Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልበዓለ መስቀሉና ትውፊቱ

በዓለ መስቀሉና ትውፊቱ

ቀን:

በየዓመቱ ወቅታቸውን ጠብቀው የሚከናወኑ ሃይማኖታዊ በዓላት በተለይ በኢትዮጵያ ልዩ ትኩረት ሲሰጣቸው ይስተዋላል፡፡ ሁሉም ሃይማኖቶች ሥርዓቱ በሚፈቀደውና የሃይማኖት አባቶች በሚያስተላልፉት መመሪያ መሠረት ወቅታቸውን ጠብቀው በድምቀት ይከበራሉ፡፡

በኢትዮጵያ በተለይ ሃይማኖታዊ በዓላት ሲከበሩ ምዕመኑ የሚያሳየው ሥነ ሥርዓት አለባበስና አመጋገብ የብዙዎችን ቀልብ ይስባል፡፡

በተለይ ደግሞ በዓሉ በአደባባይ የሚከበር ሲሆን፣ ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ በስተጀርባ የሚከወኑ ልዩ ልዩ ሁነቶች በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎችን ከማስደመማቸው ባለፈ፣ የአገሪቱን ባህልና ቋንቋ ጭፈራና የመሳሰሉትን ትውፊቶች ሁሉም በአግራሞት እንዲያስተውሏቸው ያደርጋሉ፡፡

በዓለ መስቀሉና ትውፊቱ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የበዓሉን ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ትውፊታዊ ገጽታ በጥቂቱ

ሃይማኖታዊ በዓላት በአደባባይ ሲከበሩ በሃይማኖቱ ጥላ ሥር ያሉ ምዕመናንና ከሃይማኖቱ ውጭ ያሉ ሰዎች እርስ በርሳቸው ይጠያየቃሉ፣ ያለው ለሌለው ያካፍላል፡፡ ከዚህ ባሻገር ዘፈንና ጭፈራው የባህል አለባበሱ በኅብረት ደምቀው እንዲውሉ ያደርጋል፡፡

ከእነዚህ በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት መካከል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ድምቀት የሚከበረው የመስቀል በዓልና መገለጫው ደመራ ይገኝበታል፡፡

የመስቀል ክብረ በዓል

በክርስቲያናዊ የዘመን መቁጠሪያ ካሉት የመስቀል በዓላት አንዱ በመስከረም ወር ውስጥ የሚውለው ነው፡፡ ከአንድ ሺሕ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ሁለት ዓመታት በፊት፣ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል የተገኘበት በዓል፣ ከዛሬ መስከረም 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት በኢትዮጵያ ክርስቲያኖች እየተከበረ ነው፡፡

በዓለ መስቀሉና ትውፊቱ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የበዓሉን ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ትውፊታዊ ገጽታ በጥቂቱ

መስቀሉ በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት በቅድስት እሌኒ አማካይነት በ326 ዓ.ም. መገኘቱ ይወሳል፡፡ ድርሳናት እንደሚያመለክቱት፣ የእሌኒ ልጅ ቆስጠንጢኖስ በጌታ ኢየሱስ መካነ መቃብርና በቀራንዮ የመሠረተው ቤተክርስቲያን ቅዳሴ ቤቱ የተከበረው መስከረም 16 ቀን 335 ዓ.ም. ነበር፡፡

የመስቀል በዓል፣ በኢትዮጵያ ለሁለት ሺሕ ግድም ዓመታት ሲከበር ኖሯል፡፡ የበዓሉን ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ትውፊታዊ ገጽታ የተመለከተው ዓለም አቀፉ የባህል ተቋም ዩኔስኮ የዓለም ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ አድርጎ መመዝገቡ ይታወቃል፡፡

 ክብረ በዓሉ በትግራይና በአማራና ‹‹መስቀል›› ሲባል፣ በተለያዩ ብሔረሰቦች እንደ አካባቢው ቋንቋ የተለያየ መጠሪያ አለው፡፡ ለምሳሌ በኦሮሞ ‹‹ጉባ›› ወይም ‹‹መስቀላ››፣ በሐዲያ፣ በወላይታ፣ በዳውሮ፣ በጋሞ፣ በጎፋ ‹‹መስቀላ››፣ በከምባታ ‹‹መሳላ››፣ በየም ‹‹ሔቦ››፣ በጉራጌ ‹‹መስቀር››፣ በካፊቾና ሻኪቾ ‹‹መሽቀሮ›› ይባላል፡፡ 

የመስቀል ክብረ በዓል በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ በድምቀት የሚከበር ብሔራዊ በዓል ነው፡፡ በዓሉ የመስቀሉ አንድ ክንፍ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በግሸን ዓምባ መቀመጥ ጋር ቢገናኝም፣ እያንዳንዱ ብሔረሰብ በዓሉን የሚያከብርበት እንደ ባህሉ፣ አኗኗሩ፣ ወጉ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ገጽታው የራሱ መንገድ አለው፡፡

የኢትዮጵያ የመስቀል በዓል መለያው ደመራው ነው፡፡ ደመራ ንግሥት እሌኒ፣ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል  ከተቀበረበት ለማውጣት በኢየሩሳሌም ቀራንዮ በሚባል አካባቢ በጎልጎታ ቁፋሮ ያስጀመረችበትን ቀን ለማሰብ የሚከበር ሥነ ሥርዓት ነው፡፡

የመስቀል በዓል ከዋዜማው ከዛሬው መስከረም 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ደመራ የሚደመርበት በሌሎቹ በተለይ በሰሜን በነገው ዕለት መስከረም 17 ቀን የሚደመርበት፣ በዓሉም በድምቀት በሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚከወንበት ሆኖ ይውላል፡፡

‹‹የመስቀረንዳ በቃያንዳ››

በዓሉ ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሻገር ያለው ባህላዊ ትውፊቱ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላው አካባቢ የተለያየ ሆኖ ሲቀርብ ይስተዋላል፡፡

በተለይ መስቀል በጉራጌ ብሔረሰብ የተለየ ስሜትና ውበት ድምቀትና ታላቅ ድባብ ጎልቶና ሰፍቶ የሚታይበት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

በዓሉ በጉራጌ ብሔረሰብ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሲሆን፣ ከፍተኛ የሆነ ማኅበረሰባዊ ፋይዳ እንዳለውም ይነገራል፡፡ የብሔረሰቡ ተወላጆች ከሩቅም ከቅርብም ያሉት የሚሰባሰቡበት፣ ተነፋፍቀው የከረሙ ሰዎች የሚገናኙበት፣ ማኅበራዊ ችግሮቻቸው ላይ ሰብሰብ ብለው የሚወያዩበት፣ የሚመክሩበት፣ ወጣቶች የሚተጫጩበት፣ የተቀያየሙ ሰዎች ይቅር የሚባባሉበት ታላቅ በዓል ነው፡፡

በአገር ሰላምና ፍቅር ይዘንብ ዘንድ መተጋገዝና መረዳዳት እንዲኖር የሚፀለይበት ሲሆን፣ የተራቡና በችግር ላይ ያሉ ሰዎች የሚጠያየቁበት፣ ወጣቶች ከሽማግሌዎች ምርቃትን የሚቀበሉበት፣ ጎልማሶች ከአባቶቻቸው ኃላፊነትን የሚረከቡበትና ሌሎች በርካታ ማኅበራዊና ባህላዊ ክንውኖች የሚደረጉበት በዓል ነው፡፡

በዓሉ በጉራጌ ብሔረሰብ ዘንድ ያለውን የአከባበር ሥርዓት ከምግብ አዘገጃጀት ጀምሮ አጠቃላይ ሰፊ ጊዜን ወስዶ ስለሚደረገው ክንውን፣ ያለውን አለባበስና ባህላዊ ጭፈራ፣ እንዲሁም የበዓሉን ባህላዊ ዕሴቶች ለሌሎች ኢትዮጵያውያንና ለውጭ ማኅበረሰብ በተለያዩ ዝግጅቶች በማቅረብ እያስተዋወቁ እንደሚገኙ የዮድ አቢሲኒያ የባህል ምግብ ቤት ባለቤት የሆኑት አቶ ትዕዛዙ ኮሬ ተናግረዋል፡፡

‹‹ድርጅታችን ዮድ አቢሲኒያ በዓመት ውስጥ ባሉት 365 ቀናት የአገራችንን ወግና ባህል፣ ታሪክና ቅርስ ሲያስተዋውቅና የአገርን ገጽታ ሲገነባ ቆይቶ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የዓመቱን 365ኛዋን ቀን ላፈራኝ የጉራጌ ብሔረሰብ ባህል ዕሴቶች በመጠኑም ቢሆን በማስተዋወቅ እገኛለሁ፤›› ያሉት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. በባህል አዳራሻቸው ባዘጋጁት መሰናዶ ላይ ነው፡፡

ላለፉት ሁለት አሠርታት ከተለያዩ አገሮች ለሚመጡ የኢትዮጵያ ወዳጆች፣ የአገር መሪዎች፣ ዲፕሎማቶችና በሺዎች የሚቆጠሩ ከየአገሩ ለሚመጡ እንግዶችና ለአገር ውስጥ እንግዶች አገራዊ ባህል ሲያስተዋውቁ መክረማቸውን ገልጸዋል፡፡

ላለፉት 12 ዓመታት ሲያከናውን እንደነበረው ዘንድሮም መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የብሔረሰቡ ተወላጆችና ሌሎች በርካታ እንግዶች የተገኙበት መርሐ ግብር ‹‹የመስቀረንዳ በቃያንዳ›› በሚል መሪ ቃል ነበር የተከበረው፡፡

የመስቀል በዓል በመንግሥታቱ ድርጅት የባህል ተቋም ዩኔስኮ በቅርስነት ሲመዘገብ ድርጅታቸው የበኩሉን ድርሻ እንደተወጣ የተናገሩት አቶ ትዕዛዙ ከተመዘገበ በኋላ አከባበሩ ላይ መቀዝቀዝ እንዳይኖር ሰፊ ሥራን እየሠሩ እንደሚገኙ አክለዋል፡፡

 ከምዝገባው በኋላም ባህልና ወጉን በሚመጥን ሁኔታ በልዩ ልዩ ሁነቶች ሲያከብሩ መቆየታቸውን ገልጸው ዘንድሮም በተለያዩ ዝግጅቶች ማክበራቸውን አውስተዋል፡፡

የጉራጌ ዞን የመንግሥት ኮሚንኬሽን በዓሉን በማስመልከት በተደረገ ፌስቲቫል ላይ የመስቀል በዓል የጉራጌ ብሔር የመቻቻል፣ የአብሮነትና ማንነቱን የሚገለጽበት በመሆኑ ትውልዱ ይህንን አጠናክሮ ማስቀጠል አለበት ብሏል፡፡

ከዚህም ባሻገር የጉራጌ የክትፎ አዘገጃጀት፣ ባህላዊ የቤት አሠራር፣ የጉራጌ የመንደር (ጀፎረ) አሠራርና ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት (ቂጫ) በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ ዞኑ ጥያቄ ያቀረበ መሆኑንና የሚመለከተው አካልም ጥያቄውን ተቀብሎ በትኩረት እየሠራ መሆኑም ተመላክቷል።

  • (ለመጣጥፉ ሔኖክ ያሬድ አስተዋጽኦ አድርጓል)
spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...