Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ ተንፍሶባቸው እየቀየሩ ናቸው። በዚህ ስንሞላው በዚያ እየፈሰሰ፣ በዚያ ስናጠጣ በዚህ እየደረቀ፣ ደግሞ ወዲያ ስናፍስ ወዲህ እየተዘረገፈ ጉዳያችን ሁሉ በዋለበት ይቀራል። ‹አንድ አይፈርድ አንድ አይነድ› ሆኖ ሰሚ ያጣው የኑሯችን ነገር ያብሰለስለናል። ተብሰልስለን የማንበስል፣ ተንተክትከን የማንገነፍል፣ ተንደቅዱቀን የማንከነበልበት ምክንያትም ግራ ያጋባል። እንዲያው ዝም እንዲያው ዝም ሆኗል ነገራችን ሁሉ። ይህ ነው የለ፣ ያ ነው የለ ዝም ብሎ መጓዝ ብቻ። መሄድ… መሄድ… መሄድ… ፌርማታችን ብዙ፣ ባጣ ቆያችን እልፍ። ዘመን በዘመን ቢባዛ ሰቀቀናችን ጫፍ የማይደርስብን፣ ለአፍታ ከገዛ ህሊናችን መተያየት ማውጋት የፈራን ጤዛዎች። ፍጥረት በምኞቱ ቀለበት እየታሰረና በሚዋልለው ሐሳቡ ተቀፍድዶ በከንቱነት የሚጋራው ጎዳናም አይናገር አይጋገር፡፡ ‹‹ወይ ዘንድሮ…›› እንዳለው ዘፋኝ በዘንድሮ ነገር እየተገረምንና እየተብሰለሰልን ጎዳናውን ተያይዘነዋል። ሳይሻለን አይቀርም!

ሳር ያለ ሐሳብ እየለመለመ፣ የሜዳ አበባ ያለ አትክልተኛ እያበበ፣ አዕዋፍ ያለ ጭንቅ አየር እየቀዘፉ የሰው ልጅ ለአንገት ማስገቢያ፣ ለዕለት ጉርሱ መታገል አቅቶት ሲንገዳገድ ሳቅ ሳቅም ይላል፣ ዕንባ ዕንባም ይላል። ፍልስፍናችን ያው የድግግሞሹ ሕይወታችን ውልድ ነውና ተደጋገመ ብሎስ ማን በምን ጥበቡ ይጠይቀናል? በዛና አነሰስ የማን አንጡራ ቃላት ናቸው? ዝምታስ ማን ያፀደው ሕገ መንግሥት ነው? የመሬት ነው ወይስ የሰማይ? ስንጠይቅ ውለን ስንጠይቅ ብናድር ቋቱ አይሞላም። የድካማችን ምንዳም ለወሬ አይመችም። እንዲሁ ድካም፣ እንዲሁ ዋይታ፣ እንዲሁ ነገር፣ እንዲሁ ሁካታ እንደ ቀን፣ ሌትና ወራት ዘመናት ይፈራረቃሉ። መቆም የሚባል ነገር አይታሰብም። እንኳን ለመቆም እየተፍጨረጨርን ተኝተንም ካልተገላበጥን አይሆንም። ምናልባት የዘመኑ መርህ መገላበጥ የሆነው ለዚያ ይሆን? አይታወቅም!

‹‹ጎማውን ቀይራችሁ አልጨረሳችሁም?›› ፊቷ መጠጥ ያለ ዘንካታ ወያላውን ታናግረዋለች። ‹‹ምናለበት ብትታገሱን? እንኳን እኛ ስንቱን አልታገሳችሁም?›› ወያላው ነገር ይፈትላል። በላብ የወረዛ ግንባሩን በአደፈ እጁ እየጠረገና ጎማውን እያጠበቀ በሉ ግቡ ሲለን ገብተን ተጫንን። ሾፌሩ ሞተሩን አስነሳ። ‹‹የማን ነው ደፋር? ታክሲና የገዛ ሕይወታችንን ያወዳድራል?›› እያለች ልጅት መጨረሻ ወንበር ላይ አጠገቤ ተቀመጠች። ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ባይታወጅ ኖሮ እንደ ፈለገ በሚያላቅቀው አፉ፣ እኛንም መንግሥትንም እንደ ኳስ እየጠለዘ ያላግጥብን ነበር…›› እያለችኝ መሳቅ ጀመረች። መሀል መቀመጫ ላይ ከአንድ ጎልማሳ አጠገብ የተሰየመች ወይዘሮ ሰምታት፣ ‹‹ምናለበት ይኼን የቆረፈደ ፖለቲካ በየቦታው አሥር ጊዜ እያነሳችሁ በስቅታ ባታጨናንቁን? ይኼ ከንቱ ፖለቲካ እኮ ትናንት ለምርጫ ቅስቀሳ፣ ከዚያ ደግሞ ለእርስ በርስ ጦርነት፣ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ አገራችንን በሐራጅ ለማሸጥ እንደሚውል አትጠራጠሩ…›› ብላ ስታሽሟጥጥ ጎልማሳው ቀበል አድርጎ፣ ‹‹ኧረ መቀስቀሻም መገኘቱ ትልቅ ለውጥ ነው። ይኼንንስ ማን አየብን?›› ብሎ ትግ ትጉን ለማስቀጠል የድርሻውን አዋጣ። ጉድ እኮ ነው!

ጉዟችን ቀጥሏል። ጋቢና ከተሰየሙት አንዱ በስልክ ይነታረካል። ‹‹ስማ ስልኩ እኮ የሚሠራው በገንዘብ በተሞላ ካርድ ነው፣ ገለባውን ትተህ ፍሬውን አውራ…›› ይላል። ‹‹እንኳን ስልኩ ሰውም በካርድ መሥራት ጀምሯል በለው እባክህ…›› ይላል ከመጨረሻዎቹ በዚያ ጥግ የተቀመጠው። ‹‹ታዲያ ካርድ መሙላት ያቃተው አለቀለት በለኛ?›› ስትል ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠች ዘመናይ ከሩቅ ቅርብ ሆና ማይኩን ተቀበለችው። ‹‹ለስንቱ ይሆን ከሆዳችን ቀንሰን ካርድ እየሞላን የምንዘልቀው? ያም አምጡ፣ ይኼም አምጡ ባይ ሆኗል…›› ይላል ከጎኗ የተቀመጠ ቀጠን ያለ ወጣት። ‹‹ሁሉም አጉርሱኝ ባይ ሆነ ብሎ ዝም ምንድነው ልጄ? ሁሉም ካልክ ዘንዳ ራስህንም ጨምርና ንሰሐ ግባ…›› አሉት ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየሙ አዛውንት። ‹‹አይ አባት ጣት መቀሳሰሩን ትተን ሸክማችንን በጋራ መሸከም ብናውቅ፣ እስከ ዛሬ እርስ በርስ በዓይነ ቁራኛ ስንተያይ እንኖር ነበር?›› ቢላቸው ሰውነቱ የከበደው ወጣት እሳቸውም መልሰው፣ ‹‹እሱስ ልክ ነህ ልጄ፣ ምን ይደረግ የአንዱን ሥጋ አንዱ መሸከም እያቃተው እኮ ነው…›› ብለውት አኮሳተሩት። አያድርስ ነው!

