መስከረም ጠብቶ ዓመቱን በብሩህ ተስፋ ለመጀመር ትልቅ ጉጉት ካላቸው ሰዎች አንዱ ነኝ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመቁጠር የሚያዳግቱ በርካታ ችግሮች እንዳሉ በሚገባ ከሚረዱ መካከልም እመደባለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ በርካታ ችግሮች ባሉባት አገር ውስጥ እየኖሩ መልካም ነገሮችን መመኘት የግድ ቢሆንም፣ ችግሮቹን ለመፍታት በሚደረግ ጥረት ውስጥ ተሳታፊ መሆን ያስፈልጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ተሳትፎ ሲባል ለይስሙላ የሚደረግ አጉል የሚዲያ ፍጆታ ሳይሆን፣ በየተሰማራንበት መስክ በባለቤትነት ስሜት አስተዋጽኦ ለማድረግ በትክክል ዕድል ማግኘት ማለት ነው፡፡ እኔ ይህንን ሐሳብ የማቀርበው እንዲሁ አይደለም፡፡ ነገር ግን በየዕለቱ በአካባቢዬ የማያቸው አሳዛኝ ክስተቶች ይህንን ገጠመኝ እንድጽፍ አስገድደውኛል፡፡
ዋናው ጉዳዬ በአገሪቱ የሚስተዋለው የምግብ ችግር ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ያለ ምንም ማጋነን በኢትዮጵያ ምግብ ማግኘት በጣም አንገብጋቢ እየሆነ ነው፡፡ የምግብ ዋጋ አልቀመስ ከማለቱ የተነሳ ብዙዎች ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠዋል፡፡ አስቤዛ ለማድረግ ወደ ገበያ ጎራ ሲባል የሚሰማው የዋጋ ጭማሪ አስደንጋጭ ነው፡፡ በቀደም ዕለት ዘወትር ከምገበይበት ግሮሰሪ የአንድ ኪሎ ሽንኩርት ዋጋ 120 ብር ስባል በጣም ነበር የደነገጥኩት፡፡ ለአንድ ፍሬ ዕንቁላል 15 ብር ክፈል ተብያለሁ፡፡ ይህ ዋጋ በነጋታው ሲኬድ ሊጨምር እንደሚችል የታወቀ ነው፡፡ ጤፍ፣ የስንዴ ዱቄት፣ በርበሬ፣ ወተት፣ ዘይትና ሌሎች ሸቀጦች በየቀኑ ዋጋቸው እየተሰቀለ ነው፡፡
አብሮኝ የሚሠራ ወንደላጤ የሥራ ባልደረባዬ ምሳ የሚቋጥርለት ስለሌለ፣ ምሳውን የሚመገበው መሥሪያ ቤታችን አካባቢ የሚገኙ ምግብ ቤቶች ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምግብ ቤቶቹን ዋጋ ጭማሪ ባለመቻሉ ተቸግሯል፡፡ ቀደም ሲል በ150 ብር የሚገላገለው ምሳ ከሁለት እጥፍ በላይ ጨምሮበት፣ ዝቅ ያሉ ምግብ ቤቶች ሲሄድ የጤና ችግር ገጠመው፡፡ በዚህ ምክንያት ምሳውን አቁሞ ‹‹አስፋልት ለብለብ›› በማለት የሚጠራውን የእግር ጉዞ፣ ለምሳ ማካካሻ ማድረጉን ሲነግረኝ በከፍተኛ መከፋት ውስጥ ሆኖ ነው፡፡ በዳቦና በድንች የሚሠራውን ‹‹እርጥብ›› የሚባል ምግብ ቢሞክረውም ሊስማማው ባለመቻሉ ነው ምሳን በእግር ጉዞ የተካው፡፡
ሌላው የሥራ ባልደረባዬ ደግሞ ደመወዙ ከቤት ኪራይ ተርፎ ለምግብ ቤት ክፍያ ስለማይበቃው፣ በዘይት የተጠበሰ ሳምቡሳና ብስኩት በሻይ እያወራረደ ነበር የምሳ ክፍለ ጊዜውን የሚያሳልፈው፡፡ ‹‹አሁን ግን ከምግብ ቤቶች ሸሽተው የመጡ በርካታ የመንግሥትና የግል ድርጅት ሠራተኞች አላስቀምሰን አሉ…›› ነበር ያለኝ፡፡ በየጥጋጥጉ ሳምቡሳና እርጥብ የሚሠሩ ሰዎች ዘንድ በምሳ ሰዓት ብዙዎች ስለሚመጡ፣ የበፊት ደንበኞች ያልጠበቁት ግፊያ እንደገጠማቸውና ነገሩ አስደንጋጭ እንደሆነበት ነበር የነገረኝ፡፡ መካከለኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል ወደ ታች እየተገፋ መሆኑን አመላካች መሰለኝ፡፡
