Monday, December 4, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት መሠረት በፍቅርና በመተሳሰብ መንፈስ ሲያከብሩ ለኢትዮጵያ እንደ ትልቅ በረከት ይቆጠራል፡፡ አዲሱ ዓመት ከባተ ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች የዘመን መለወጫ በዓላት በታላቅ ድምቀት እየተከበሩ ነው፡፡ በተለይ በደቡብ አካባቢዎች እየተከበሩ ያሉት የዘመን መለወጫ በዓላት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን፣ የምግብ፣ የአልባሳት፣ የተለያዩ መጠቀሚያ ቁሳቁሶችን፣ ወጎችን፣ ባህሎችን፣ ልምዶችንና የመሳሰሉትን በማካተት የኢትዮጵያን ኅብረ ብሔራዊነት በስፋት እያንፀባረቁ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በብሔርም ሆነ በእምነት ማንነቶች የተለያዩ መገለጫዎችን ይዞ በፍቅርና በመከባበር በዓላቱን ሲያከብር፣ ከምንም ነገር በላይ የአገሩን ውሎና አዳር በከፍተኛ ንቃት እየተከታተለ ነው፡፡ አንዱ አካባቢ አንፃራዊ ሰላም ሰፍኖ ሌላው ዘንድ ሰላም ሲጠፋ የበዓላቱ ስሜት ይደብዛዛል፡፡ ሕዝባችን በዘመን ተሻጋሪ የጋራ ማኅበራዊ እሴቶቹ ምክንያት የአንዱ ሕመም ሌላውንም ይሰማዋል፡፡ ለዚህም ነው በዓላት በመጡ ቁጥር ለሰላም መስፈን ከፍተኛ ሥፍራ የሚሰጠው፡፡

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝብ ክርስቲያኑ በዓላቱን እያከበሩ ባለበት በዚህ ጊዜ፣ ከመንፈሳዊ አባቶችም ሆነ ከአገር ሽማግሌዎች የሚሰማው ድምፅ ለአገር የሰላም ምኞት መግለጫ ነው፡፡ በዓላቱ ሲከበሩ የሚተላለፉ መልዕክቶችም ሆኑ የመልካም ምኞት መግለጫዎች ለአገር ህልውና የሚጠቅሙ ሲሆኑ፣ በመሀል ግን ፖለቲከኞች አጋጣሚውን በመጠቀም አደፍራሽ ሲሆኑ ይስተዋላሉ፡፡ የቆዩ ቂሞችንና በቀሎችን እያመረቀዙ በሕዝብ ውስጥ ልዩነት የመፍጠር አባዜ ስላለባቸው፣ የመንግሥት ሥልጣንና የፓርቲ ፖለቲካ ሥራን መቀላቀል ልማዳቸው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እነዚህን ችላ በማለት ዓላማውን ማስተባበር ያለበት አንዲት አገሩና የጋራ ሰንደቁ ላይ ነው፡፡ ብሔራዊና ሃይማኖታዊ ማንነትን ይዞ አንድ አገርና አንድ ሕዝብ መሆን ተችሎ ነው እዚህ የተደረሰው፡፡ በመሆኑም ከጥንት ጀምሮ በትውልዶች ጅረት ሲቀባበል የመጣውን አገራዊ ራዕይ ይዞ ማስቀጠል ያዋጣል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ፊት በገዘፈ ታሪክና ስያሜ የታወቀችውም ከድሮ ጀምሮ ልጆቿ በአንድነት ስለጠበቋት ነው፡፡ ይህ ታሪካዊ አንድነትና የአገር ፍቅር ስሜት ለመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት መሆን ችሏል፡፡

እርግጥ ነው ኢትዮጵያ የታሪኳ አብዛኛው ክፍል የግጭትና የጦርነት ነው፡፡ በአገር ውስጥ ለሥልጣን በሚደረግ ሽሚያ በየአካባቢው ይነሱ በነበሩ መሣፍንት መካከል ከፍተኛ ግጭቶች ተካሂደዋል፡፡ አንዱ ሌላውን አስገብሮ የበላይነት ለመያዝ በተደረጉ ግጭቶች ከፍተኛ መስዋዕትነት ተከፍሏል፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ለማስከበር የተደረጉ ትንቅንቆችም ዋጋ ተከፍሎባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ቅርፅና ይዘት እዚህ የደረሰችው በሌላው ዓለም እንደተደረገው በግዛት ማስከበር ትግል ነው፡፡ ከዚያ በተረፈ ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ካሰፈሰፉ ወራሪዎችና ተስፋፊዎች ጋር በተደረጉ ጦርነቶች፣ መላ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ የአገር ፍቅርና አርበኝነት ተሠልፈው ከባድ መስዋዕትነቶችን ከፍለዋል፡፡ በተለይ ከኮሎኒያሊስቶች ጋር አገርን ለመጠበቅ የተደረጉ ጦርነቶች በርካታ ናቸው፡፡ እንደ ሰሃጢ፣ ጉራዕ፣ ጉንደት፣ ዓድዋ፣ ካራማራና ሌሎች ታላላቅ ጦርነቶች ዛሬም ድረስ አይረሱም፡፡ ከሁሉም ከሁሉም ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱታን ያተረፈላት ታላቁ የዓድዋ ጦርነት ድል፣ በዓለም ጥቁር ሕዝቦች ለዝንተዓለም ሲታወስ የሚኖር የነፃነት ተምሳሌት ነው፡፡ ዓድዋ ሲታወስ የመላ ኢትዮጵያውያን ጀግንነት አብሮ ይታሰባል፡፡

