Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርማን በማን ላይ ተስፋ ይኑረው?

ማን በማን ላይ ተስፋ ይኑረው?

ቀን:

በአንድነት ኃይሉ

ችግሮቻችንን ለይተን ካወቅን መፍትሔውንና ተስፋ የምናደርግበትን ማወቅ እንችላለን፡፡ መሪዎቻችን በምን ጉዳይ ላይ ምን ያህል በሕዝባችን ተስፋ ያድርጉ? ሕዝቡስ ምን ያህልና በምን ጉዳይ ላይ መሪውን ተስፋ ያድርግ? አንዳችን አንዳችን ላይ ተስፋ ማድረግ የምንችለው በትክክል ችግራችንን ስናውቅ፣ ችግራችንን ለመቅረፍ እየተጓዝንበት ያለውን መንገድ በትክክል ካወቅነው ነው፡፡ አለበለዚያ አሁንም በድፍኑ ሁሉንም ጉዳያችንን የምናቀላቅለው ከሆነ፣ አንድም ነገር ለቁምነገር ሳናበቃ ጊዜ እናባክናለን፡፡ በአብዛኛው ሰው የሚነገሩ ችግሮቻችንና የሚጠበቀው ውጤት ላሉብን ፈተናዎች ምክንያትና ትክክለኛው መፍትሔ ነው ብዬ አላምንም፡፡ በአብዛኛው የሚነገረው ፊት ለፊት የገጠመን እንጂ የችግሩን ምክንያት ከሥሩ አልተረዳንም፡፡

ለምሳሌ ሙስናን ብናነሳ የሚያደርሰውን ጉዳት፣ የተፈጠረውን ችግር ብናውቅም ሙስና በሰው ሕይወት ውስጥ ሊኖር የቻለበትን ምክንያት ካላወቅን ትክክለኛውን መፍትሔ ማስቀመጥ አንችልም፡፡ ደሃ መሆናችንን እንጂ ትክክለኛውን ምክንያት ካላወቅን ድህነታችንን እያስታመምን እንጂ ማዳን ስለማንችል፣ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አንችልም፡፡ እኛ ጥሩ መሪና ጥሩ አገር እንዲኖረን እንጂ፣ ጥሩ መሪና ጥሩ አገር ለመገንባት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ያለመኖር ምክንያት ላይ የተግባባን አይመስለኝም፡፡ በዚህም ምክንያት ነው መልካሙን ለመሥራት ብንለፋና ብንመኝ ሊሳካልን ያልቻለው፡፡ ምክንያቱም ያለብን ችግር ሌላ፣ የምንፈልገው ሌላ፡፡ ያለብን ኃላፊነት ሌላ፣ የሚያስፈልገን ሌላ፡፡ የምንፈልገውም ሌላ ነው፡፡

ትክክለኛውን ችግራችንን ካላወቅን ትክክለኛ መፍትሔውን እንደማናገኝና ማናችንም የመፍትሔው አካል መሆን እንደማንችል ግልጽ ነው፡፡ ችግራችን የዴሞክራሲ ማጣት ሊሆን ይችላል፡፡ ትክክለኛው መፍትሔ የሚገኘው ለምን ልናጣው ቻልን የሚለውን መመለስ ስንችል ነው፡፡ ደሃ መሆናችን ግልጽ ነው፡፡ መፍትሔው ግን እንዴት ልንሆን ቻልን ብለን መልሱን ካገኘን የሁላችንንም ኃላፊነት እናውቃለን፡፡ ሥራ ማጣታችን ሳይሆን ለምን ሥራ አጣን የሚለው ከገባን፣ ለሥራ ማጣታችን ትክክለኛ መፍትሔውንና የሥራ ባለቤት ለመሆን ከማን ምን ይጠበቃል? ማን ምን ማድረግ አለበት? የሚለውን በትክክል እናውቃለን፡፡ አለበለዚያ ዴሞክራሲ ላይ፣ ሙስና ላይ፣ ድህነት ላይ መሟገት ጨለማ ላይ እንደ ማፍጠጥ ይቆጠራል፡፡