የኑሮው መክበድ ብዙዎችን ለልመና ጎዳና እያወጣቸው ነው፡፡ መንገዱ እንደሆነ በበርካታ ምፅዋት ጠያቂዎች መጥለቅለቁን በዓይናችን እያየን ነው፡፡ በቅርቡ አንድ ትልቅ ሰው አስቁመውኝ፣ ‹‹ልጄ ልመና ስለማልችልበት እባክህን ያለህን ያህል ስጠኝና ሁለት ቀን ሙሉ ያላገኘሁትን ምግብ ልቅመስ…›› ሲሉኝ በጣም ነበር የደነገጥኩት፡፡ እኚህ ሰው ለ35 ዓመታት በመንግሥት መሥሪያ ቤት አገልግለው በጡረታ ቢሰናበቱም፣ ጧሪ ልጅ ስለሌላቸው ብቻ በአነስተኛ የጡረታ ዳረጎት በቀበሌ ቤት በኪራይ መራሩን ኑሮ መግፋት እንዳቃታቸው በሐዘን ነበር የነገሩኝ፡፡ ‹‹ባለቤቴ ይህንን ጉድ ሳታይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታ በመሄዷ ለእሷ ማዘን መተው ከተውኩ ቆይቻለሁ፡፡ ምነው ፈጣሪ እኔንም በወሰደኝ ነው የዘወትር ፀሎቴ…›› ብለው ሲያለቅሱ አብሬያቸው ነበር ያነባሁት፡፡
ከተለያዩ አካባቢዎች ጎጆአቸው ፈርሶ ተፈናቅለው በየሜዳው የተበተኑ ወገኖች የሚቀምሱት አጥተው ለከፋ ችግር ተዳርገዋል፡፡ ቦሌ ኢድና ሞል ሕንፃ አጠገብ ሦስት ልጆቿን ይዛ ምፅዋት ስትጠይቅ ያገኘኋት አንዲት ልጅ እግር እናት፣ ሸገር ዙሪያ ቤታቸው ከፈረሰባቸው ተንከራታቾች መካከል አንደኛዋ መሆኗን ስትነግረኝ ዕንባዋ በሁለት ጉንጮቿ ላይ እየፈሰሰ ነበር፡፡ ባለቤቷ በቀን ሥራ ይተዳደር እንደነበረና ቤታቸው ከፈረሰ በኋላ የአራት፣ የስድስትና የስምንት ዓመት ልጆቿን የምታስጠልልበትም ሆነ የምታበላቸው እንደሌለ ስትናገር መፈጠርን ያስጠላ ነበር፡፡ ልክ እንደ እሷ ሕፃናት ይዘው ሜዳ ለሜዳ የሚንከራተቱ ብዙ መሆናቸውን ነግራኝ፣ ‹‹አሁንስ ፈጣሪ መቼ ይሆን እኛንም አገራችንንም በቃችሁ የሚለን…›› ብላ ስታለቅስ ህሊናዬ ነበር የደማው፡፡
ችግሮቻችን ከመብዛታቸው የተነሳ አንዱን ይዞ ሌላውን መተው ባይቻልም፣ በተቻለ መጠን ግን አንገብጋቢዎቹን ለይቶ መፍትሔ መፈለግ ካልተቻለ መከራው እየባሰ እንደሚሄድ ልንጠራጠር አይገባም፡፡ ለምሳሌ ለመኸር እርሻ በአጠቃላይ የቀረበው ማዳበሪያ ሃምሳ በመቶ ብቻ ነው ሲባል፣ ዘንድሮ ሊገኝ የሚችለው ምርት ከበፊቱ በምን ያህል መጠን ሊቀንስ እንደሚችል መዘንጋት አይገባም፡፡ የምግብ ችግሩ እየተባባሰ የሚሄድ ከሆነ አብዛኛው ሕዝብ የሚበላው ያጣና የሚከተለው ቀውስ ከወዲሁ ያስፈራል፡፡ አንድ የግብርና ኢኮኖሚክስ ባለሙያ እንደነገሩኝ የምግብ ቀውሱ ከፍተኛ ትኩረት ካልተሰጠው፣ ኢትዮጵያ ዓይታው የማታውቀው ከባድ ቀውስ ይቀሰቀሳል፡፡
ችግሮቹን ብቻ በመዘርዘር የወል ኃላፊነትን አለመወጣት ጥሩ ስላልሆነ፣ እኔ ራሴ እንደ ዜጋ ሐሳብ ስላለኝ አዳማጭ ካለ ይኸው እላለሁ፡፡ መንግሥት ሕዝብ የማስተዳደር ኃላፊነቱን መወጣት የሚችለው፣ ከራሱ ከሕዝቡና ከተለያዩ መስኮች ባለሙያዎች ጋር በመነጋገር ነው፡፡ የመንግሥት ፖሊሲና ስትራቴጂ ቅኝቶች ሕዝብን ማዕከል ሳያደርጉ ሲቀረፁ፣ ከችግር አረንቋ ውስጥ ሊያወጡ ቀርቶ የባሰ የመከራ ዶፍ ያስከትላሉ፡፡ የምግብ ችግሩን ለመቅረፍ ሰላም ያስፈልጋል፡፡ ለሰላም መስፈን መንግሥት ተነሳሽነቱን ይውሰድ፡፡ ከአድሎአዊና ከብልሹ አሠራሮች በመላቀቅ መንግሥታዊ ተቋማት በሥርዓት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ዕድሉ ይፈጠር፡፡ ተቋማቱም ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ዕሳቤ የሚመጥን አመራርና ተቋማዊ ቁመና ይኑራቸው፡፡ የመንግሥት አመራሮችም ከምንም ነገር በላይ ሕዝብና አገርን ያስቀድሙ፡፡ ከአገር ከፋፋይ አጀንዳዎች ተላቀው ለአገር አሳቢ ይሁኑ፡፡ እየመጣ ያለው ጊዜ በጣም አስፈሪ መሆኑን ይገንዘቡ፡፡
(ምናሴ ተዘራ፣ ከኦሊምፒያ)