የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በመካከለኛው ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን ቅበት ከተማ፣ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ምዕመናን ላይ የተፈጸመን ጥቃት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ምክንያት፣ የደረሰበትን ገልተኛ ባለመሆን የቀረበለትን ወቀሳ አስተባበለ፡፡
ኢሰመጉ መስከረም 10 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሥልጤ ዞን ቅበት ከተማ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት አማኞች ላይ የተለያዩ ጉዳቶች መፈጸማቸውን ገልጾ ስለነበረ፣ የዞኑ አስተዳደር በተቋሙ ላይ በቀጣዩ ቀን የገልተኝነት ጥያቄ አንስቶ ወቀሳ ሰንዝሮ ነበር፡፡
ኢሰመጉም ማክሰኞ መስከረም 15 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ወቀሳውን ያስተባበለ ሲሆን፣ ያወጣቸውን መረጃዎች ሚዛናዊነት ለመጠበቅ የመንግሥት ኃላፊዎችና የእስልምና ጉዳይ ቢሮዎችን አግኝቶ ለማነጋገር ሙከራ አድርጎ እንዳልተሳካለት፣ ‹‹ከጉዳዩ አሳሳቢነት አንፃር ትኩረት እንዲሰጠው›› መግለጫውን በወቅቱ እጁ ላይ ባለው መረጃ ማውጣቱን አስታውቋል፡፡
የስልጤ ዞን አስተዳደር መስከረም 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ለኢሰመጉ የመጀመሪያ መግለጫ ምላሽ ሲሰጥ፣ ኢሰመጉ ‹‹ሐሰተኛና ሚዛናዊነት የጎደለው›› አስቸኳይ መግለጫ እንዳወጣ ገልጾ ነበር፡፡
ተቋሙ ነፃና ገለልተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብቶች ተከራካሪ ተቋም እንደሆነ በስም በመግለጽ፣ በገቢር ግን የአንድን ቡድን የተዛባ ጩኸት ለማስተጋባት በማሰብ፣ ኢሰመጉ መግለጫውን እንዳወጣ የዞኑ አስተዳደር አስነብቦ ነበር፡፡ የኢሰመጉን መግለጫ፣ ‹‹በዝርዝር በአካል መጥቶ ያልተጣራና ፍፁም ገለልተኛ ያልሆነ፣ እንዲሁም ሐሰተኛና ግጭት አባባሽ›› እንደሆነ ነው የዞኑ አስተዳደር የገለጸው፡፡
ለዚህም ወቀሳ ማስተባበያ የሰጠው ኢሰመጉ የዞኑን መግለጫ፣ ‹‹በምንም ዓይነት ሁኔታ እንደማይቀበለው፤›› አሳውቋል፡፡ የዞኑ አስተዳደር እንደጠቀሰው ግጭትን መቀስቀስና ሐሰተኛ መረጃዎችን ማሠራጨት የኢሰመጉ ዓላማ እንዳልሆነ፣ ነገር ግን ለሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ ለዴሞክራሲና ለሕግ የበላይነት መከበር መሥራት ዋነኛ ዓላማዎቹ እንደሆነ ገልጿል፡፡
በኢሰመጉ መግለጫ ቅር የተሰኙና የገለልተኝነት ጥያቄ ላነሱ የሙስሊም ማኅበረሰብ አባላት፣ ኢሰመጉ መግለጫውን ወገንተኝነት በመያዝ እንዳላዘጋጀውና የሕግ የበላይነት እንዲከበር በማሰብ ያዘጋጀው መሆኑን አስታውቋል፡፡
‹‹ምንም እንኳን ሞትና ጉዳት መድረሱን የገለጽን ቢሆንም በግልጽ ስለደረሰው ሞትና የአካል ጉዳት ዝርዝር ባለመግለጻችንና በአጠቃላይ ስለተፈጠረው አለመግባባት ኢሰመጉ ሁሉንም የሙስሊም ማኅበረሰብ ይቅርታ ሊጠይቅ ይወዳል፤›› ሲል ኢሰመጉ በመግለጫው ይቅርታ ጠይቋል፡፡ ‹‹ኢሰመጉ በአካባቢው በመገኘት ጥልቅ ምርመራ በማድረግ የተደራጀ ሪፖርት እንደሚያወጣ እንገልጻለን፣›› ሲልም ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያደርግ አክሏል፡፡