በርካታ ችግሮች ይኖሩብን ይሆናል፡፡ ምክንያቱ ላይ ካተኮርን ችግሮቻችንን እያስታመምን ሳይሆን እያዳንን እንሄዳለን፡፡ ችግሩ ላይ ብቻ ካተኮርን በሙስና ምክንያት ሰው እንቀያይር ይሆናል፡፡ ሙስና ግን አይቀርም፡፡ ድህነቱን እንለዋውጠው ይሆናል፡፡ ለውጥ ግን አይኖርም፡፡ ዛሬ ድህነት ውስጥ የገባንበትን ምክንያት በትክክል ማስቀመጥ ባይቻል፣ ከድህነት ለመውጣት የሁሉም ሰው ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን የፍላጎት ድምር ውጤት የሚያስፈልግበት ደረጃ ደርሰናል፡፡

ምክንያቱ በአንድ አገር ውስጥ ስለምንኖርና የአገር ባለቤቶች ስለሆንን ብቻ ሳይሆን፣ ለረዥም ዘመናት የተጓዝንበት መንገድ የተሳሳተ ዕውቀት ባለቤቶች አድርጎናል፡፡ ከዚህ ጎዳና ወጥተን ወደ ራሳችን ለመመለስ የእያንዳንዱ ሰው ቤት ሊንኳኳ ይችላል፡፡ በርካታ ነገሮችን ለምደናል፡፡ በእጃችን ያሉ በርካታ የሕይወታችን ግብዓት የሆኑ ነገሮች ያለብንን ድህነት እንድናሸንፈው ሳይሆን፣ እያስታመምነው እንድንኖር እያደረጉን ነው፡፡ ድህነታችንን ማስታመም ሳይሆን ለማዳን ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ ኃላፊነት አለ፡፡ በዚህ ከተግባባን ከማን ምን እንደሚጠበቅ፣ ማን ምን ላይ ተስፋ ማድረግ እንዳለበት፣ ምን የማን ኃላፊነት እንደሆነ መግባባት እንችላለን፡፡ ተስፋችንን፣ ኃላፊነታችንና ውጤቱን ስናውቅ ለውጥን የምንገመግምበት ዕውቀታችን ትክክል ይሆናል፡፡ መግባባት ደግሞ ይኼ ነው፡፡ ኃላፊነትን፣ ግዴታንና መብትን ለይቶ በማስቀመጥ፡፡

የሚታየውን ማየት፣ የሚነገረውን ማዳመጥ መቻል ቢያንስ ዋና ዋና የሚባሉ ችግሮቻችን ላይና የምንፈልገው መፍትሔ ላይ መግባባት ያስችለናል፡፡ በአጠቃላይ ያሉብንን ችግሮች በሁለት ብንከፍላቸው አንደኛው በመነጋገርና በውይይት የሚፈቱ፣ ሁለተኛው ተገቢና ተፈላጊ የሆነ ሐሳብን በመጠቀም ብቻ በውይይት የምንፈታቸው ችግሮች የሚፈልጉት ቁርጠኝነትና ቀናነት ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ማንም እንደ መፍትሔ ከራሱ የሚጨምርባቸው አዳዲስ ሐሳቦች የሉም፡፡ ሁሉም የመፍትሔ ሐሳቦች ያሉና የነበሩ፣ ነገር ግን በሰዎች ቀናነት ማነስ ወይም በሌላ ችግር የተፈጠሩልን ናቸው፡፡ ለምሳሌ ነፃነት፣ የሕግ የበላይነት፣ ዴሞክራሲ፣ እኩልነት፣ ወዘተ. የሚባሉ ችግሮቻችንን ለመቅረፍ ግብዓቱ ሁሉም ጋር ስላለ፣ መፍትሔውም የዚያኑ ያህል በቁርጠኛ ውሳኔ ብቻ የሚፈቱ ናቸው፡፡ በሥራና በተግባር የሚመለሱ ችግሮቻችን ውስጥ ትክክለኛው ምክንያት ምን እንደሆነ ሳይገባን ማንም ማንንም ተስፋ ቢያደርግ ትርፉ ኪሳራ ነው፡፡

ደሃ የሆንነው ከኋላቀርነት የተላቀቅንበትና ለመውጣት የመረጥነው መንገድ የራሳችን ስላልሆነ ነው፡፡ ያኔ ኋላቀር በነበርንበት ዘመን የነበርንበት ሕይወት፣ ንቃተ ህሊና፣ መንገድ፣ ወዘተ በራሳችን መንገድ የራሳችንን መሥራት ሲገባን የሌሎችን መጠቀም መጀመራችን፣ ያለንን ማሻሻል ትተን የሌላውን ሕይወት መልመዳችን፣ በትክክለኛው ማንነታችን ምትክ ሌላ ማንነት መቀበላችን ውጤቱ ድህነት ብቻ ሳይሆን፣ ሌላ ማንነት ይዘን ድህነታችንን ተለማምደነው ከላያችን ላይ ለማስወገድ ፈራን፡፡

ስለዚህ ድህነትን እያስታመምን እየኖርን ነው፡፡ ድህነታችንን ልናድነው ከፈለግን ዋናው ነገር በድህነታችን ምክንያትና መፍትሔ ላይ በትክክል መግባባት አለብን፡፡ ማንም ስለመራን፣ የአገር ባለቤቶች ስለሆንን፣ መፍትሔ ስለምንፈልግ ብቻ ሳይሆን የምንመራበት መንገድ ሲገባን ነው ለመሪያችን፣ ለአገራችን፣ ለሕዝባችን፣ ለችግራችን፣ ለመፍትሔያችን ግብዓት መሆን የምንችለው፡፡ እኛ ቢያንስ ከ100 ዓመታት ወዲህ የምንጓዝበት መንገድ ትክክል አይደለም፡፡ መሪና ተመሪ ሳይግባቡ ነው የሚኖሩት፡፡ ከዛሬ 100 ዓመታት በፊት መንገድ ስተናል፡፡

ዛሬ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ውስጥ ያለው ፍላጎት በበርካታ ዕውቀቶች የተምታታ ነው፡፡ ግማሹ ለድህነታችን ምክንያት የሚሆን ነው፡፡ ለምናመጣው ለውጥ ደግሞ መሰናክል፡፡ በዚህ ምክንያት የምንፈልገውና የሚያስፈልገን ተምታቷል፡፡ ከድህነት መውጣት ብንፈልግም የምንጠቀምበትና የምንጓዝበት ግብዓት ግን ትክክል አይደለም፡፡ አገር ከድህነት መውጣት የምትችለው ማምረት ስትችል ብቻ ነው፡፡ አገር ልማትን በመግዛት ድህነትን ታስታምማለች እንጂ፣ ከድህነት መዳን አትችልም፡፡ አገር አምራች ሆና ከድህነት ለመውጣት ቢያንስ 100 ዓመታት የተጓዝንበትን መንገድ በመፈተሽ ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቀው ነገር በትክክል ታውቆ፣ ሁሉም ተስፋ የሚያደርግበት ዕውቀት ማስጨበጥ እስካልቻልን አሁንም ልፋት ነው የሚሆንብን፡፡

ዛሬ ሁለት ምርጫ የለንም፣ ያለን አንድ ምርጫ ነው፡፡ ምክንያቱም በጣም ረፍዶብናል ወደራሳችን መመለስ የምርጫ ጉዳይ አይደለም፡፡ ዕውቀታችን ባደገ ቁጥር የሕዝብን ጥያቄ የመመለሳችን አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከበደ እንደመጣ ሁሉም የሚያውቀው ነው፡፡ ወደ ራሳችን ለመመለስ ጎዳናችንን ለማስተካከል ምን እናድርግ? ከእያንዳንዳችን ምንድነው የሚጠበቀው? ዕውቀታችንንና ፍላጎታችንን በማስተካከል ወደ ራሳችን የሕይወት ጎዳና መመለስ አለብን፡፡ ዛሬ በየትኛውም አገር ጠንካራ መሪ ሳይሆን ጠንካራ ሕዝብ ነው አገሩን ከድህነት ማውጣት የሚችለው፡፡ የበለጠ አቅምና ኃላፊነት ያለበት ለአገሩ ሊተገብረው የሚገባ በርካታ ተግባራት ያሉበት ደሃው ሕዝብ ነው፡፡ ምክንያቱም ለየትኛውም ጠንካራ መሪ ከድህነት ለመውጣት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት፣ ግዴታና መብት ጠንቅቆ የሚያውቅ ጠንካራ ሕዝብ ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ ጠንካራ ሕዝብና የሚያስፈልጋትን የሚያውቅ ጠንካራ መሪ ያስፈልጋታል፡፡ አንድ አገር ለመባል ሕዝብ፣ መሪ፣ ሕግ፣ ሰንደቅ ዓላማ፣ ወዘተ. እንደሚያስፈልጋት ሁሉ፣ አንድ ሕዝብና መሪ አገሩን ለመገንባት ከገዛ ገንዘቡ፣ ዕውቀቱ፣ ሕጉ፣ ገቢው፣ ወዘተ. ውጪ ምንም ህልውና የለውም፡፡ የወጪ ንግድ፣ የውጭ ግንኙነት፣ የዓለም ገበያ፣ ወዘተ አያስፈልጉም እያልኩ እንዳልሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ አገር ግን አገር ለመባል መሠረቱ ራሷ ናት መሆን ያለባት፡፡ አንድ አገር በፍጹም በምንም ተዓምር ደሃ የመሆን ዕድል የላትም፡፡ ሕዝብ በምንም ተዓምር መሠረታዊ ፍላጎቱን ሊያጣ የሚችልበት ምክንያትና መንገድ የለም፡፡ እነዚህ ሁሉ የሚከሰቱት አገር መንገድ ስትስት ወይም መጓዝ በሌለባት መንገድ ስትጓዝ ነው፡፡ ለዚህም ነው ደሃ መሆን ሳይገባን ደሃ የሆነው፡፡ አሁንም ከድህነት መውጣት የምንችለው ትክክለኛውን ጎዳና ስንይዝ ብቻ ነው፡፡ ትክክለኛው ጎዳናችን ደግሞ በእኛው የሚገነባ መሆን አለበት፡፡ አንድ ሕዝብ በተሳሳተ ጎዳና አንዴ ደሃ ከሆነ ከድህነት ለመውጣት፣ የተወሳሰቡና በጣም ከባድ ቁርጠኝነትን የሚጠይቁ በርካታ ኃላፊነቶች ይኖራሉ፡፡

አንድ ኋላቀር ሕዝብን ለማዘመን ከጠንካራ መሪ የሚፈለገው ተግባር ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ኋላቀር ሕዝብን ማዘመንና ደሃ ሕዝብን ከድህነት ማውጣት የተለያዩ ናቸው፡፡ ደሃን ከድህነት ለማውጣት ትልቁ ቁርጠኝነት የሕዝቡ ነው፡፡ ሕዝቡ ድህነቱን ከማስታመም ይልቅ ለመገላገል ከወሰነ፣ ጠንካራ መሪ ይኼንን የሚያህል ፍላጎት ካለው ሕዝብ ግብዓት ካገኘ አገር ለመገንባት ቀላል ይሆናል፡፡ የየትኛውም አገርና ሕዝብ መሠረቱ የገዛ ዕውቀቱ፣ ገንዘቡ፣ ገበያው ብቻ ነው፡፡ ሌላው ተጨማሪ ግብዓት ለጋራ ተጠቃሚነት የሚከናወን እንጂ፣ ለአንድ ግዴታ ለመኖር ሲባል የሚተገበር ከሆነ ስህተት ነው ተብሎ ብቻ የሚታለፍ አይደለም፡፡

ማንም ዕውቀት አልባ፣ ገንዘብ አልባ፣ ሕግ አልባ… ሆኖ የተፈጠረ የለም፡፡ ሊጠቀምባቸው ካልቻለ፣ እንዴት እንደሚጠቀምባቸው ካልገባው፣ የባሰ ለድህነቱ መስፋፋት የገዛ ሀብቱ ተጨማሪ ግብዓት ነው የሚሆነው፡፡ በታሪካችን ውስጥ በርካታ ስህተቶች ይኖራሉ፡፡ በታሪክ አጋጣሚ ከሚፈጠሩ ችግሮች ደግሞ መልካሙን በማሰብ ክፉውን ካልረሳነው ሌላ ስህተት ይሆናል፡፡ እንኳንስ በታሪክ አጋጣሚ የተሠራ ይቅርና ሆን ተብሎ የተደረገም ቢሆን እንደ ሕዝብ ልንረሳው ካልቻልን፣ ለነገ ምንም ግብዓት የሚሆን ፍሬ የለውም፡፡ መጥፎ ታሪክ መጥፎ ነው፡፡ መጥፎነቱ መልካም የሚሆነው ስንረሳውና ላለመድገም ቆራጥ ስንሆን ነው፡፡ ብዙ መሪዎች በሕዝቦቻቸው የተወደዱት ሕዝብ የሚሻገርበትን ድልድይ መሥራት ስለቻሉና መጥፎውን ማስረሳትም ስለቻሉ ነው፡፡ እኛም የመጣንባቸው የተለያዩና የተሳሳቱ ፍላጎቶች፣ ታሪኮችና ተረቶች የሚያስረሳንና የሚያሻግረን መሪ ያስፈልገናል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የመጣንበትን መንገድ የሚፈትሽ የሚያስተካክል ኃላፊነት የሚወስድ ሕዝብ ያስፈልገናል፡፡

እኛ ደሃ የሆነው አብዛኛው ሰው ከሚሰጠው ምክንያት አለመሆኑን ደጋግሜዋለሁ፡፡ ልንነጋገርበትና ልንግባባበት ይገባል፡፡ መቼም መሬት ከሚለው ቃል ማሳ የሚለው ቃል ለመሬት የተሻለ ክብርና ሞገስ ይሰጣል፡፡ ምክንያቱም ዘርን ለመቀበል፣ ፍሬን ለመስጠት፣ ሕይወትን ለማስቀጠል የተዘጋጀ ግብዓት ስለሆነ ነው፡፡ የሕዝብም ዕውቀት እንደዚያው በአንድ ዓላማ፣ በጋራ ፍላጎት፣ መተማመን፣ ወዘተ. ሲቆምና ሲተሳሰር በተለየ ውጤት ስለሚታይ የበለጠ ስኬታማ ይሆናል፡፡ መሬት ማሳ እንደሚሆን ሕዝብም አንድነት ሲኖረው ሐሳብን ማመንጨት ቀላል ይሆናል፡፡ ሐሳቡ የሚወድቅበት ዕውቀትና ዘሩ የሚዘራበት ፍሬ ለማፍራት ወሳኝ ሚና እንዳለው ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡

መሪ አገሩን መምራት፣ ሕዝብም ፍላጎቱ መሟላት የሚችለው በገንዘብ ከመሰለን እጅግ በጣም ከፍተኛ የተሳሳተ ጎዳና ነው፡፡ መንግሥት መንግሥት የሚሆነው ገንዘብ ስላለው ሳይሆን ሐሳብ ስላለው ነው፡፡ አገር ገንዘብን በሥራ ላይ የምታውለው ሐሳብን ሥራ ላይ ለማዋል የግድ ስለሚያስፈልግ ብቻ ሳይሆን፣ ሁላችንም ውስጥ የተለያየ የሚመስል፣ እንደደረጃው የሚለያይና የሚጠቅም በሥራ ላይ መዋል ያለበት ሐሳብ ስላለ ነው፡፡ መሪ ሐሳብ ሳይኖረው መሪ መሆን እንደማይችል ሁሉ፣ የትኛውም ሕዝብ ያለ ሐሳብ መኖር እንደማይችል ግልጽ ነው፡፡ ሐሳብን ከሐሳብ ጋር፣ አገርን ከሐሳብ ጋር የምናመጣጥንበትና የምናስተሳስርበት ብቸኛው መንገድ ገንዘብ ስለሆነ እንጂ፣ ሕዝብ ለመኖር ተቀዳሚውና አስፈላጊው ሐሳብ እንጂ፣ ገንዘብ አይደለም፡፡

አገር በሐሳብ ብቻ ነው የምትሠራው፡፡ ሌላው ግብዓት ሐሳቡ ሲኖር ነው የሚገኘው፡፡ አገራችን የገባችበትን ድህነት በገንዘብ የማስታመሙ ሕይወት፣ እያመረተች መኖር ሲገባት እየገዛች እንድትኖር የተደረገችበትን ምክንያት ካላስተካከልን፣ ከዚህ በላይ መቀጠል አደጋው ብዙ ነው፡፡ አገራችንን አምራች ለማድረግ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሳተፍበትና ሊያምንበት የሚገባ ዕውቀት፣ ሊይዘው የሚገባ ተስፋ አለ፡፡ ለዚህም ለሁለት መከፈል አለብን፡፡ አንድ በገዛ ገንዘቡና በገዛ ዕውቀቱ ወደኋላ ተመልሶ መሠረቷን የሚሠራ፣ ሁለተኛው ያለውን ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ይዞ በመቀጠል የታችኛው የላይኛውን ሳያውክ፣ የላይኛው የታችኛውን ሳያውክ በመናበብ የሚሠራ ነው፡፡ የአገር ውስጥ ዕውቀትን፣ የተፈጥሮ ሀብትን፣ ምርታማነትን በማጠናከር በሁለት እግር መቆም ይቻላል፡፡

ደሃ የሆንበት ምክንያት ድህነታችንን ያየንበት ዕውቀት ነው፡፡ ችግራችን ሙስና፣ ዴሞክራሲ፣ የሕግ የበላይነት፣ ወዘተ. ማጣት ብቻ ሳይሆን ልናጣበት የቻልንበት ምክንያት አለማወቅ ነው፡፡ ትክክለኛውን መፍትሔ በማምጣት የምንፈልገውን ማግኘት እንችላለን፡፡ ለየትኛውም ጉዞ በርካታ አማራጭ መንገዶች ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን ወደ ምንፈልገው ግብ የሚያደርስ አንድ መንገድ ሊኖር እንደሚችል ይታወቃል፡፡ አገር ከራሷ ገንዘብ፣ ዕውቀትና ገቢዋ ውጪ የምታደርገው ጉዞ መቼም ከድህነት አያወጣትም፡፡ ችግሩ ላይ ስናፈጥ እንኖራለን እንጂ ወደ መፍትሔው አንሄድም፡፡ የአገራችን ችግርና መፍትሔው በእያንዳንዳችን እጅ ነው ያለው፡፡ ከአገራችን ዕውቀትና ምርታማነት ጋር መተሳሰር ወደኋላ መቅረት ከመሰለን ወደፊት የተራመድን ቢመስለን መጨረሻችን አሁንም ተስፋ መቁረጥ ይሆናል፡፡ የመጣንበትንና የለመድነውን ይዘን እንቀጥል ካልን ንቅንቅ አንልም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...