍትሔ ሐሳቦች ውስጥ አንዱ፣ ከዳያስፖራ የሚመጣውን የውጭ ምንዛሪ በገበያ ዋጋ ይመንዘር የሚል ነበር፡፡ ይህንን ማድረግ ሱዳን ውስጥ ያሉ አንድ እናት ከውጭ ካለ ልጃቸው 100 ዶላር ቢላክላቸውና ይህ 100 ዶላር በጥቁር ገበያ ዋጋ ተመንዝሮ ቢሰጣቸው ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ በዚህ ውሳኔ ብዙዎችን ይጥቅማል በሚል ተስማምተው እንዲተገበር አደረጉ፡፡ ምክንያቱም ከዳያስፖራ ገንዘብ የሚላከው ቤተሰብ ለመደጎም ነው፡፡ በዚህ ዕርምጃ መሠረት ዳያስፖራው የሚልከው የውጭ ምንዛሪ በገበያ ዋጋ ምንዛሪ እንዲካሄድ በመፈቀዱ፣ በአንድ ጊዜ ወደ ሱዳን የሚላከው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ጨመረ፡፡ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙም አስቻላቸው፡፡ በኢትዮጵያም እንዲህ ያለው አሠራር መሞከር አለበት፡፡

      ስለዚህ የዳያስፖራው ገንዘብ በቀጥታ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ማድረግ የሚቻለው፣ በጥቁር ገበያ ዋጋ ልክ ወይም በወቅቱ የገበያ ዋጋ ሲመነዘር ነው፡፡ ካልሆነ ግን አስቸጋሪ ነው፡፡ ከዳያስፖራ የሚመጣውን የውጭ ምንዛሪ በጥቁር ገበያ ዋጋ ማስተናገድ ካልተቸለ፣ አውሮፓና አሜሪካ ቁጭ ብለው የጥቁር ገበያ የሚሠሩ ሰዎችን እያበረታቱ መሄድ ነው፡፡ እነዚህን ማስቆም የምንችለው ሰዎች በነፃነት ገንዘባቸውን ወደ አገር ቤት መላክ ሲችሉ ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን ከዳያስፖራ የሚመጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ አንዱ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው፣ ከዳያስፖራ የሚላከውን የውጭ ምንዛሪ ከጥቁር ገበያው ጋር በማስተካከል የውጭ ምንዛሪ ገበያውን በማሳደግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ያለባትን ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ የውጭ ባንኮች መግባት ዕገዛ ያደርጋው የሚል አመለካከት አለ፡፡ ይህ አመለካከት የሚታመንበት ነው? በአጠቃላይ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ መፍቀድና ወደ ሥራ መግባታቸው በአገራዊ ኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረው አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖ ምንድነው?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- የውጭ ባንኮች በውጭ ምንዛሪ ካፒታል ብቻ ይዘው አይደለም የሚመጡት፡፡ የፋይናንስ አስተዳደር ይዘው ይመጣሉ፡፡ የእነሱን ልምድ ይዘው ይመጣሉ፡፡ ከዚህም ሌላ የውጭ ኢንቨስተሮች እንዲገቡ መንገድ ይከፍታሉ፡፡ ምክንያቱም የውጭ ኢንቨስተሮች ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያበድሩን የውጭ ባንኮች አሉ ብለው እንዲመጡ ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህ ብዙ ኢንቨስተሮች ገንዘባቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲያፈሱ የውጭ ባንኮች መምጣት አንዱ ጠቀሜታ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የካፒታል ገበያ መምጣትም ከዚህ ጋር ይያዛል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አክሲዮን እሸጣለሁ ቢል አንድ ሰው ቶኪዮ፣ ለንደን፣ ኒውዮርክ ወይም ሌላ ቦታ ሆኖ የመቶ ሚሊዮን ዶላር አክሲዮን ሊገባ ይችላል፡፡ የሌሎች የኢትዮጵያ ኩባንያዎችን አክሲዮኖች በተመሳሳይ መንገድ ለመግዛት ያስችላል፡፡ በተለይ ስም ያላቸው ኩባንያዎች ብዙ ኢንቨስተሮች እንዲያገኙ ያስችላል፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮችንም ስንመለከት የውጭ ባንኮች መግባት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ በማምጣት ትልቅ ጥቅም ያስገኛሉ፡፡ የውጭ ባንኮች መግባት የሚያስገኘውን ጥቅም የተለያዩ አገሮችን በምሳሌነት በመጥቀስ ማሳየት ይቻላል፡፡

