Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹ጨው እንዳላመርት በክልሉ መንግሥት ታግጃለሁ›› ሲል የዶቢ ጨው አምራች ማኅበር ቅሬታ አቀረበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአፋር ክልል የሚገኘው የዶቢ ጨው አምራቾች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኅብረት ሽርክና ማኅበር፣ ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ ጨው እንዳያመርት መከልከሉን አስታወቀ።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ 409 አባላቱን ጨምሮ ከ“ጨው ፖለቲካ” ጋር በተያያዘ ከ1,700 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን መስከረም 10 ቀን 2016 ዓ.ም. ማኅበሩ በአዲስ አበባ ከተማ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።

አባላቶቹ በሰመራ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ እንደሚገኙ የማኅበሩ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሁሴን ዓሊ ገልጸው፣ የታሰሩበት ምክንያትም ጨው ለማምረት መከልከላቸውን በተመለከተ ቅሬታ በማንሳታቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግሥት አካላት ከዚህ በፊት መርማሪ ቡድን በመላክ ያለውን ችግር የተመለከቱ ቢሆንም፣ መፍትሔ ማግኘት አልተቻለም ብለዋል፡፡

‹‹ከጨው መሬት ድልደላ ጀምሮ እስከ ክፍፍል ያለው የጨው ገበያ ሰንሰለት ከፖለቲካ አሠላለፍና ከፖለቲከኞች ነፃ ሆኖ አያውቅም፤›› ያሉት አቶ ሁሴን፣ ‹‹በለውጡ ጊዜ ለሚዲያ ሽፋን ሲባል በአካባቢው ቀድመው ሲያመርቱ ከነበሩ ግለሰቦችና ተቋማት ተነጥቆ ለአፋር ወጣቶች ይሰጣል፣ የገበያ ትስስር ይፈጠርላችኋል፣ እንዲሁም ጨው ከአገር ውስጥ ፍጆታ ባሻገር ለውጭ ገበያ የሚቀርብበት ሁኔታ ይመቻቻል በማለት ሲነገር የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት በሌሎች ግለሰቦች እንዲያዝ ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡

የጨው አምራች ማኅበሩ ዕገዳው እንዲነሳለት ለሚመለከታቸው የክልሉ የመንግሥት አካላት ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም አጥጋቢ ምላሽ እንዳላገኘ ገልጿል።

ከዚህም ባሻገር ጨው አምራቾች ምርታቸውን የሸጡበት የስድስት ወራት ክፍያ እንዳልተከፈላቸው የተናገሩ ሲሆን፣ በዚህም ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ጠቁመዋል፡፡  

ዶቢ የጨው አምራች ማኅበር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኅብረት ሽርክና ማኅበር በአፋር ክልል በ1992 ዓ.ም. በባህላዊ አመራረት የተመሠረተና በሒደት ወደ ዘመናዊነት የተሸጋገረ 409 አምራች አባላት ያሉት ማኅበር መሆኑ ተገልጿል።

በማኅበሩ በኩል በተነሱ ቅሬታዎች ዙሪያ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የክልሉ የሥራ ኃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች