Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከህዳሴ ግድቡ በዓመት የሚለቀቅ የውኃ መጠንን በአኃዝ የሚጠቅስ ውል እንዳይፈረም ጥሪ ቀረበ

ከህዳሴ ግድቡ በዓመት የሚለቀቅ የውኃ መጠንን በአኃዝ የሚጠቅስ ውል እንዳይፈረም ጥሪ ቀረበ

ቀን:

የኢትዮጵያ መንግሥት ከህዳሴ ግድቡ ወደ ታችኞቹ የናይል (ዓባይ) ተፋሰስ አገሮች በዓመት የሚለቀቅ የውኃ መጠንን በአኃዝ የሚጠቅስ ስምምነት (ውል) ውስጥ እንዳይገባ ጥሪ ቀረበ።

ጥሪውን ያቀረበው መቀመጫውን በውጭ ያደረገው የኢትዮጵያ ውኃ ጉዳዮች መማክርት (Ethiopian Water Advisory Council) ነው። መማክርቱ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ መንግሥት ከግብፅና ከሱዳን ጋር አዲስ በጀመረው ድርድር፣ ከህዳሴ ግድቡ በዓመት ለታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች (ግብፅና ሱዳን) የሚለቀቀውን የውኃ መጠን አስቀድሞ በአኃዝ መግለጽ የለበትም ብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት ለኢትዮጵያ ጠቃሚና አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ፣ ከህዳሴ ግድቡ ወደ ታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች የሚለቀቅ የውኃ መጠንን በአኃዝ የሚጠቅስ ስምምነት እንዳይፈርም የኢትዮጵያ ውኃ ጉዳዮች መማክርት ጥሪውን አቅርቧል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሦስቱ አገሮች ከአሥር ዓመታት በላይ የፈጀ ድርድር ውስጥ ማለፋቸውን፣ በዋናነትም በአሜሪካ መንግሥት አደራዳሪነት፣ በኋላም በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት፣ እንዲሁም በቅርብ ጊዜ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ አደራዳሪነት ይፋ ያልተደረገ ድርድር ማድረጋቸውን ገልጿል።

በተለይ በአሜሪካ መንግሥት አደራዳሪነት ሲካሄድ በነበረው ድርድር ወቅት ከህዳሴ ግድቡ ለታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች የሚፈሰው የውኃ መጠን ከ37 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ያነሰ ከሆነ፣ የድርቅ ሁኔታ ተከስቷል የሚል ትርጓሜ የያዘ ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ቀርቦ እንደነበር አስታውሷል።

ከላይ የተጠቀሰው የድርቅ አመላካች ሁኔታ ከተከሰተ በታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች የሚገኙ የውኃ ማጠራቀሚያ ግድቦች ውስጥ ያለው የውኃ መጠን ምን ይሁን ምን (ከግንዛቤ ሳይገባ)፣ ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድቡ ከያዘችው ላይ ተጨማሪ ውኃ ለታችኞቹ አገሮች እንድትለቅ የሚጠይቅ አንቀጽ በወቅቱ ቀርቦ በነበረው ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ላይ ተካቶ እንደነበር አስረድቷል።

‹‹ይህ አንቀጽ ኢትዮጵያ ትንሽ ተጠቅማ ብዙ ውኃ ወደ ታችኞቹ አገሮች እንድትለቅ የሚያስገድድ ከመሆኑ ባለፈ፣ ኃይል ማመንጨት እንዳትችልና የውኃ ሀብቷን ሕጋዊ ድርሻ እንዳትጠቀም የሚያደርግ ነበር፤›› ብሏል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ለታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች የምትለቀው የውኃ መጠን ስልት ወደ ህዳሴ ግድቡ ማጠራቀሚያ የሚገባው የውኃ መጠንን መሠረት አድርጎ ወደ ግድቡ ከገባው የውኃ መጠን ላይም ለአካባቢው ማኅበረሰብ ጥቅም የሚውለውና፣ በትነት ምክንያት የሚታጣው ተቀናሽ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝቧል። ከዚህ ውጪ ለታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች የምትለቀውን የውኃ መጠን አስቀድማ በአኃዝ መግለጽ እንደማይገባት መማክርቱ አሳስቧል።

በተጨማሪም ሦስቱ አገሮች ድርቅ በሚከሰትበት ወቅት በጋራ የሚኖራቸው የድርቅ ማካካሻ ኃላፊነትና የኢትዮጵያ የውኃ ድርሻ በቅድሚያ ሳይወሰን፣ ኢትዮጵያ በዓመት ለታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች በአኃዝ የተጠቀሰ የውኃ መጠን ለመልቀቅ ቃል ልትገባ እንደማይገባ ጥሪውን አቅርቧል።

‹‹እንዲህ ያለ ስምምነት ውስጥ ከተገባ ግን ኢትዮጵያ ከህዳሴ ግድቡ ማዶ (በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል) የዓባይን ውኃ የሚጠቀም ምንም ዓይነት የልማት እንቅስቃሴ እንዳታደርግ ትገደባለች፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ልማታዊ እንቅስቃሴ ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ ለሌላቸው ግብፅና ሱዳን ውኃ ማጠራቀሚያነት እንዲያገለግል በኢትዮጵያዊያን ሀብት የተገነባ ግድብ ያደርገዋል፤›› ብሏል።

ስለሆነም፣ ‹‹ለታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች በዓመት የሚለቀቀው የውኃ መጠን በአኃዝ ከመገለጹ በፊት በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል የውኃ መጋራት ስምምነት ሊኖር ይገባል፤›› ሲል ምክረ ሐሳቡን አቅርቧል።

በተዘጋጀው የታላቁ ህዳሴ ግድብ የኦፕሬሽን ዕቅድ መሠረት ከግድቡ ከፍተኛ ኃይል ማመንጨት የሚቻለው የግድቡ የውኃ ከፍታ ከባህር ጠለል በላይ በ625 ሜትርና በ640 ሜትር መካከል በማድረስ እንደሆነ የጠቆመው የውኃ ጉዳዮች መማክርቱ፣ የሚፈለገውን ከፍተኛ ኃይል ማመንጨት የሚቻለው በግድቡ የሚያዘው ውኃ ከተጠቀሰው ዝቅተኛ ደረጃ ከፍታ (625 ሜትር) በላይ ከሆነ ነው ብሏል። የውኃ መጠኑን ከ625 ሜትር ከፍታ በላይ ማድረግ የሚፈለገውን ከፍተኛ ኃይል ለማመንጨት ከማስቻሉ በተጨማሪ፣ በተርባይኖቹ ላይ የሚደርሰውን የረዥም ጊዜ ጉዳት እንደሚከላከል አስረድቷል።

የውኃ ከፍታው ከተጠቀሰው ዝቅተኛ የከፍታ ደረጃ (625 ሜትር) በታች ከሆነ ግን፣ ከግድቡ የሚገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል ከታቀደው በጣም ያነሰ እንደሚሆን፣ የሚገኘውም የኤሌክትሪክ ኃይል አስተማማኝነት እንደማይኖረው አስገንዝቧል። በተጨማሪም ከአማካይ የዝናብ መጠን በታች በሚፈጠርበት ወቅት ወደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚገባው የውኃ መጠን አነስተኛ ስለሚሆን፣ የግድቡን የውኃ ከፍታ ሁልጊዜ ከ625 ሜትር ከፍታ እንዳይወርድ ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስቧል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ከአማካይ የዝናብ መጠን በታች በሚፈጠርበት ወቅት የታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች (ግብፅና ሱዳን) ፍላጎት በማስተናገድ፣ ግድቡን በድጋሚ ውኃ መሙላት ፈታኝ እንደሚሆን ልብ ሊባል እንደሚገባ አሳስቧል። 

ይህንንም ከግንዛቤ በማስገባት የመንግሥት ኃላፊዎች የግድቡ የውኃ ሙሌትን አስመልክቶ ስለሚሰጡት መግለጫ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፣ የመገናኛ ብዙኃንም ይህንኑ ተገንዝበው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ውኃ ጉዳዮች መማክርት በአባልነት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካዊ ያልሆነ በጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑ የውኃ ልማት ሳይንቲስቶችን፣ ምሁራንን፣ ተመራማሪዎችን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ባለሙያዎችን በአባልነት ይዟል። የተመሠረተበት ዓላማም ኢትዮጵያ የውኃና የምግብ ዋስትናን እንድታገኝና ከአስከፊ ድህነትና ችግር እንድትላቀቅ ለማገዝ ነው።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...