Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በትብብር ለመሥራት በባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ እየገቡ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከህንድ፣ ከቻይና፣ ከእስራኤልና ከሌሎች አገሮች ኩባንያዎች ጋር በትብብር በባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ እየገቡ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ቦርድ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ እንዲገቡ ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ፣ በባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ አራት አዳዲስ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በጆይንት ቬንቸር መግባታቸውን፣ የኮሚሽኑ የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ናታንዬ ካሳ ተናግረዋል፡፡

በኮሚሽኑ ውሳኔ መሠረት የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የምርታቸውን 50 በመቶ ለአገር ውስጥ፣ 50 በመቶ ደግሞ ለውጭ ገበያ እንዲልኩ ማበረታቻ መደረጉን ሥራ አስኪያጁ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች የተገነቡበት ዋነኛ ዓላማ የውጭ ባለሀብቶችን ማዕከል ያደረገ ቢሆንም፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችም እንዲገቡ የሚያበረታታ ውሳኔው በመደረጉ በጆይንት ቬንቸር ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ሥራ ሊጀምሩ መሆናቸውን አቶ ናታንዬ ገልጸዋል፡፡

የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ከገቡት መካከል ፓሮን ትሬዲንግ የአገር ውስጥ ኩባንያ አንዱ መሆኑን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ በፓርኩ ውስጥ ሁለት ሔክታር ወስዶ የራሱን ሼድ ገንብቶ ጨርሷል ብለዋል።

ኩባንያው በዚህ ዓመት ሥራ ለመጀመር ያቀደ ሲሆን፣ በገነባው ሼድ ውስጥ የስታርች ምርት ለማምረት በዝግጅት ላይ መሆኑን አቶ ናታንዬ ጠቁመዋል፡፡

የእስራኤላዊና የኢትዮጵያዊ ዜግነት ባላቸው ሁለት ባለሀብቶች የተመሠረተው አንበሳ ኤሊት ታክቲካል ቴክስታይል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ የገባ ሌላኛው ኩባንያ ሲሆን፣ ወታደራዊ የደንብ ልብሶችን የሚያመርት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የማሽን ግዥና የሰው ኃይል ቅጥር እያከናወነ እንደሚገኝ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ ሥራውን ከመጀመሩ በፊት በአሜሪካና በእስራኤል የተመረቱ ወታደራዊ የደንብ ልብሶች ናሙና ማቅረቡን አስረድተዋል፡፡

የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ በመግባት በቀጣይ ሁለት ወራት ውስጥ ሥራ ለመጀመር ያቀደው ኒርቫና አግሮ ፕሮሰሲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሌላው ኩባንያ ነው፡፡

በኢትዮጵያዊና በህንድ ባለሀብት በትብብር የተመሠረተ መሆኑን፣ የአኩሪ አተር ዘይትና ተያያዥ ምርቶችን ለማምረት እየተዘጋጀ እንደሚገኝ አቶ ናታንዬ ገልጸዋል።

ኩባንያው በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ሥራ ለመጀመር የሚያስችሉ ማሽኖችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጥያቄ ማቅረቡ ተገልጿል።

የቻይና እና የኢትዮጵያ ባለሀብቶች በትብብር የመሠረቱት አፍሉዌንስ ኤሌክትሪክ አፒሊያንስ ማን (Affluence Electric Man PLC) ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አራተኛው ወደ ፓርኩ የገባ ኩባንያ መሆኑን አቶ ናታንዬ ተናግረዋል፡፡

ትራንስፎርመር ለማምረት የተመሠረተው ኩባንያ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሼድ ኪራይ ውል በመውሰድ፣ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር የኢንቨስትመንት ስምምነት መፈራረሙን አክለዋል።

ከወራት በፊት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አክሊሉ ታደሰን ጨምሮ፣ የፌዴራልና የክልል አመራሮች የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክን በጎበኙበት ወቅት፣ የአገር ውስጥና የውጭ አምራች ኩባንያዎች፣ ባለሀብቶችና በኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ የማምረቻ ሼዶችንና ሌሎች መገልገያዎች እንዲጠቀሙባቸው ጥሪ ማስተላለፋቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች