Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን በተመለከተ ተከታታይ የሆኑ ማሻሻያዎችና አዲስ መመርያዎችን እያወጣ ነው፡፡ የዋጋ ንረትን ለመከላከል ባወጣው የገንዘብ ፖሊሲ የወጪ ንግድን በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የወጪ ንግድ እንዲንሠራራ ለማድረግ ዘርፉ ከሚያመነጨው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ውስጥ ለብሔራዊ ባንክ እንዲያስተላለፍ የተጣለበትን አስገዳጅ የውጭ ምንዛሪ ገቢ መጠን እንዲቀንስ አድርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ቀደም ሲል ላኪዎች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ ገቢ 30 በመቶውን ብቻ ለራሳቸው አስቀርተው ቀሪውን ለብሔራዊ ባንክ እንዲያስተላልፉ የተጣለውን ግዴታ እንዲሻሻል አድርጓል፡፡

በማሻሻያው መሠረትም፣ የሸቀጦችና አገልግሎት ላኪዎች ካፈሩት የውጭ ምንዛሪ ገቢ 50 በመቶውን ለብሔራዊ ባንክ፣ 10 በመቶውን ለባንኮች፣ ቀሪውን 40 በመቶ ደግሞ ለራሳቸው እንዲጠቀሙበት ፈቅዷል። ብሔራዊ ባንክ ይህንን መመርያ ከወጣ ከአንድ ወር  በኋላም ከውጭ ምንዛሪ ጋር የተያያዙ ሁለት ተከታታይ መመርያዎችን አውጥቷል፡፡ 

ከሰሞኑ ከወጡት መመርያዎች መካከል አንዱ በቀጥታ የውጭ የኢንቨስትመንት ስትራቴጂክ የሚባሉ ፕሮጀክቶች ላይ የሚሳተፉ አልሚዎች ከኢትዮጵያ ውጪ የባንክ ሒሳብ ከፍተው ገንዘባቸውን ማንቀሳቀስ እንዲችሉ የሚፈቅድ ነው። ሁለተኛው ደግሞ መኖሪያቸውን በአገር ውስጥ ያደረጉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለጉምሩክ አሳውቀው፣ ወደ አገር ይዘው ሊገቡ የሚችሉትን የውጭ ምንዛሪ መጠን ከፍ ያደረገበት ነው።   

ብሔራዊ ባንክ ስትራቴጂክ (ቁልፍ) ተብለው የተለዩ ፕሮጀክቶችን ለሚያንቀሳቀሱ አልሚዎች ከኢትዮጵያ ውጪ የባንክ ሒሳብ በመክፈት ገንዘባቸውን እንዲያንቀሳቅሱ የፈቀደበት መመርያ በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የተፈቀደ መሆኑ ታውቋል፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉ አካላትንና የመመርያውን አተገባበር በዝርዝር ያስቀመጠ ነው፡፡ 

በዚህ መመርያ ተጠቃሚው ይሆናሉ ተብለው ከተዘረዘሩት መካከል በዋናነት በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት (ፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሽፕ) የሚሠሩ ቁልፍ የልማት ፕሮጀክቶች የሚሳተፉ ይገበኙበታል፡፡ በተለይ ትልልቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችና ከፍተኛ የማዕድን ልማት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ሆነው፣ የኤክስፖርት የሚያደርጉ ተቋማት በዚህ መመርያ ሊስተናገዱ የሚችሉ ናቸው፡፡  ከዚህም ሌላ የወጪ ንግድ በማሳደግ የሚታመንባቸው ሠራተኞችን የሚቀጥሩ፣ የውጭ ምንዛሪን በአገር ውስጥ የሚያስቀሩና ገቢ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ ሊያመርቱ ለሚችሉ አስፈላጊ የሚባሉ ዘርፎች በዚህ መመርያ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ከመመርያው መገንዘብ ተችሏል፡፡ 

በዚህ መመርያ ዙሪያ ያነጋገርናቸው እንድ የባንክ ባለሙያ እንደጠቆሙት፣ ኢትዮጵያ ለቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንቶች በውጭ አገር አካውንት ከፍተው እንዲያንቀሳቅሱ ፈቃድ ሳትሰጥ የቆየች አገር መሆኗን አስታውሰው፣ ይህ ዓይነቱ አሠራር፣ የተመረጡ ወይም ስትራቴጂክ ለሆኑ ትልልቅ ፕሮጀክቶቻችን ለሚያንቀሳቅሱ ኢንቨስተሮች ታስቦ የወጣ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ ከመንግሥት ጋር ለሚሠሩ የውጭ ኢንቨስተሮች የሚያገለግል ሲሆን፣ አካውንቱን በመክፈት እንደ ብድርና ሌሎች ክፍያዎችን ከዚህ አካውንት በቀጥታ እንዲከፍሉ ያስችላቸዋል፡፡   

ከዚህ በፊት እንዲህ ያሉ ተቋማት ከመንግሥት ጋር ሥራ ከሠሩ በኋላ፣ ከመንግሥት ያገኙትን ገቢ ወይም ክፍያ ይዘው ወደ ውጭ መውጣት ሲፈልጉ፣ ባንክ ላይ የውጭ ምንዛሪ ችግር ስላለ ያንን ማድረግ ይቸገሩ እንደነበር፣ የዚህ መመርያ መውጣት የነበረባቸውን ችግር ለመቅረፍ ያለመ መሆኑን የባንክ ባለሙያው አስረድተዋል።

እንዲህ ያለውን አካውንት ከፍተው መገልገላቸው ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው የማያመለከቱት እኝሁ ባለሙያ፣ ለምሳሌ ዓመታዊ ትርፋቸውን ይዘው ለመሄድ ቢፈልጉ፣ በውጭ ወደ ከፈቱት የባንክ ሒሳብ በቀጥታ ማስገባት የሚያስችላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህ መመርያ ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ አወት ተክኤ፣ ይህ መመርያ አስፈላጊና መሠረታዊ ነው ይላሉ፡፡ ስትራቴጂክ በሚባሉ ፕሮጀክቶች የሚሳተፉ የውጭ ኢንቨስተሮችን ሊደግፍ የሚችል እንደሆነም አመልክተዋል፡፡  

ስትራቴጂክ የሚባሉ ኢንቨስተሮች ቀጣይነት ላለው ዕድገት ጥቅም ስላላቸው፣ እንዲሁም ደግሞ ፍለክሰብል የሆነ ኢንቫይሮመንት ለመፍጠር እንዲህ ያለውን አካውንት ከፍተው እንዲጠቀሙ በማድረግ ገንዘባቸውን ያለ ችግር እንዲያንቀሳቅሱ ዋስትና እንዲኖራቸው የሚያደርግ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ መመርያው ስትራቴጂካዊ ኢንቨስተሮችን የሚጠቅም ስለመሆኑ ምሳሌ አድርገው የጠቀሱት በቅርቡ ዳንጎቴ አጋጠሙ የተባሉትን ችግር ነው፡፡ እንደ ዳንጎቴ ያሉ ትልልቅ ኩባንያዎች ገንዘባቸውን ወደ ውጭ ምንዛሪ ለመለወጥ ይቸገሩ ነበር፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ኩባንያዎችን በውጭ እንዲከፍቱ በተፈቀደላቸው አካውንታቸው ማስገባት የሚችሉ በመሆኑ የውጭ የባንክ ሒሳብ (ኦፍሾር አካውንት) እንዲከፍቱ መፈቀዱ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የበለጠ መተማመኛ ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡ ለብድርና መሰል ክፍያዎችን በመመርያው በተቀመጠው መሥፈርት መሠረት መክፈል የሚያስችላቸውም ነው፡፡  

በእነዚህ መመርያዎች ዙሪያ ያነጋገርናቸው ሌላው የባንክ ባለሙያ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ስትራቴጂክ ተብለው ለተለዩት ኢንቨስትመንቶች በውጭ አካውንት እንዲከፍቱ የሚፈቅደው መመርያ ዋነኛ ዓላማው መተማመንን ለመፍጠር ነው፡፡ የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪ እዚያ አካውንት ውስጥ እየከተቱ እንዲያንቀሳቅሱ ያግዛል፡፡ እዚህ አገር ውስጥ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ስላለ፣ ይህንን ገንዘብ ብንሰጥም ላይከፈል ይችላል የሚለውን ሥጋት ለመቅረፍና መተማመኛ አግኝተው ሥራቸውን ለመሥራት  ታስቦ የወጣ መመርያ አድርገው እንደሚመለከቱት አመልክተዋል፡፡ መመርያው ለተወሰኑ ዘርፎች መሆኑን ያስታወሱት ባለሙያው፣ በተለይ እንደ ማዕድን ያሉ ዘርፎች ላይና የመሳሰሉ ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች ላይ ተፈጻሚ የሚሆን መሆኑ መጥቀሱ የዘርፉን ኢንቨስትመንት ለማሳደግ አጋዥ ይሆናልም ብለው ያምናሉ፡፡

ይህንን መመርያ ማውጣት አሉታዊ ተፅዕኖ አለው የሚሉም አሉ፡፡ በአገር ውስጥ ያካበቱትን ሀብት እንዲያሸሹ ሊያደርግ ይችላልም የሚል ሥጋት ያላቸው አሉ፡፡ ለምሳሌ በዚህ በተፈቀደላቸው የውጭ አካውንት ውስጥ የእነሱ ያልሆነ ገንዘብ አስገብተው ያልተገባ ተግባር ሊፈጽሙ ይችላሉ የሚል አመለካከት ይንፀባርቃል፡፡ የባንክ ባለሙያውም ይህ መመርያ በተገቢው መንገድ ሥራ ላይ እንዲውል ከተፈለገ ችግርም ሊኖረው ስለሚችል በጥንቃቄ ሊሠራበት ይገባል ይላሉ፡፡ 

በሌላ በኩልም ጉዳዩ ከአጠቃላይ የቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ጋር የሚያያዝ በመሆኑ፣ ይህ መመርያ የኢንቨስትመንት ኮሚሽንን አሠራሮችን እንዲከልስ ሊያደርገው ይችላል የሚል ምልከታ አላቸው፡፡ ምክንያቱም እስካሁን ባለው አሠራር የቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ሲገባ እዚህ ገንዘቡን አሳይቶ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ መመርያ ይመለከተናል የሚሉ የቀጥታ ኢንቨስትመንቶች መመርያውን በሌላ እንዳይተረጉሙ መጠንቀቅ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

‹‹መንግሥት ይህንን መመርያ ማውጣት ለምን አስፈለገው?›› የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ከባድ ቢሆንም፣ የራሱ ምክንያት ሊኖረው ይችላል፡፡ ኢንቨስተሩ ከአገር ውጪ እንዲያስቀምጥ መፍቀዱ ‹‹ለምን?›› የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ከዚህ ቀደም ሲደረግ የነበረው አንድ ኢንቨስተር፣ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ሲሰጠው ኢትዮጵያ ውስጥ ከአካውንት ከፍቶ እንዲያስቀምጥ ነው፡፡ ያን ያስቀመጠውን ገንዘብ በኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኩል መግባቱ ተረጋግጦ ነው ፈቃድ የሚሰጠው፡፡ አሁን ግን ከመንግሥት ጋር ነው የምንሠራው፣ ተፈቅዶልናል የሚሉ ካሉ ይህንን ነገር ያስቀረዋል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ገንዘብ ወደ አገር ሳያስገቡ ኢንቨስትመንታቸውን እየቆነጠሩ እንዲያስገቡም ሥጋት እንዳላቸው ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡  

በዚህ ጉዳይ ላይ አቶ አወት ያጋጥማሉ የተባሉ ሥጋታቸውን ለመቅረፍ የራሱ የሆነ መቆጣጠሪያ ሥልት አለው፡፡ በየሩብ ዓመቱ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ሪፖርታቸውን የሚቆጣጠሩበት አሠራር ይኖረዋል፡፡ ወጪና ገቢያቸውን በሙሉ የሚያሳይ የገንዘብ እንቅስቃሴያቸውን ክሬዲብል የሆነ ማሳያዎችን እንደ ማንኛውም የንግድ ዘርፍ ሊቆጣጠርበት የሚያስችል አሠራር አለው፡፡ 

የገንዘብ እንቅስቃሴያቸው ከባንክ ባንክ በሙሉ የተጠቀሱትን ሥጋቶች የሚያስወግዱ ማረጋገጫ መንገዶች ስላሉ፡፡ እነሱ ኦፍ ሾር አካውንት ሲኖራቸው እንቅስቃሴውና አጠቃቀሙ ያለበትን ሁኔታ፣ እንዲሁም ደግሞ ፕሮጀክሽኑ ራሱ ሞኒተር ለማድረግ ባላንስ ቼክ ስለሚያደረግ ብዙ አሳሳቢ አይሆንም፡፡ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስተሮች አለባቸው የተባሉ ችግሮችን ዓይቶ፣ ለችግሩ መፍትሔ የሚሆን መመርያ ማውጣት ትልቅ ዕርምጃ ነው፡፡ ምክንያቱም ስትራቴጂካዊ የሚባሉ ኢንቨስተሮች ለዕድገት ከሚያመጡት ጥቅም በተጨማሪ፣ ሌሎችን የቢዝነስ ዘርፎች የሚያሳድጉና ሌሎችም እንዲከተሏቸው ማስቻያ ዘዴ ናቸው፡፡   

ሁለተኛው መመርያ ዙሪያም እነዚሁ ባለሙያዎች በሰጡት አስተያየት፣ በኢትዮጵያ ለሚኖሩና ውጭ ለሚገኙ ለትውልደ ኢትዮጵያውያን ሰዎች ይዘውት የሚመጡት የውጭ ምንዛሪ መጠን ላይ በየጊዜው ሲቀየር መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው መመርያ ከሦስት ሺሕ ዶላር በላይ ይዘው ሲመጡ ዲክላር ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ አሁን በወጣው አዲሱ ማሻሻያ መጠኑ ወደ አሥር ሺሕ ዶላር ማደጉ ዲክላር ያደረገው ሰው በአንድ ወር ውስጥ ተመልሶ ሲወጣ ዲክላር ያደረኩት ገንዘብ ነው ብሎ ያሳያል፡፡ ወይም ደግሞ ያንን ገንዘብ ወደ ባንክም ሲያስገባ ከየት አመጣህ ተብሎ ስለሚጠየቅ ዲክላር አድርጌ ነው የመጣሁት ብሎ ለማሳየት የሚያስችለው ነው፡፡ 

ቀደም ብሎ የነበረው መመርያ ክፍተቶች ነበሩበት ስለሆነ፣ ለሕገወጥ ሥራዎች የተጋለጠም ስለነበር፣ የአሁኑ መመርያ ይህንን ክፍተት ሊደፍን በሚችል መልኩ የወጣ ነው፡፡ ጉምሩክ ዲክሌር ሲያደርጉ ይፈጠር የነበረው ችግር ወይም ሕገወጥ አሠራር በሙሉ ያስቀራል፡፡ ስለዚህ ይህም መመርያ ቢሆን አስፈላጊና ጠቃሚ ነው፡፡ በተለይ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ በሕጋዊ መንገድ የውጭ ምንዛሪ እንዲገባና እንዲወጣ የሚያስችል በመሆኑ ተገቢ መመርያ ስለመሆኑ አቶ አወት ያስረዳሉ፡፡

ይህ መመርያ ዶላር አካውንት ላላቸው፣ ኢትዮጵያውያን ለሆኑ ከኢትዮጵያ ውጪ ለሚኖሩ፣ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ኢትዮጵያ ለሚኖሩ  ሰዎች የሚያገለግል ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ከአሥር ሺሕ ዶላር በላይ ይዘው ሲመጡ ዲክሌር አድርገው ውጭ ምንዛሪ አካውንታቸው ማስቀመጥ ይችላሉ፡፡ 

ለምሳሌ ከጎረቤት አገሮችና ከመካከለኛው ምሥራቅ የሚመጣ ከሆነ ምንም ዓይነት መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ የሚገባ ከሆነ ዲክሌር ማድረግ የሚጠበቅባቸው ይሆናል፡፡ ከመካከለኛው ምሥራቅና ከጎረቤት አገሮች ውጭ ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ግን፣ የ30 ቀናት ያላለፈው ቪዛ እስከያዙ ድረስ ከ10 ሺሕ በታች የሆነ የውጭ ምንዛሪ ይዘው ከገቡ ዲክሌር ያደረጉበትን መረጃ ማምጣት አይጠበቅባቸውም፡፡ 

በዚህ መንገድ ይዘውት የሚገቡትን ገንዘብ በባንክ በዳያስፖራ አካውንታቸው ያስገቡና ከዚያ አካውንታቸው ላይ ለተለያዩ አገልግሎቶች መጠቀም ይችላሉ፡፡ 

የዚህ መመርያ ዋነኛ ዓላማውም ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ እንዲጨምር ለማበረታታት እንደሆነ የሚገልጹት ያነጋገርናቸው  ባለሙያዎች፣ ትልቁ ነገር ጉምሩክ አካባቢ ያለውን ክፍተት የሚደፍን መሆኑን ያስምሩበታል።                         በመመርያው መሠረት አንድ ከውጭ የመጣ ሰው ገንዘቡን ይዞ ሁለት አማራጭ እንዳለው ያመለከቱት የባንክ ባለሙያ ደግሞ፣ አንዱ ገንዘቡን ያመጣው ዳያስፖራ ከሆነ ያንን ዶላር ሳይመነዝር ዶላሩን ባንክ ማስቀመጥ ይችላል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አገር ውስጥ ለፈለገው አገልግሎት እየመዘነረ መጠቀም ያስችለዋል፡፡ 

በአጠቃላይ እንዲህ ያሉ አዳዲስ መመርያዎች በተለይ ከውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ያሉትን ችግሮች ቀስ በቀስ እያቃለሉ ለመሄድ፣ የታሰቡ ሆነው እንዳገኟቸው ከባለሙያዎቹ ገለጻ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ ወደ አገር የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ በማሳደጉ ረገድ ጠቀሜታ ይሰጣል፡፡ የቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ የወጣውም መመርያ ቢሆን ብዙ ጊዜ ጥያቄ ሲቀርብበት የነበረ ሲሆን፣ አሁን በዚህ ዓይነት መልኩ ምላሽ ማግኘቱ ቀስ በቀስ ሌሎችንም ዘርፎች ለማካተትና የተሻለ ጥቅም ለማግኘት ያግዛል የሚል እምነታቸውንም አንፀባርቀዋል፡፡ ከዚህም በኋላ ተያያዥ ዕርምጃዎች ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ እነዚሁ ያነጋገርናቸው የባንክ ባለሙያዎችና የኢኮኖሚ ባለሙያዎቸ መመርያዎቹን በአግባቡ ማስፈጻም ግን ይገባል ይላሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች