Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በጦርነት የወደመውን የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያ ለመጠገን ተቋራጮች ሊመረጡ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰበት የባህር ዳር አውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናል ምትክ እየተገነባለት መሆኑ ታውቋል

በትግራይ ክልል በተካሄደው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት የደረሰበትን የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያ መጠገን የሚችሉ የሥራ ተቋራጮችን የመምረጥ ሒደት ላይ እንደሆነ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አስታወቀ፡፡

አየር መንገዱ መስከረም 2 ቀን 2016 ዓ.ም. በድጋሚ ያወጣው የጨረታ ማስታወቂያ ደረጃ 2 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጮችን በመጋበዝ፣ የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያን መጠገን እንደሚፈልግ ይገልጻል፡፡

እስከ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም. በሚቆየው ጨረታ ለዲዛይንና ለግንባታ ውል ገብተው በጥገና ፕሮጀክቱ ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ ተቋራጮችን የጨረታ ሰነድ  እንዲወስዱ፣ ጨረታውም መስረከም 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ እንደሚከፈት ተመልክቷል፡፡

አየር መንገዱ በተመሳሳይ ጨረታውን በተጠናቀቀው 2015 ዓ.ም. በነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ሊያካሂድ አቅዶ አልተሳካለትም ነበር፡፡ ምክንያቱንም ለሪፖርተር በላከው የኢሜይል መልዕክት እንዳስታወቀው፣ ከኩባንያው የግዥ ፖሊሲ አኳያ በቂ ቁጥር ያላቸው ተወዳዳሪዎች በጨረታው ሳይሳተፉ ቀርተው በመሰረዙ ነው፡፡

በአክሱም የአውሮፕላን ማረፊያ ሁሉም መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት እንደደረሰ፣ የጥገና ዋናው ማዕቀፍም የአውሮፕላን መንደርደርያውን፣ የተርሚናል ሕንፃውን መጠገንና እንደ አዲስ ማደስ ላይ የሚያተኩር እንደሆነ አየር መንገዱ አስታውቋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስ፣ ጦርነቱ በ2015 ዓ.ም. ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነቱ ቢገታም፣ እስካሁን ድረስ አገልግሎት የማይሰጥ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከጦርነቱ በፊት ከአዲስ አበባ ወደ አክሱም በየዕለቱ እስከ ሁለት ጊዜ በረራዎች ይደረጉ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

በሚያዝያ ወር መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ የአውሮፕላን ማረፊያው ጥገናና መልሶ ግንባታ በርካታ መቶ ሚሊዮን ብሮችን ሊፈጅ እንደሚችል ለሪፖርተር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ትክክለኛ ወጪውን ለማወቅም ጥናት እየተደረገ እንደነበር መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

ሪፖርተር ጥናቱ ተጠናቆ እንደሆነና የሚያስፈልገውን ትክክለኛ የገንዘብ መጠን በሚመለከት ለአየር መንገድ ግሩፕ ላቀረበው ጥያቄ በኢሜይል በተሰጠው ምላሽ ጥናቱ መጠናቀቁን፣ የጥገናና መልሶ ግንባታ ሥራ ማዕቀፉም መለየቱ ተገልጿል፡፡

‹‹ጨረታው እየተካሄደ ስለሆነ የገንዘቡን መጠን የያዘ መረጃ ማጋራት በጨረታ ሒደቱ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፤›› ሲል ተቋሙ አስረድቷል፡፡

የደረሰው ጉዳትን በሚመለከት በተደረገው ጥናት መሠረት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ለጥገናውና ለመልሶ ግንባታ ሥራ በቂ በጀት መያዙንም አስታውቋል፡፡

ተቋራጭ ተመርጦ ሥራ ከጀመረ በኋላም በአምስት ወራት ጥገናው እንደሚጠናቀቅ፣ የጥገናው ሥራም ከተጠናቀቀ በኋላ በተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት ጥናት ተደርጎበት በረራ ወዲያው እንደሚጀምርም ተብራርቷል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ በባህር ዳር አውሮፕላን ማረፊያ የሚገኘው ተርሚናልም በሰሜኑ ጦርነት ግጭት ጉዳት ስለደረሰበት፣ በምትኩ ሌላ ተርሚናል እየተገነባለት እንደሆነ አየር መንገዱ ለሪፖርተር አሳውቋል፡፡

የበርካታ አውሮፕላን ማረፊያዎች ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገዱ ግሩፕ በሚያወጣው ፕሮግራም መሠረት ለአገር ውስጥ አውሮፕላን ማረፊያዎች ጥገና እንደሚያካሂድ፣ ለዚህም አስፈላጊ በጀቶችን እንደሚመድብ ገልጿል፡፡

‹‹በተወሰኑ አውሮፕላን ማረፊያዎች የሚደረጉ የአዳዲስ ሕንፃዎች ግንባታም አለ፤›› ሲል በላከው መልዕክት ጠቁሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች