Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበሰሜን ጎንደር ዞን በተከሰተ ድርቅ ከ30 በላይ ሰዎችና ከ50 ሺሕ በላይ እንስሳት...

በሰሜን ጎንደር ዞን በተከሰተ ድርቅ ከ30 በላይ ሰዎችና ከ50 ሺሕ በላይ እንስሳት መሞታቸው ተሰማ

ቀን:

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በተከሰተ ድርቅ ከ30 በላይ ሰዎችና ከ50 ሺሕ በላይ እንስሳት መሞታቸውን፣ እንዲሁም ከ200 በላይ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው፣ የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በዞኑ ከተከሰተው ድርቅ ጋር ተያይዞ ረሃብና ተላላፊ በሽታ የተከሰተ መሆኑን፣ በዚህም እስካሁን በተደረገ ክትትል ከ30 በላይ ሰዎች መሞታቸውንና 452 ሺሕ ዜጎች መጎዳታቸውን የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰላምይሁን ሙላት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ድርቁ በዞኑ የሚገኙ ስድስት ወረዳዎችና 86 ቀበሌዎችን ማዳረሱን፣ በዚህም 19,800 ሔክታር መሬት ላይ የነበረ ቡቃያ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መጥፋቱን አቶ ሰላምይሁን ገልጸዋል፡፡

‹‹ድርቁ የበየዳ ወረዳዎችን ጨምሮ፣ ምሥራቅና ምዕራብ ጠለምት የተወሰኑ የደባርቅ አካባቢዎችን ያዳረሰ ሲሆን፣ የጃናሞራ ወረዳ በከፍተኛ ሁኔታ ለችግር የተጋለጠ ነው፤›› ያሉት አቶ ሰላምይሁን፣ የሞት አደጋ መታየቱንና ኮሌራን ጨምሮ ሌሎች ወረርሽኞች መከሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

ለችግሩ መፍትሔ የተባሉ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ ቢሆንም፣ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በዞኑ ከተከሰተው ችግር አንፃር ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ኃላፊው አክለዋል፡፡

እስካሁን በክልል ደረጃ ከ1,500 ኩንታል በላይ የምግብ እህል ድጋፍ የተደረገ መሆኑን፣ ዕርዳታ ከሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር አንፃር ዕርዳታው ሲታይ በጣም የተራራቀ ነው ሲሉ አቶ ሰላምይሁን አብራርተዋል፡፡

‹‹አሁን በአስቸኳይ የምንፈልገው የዕለት ምግብ፣ ውኃ፣ የሰውና የእንስሳት መድኃኒት ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በዞን ደረጃ የተዋቀረ ቡድን ተጎጂዎች ዘንድ በመድረስ ያለውን ችግር ተመልክቶ ያገኘውን መረጃ ለክልል ያደረሰ ሲሆን፣ ክልሉም መረጃውን ተመልክቶ በእጁ ላይ ያለውን አምስት ሺሕ ኩንታል ልኮልናል፤›› ያሉት አቶ ሰላምይሁን፣ የተላከው ዕርዳታም በአግባቡ መከፋፈሉን አክለዋል፡፡

ችግሩ አሁን ባለው ሁኔታ በቀላሉ ሊፈታ ስለማይችል ክልሉ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

 በተከሰተው የዝናብ እጥረት 103 ሺሕ እንስሳት ለድርቅ አደጋ መጋለጣቸውን ጠቁመው፣ 53 ሺሕ ያህል እንስሳት በድርቁ ሳቢያ መሞታቸውን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በዋግኸምራ ዞን በሰሀላ ሰየምት ወረዳ በተከሰተው ድርቅ በርካታ ሰዎች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸውንና ሁለት ሰዎች መሞታቸውን፣ የዞኑ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምሕረት መላኩ ተናግረዋል፡፡

ወረዳው ከ52 ሺሕ በላይ ሕዝብ የሚኖርበት መሆኑን፣ 46 ሺሕ ያህሉ አፋጣኝ ዕርዳታ ካላገኙ ለሞትና ለመፈናቀል መዳረጋቸው የማይቀር ነው ሲሉ አቶ ምሕረት አስረድተዋል፡፡

ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ 500 ሺሕ እንስሳት በከፋ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ገልጸው፣ ከ3,800 በላይ መሞታቸውን አቶ ምሕረት አክለዋል፡፡

እስካሁን በክልሉም ሆነ በተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የተደረገ ዕርዳታ አለመኖሩን ገልጸው፣ አሁንም ቢሆን በአፋጣኝ ዕርዳታ ካልቀረበ የሰዎችም ሆነ የእንስሳት ሞት ቁጥር በፍጥነት ሊጨምር ይችላል ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ለክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ሪፖርት ከማድረግ ባለፈ የችግሩን አሳሳቢነት ብንገልጽም፣ እስካሁን ምላሽ አልተሰጠንም፤›› ብለዋል፡፡

የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና በበኩሉ በቂ የሆነ የምግብ እህል ዕርዳታ ባለመኖሩ ምክንያት ማቅረብ አለመቻሉን ተናግሯል፡፡

‹‹በክልል ደረጃ የመጀመሪያው ተግባር መረጃን ማሰባሰብ ነው፤›› ያሉት የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ዘውዱ ናቸው፡፡

መረጃውን ለማሰባሰብ በክልሉ ያለው ግጭት፣ የትራንስፖርት መቋረጥና የኢንተርኔት መጥፋት ሙሉ መረጃ ለማግኘት በእጅጉ እንደፈተናቸው ገልጸዋል፡፡

‹‹አሁን በተገኘው መረጃ ችግሩ ሰፋ ያለ ሳይሆን አይቀርም፤›› ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ ‹‹ከክልሉ ከነበረው አምስት ሺሕ ኩንታል የሚሆን የመጠባበቂያ እህል በድርቅ በጣም ተጎጂ ለተባሉ 12 ወረዳዎች የደረሰ ሲሆን፣ የተወሰነው የዕርዳታ እህል ደግሞ በፀጥታው ምክንያት ማድረስ አልተቻለም፤›› ብለዋል፡፡

ደቡብ ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደርና ዋግ ኸምራ ብሔረሰብ ዞንና ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች እንዳልተዳረሳቸው አቶ ብርሃኑ አብራርተዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ ከ600 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮችን ጨምሮ 3.5 ሚሊዮን ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች መኖራቸው በተደረገ ጥናት መረጋገጡን የተናገሩት አቶ ብርሃኑ፣ ድጋፍ ለማቅረብ ግን ክልሉ ከአቅሙ በላይ ነው ብለዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ከዚህ ቀደም ለ88 ሺሕ ካምፕ ውስጥ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ለሁለት ወራት ድጋፍ ማድረጉን ተናግረው፣ ይህም በድርቅ በተጎዱና ተፈናቅለው በኅብረተሰቡ ውስጥ በሚገኙ ተፈናቃዮች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማድረሱን አክለዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በአሁኑ ወቅት በክልሉ ባለው ግጭት ምክንያት ማሳቸውን መንከባከብ የማይችሉ አርሶ አደሮች መብዛታቸውን ጠቅሰው፣ በዚህም ምክንያት ለምግብ እጥረት ተጋላጭ እየሆኑ ነው ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...