      ለምሳሌ ዱባይ በ1970ዎቹ ነው ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጣችው፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ እ.ኤ.አ. በ1980 ነው የራሳቸውን ‹‹ድርሃም›› ገንዘብ የፈጠሩት፡፡ አሁን የመካከለኛው ምሥራቅና የአፍሪካ የፋይናንስ ማዕከል ናቸው፡፡ ይህንንም ያደረጉት ከ1980 ጀምሮ የውጭ ባንኮችን በማምጣት ነው፡፡ አሁን በዓለም ላይ ካሉ ከፍተኛ ከሚባሉ 26 ባንኮች መካከል 14 ያህሉ ዱባይ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ባንኮች እስካሁን ድረስ ገንዘብ ከውጭ እያስገቡ ነው እንጂ እያስወጡ አይደለም፡፡ ኤምሬትስ ነዳጅ አላት፡፡ እሱም አምስት በመቶ ነው፡፡ የእነሱ ሀብት ነዳጅ አይደለም፣ ፋይናንስ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ አሁን በፋይናንስ አገልግሎት ዱባይ ለንደንን ተክታለች፡፡ በተመሳሳይ የቻይናም ታሪክ ይህንን የሚያመላክት ነው፡፡ ቻይና እ.ኤ.አ. በ2001 ነው የዓለም ንግድ ድርጅት አባል የሆነችው፡፡ ይህንንም ተከትለው የውጭ ባንኮች ገብተው እንደ ማይክሮ ሶፍት፣ አፕልና የመሳሰሉት ትልልቅ ኩባንያዎች እንዲመጡ አደረጉ፡፡ እነዚህን ቻይና የገቡ ትልልቅ ኩባንያዎች የውጭ ባንኮች ፋይናንስ አደረጓቸው፡፡ ቻይና አሁን የዓለም ሁለተኛ ኢኮኖሚ እንድትይዝ ዕገዛ ካደረጉላት መካከል አንዱ የውጭ ባንኮችን ማስገባቷ ነው፡፡ አሁን ከ30 ዓመታት በኋላ ደግሞ የቻይና አገር በቀል ባንኮች እኩል እንዲወዳደሩም አስችሏል፡፡ ዋናው ነገር የውጭ ባንኮች ሲመጡ የፖሊሲ ማዕቀብ ይኖራቸዋል፡፡ ለምሳሌ ቅርንጫፍ አይከፍቱም፡፡ ለአገሬው ዜጋ የቁጠባ አካውንት አይከፍቱም፡፡ ከፍተኛ ብድሮችን ለመንግሥት፣ ለመሠረተ ልማት ግንባታና ለግል ዘርፉ በቀጥታ ሊያበድሩ ይችላሉ፡፡ ትንንሽ ብድሮች እንደ ሌተር ኦፍ ክሬዲት በአገር ውስጥ ባንኮች በኩል ስለሚሠሩ ሁሉንም ተጠቃሚ ያደርጋሉ፡፡

      ስለዚህ የውጭ ባንኮች መግባት ምንም የሚያስፈራ ነገር የለውም፣ የሚያስጨንቅም አይደለም፡፡ እንዲያው ዝም ብሎ አገር ተዘረፈ፣ የአገር ውስጥ ባንኮች ይሞታሉ ብለው የሚናገሩ ሰዎች ምንም ዓይነት ማስረጃ የላቸውም፡፡ እስካሁን ድረስ የባንክ ዘርፍ ሊበራላይዝ ሲደረግ አገሮች በጣም ነው ያደጉት፡፡ እነ ቬትናም፣ ሲንጋፖር፣ ኤምሬትስ፣ ቻይናና የመሳሰሉት አገሮች አድገውበታል፡፡ እርግጥ በአፍሪካ እንዲህ ዓይነት ሊብራላይዜሽን ሲደረግ በሙስና የዋዠቁ መንግሥታት ሰለሆኑ አገሮችን ለጥፋት ሊዳርግ ይችላል፡፡ ይህንን ለመከላከል የየአገሩ ብሔራዊ ባንክ እንደ ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ሆኖ ሊቆጣጠር ይገባል፡፡ ጠንካራ ተቆጣጣሪ ያስፈልጋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በእኛ አገር የውጭ ባንኮች እንዲገቡ መፈቀዱ ትልቅ ዕርምጃ ሆኖ ሳለ፣ እንዲገቡ የሚፈቀደው ለአራትና ለአምስት ባንኮች ነው የሚለው ነገር አይገባኝም፡፡ የፈለገው ባንክ መጥቶ እሠራለሁ፣ አተርፋለው፣ አገርንም እጠቅማለሁ እስካለ ድረስ ለሁሉም መፍቀዱ ነው የሚበጀው፡፡ ዋናው ጉዳይ ጥሩ ሕግ ኖሮ በአግባቡ መቆጣጠር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ብለው እንደገለጹልኝ የውጭ ባንኮች እዚህ ሥራ ቢጀምሩ የቁጠባ ሒሳብ አይከፍቱም ወይም የቁጠባ ገንዘብ አይሰበስቡም ብለዋል፡፡ እንዲህ ያለውን ሥራ የውጭ ባንኮች ሊሠሩ የማይችሉበት ምክንያት ምንድነው?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- የቁጠባ ሒሳብ (ሴቪንግ አካውንት) መክፈት አይችሉም፡፡ 

ሪፖርተር፡- እንዴት ሊሆን ይችላል? ሥራቸው ምን ሊሆን ነው?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- እንግዲህ በሌሎች አገሮች ያለውን ልምድ ነው የምነግርህ፡፡ በሌሎች አገሮች የቁጠባ አካውንት እንዲከፍቱ አልፈቀዱላቸውም፡፡

