የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሊቀመንበር ጫኔ ከበደ (ዶ/ር)፣ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ውለው መታሰራቸውን ፓርቲው አስታወቀ።
ጫኔ (ዶ/ር) እሑድ መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የእስር ማዘዣ ሳይኖር ስድስት የፌዴራል ፖሊስና የሲቪል ልብስ የለበሱ የፀጥታ ኃይሎች ከአንድ ጓደኛቸው ጋር በተቀመጡበት ሥፍራ እንደያዟቸው፣ የኢዜማ የሕግና የአባላት ደኅንነት ጉዳይ መምርያ ኃላፊ አቶ ሥዩም መንገሻ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ሊቀመንበሩ የተያዙት በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ በመጣረስ ነው ያሉት አቶ ሥዩም፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መሠረት ያደረገ እንኳን ቢሆን የታሰሩበት ምክንያት ምን እንደሆነ የማወቅ መብት ሊኖራቸው ይገባ ነበር ብለዋል፡፡
ሊቀመንበሩ የተወሰዱት የሰሌዳ ቁጥር በሌለው ተሽከርከሪ መሆኑንና በምን ምክንያት እንደተያዙም ማወቅ ስላልተቻለ፣ በሕግ ቁጥጥር ሥር ውለዋል ሳይሆን አፈና ነው የተካሄደው ሲሉ አቶ ሥዩም ሁኔታውን ገልጸዋል፡፡
ኢዜማ ጉዳዩን በጥንቃቄና በቅርበት እየተከታተለ እንደሚገኝ፣ ይህንንም ለማድረግ የሚያስችል ሦስት አባላት ያሉት ኮሚቴ መቋቋሙን አቶ ሥዩም አስረድተዋል፡፡
የፓርቲው ሊቀመንበር በቁጥጥር ሥር ከዋሉበት ሰዓት ጀምሮ በሕጉ መሠረት 48 ሰዓት ቢሞላም ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን አቶ ሥዩም ተናግረዋል፡፡
ሊቀመንበሩ ከተያዙ በኋላ ፓርቲው ከቤተሰቦቻቸው መረጃ በመነሳት ያሉበትን ቦታ ለማወቅ ጥረት በማድረግ፣ ሜክሲኮ የሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ እንደሚገኙ ማረጋገጥ መቻሉን አቶ ሥዩም ገልጸዋል፡፡
ፓርቲው በሰላማዊ መንገድ የሚታገል እንደመሆኑ መጠን፣ ማናቸውም መረጃዎችና የሥራ እንቅስቃሴዎች ሕግና ሥርዓትን የተከተሉ መሆናቸውን አቶ ሥዩም አክለዋል፡፡
ጫኔ (ዶ/ር) የፓርቲውን የየዕለት ሥራዎች የመከታተል ተግባር የሚያከናውኑ እንጂ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚፃረሩ ሥራዎች ላይ ተሳትፎ የላቸውም ብለዋል፡፡
ያላግባብ መታሰር በኢዜማ ሊቀመንበር ጫኔ (ዶ/ር) የተጀመረ አለመሆኑን የተናገሩት አቶ ሥዩም፣ ከዚህ በፊት በአባላት ላይ በተደጋጋሚ የተፈጠረና አሁንም እየተፈጠረ ያለና ወደፊትም የሚቀጥል ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የፓርቲው አባላት ያላግባብ እንደሚታሰሩ፣ የተለያዩ ቦታዎች እንደሚቆዩና ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ከፖሊስ ጣቢያ እንደሚለቀቁ አቶ ሥዩም አስረድተዋል፡፡
በተደጋጋሚ በተፈጠረው የፓርቲው አባላት ያላግባብ እስሮች ፓርቲው የሚከተለው አካሄድ ከሚመለከታቸው አካላት ማለትም ከምርጫ ቦርድ፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና ከሌሎች አካላት ጋር የደብዳቤ ልውውጥ በማድረግ አበላቱ ወደ ቤተሰባቸውና ወደ ሥራዎቻቸው እንዲመለሱ ማድረግ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመታወጁ በፊትም ሆነ በኋላ በደቡብና በኦሮሚያ አካባቢዎች በብዛት የሚታሰሩ አባላት እንዳሉ የገለጹት አቶ ሥዩም፣ በአሁኑ ወቅት በአዳማ ከተማ የታሰሩ ሁለት አባላት እንዳሉ ተናግረዋል፡፡
‹‹ፖሊስ አንድን ሰው የመጠርጠርና የመያዝ መብት ቢኖረውም፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅትም ቢሆን በሕገ መንግሥቱ የተጠቀሰው ሰብዓዊ መብት ሊከበርላቸው ይገባል፤›› ሲሉ አቶ ሥዩም ገልጸዋል፡፡
ሊቀመንበሩ በፀጥታ አካላት ለምን እንደተያዙ ባይገለጽም የተቋቋመው ኮሚቴው ምክንያቱን ለማወቅ ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል የኢዜማ ምክትል ሊቀመንበርና አሁን የፓርቲው ሊቀመንበር ጫኔ (ዶ/ር)፣ በመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) እና በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ውስጥ በተለያዩ የአመራርነት ቦታዎች አገልግለዋል።
በተጨማሪም ከ1997 ዓ.ም. እስከ 2002 ዓ.ም. በነበረው ወቅት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እንደነበሩ ይታወሳል።