ነገር በፌስቡክና በቲክቶክ ብቻ የሚገባቸው ግራ ተጋብተው ዝም ሲሉ የገባቸው ደግሞ ሳቁ። ሌላ አዛውንት በፈገግታ ጣልቃ ገብተው፣ ‹‹ይኼን ካወቅክ ዘንድ ሆድ አየሁ ማለትን እንደማያውቅ ከተረዳህ ይኼ ሁሉ ስብ ምንድነው? ለሰማዩም ለምድሩም እኮ አይበጅም። ኧረ ለጤናም ጥሩ አይደለም…››  ሲሉት ወጣቱ ወዲያው የጨዋታውን መንፈስ ቀየረው። የሰውነቱ ውፍረት አገር እንደ ነቀዝ እየሰረሰረ ከሚያፈርሰው ‹ብቻዬን ጠብድዬ ልሙት› ብሂል ጋር መነካካቱ አናደደው መሰል ቁጣው ድምፁ ስርቅርቃ መሀል አታሞ እየደለቀ፣ ‹‹መሆንን ትተን መምሰል ካልን አይቀር ምናለበት እኛስ ስብ ጠናባቸው ብንባል? ቀለን ተቀብረን ማን አከበረን?›› ብሎ አዋዝቶ የልቡን ተናገረ። ስንቱ ነው ግን የልቤን ልናገር እያለ ልቡን የሚያጣው እናንተ? ብቻ ዘንድሮ ከአፍ ብቅ ሲል ቀጨም የሚያደርገው እየበዛ ስለሆነ ጠንቀቅ ማለት ይበጃል፡፡ የግድ ነው!

ወያላችን ሒሳብ እየተቀበለ እጅ በእጅ መልስ ይመልሳል። ‹‹እሰይ እንዲህ እጅ በእጅ ውለታህን የሚመልስልህ አትጣ…›› ትለዋለች ወይዘሮዋ። ‹‹በገዛ መልሳችን ደግሞ የምን ውለታ ነው? እንዲህ እያልን መሰለኝ የገዛ ሀብታችንንና ርስታችንን በአረም ያስበላነው…›› አለ ጎልማሳው በስጨት ብሎ። ‹‹ምን ሆኖ ነው ግን ሰው ትንኝ ስትነክሰውም  ዕባብ ሲነድፈውም እኩል የሚበሳጨው?›› ትለኛለች ከጎኔ ያለችው። እሷን የምትለውን የሰማ ጥግ የተቀመጠ ጎልማሳ፣ ‹‹ገበያው ነዋ፣ የሸቀጥና የአሻቃጭ ዘመን ሆነ። ቴሌቪዥኑ ሳይቀር ተከፍቶ እስኪዘጋ ድረስ ‹ተገዛ፣ ተሸጠ፣ ይሸጣል፣ ግዙ፣ አውጡ፣ ክፈሉ…› ፈሊጡ ነው። ሬዲዮውም ያው ነው። ውሸቱም እውነቱም አንድ ላይ ገበያ ይወጣል። ይኼው ከተማውም ለሽያጭና ለግዥ በማስታወቂያ ብቻ ተጨናንቋል። ክፍያ በቴሌ ብር፣ በኤምፔሳ እየተባለ ቁስ በቁስ ሆነናል በአጭሩ…›› ብሎ በረጅሙ ተነፈሰ። ‹‹ኧረ ቆጠብ አድርገህ ተንፍስ። በዚህ አያያዛችን አየርም ገበያ መውጣቱ ይቀራል ብለህ ነው?” ብለው አንደኛው ውስጣቸው እያረረ ተናገሩ። እያረሩ የሚስቁ ብፁዓን ናቸው ተብሏል እንዴ? ሊሆን ይችላል!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ታክሲያችን መስቀለኛ መንገድ ላይ ደርሶ የትራፊክ መብራት ሲያስቆመው፣ አንድ በኑሮ መጎሳቆል ሳቢያ ሰውነቱ የገረጣ ጎልማሳ ጠጋ ብሎ በመስኮት በኩል ዕርዳታ መጠየቅ ጀመረ፡፡ ወያላው ከዚህ በፊት እንደሚያውቀው ሁሉ፣ ‹‹አጅሬው ታክሲ ተራ መጥተህ ለበዓል