አገርን ከባዕዳን ወረራ መከላከልንም ሆነ በአገረ መንግሥት ግንባታ የተከፈሉ መስዋዕትነቶች፣ በአራቱም ማዕዘናት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በእኩልነት የሚዘክሯቸው የጋራ ታሪክ ውጤቶች ናቸው፡፡ እንደ ማንኛውም አገር በኢትዮጵያም ከታሪክ ጋር የሚነሱ መዛነፎች መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ ዋናው ቁምነገር የታሪክ ዝንፈቶችን አስተካክሎ የጋራ አገርን በእኩልነት መርህ መገንባት ነው የሚያስከብረው፡፡ በታሪክ ያጋጠሙ ስብራቶችን ከትውልድ ወደ ትውልድ እያወራረሱ ለአገር የማይጠቅሙ ትርክቶች ላይ ተቸንክሮ መቅረት፣ ከ21ኛው ክፍለ ዘመን ፈጣን ግስጋሴና አስተሳሰብ ጋር አብሮ አይራመድም፡፡ በዓለም በሥልጣኔ ወደፊት ገፍተው ሀብታም የሆኑ አገሮች የታሪክ ዝንፈቶችን እያስተካከሉ ነው ወደ ዕድገት ያመሩት፡፡ የታሪክ ዝንፈቶችን አስተካክሎ ወደፊት መራመድ የሚቻለው፣ ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ በማስተናገድና በሁሉም ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ፈቃደኝነት ሲኖር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግሮች ሲያጋጥሙት ግጭት ከመቀስቀስ ይልቅ፣ እንደ ባህሉና እምነቱ በሽምግልና የሚፈታባቸው በርካታ ሥልቶች አሉት፡፡ ከእነዚህ አገር በቀል ሥልቶች በመማር ከግጭት አባዜ መውጣት ይለመድ፡፡

የኢትዮጵያ ሁሉም ፖለቲከኞች ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ፣ ሕዝቡ ውስጥ ያሉትን አገር በቀል የችግር መፍቻ ዘዴዎች ለመጠቀም ያለው ፍላጎት በጣም አናሳ ነው፡፡ ችግሮች ሲያጋጥሙ ከእምነት መሪዎችና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር ተቀምጦ በፅሞና ከመመካከር ይልቅ፣ ለአገሪቱም ሆነ ለሕዝቡ ባህሎችና ወጎች ዕውቅና ከማይሰጡ የውጭ ተሞክሮዎች ለመቅሰም የሚኬድበት ርቀት ያሳዝናል፡፡ ሌላው ቀርቶ የተለያዩ ሕጎች፣ መመርያዎችና ደንቦች ሲወጡ ጭምር የኢትዮጵያን ሕዝብ ሥነ ልቦና የማያማክሉ ልምዶች ይቀሰማሉ፡፡ ለምሳሌ ገዥው ፓርቲና ተፎካካሪዎቹ የመረረ ጠብ ውስጥ ሲገቡ ገላጋያቸው ፈረንጅ ነው፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ ውስጥ መከናወኑ ቢነገርም፣ ከማንም የበለጠ ግፊት ስታሳድር የነበረችው አሜሪካ ዋናዋ እንደነበረች ነው የሚታወቀው፡፡ ጦርነቱ ከመነሳቱ በፊትም ሆነ በኋላ አገር በቀል የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን ለመቀበል ምንም ፍላጎት አልነበረም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ተቀምጦ የሚነጋገርበት ዕድል ቢኖርና ፖለቲከኞች እረፍት ቢሰጣቸው፣ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም እንደሚሰፍን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በነፃነት የሚነጋገርበት ዕድል ቢሰጠው በዓላቱን በፍቅርና በመተሳሰብ እንደሚያከብራቸው ሁሉ፣ የአዘቦት ኑሮም ፍፁም ሰላማዊና የተረጋጋ እንዲሆን ትልቅ ትምህርት መስጠት ይችላል፡፡ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሚያዘጋጃቸው የውይይት መድረኮች የኢትዮጵያ ሕዝብ በትክክል ድምፁ የሚሰማበትን ጉዳይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡ ጥቂት ፖለቲከኞች ሲስማሙ ሰላም እየሰፈነ እነሱ በተኳረፉ ቁጥር አገር እየታመሰች መቀጠል የለበትም፡፡ አገራዊ ምክክሩ በርካታ ጉዳዮችን እያነሳ ውይይት ሲካሄድ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት የሚወክሉ ድምፆች በተለመዱ የፖለቲካ ተዋንያን እንዳይጠለፉ ጥረት ይደረግ፡፡ ሕዝባችን አብሮ መኖር ብቻ ሳይሆን እምነትና ብሔር ሳይገድበው ተጋብቶ ተዋልዷል፡፡ ይህንን ኅብረ ብሔራዊ ሕዝብ የማይወክሉ የታሪክ ትርክቶችን እያነበነቡ ልዩነት ማስፋት ማብቃት አለበት፡፡ ሕዝባችን በደስታውም ሆነ በሐዘኑ አብሮ መኖርን ያውቅበታል፡፡ የተጣላን እያስታረቀ፣ የሟችና የገዳይን ቤተሰቦች በደም መፈላለግ እያስቆመ፣ በዳይን እየገሰፀና ተበዳይን እያስካሰ በባህላዊ ዘዴዎች ፍትሕ ማስፈንም ይችልበታል፡፡ በበዓላት ወቅትም እየተደጋገፈ በፍቅር አብሮነቱን ማሳየት አንዱ ታላቅ እሴቱ ነው፡፡ ለዚህም ነው የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ የሚባለው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...

በሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ የታየው ተሞክሮ በሌሎች ምርቶች ላይም ይስፋፋ!

ሰሞኑን በኢትዮጵም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ግዙፍ ስለመሆኑ የተነገረለትን የለሚ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...