አቶ አሸብር ወርቄ የኢትዮጵያ ባዮ ሜዲካል ኢንጂነሮችና ቴክኖሎጂስቶች ሙያ ማኅበር ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ የመጀመርያና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተወልደው ባደጉበት አሰላ ከተማ አጠናቀዋል፡፡ ከዚያም ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በባዮ ሜዲካል ኢንጂነሪንግ በመጀመርያ ዲግሪ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት የሆኑትን አቶ አሸብርን በማኅበሩ እንቅስቃሴና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ባዮ ሜዲካል ኢንጂነሮችና ቴክኖሎጂስቶች የሙያ ማኅበር አመሠራረትን በተመለከተ ቢገልጹልን፡፡
አቶ አሸብር፡- የማኅበሩ አመሠራረት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እያደገ የመጣ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ለመጀመርያ ጊዜ የሕክምና ላቦራቶሪ ማሽነሮችን የሚጠግኑ ኢንጂነሮች ተሰብስበው የኢትዮጵያ ላቦራቶሪ ኢክዩፕመንት አሶሴሽን፣ ቀጥሎም የኢትዮጵያ ባዮ ሜዲካል ኢንጂነሮች የሙያ ማኅበርን መሠረቱ፡፡ ይህንን ማኅበር የመሠረቱትም ከ20 የማይበልጡ የባዮ ሜዲካል ኢንጂነሮች ናቸው፡፡ ይህ ከሆነና በርካታ የባዮ ሜዲካል ኢንጂነሮች ከጅማና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች እየተመረቁ፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ የሚገኘው ተግባረዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የሦስት ዓመት የባዮ ሜዲካል ቴክኒሽያን ሥልጠና ሲጀምር የባዮ ሜዲካል ኢንጂነሮችና ቴክኖሎጂስቶች ቁጥር ከፍ እያለና እየጨመረ መጣ፡፡ በዚህም የተነሳ ማኅበሩ በ2008 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔው ቴክኖሎጂስቶችን በአባልነት መቀበል አለበት ከሚል ስምምነት ላይ ደረሰ፡፡ በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ ባዮ ሜዲካል ኢንጂነሮችና ቴክኖሎጂስቶች የሙያ ማኅበር ተብሎ እንደገና ተመሠረተ፡፡ ከዚህ አኳያ ማኅበሩ በሙያ ደረጃ ኢንጂነሮችና ቴክኖሎጂስቶች የሆኑ ከ500 በላይ አባላትን አቅፏል፡፡ የኢንተርናሽናል ፌዴሬሽን ፎር ሜዲካል ኤንድ ባዮሎጂካል ኢንጂነሪንግ አባል ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የባዮ ሜዲካል ኢንጂነሪንግ ሙያ ሥልጠና እንዴት እንደተጀመረና በአሁኑ ጊዜ በምን ደረጃ እንዳለ ቢገልጹልን?
አቶ አሸብር፡- የባዮ ሜዲካል ኢንጂነሪንግ ሙያ በኢትዮጵያ አዲስ ሲሆን፣ በሥራ ላይ ከዋለም 15 ዓመት ይሆነዋል፡፡ ሙያም በመጀመርያ ዲግሪ መርሐ ግብር የተጀመረው በጅማ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ወጣቶችን ተቀብሎ የአምስት ዓመት ትምህርት የጀመረውም በ2001 ዓ.ም. ሲሆን፣ እነዚሁ የመጀመርያዎቹ ወጣቶች የተመረቁት በ2006 ዓ.ም. ነው፡፡ ከዚያም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዚሁ ሙያ ላይ ያተኮረ የአምስት ዓመት የትምህርት ፕሮግራም አዘጋጅቶ በመጀመርያ ዲግሪ ወጣቶችን ማሠልጠን ጀመረ፡፡ ሥልጠና የሚሰጡትም ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ከበፊቱ በአሁኑ ጊዜ ጨምሯል፡፡ በዚህም መሠረት የጎንደር፣ የወሎና የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች በመጀመርያ ዲግሪ፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ በመጀመርያና በሁለተኛ ዲግሪ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመጀመርያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር ትምህርቱን በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡
ሪፖርተር፡- የባዮ ሜዲካል ኢንጂነሪንግ ሙያ ከጤናው ዘርፍ አኳያ ሲታይ ፋይዳው ምን ያህል ነው?
አቶ አሸብር፡- መጀመርያ ማኅበሩ እንደ ዋና ዓላማ አድርጎ የተነሳው ሙያውን በማስተዋወቅ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ምክንያቱም ሙያው አዲስ ከመሆኑ የተነሳ በየሆስፒታሉ የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ሲበላሹ ብቻ በመጠገን ነው የሚታወቀው፡፡ ነገር ግን ሙያው ከዚህ ከፍ ያለ ከመሆኑም ባሻገር በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም ከፍተኛ ሥፍራ የሚሰጠው ሆኗል፡፡ ምክንያቱም የሕክምናው ዘርፍ በቴክኖሎጂ መታገዝ አለበት፡፡ ቴክኖሎጂ ሲባል ደግሞ በዋነኛነት የሚነሳው የሕክምና መገልገያ መሣሪያ ነወ፡፡ ይህም ማለት መሣሪያዎቹን በትክክል ኦፕሬት (መቆጣጠር)፣ ኢንስቶል (መትከል) እና ዲዛይን ማድረግ የሚችል ባለሙያ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ባለሙያው ደግሞ የባዮ ሜዲካል ኢንጂነር ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ ሙያው በእጅጉ አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም፡፡ ስለሆነም ቀደም ባሉት ዓመታት የተበላሹ መሣሪያዎችን በመጠገን ብቻ ተወስኖ የነበረው ሙያ በአሁኑ ጊዜ ግዢዎች ከመፈጸማቸው በፊት ዲዛይን፣ አሴስመንት (ግምገማ) እና ኢንስቶል ማድረግንና ሌሎችንም ተግባራት ያከናውናል፡፡
ሪፖርተር፡- የባዮ ሜዲካል ኢንጂነሪንግ ሥልጠና የሚሰጡት ዩኒቨርሲቲዎች ገበያው የሚፈልገውን የሰው ኃይል እየሠለጠኑ ለመሆኑ እንዴት ይታወቃል? በዚህ ዙሪያ ማኅበሩ የሚጠበቅበትን ምክረ ሐሳብ በመስጠት ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው?
አቶ አሸብር፡- የባዮ ሜዲካል ኢንጂነሪንግ ሥልጠና ለሚሰጡ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያወጧቸው ካሪኩለሞችና አሠለጣጠናቸው ገበያ ተኮር ወይም ገበያው በሚፈልገው መልክ መካሄዱን በተመለከተ ማኅበሩ ምክረ ሐሳብ እየሰጣቸው ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ለአባሎቻችን ተከታታይ የሆነ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየሰጠን ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜም ለጤና ሚኒስቴርም የሕክምና ሜዲካል መሣሪያን በተመለከተ እንዲሁ ምክረ ሐሳብ እንሰጣለን፡፡ ምክረ ሐሳቡም የሕክምና መሣሪያዎች አጠቃቀምና አያያዝንም ጭምር ያካተተ ነው፡፡ በአሁን ወቅት ደግሞ የሕክምና መገልገያ መሣሪያ ፖሊሲ በረቂቅ ደረጃ ተዘጋጅቷል፡፡ በዚህም ምክረ ሐሳቡ እየሰጠንና አብረን እየሠራን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የምትሰጧቸው ምክረ ሐሳቦች የቱን ያህል ነው ተቀባይነታቸው?
አቶ አሸብር፡- ተቀባይነቱ በጥሩ መልኩ ነው፡፡ እንደሚታወቀው እንዲህ ዓይነት ነፃ ምክረ ሐሳብ ለሥራው ስኬታማነት ይጠቅማል ከሚል እንጂ ሌላ ዓላማ የለንም፡፡ ሥራውንና ባለሙያውን ማገናኘት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በጤናው ዘርፍ ከሚመደበው በጀት አብዛኛው በሕክምና መሣሪያዎች ግዥ ላይ ያለመ ነው፡፡ አንድ ሲቲ ስካን ለመግዛት እስከ 100 ሚሊዮን ብር የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ነው ነን፡፡ ስለዚህ ይህን ያህል ገንዘብ ፈስሶበት ወደ አገር ውስጥ የገባ መሣሪያ በትክክል ሥራ ላይ የማይውል ከሆነ ለአገሪቷ ትልቅ ኪሣራ ያስከትላል፡፡ ስለሆነም የዓለም ጤና ድርጅት በወጣው ደረጃ መሠረት መሣሪያው ባግባቡ ካልተመራ ዕዳው/ውጤቱ በአገር ደረጃ የከፋ ነው የሚሆነው፡፡
ሪፖርተር፡- የጤና ተቋማት ውስጥ አንዳንዶቹ በብልሽት ምክንያት፣ ሌሎቹ ደግሞ አዲስ ቢሆኑም አገልግሎት ሳይሰጡ ተቀምጠውና አቧራ ለብሰው የሚገኙ የሕክምና መሣሪያዎች አሉ፡፡ ይህ የሆነው ከምን አንፃር ነው?