የሚሆን ጣል ላደርግብህ ብፈልግ ጠፋህ…›› ሲለው፣ ‹‹እመጣለሁ ብዬ አስቤ ነበር፣ ነገር ግን ሳስበው ሳስበው ደከመኝና ተውኩት…›› ብሎ ፈገግ ሲል፣ ‹‹አንተ ጎዳና ላይ እንጂ እዚያ መምጣት እንደሚደብርህ መቼ አጣሁኝ…›› ብሎ ሃምሳ ብር እጁ ላይ ሲያስቀምጥለት፣ ‹‹ነፍሱ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፣ በቅርቡ ከዚህ አሰልቺ ሥራ ተላቀህ ራይድ ለመንዳት ያብቃህ፣ ከዚያ ደግሞ ዓለም ባንክ ካሉ ሪል ስቴቶች በአንደኛው ባለሦስት መኝታ አፓርታማ ለማግኘት ፈጣሪ ይርዳህ…›› እያለው ሲመርቀው ሾፌሩም ሃምሳ ብር መርቆለት መብራቱ ለቆን ጉዞ ቀጠለ፡፡ ለካ ይህ ሰው ከዚህ በፊት ሾፌር ሆኖ ሲሠራ በደረሰበት የአዕምሮ ሁከት ምክንያት ለጎዳና ኑሮ ተጋልጦ ነው፡፡ ‹‹እንዴት ያለ የተባረከ ምርጥ ሾፌር ነበር መሰላችሁ… ምን ዋጋ አለው ድንገት ሳይታሰብ ታመመና ተኛ… ከዚያ አገግሞ ሲነሳ ግን አዕምሮው ታወከ… ወይ ወንድሜን…›› እያለ ሲያዝን አብረን ተከዝን፡፡ ስንቱ ጉድ አለ መሰላችሁ!

በዚያ ጎልማሳ ድንገተኛ ገጠመኝ የተቆጩት አንደኛው አዛውንት፣ ‹‹የዚህን ወንድማችንን ታሪክ ሰምተን ዝም ማለት ተገቢ አይደለም…›› ብለው ከኮታቸው የውስጥ ኪስ ውስጥ በግድ ፈልቅቀው ያወጡትን መቶ ብር እያሳዩ፣ ‹‹ወገኖቼ እባካችሁ የተቻላችሁን ለግሱና በሾፌራችንና በወያላው አማካይነት ይህ ወገናችን ዕገዛችን ይድረሰው…›› ሲሉ ወዲያው ተሳፋሪዎች በሙሉ እንደ አቅማቸው አበረከቱ፡፡ ገንዘቡ ተቆጥሮ ካለቀ በኋላ አደራው ለሁለቱ ተሰጥቶ እንዲያደርሱ ተወሰነ፡፡ ‹‹እኛ እኮ ማለት ለተጨነቀ ደራሽ፣ ለአዘነ አፅናኝ፣ ለተራበ አጉራሽ፣ ለታረዘ አልባሽ፣ ምናለፋችሁ በአጠቃላይ የመልካምነት ምሳሌ ከሚሆን ድንቅ ሕዝብ የተገኘን ነን…›› ሲሉ አዛውንቱ ያ ሰውነተ ከባድ ወጣት፣ ‹‹አባቴ ነበር ባይሰበር፡፡ ያ ሁሉ መልካምነትና በጎ አድራጊነት የክፋት አምባሳደርና የዲያብሎስ ተላላኪ በሆኑ ጨካኞች ተሸፍኖ ምድራችን ተጨንቃለች…›› እያለ በንዴት ሲናገር፣ ‹‹አይዞህ ልጄ ለበጎውም ሆነ ለክፉ ሥራ ፈራጅ ፈጣሪ አለ፡፡ ለጊዜው የዘገየ ቢመስለንም ድንገት ሳይታሰብ ከተፍ ይላል፡፡ ያኔ ሰበብ ብንደረድር፣ አላወቅኩም ነበር አጥፍቻለሁ ብንል ሰሚ የለም…›› እያሉ ሲናገሩ ታክሲያችን ጉዞዋ ተገባዶ ‹‹መጨረሻ›› ተብለን ስንለያይ ሰበብ ድርደራ እንደማያዋጣ ተግባብተን ነበር፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት