በየዕለት ኑሯችን ሊሻሻሉ ሲገባቸው የማይሻሻሉ ጉዳዮች ሲበራከቱ፣ ‹‹ኧረ ወዴት እየሄድን ነው?››፣ ወይም ደግሞ ከዚህ ከፍ ብሎ፣ ‹‹ይህች አገር ወዴት እየሄደች ነው?›› የሚል ምሬት አዘል አገላለጽ መደመጡ አይቀሬ ነው። እነዚህ ምሬት አዘል አገላለጾችም ዛሬ ከማኅበረሰቡ መደመጥ ጀምረዋል። እነዚህ ምሬት አዘል ንግግሮች ተደጋግመው የመደመጣቸው ሚስጥር በዕለት ተዕለት ኑሯችን የሚያጋጥሙን የተለያዩ ክስተቶች ከመሻሻል ይልቅ ብሰው የሚታዩ በመሆናቸው ነው፡፡
የተሻለ አገልግሎት ሲጠበቅ የተበለሻሸ ሆኖ ሲገኝ የቀደመውን እስከ ማመሥገን የምንደርስበት ጊዜ አለ፡፡ በተለይ ደግሞ ወደ ገበያ ወጣ ብሎ አስቤዛ የመሸመት ልምድ ያለው የገበያውን ሁኔታ እያየና እያጋለ እንጂ፣ እየበረደ ያለ ነገር ያለ መኖሩን በመታዘብ፣ ‹‹ኧረ ወዴት እየሄድን ነው? ማብቂያውስ መቼ ነው?›› የሚለው ጥያቄ ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ አሁን አሁን እንዲህ ያለው ምርት ዋጋው ቀነሰ የሚለውን ቃል መስማት ብርቅ ሆኖብናል፡፡ ሰነባብተን አንድ የምንፈልገውን ምርት ለመግዛት ጎራ ካልን ‹‹ዋጋው ጨምሯል›› የምትለዋ ቃል በአገራችን ግብይት ውስጥ ደጋግመን የምንሰማው ሆኖ ቀጥሏል፡፡
መሠረታዊ ከሚባሉ የተለያዩ የዕለት የፍጆታ የዕቃዎችና ለተለያዩ ግብዓቶች የምንጠቀማቸው ምርቶች ሁሉ ከቀናት በኋላ መልሰን ስንገዛቸው በቀደመው ዋጋ የማናገኛቸው ከሆኑ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን እንደ ሸማች ግብግብ የሚያረገኝ፣ እምብዛም አይመቸኝም ያልኩትን፣ ‹‹ይህች አገር ወዴት እየሄደች ነው?›› የሚለውን አባባል ደፍሬ እንዳወጣው የሚያስገድደኝ በኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ በቀላሉ ልናመርታቸው የሚችሉ ምርቶችን በአግባቡ ማምረት ተስኖን፣ ነጋ ጠባ በእነዚህ ምርቶች ሸማቹ ዘወትር እየተማረረ ነው፡፡ በገበያ ውስጥ በምንም ምክንያት ይሁን አንድ ምርት በተደጋጋሚ እጥረት ሲፈጠርና ዋጋው ሲሰቀል ችግሩን ከሥሩ ተረድቶ ለከርሞ እንዳይደገም ለማድረግ የሚሠራም፣ የሚያሠራም መጥፋ በእጅጉ ያስቆጫል፡፡
በእጃችን ያለውን አቅም ባለመጠቀም ብቻ ለዋጋ ንረት የምንዳረግባቸው እጅግ ብዙ የምርት ዓይነቶች እንዳሉም እንገነዘባለን፡፡ ሌላውን ሁሉ ነገር ትተን ሽንኩረትን ብቻ ብንወስድ በተወሰኑ ወራት ልዩነት ዋጋው እላይ እየተሰቀለ፣ ለሸማቾች ፍዳ መሆን ከጀመረ ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም፣ ዛሬ ላይ ፍፁም ሊታመን የማይችል ዋጋ ተሰጥቶ ሲሸጥ ማየት እውነት በጣም የሚያስቆጭና የስንፍናችንንም ልክ የሚሳይ ነው ማለት ይቻላል፡፡
በዚህ ሳምንት አዲስ አበባ ላይ አንድ ኪሎ ሽንኩርት ከ110 እስከ 120 ብር ተሸጠ ሲባል ለማመን የሚከብድ ቢሆንም በተጨባጭ እየሆነ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ሩቅ ሳንሄድ ከአንድ ዓመት በፊት ሽንኩርት ተወደደ ብለን የአገር መነጋገሪያ ለመሆን የበቃው የአንድ ኪሎ ሽንኩርት 50 ብር ገባ ተብሎ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ኪሎ ሽንኩርት ለዓመታት ከ15 እስከ 20 ብር ሲሸጥ ነበር፡፡ አሁን ይለይላችሁ ብሎ የአንድ ኪሎ ሽንኩር 120 ብር ዋጋ ‹‹ለምን ሆነ?›› ብሎ የሚጠይቅ አካል ያለመኖሩ ብቻ ሳይሆን፣ ይህንን እየደጋገመ የሚፈትነንን የሽንኩርት እጥረትና የዋጋ ንረት ዘላቂ መፍትሔ የሚያበጅ ጎበዝ ማጣታችንም በራሱ የዘፈቀደ ጉዟችንን ንጥር አድርጎ የሚያሳይ ነው ብሎ ደፍሮ ለመናገር ያስገድዳል፡፡
የሚገርመው ነገር ሰሞኑን ሽንኩርት 120 ብር ገባ ሲባል ጥቂት የማይባሉ ሸማቾች የፈጠሩት ቀውስ ገበያውን ለበለጠ እጥረት መዳረጋቸው ነው፡፡
ስግብግብ ነጋዴ እንደምንለው ሁሉ፣ ስግብግ ሸማችም አለና ሽንኩርት 120 ብር ገባ ሲባል ተሽቀዳድሞ በመግዛት ጭራሽ የሽንኩርት እጥረት እንዲፈጠር አድርገዋል፡፡ እንዲህ ያለው ልምድ እጅግ ፅዩፍ ብቻ ሳይሆን ከመስገብገብም በላይ ነው፡፡ ለማንኛውም ኢትዮጵያን የሚያህል ትልቅ አገር ካለማችው ይልቅ ያላለማችው መሬት የበረከተበት ምድር ላይ በተደጋጋሚ በሽንኩርት ዋጋ መማረራችን ሊያሳርፈን ይገባል፡፡
አንድ ሰሞን እጥረቱን ለመድፈን ከሱዳንም ሽንኩርት ይገባ ነበርና፣ አሁን ይህንን ማድረግ ባለመቻሉ ችግሩን እንዳባባሰው ይታመናል፡፡ ይህም ቢሆን እንደ ኢትዮጵያ ልናፍርበት የሚገባ ነው፡፡ ቢያንስ የሽንኩርት ፍላጎታችንን ለማሟላት የተሻለ ዘዴ የሚፈጥር ትውልድ አጣን ወይ? ያስብላል፡፡
‹‹ኧረ ወዴት እየሄድን ነው?›› የማለታችንን ያህል እንዲህ ያሉ ቀላል ነገሮችን እንዴት አድርገን ማስተካከል እንችላለን ከማለት ይልቅ ዘወትር እናማርራለን፡፡ ስለዚህ የሽንኩርት ዋጋ ለምን 120 ብር እንደገባ ማጣራትና ትክክለኛውን መረጃ መስጠት እንደተጠበቀ ሆኖ በሽንኩርት ራሳችንን ያለመቻላችን ጉዳይ አንገት የሚያስደፋን ነው፡፡
በተደጋጋሚ የሽንኩርት ዋጋ ያላግባብ ከዋጋ በላይ እየተጠየቀበት ያለው በግብይት ሥርዓታችን ብልሹነት ቢሆንም፣ ፍላጎቱ ከመጨመሩ አንፃር የምርት እጥረት በመኖሩም ይሆናል፡፡ ስለዚህ እጥረት የሚታይባቸው በቀላሉ ሊመረቱ የሚችሉ እንደ ሽንኩርት ያሉ ምርቶች በብዛት እንዲመረቱ ወይም የተጠቃሚ ቁጥር እየጨመረ መሆኑ አሥልቶ፣ በእነዚህ ምርት ላይ መሰማራትና ገበያን ለማረጋጋት የሚችሉ ቀና ልቦች እንዴት እናጣለን?
ገበያን ለማረጋጋት የግብይት ሥርዓቱን ጤናማነት ለመቆጣጠር ኃላፊነት ያለባቸው ተቋማትስ ቢሆኑ የአገሪቱን የሽንኩርት ምርት መጠንና ፍላጎት አሥልተው፣ ተጨማሪ ምርት ለምን እንዲያመርቱ አይደረግም? ገበያን ማረጋጋት አንዱ መንገድ እኮ ክፍተት የሚታይባቸውን ምርቶች በማየት ይህንን ክፍተት ለመሙላት መሥራት ነው፡፡ ሽንኩርት በተደጋጋሚ በገበያ ውስጥ የሚፈጥረውን ቀውስ በማየት ይህ ጉዳይ ነገም የበለጠ ተግዳሮት ሊሆን ስለሚችል ‹‹ይህንን ምርት ለመጨመር ምን ይደረግ?›› ብሎ የሚያነሳ አካል እንዴት ይጠፋል? ሽንኩርትን በምሳሌነት አነሳን እንጂ፣ እዚሁ በቀላሉ የምናመርታቸው ምርቶች ሁሉ በተመሳሳይ የሚታዩ ናቸው፡፡
ለማንኛውም መንግሥት ኅብረተሰቡን መታደግ ካለበት ብዙ ውጣ ውረድ የሌላቸውን እንደ ሽንኩርት ያሉ ምርቶችን በሰፊው እንዲመረቱ ማድረግ የሚቻልበት ሰፊ ዕድል ያለው ሲሆን፣ ሁሌም እሳት በማጥፋት ሥራ ላይ መጠመዱ ለችግሩ መባባስ አንዱና ትልቁ ምክንያት ሆኗል፡፡
በተለይ መሠረታዊ የሚባሉ ምግብ ነክ የሆኑ ምርቶችን ዋጋ ልጓም ማበጀት የዋጋ ንረቱን ለማርገብ ሆነ በአገራችን በቀላሉ የሚመረቱ ሽንኩርትና ሌሎች የግብርና ምርቶችን ከተንዛዛ የንግድ ሰንሰለትና ውጣ ውረድ ለገበያ ማቅረብ ያስችላል። ለዚህ ደግሞ የተወሰነ ብድር አመቻችቶ መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች በስፋት እንዲያመርቱ ማድረግ ይቻላል። አሁን ላይ ምርታማነትን ሳይጨምሩ ወይም ለምርታማነት በግልጽ የሚታይ ድጋፍ እየተሰጠ ባልሆነበት ሁኔታ፣ ዓምና 60 ብር መግባቱ አጀብ ያስባለው ሽንኩርት፣ በወቅቱ ዘላቂ መፍትሔ ባለመበጀቱ ዛሬ 120 ብር ገብቷል። ነገ ደግሞ ከዚህ መባሱ አይቀርም፡፡
በአገሪቱ ስታትስቲክስ መሥሪያ ቤት መረጃ መሠረት በዓመት 2.7 መቶ እየጨመረ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ዓመታዊ የሕዝብ ብዛት ዕድገትን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ተጨማሪ ምርት ካልተመረተለት ፍዳው ይበዛል፡፡ የአገሪቱን የምርት አቅምን ለማሳደግ የሚችሉ ብርቱ እጆች የአገርን ምርት ለመጨመር ለሚያስችሉ ተግባራት ካልተዘረጉ ዛሬ የምንማረርበት የዋጋ ንረት ይበዛል፡፡