አቶ አሸብር፡- ‹‹ሔልዝ ኬር ቴክኖሎጂ›› (የጤና አጠባበቅ ቴክኖሎጂ) ውስጥ በዓለም ጤና ድርጅት ተቀባይነት ያላቸው ስምንት ክፍሎች አሉ፡፡ ከእነዚሁም መካከል አንደኛው ፕላኒንግ ኤንድ አሴስመንት ይባላል፡፡ ይህም ማለት ሕክምና መሣሪያ ስላገኘን ብቻ መግዛት ሳይሆን፣ ለመግዛት ተገቢ የሆነ ፕላን ያስፈልጋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሚፈለገው ባለሙያ ሳይኖር የሕክምና መገልገያ መሣሪያ ተገዝቶ ምንም ጥቅም ሳይሰጥ መደርደርያ ላይ ተቀምጦ ይታያል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ውስብስብ (ሶፎስትኬትድ) የሆነ መሣሪያ በሪፈራል ሆስፒታል ብቻ መገኘት ሲገባው የታካሚ ፍሰት እምብዛም በማይታይበት የመጀመርያ ደረጃ (ፕራይመሪ) ሆስፒታል ውስጥ ይገኛል፡፡ እንደ እነዚህ ዓይነቶቹን ችግሮች ማስወገድ የሚቻለው ጥንቃቄ የተሞላበት የግዥና የፕላን ግምገማ ሥርዓት ሲከናነወን ነው፡፡ ፕላን ከተደረገ በኋላ ምን ዓይነት ቴክኖሎጂ ነው የሚያስፈልገው የሚለው ይታያል፡፡ ከዚያም ተፈላጊው ቴክኖሎጂ ይመረጥና ገዥው ይፈጸማል፡፡ የተገዛው መሣሪያ ልዩ ልዩ አክሰሰሪዎችና የመለዋወጫ ዕቃዎችን ያካተተ መሆን ይገባዋል፡፡ የተገዛውም መሣሪያ ወደ ጤና ተቋም ተወስዶ ኢንስቶል መደረግ አለበት፡፡ በመሣሪያው ለሚለገሉ የጤና ባለሙያዎች ሥልጠና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ኢንስቶል የሚደረግበት ክፍል ተስማሚ መሆኑ በቅድሚያ ይረጋገጣል፡፡ ለምሳሌ ያህል ‹‹ኤምአር›› መሣሪያ የሚቀመጥበት ክፍል ቬንትሌተር ያስፈልገዋል፡፡ የሚያገኘውም የኤሌክትሪክ ኃይል የተቆራረጠ መሆን የለበትም፡፡ ክፍሉ ጨረራ ማስተላለፍ የለበትም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የተበላሹት የሕክምና መሣሪያዎች ትልቁ ችግራቸው የጥገና በጀት አልተመደበላቸውም፡፡ ይህም በመሆኑ ሳይጠገኑ የተቀመጡት በባዮ ሜዲካል ኢንጂነሩ ችግር ሳይሆን በጀት ሳይመደብላቸው በመቅረቱ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ተስማሚና ምቹ የሆኑ የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ሲባል ምን ማለት ነው?
አቶ አሸብር፡- ለአገራችን ተስማሚ የሆኑ የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎችን መምረጥ ግድ ይላል፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ በከፍተኛ ቦታ ላይ ነው የምትገኘው፡፡ ይህም ማለት ግፊቱ በጣም ዝቅ ያለ ነው፡፡ ስለሆነም ዝቅ ባለ መሬት ዲዛይን ተደርጎ የተመረተ መሣሪያ ወደ አዲስ አበባ ቢገባ በሕክምና ምርመራ ላይ የሚገኘው ውጤት የተሳሳተ (ፎልስ ሪዲንግ) ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ የሕክምና ውሳኔን ሊያዛባ ይችላል፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ ችግር መላቀቅ የሚቻለው ግዥው በሚከናወንበት ጊዜ መሣሪያው ከአገራችን መልክዓ ምድር፣ ቴምፕሬቸር፣ አልቲቲዩድና ኤሌክትሪካል ሲስተም ጋር የሚስማማ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ያህል የአገራችን ኤሌክትሪካል ሲስተም 220 ቮልት ነው፡፡ የምንጠቀመው መሣሪያ የአሜሪካን ቢሆንና ያን መሣሪያ አምጥተን ብንሰካው መሣሪያ ወዲያውኑ ይበላሻል፡፡ ይህም የሚሆንበት ምክንያት አሜሪካን ያላት 110 ቮልት ነው፡፡ አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር የሕክምና መሣሪያዎችን መምረጥ፣ በአግባቡ ኢንስቶል ማድረግና በመሣሪያው ለሚገለገሉ የሕክምና ባለሙያዎች ሥልጠና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ይህን ሁሉ የሚያደርገው የባዮ ሜዲካል ኢንጂነር ነው፡፡