ሪፖርተር፡- ምክንያቱ ምንድነው?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- የአገር ውስጥ ባንኮች ብቻ ቁጠባ ሰብስበውና ካፒታል ኖሯቸው ማበደር እንዲችሉና ሥራ እንዲሠሩ ነው፡፡ የውጭ ባንኮች የቁጠባ ሒሳብ ከፍተው ከተሻሙ የአገር ውስጥ ባንኮቹ ሊሞቱ ይችላሉ በሚል የሚተገበር ነው፡፡ በሌላ በኩል  ግን የውጭ ባንኮች መግባት የአገር ውስጥ ባንኮችን ጠንካራ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማስቻል ያስፈልጋል፡፡ ይህም አሁን በየመንደሩ ብቅ ብቅ የሚሉ ባንኮች ተሰብስበው ጠንከር ያለ ባንክ በመፍጠር የተወሰኑ ጠንከር ጠንከር ያሉ ባንኮችን የመፍጠር ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የአገራችንን የግል ባንኮች አሁን ባለው ቁመናቸው ሁሉንም ብትሰበስባቸው አንድ ግድብ መሥራት የሚችል ካፒታል የላቸውም፡፡ ወይም አንድ መንገድ ወይም ትልቅ ኢንዱስትሪ ለመገንባት የሚያስችል ብድር የመስጠት አቅም የላቸውም፡፡ ለሕንፃና ለትንንሽ ጉዳዮች የሚያበድሩ በመሆኑ የግል ባንኮች ሰብሰብ ብለው ጠንከር ያሉ ጥቂት ባንኮችን ለመፍጠር ቢሠሩ እንደ አገር ጠንካራ ተወዳዳሪ ባንክ እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ በናይጄሪያ ወደ 300 የሚጠጉ የግል ባንኮች ነበሯቸው፡፡ መጨረሻ ላይ በተወሰደ የፖሊሲ ውሳኔ በከፍተኛ ደረጃ ቁጥራቸው ቀንሷል፡፡ አሁን በዓለም የሚታወቁትን እንደ ዜኒትና አክሰስ የተባሉ ባንኮችን ፈጥረው ምዕራብ አፍሪካን እያጥለቀለቁ ነው፡፡ ስለዚህ የአገራችንም ባንኮች ሰብሰብ ማለት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምናልባት ብሔራዊ ባንክ አሁን ያወጣው የብድር ገደብ ውሳኔ ዝም ብሎ ባንኮች በየመንደሩ እንዲፈጠሩ ሳይሆን፣ ባሉት ባንኮች ላይ እያጠናከሩ ለመሄድ የታሰበ ነገር ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ባንኮች ከአገር ውስጥ ባንኮች ጋር ተወዳዳሪ የሚሆኑት እንዴት ነው? ካፒታላቸውን ይዘው በመምጣት ብቻ ነው?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- የውጭ ባንኮች ካፒታላቸውን ከውጭ ነው ይዘው የሚመጡት፡፡ ያበድራሉ፣ አበድረውም ከወለድ ገቢ ያገኛሉ፡፡ ትርፋቸው ይኼ ነው፡፡ ሌተር ኦፍ ክሬዲት በመክፈት ከትልልቅ ኩባንያዎች ጋር ይሠራሉ፡፡ ትንንሽ ነገሮች ለእነሱ የማኔጅመንት ሥራ አይመቻቸውም፡፡ ለምሳሌ ሻይ ቅጠል ለማምጣት ሌተር ኦፍ ክሬዲት ለሚከፍት ሰው የአድሚኒስትሬቲቭ ሰዓት በጣም ይወስድባቸዋል፡፡ እንዲህ ያለውን ሥራ ለአገር ውስጥ ባንኮች ነው የሚተውላቸው፡፡ ይህ ደህና ውይይት የሚያስፈልገው ነው፡፡ ከባንኮች፣ ከተጠቃሚዎች፣ ከንግድ ማኅበራትና ከሙያ ማኅበራት ጋር ከፍተኛ ውይይት የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ ለመፍጠር ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን የውጭ ባንኮች ከገቡ ያጠፉናል የሚለው አስተሳሰብ አገራችንን ተባብረን እናጥፋ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የውጭ ባንኮች መግባት ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የውጭ ባንኮች መግባት የኢትዮጵያን ባንኮች እስከ ዛሬ ሲጓዙበት የነበረውን አካሄድ ሊቀይር የሚችልበት ሁኔታም ሊኖር ይችላል፡፡ ይህም ከፋይናንስ ተቋማት የትርፍ ምጣኔ ጋር ይያያዛል፡፡ እኔ ሁሌ የሚገርመኝና በዓለም ታሪክ ሰምተን በማናውቀው ሁኔታ የኢትዮጵያ የግል ባንኮች 60 እና 70 በመቶ ዲቪደንድ (የትርፍ ክፍፍል) ይከፍላሉ፡፡ ይኼንን ሰምቼ አላውቅም፣ በዓለም ላይ የለም፡፡ ምናልባት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አንደንድ አገሮች ላይ ታይቶ ካልሆነ በቀር ካለው የዋጋ ንረትና የወለድ ምጣኔ ትንሽ ከፍ ያለ የትርፍ ክፍፍል (ዲቪደንድ) የሚሰጡት እንጂ 60 እና 70 በመቶ ትርፍ የሚሰጥበት አገር የለም፡፡

      የሌሎች አገሮችን የትርፍ ድርሻ ጎግል ብታደርግ የሚያሳይህም ይህንኑ ነው፡፡ ስለዚህ የአገር ውስጥ ባንኮች እንዲዘጋጁ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ የሚገልጹትም እስከ ዛሬ በመጡበት መንገድ ሊቀጥሉ ስለማይችሉ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ጨዋታ ያበቃል ማለት ነው፡፡ ባለአክሲዮኖች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ብቻ የሚያደርገው ሒደት ይለወጣል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ቀደም ብዬ እንደ ገለጽኩልህ የካፒታል ገበያው ሲጀመር፣ ይህም የውጭ ኩባንያዎች በአገር ውስጥ ኩባንያዎች ላይ ኢንቨስት ያደርጋሉ፡፡ ሰዎች ባንክ የሚያስቀምጡትን አክሲዮን ይገዙበታል፡፡ ምክንያቱም የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ የሌላቸውንም ገንዘብ ከሚመጣው ገቢያቸው ሊያበድሩ የሚችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ በተወሰነ ደረጃ ተቆጣጣሪው ባንክ ሊፈቅድላቸው ይችላል፡፡ በቅርቡ እንደሰማነው በአሜሪካ ሁለት ባንኮች ከስረዋል፡፡ እነዚህ ባንኮች ካላቸው መጠን በላይ አበድረው መተካት አልቻሉም፡፡ መጨረሻ ላይ ደንበኛ መጥቶ ገንዘቡን ሲጠይቃቸው የላቸውም፡፡ እንዲህ ያለው ነገር እንዳይፈጠር ብሔራዊ ባንኩ ይቆጣጠራል፡፡ ከአጠቃላይ የፋይናንስ ዘርፉ እንቅስቃሴና በተለይ ከውጭ ባንኮች መግባት ጋር ተያይዞ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ራሱን በሚገባ ማደራጀት አለበት፣ አቅሙን ማጎልበት አለበት፡፡

የዓለም የፋይናንስ ቀውስ በተከሰተ ጊዜ የእንግሊዝ ብሔራዊ ባንክ የተሻለ የባንክ ገዥዎች ለማግኘት ያደረገውን ጥረት እዚህ ላይ ማስታወስ ይገባል፡፡ የተሻለ የባንክ ገዥ ለማግኘት በዓለም ደረጃ አስተዋውቀው መጨረሻ ላይ አሸናፊ ሆኖ የቀጠሩት በሙያው አንቱ የተባለን ካናዳዊ ነው፡፡ እንግሊዞች ኢኮኖሚክስን የፈጠሩ፣ ባንክን የፈጠሩ፣ ገንዘብን በዓለም ደረጃ ያስተዋወቁ ናቸው፡፡ ከዶላር በፊት ፓውንድ ዓለም አቀፍ ገንዘባቸው ነበር፡፡ እንዲህ ያለ ታሪክ ያላቸው እንግሊዞች ሳይቀሩ ካናዳዊውን ባለሙያ አምጥተው አሠርተዋል፡፡ እኛም ዘንድ ተቆጣጣሪው አካል ሲቋቋም ከብሔራዊ ባንክ ውጪ ከሆነ በዚህ ጉዳይ ላይ ቅርበት ያላቸው ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው ሰዎች ማሰባሰብ ግዴታ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው›› ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞ ሜቴክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ከጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ...

‹‹ባለፉት 25 ዓመታት ባለን አቅም ሁሉ የተለያዩ አጀንዳዎችን ለመዳሰስ ሞክረናል›› የራስወርቅ አድማሴ (ዶ/ር)፣ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› በመባል የሚታወቀውን በኢትዮጵያ ታሪክ ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ አካል ገለልተኛ ሆኖ የተቋቋመ ሐሳብ አመንጪ የጥናት ተቋም (ቲንክ ታንክ) ከመሠረቱት አንዱ መሆናቸውን...

‹‹ብሔራዊ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን ሊያግዙ የሚችሉ ወጥ የሆኑ ሕጎች ያስፈልጉታል›› አቶ ኑሪ ሁሴን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት (ከወለድ ነፃ ባንክ...

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስጀመር ብርቱ ትግል ተካሂዷል፡፡ ከብዙ ጥረት በኋላ አገልግሎት በመስኮት ደረጃ እንዲሰጥ ተወስኖ፣ ከዚያም ከለውጡ ወዲህ ሙሉ በሙሉ ከወለድ...