ሰላም! ሰላም! እነሆ መስከረም እንደ አመጣጡ ተገባዶ ሊጠናቀቅ የሳምንት ያህል ዕድሜ ሲቀረው፣ ለፈጣሪያችን ምሥጋና እያቀረብን ጥቅምትን ለመቀበል ሽር ብትን ከማለት ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም፡፡ ዕድሜ ሲቆጥር ምን ይደረጋል ታዲያ፡፡ ‹‹ይህ ሕይወት ካለፈው የቀጠለ ነው፣ አሁን የምትኖረው የተሰጠህን ነው…›› አለኝ አንዱ በቀደም ዕለት። አንዱ የምለው ወድጄ እንዳይመስላችሁ። አንድ አንድ እያልን ካልነጣጠልነው የዘንድሮ ቅዠት ተደራጅቶ ገና ጉድ ይሠራናል። አስቡት እስኪ ለዓመታት የኮንዶሚኒየም ቤት ዕጣ እንዲወጣልን ብለን ለቁጠባ ያበራነው ጧፍ ሳይጠፋ፣ ከአመድ መጣችሁ ወደ አመድ ትመለሳላችሁ ሲሉን፡፡ ሰው ዓይኑ እያየ የሚድርበት ታዛ ሳይኖረው ከገዛ ሐሳቡ በታች ውሎ እያደረ ልፋቱ ሁሉ ህልም ነው ሲባል። ኧረ ህልምና ራዕይ አይምታታብን ተው እባካችሁ። እኔ እኮ የምለው ይኼ አምታችነት የሚሉት ነገር መልኩን ቀይሮ አንድ በአንድ መለመለን እንዴ? እንዴት ማለት ጥሩ። አንድ በአንድ የመተንተን ችሎታ የምሁሩን የባሻዬ ልጅ ያህል ባላዳብርም ነገር መበተንን በደም የወረስኩት ነው። ምነው የሚወራውና የሚሠራው ሁሉ ‹ደም… ደም…› ይላል እያሉ የሚያስፈራሩ እያሉላችሁ፣ በእኔ ደም የማጥለል ሥልት ተገረማችሁ? እሺ እሱን ልተወው ይቅር፡፡ ይቅር ማለት ይሻላል!
ምን እያልኩ ነበር? አዎ የማምታት ዘዴ ገጽታውን ሳይቀይር አልቀረም ነበር ወሬያችን፡፡ እንግዲህ እንደምታውቁት ጎዳናው በሁለት ምድብ ከተከፈለ ቆይቷል። ተስፋ በቆረጡና ተስፋ በቀጠሉ፡፡ በነገራችን ተስፋ መቀጠልና መቁረጥ ወሬ ቆርጦ እንደ መቀጠል ቀላል አይደሉም፡፡ ስላልሆኑ ምን ሆነ? ‹ማን አቀርቅሮ ማን ተዝናንቶ ይኖራል› የምትል ነገር ተወልዳለች፡፡ ስለዚህ የትም ሳታውቁት አንዱ ቀረብ ብሎ ‹ዘመኑ አልቋል ንሰሐ ግቡ› ሲላችሁ፣ ዕውን ስለእናንተ መዳን ተጨንቆ መሆኑን መጠራጠር አለባችሁ። እኔማ እንዴት አልጠራጠር? ያ አንዱ ያልኳችሁ ተስፋ አስቆራጭ ከቀበጣጠረ በኋላ ምን እንዳለኝ አልነገርኳችሁም ለካ? ‹‹ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለመንግሥት ግብር አስገባ፡፡ ከዚያ ወደ ቀድሞ ሕይወትህ ዞረህ ተንፍስ…›› አይለኝ መሳለችሁ? ካፒታሊስቶች ይህንን ቢሰሙ አስቡት በታደሰና ባልታደሰ ኦክስጂን ሲበዘብዙን። ኧረ ኡኡ ማለት አሁን ነው!
ስለቤትና ቤተኛ እያሰብኩ ቤት ላሻሽጥ ደፋ ቀና እላለሁ። ቡልቡላ አካባቢ 175 ካሬ ላይ ያረፈች ቅልብጭ ያለች ‹ጂፕላስ ዋን› ካልገዛችሁ ብዬ መቆሚያ መቀመጫ ያሳጣኋቸው ደንበኞቼ ጠየቁኝ። አዲስ ደንበኛ ማፍራት እንደሆነ ድሮ ቀርቷል። ምክንያቱማ ጊዜው የሞኖፖሊስቶች ነዋ፡፡ እና ከአሁን አሁን አንዱ ደወለ እያልኩ ስቁነጠነጥ ስልኬ ይጮሃል፡፡ ‹‹ሃሎ?›› ስል፣ ‹‹አንበርብር አውጣኝ፣ የዘንድሮን አውጣኝ…›› አለኝ ከወዲያ፡፡ ‹‹ማን ነህ? ለምን አትረጋጋም?›› እላለሁ ዕርጋታ በጠፋበት በዚህ ጊዜ፡፡ ‹‹እንዴት ብዬ ልረጋጋ ፊልሜ ተሰርቆ?›› አይለኝ መሰላችሁ? ቀስ ብዬ ሳጣራ እውነትም ፊልሙ ተሰርቆ አንበርብር ዘንድ ደውል ተብሎ ነው የደወለው፡፡ የዘመኑ ባለፀግነት የሕዝብ ሀብት በመመዝበር ላይ የተመሠረተ ይመስለኝ ነበር፡፡ ለካ ፊልም መስረቅንም ይጨምራል። ቆም ብዬ ሳስበው ያበሽቀኝ ጀመር። ጊዜያችን አብሻቂ ብቻ ሳይሆን አሰልቺ የበዛበት ሆኖ ነው መሰለኝ ትክት ይለኛል፡፡ ምን ላድርግ ታዲያ!
‹እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ገዥና ሻጭ የማገናኝ ፕሮፌሽናል ደላላ እንጂ ሌባና ፖሊስ የምጫወት ሕገወጥ ደላላ ነኝ እንዴ?› ብዬ ራሴ ላይ ጮህኩ፡፡ ውሎ አድሮ ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር ስናወራው፣ ‹‹ይቀልዳል እንዴ? ሰው ኑሮውን፣ ቤተሰቡን፣ አገሩን፣ ማንነቱን በቁሙ በሚዘረፍበት አገር ፊልሜ ተሰረቀ ብሎ ለአንተ ሲደውል ትንሽ አያፍርም?›› ነበር ያለኝ፡፡ ‹የተማረ ይግደለኝ› ብዬ ሳልጨርስ የባሻዬ ልጅ የዘረዘራቸው ነገሮች ሌላ ራስ ምታት ሆኑብኝ። ‹‹የት ሄጄ ልሰደድ?›› አለ የታከተው የአገሬ ሰው። ቆይ እኔ ምለው ህልምና ሐሳብ አልቆ ነው ሰው ፊልም ወደ መሰራረቅ የዞረው? ቢሆንስ እኔን የመሰለ ስመ ጥር ደላላ እዚህ ውስጥ ምን አገባው? አቤት የእኛ ሰው ግን አነካኪ ነው። በፎቅ ላይ ፎቅ መሥራት የሚያቅተውን ተውት። ችግኝ ላይ ችግኝ ደርቦ የሚተክለውን ፊልመኛ ማን ይሆን ግን የሚሰርቀው? ያልተያዘ ግልግል ያውቃላ!
ግልግል ስል በቀደም ከአንድ ለማኝ ጋር በገላጋይ ተለያየሁ። እንጃ ዘንድሮ አመሌ ከፋ መሰል። ሆድ አልሰፋ ሲል ምን ይሁን? መታሰቢያ ማጣትም እኮ አንዱ ችግር ነው። በአፍ ሁላችንም እኩል ሆነን። ዕድሜ ለገንዘብ፡፡ ሐውልት የሚቆምለት ትልቅ ሰው ጠፋ፡፡ እና ምን ይመጣ ከዚህ በላይ? ለማኙ፣ ‹‹በመስከረም!›› ይለኛል ወር አያልቅም ብሎ፡፡ በኋላ፣ ‹‹አንተ ሰውዬ ከእኔ ምን አለህ?›› ስለው እጁን ዘርግቶ ያራግበው ጀመር። ልመና መሆኑ ነዋ፡፡ ‹‹ጋሼ በመስከረም አንድ ባለሁለት መቶ ይጣሉልኝ…›› ይለኛል። ጭራሽ ይኼ ደግሞ እንደ ግብር አስከፋይ (ቀራጭ) ተመን አውጥቶ ነው አምጣ የሚለኝ፡፡ ‹‹አንተ ማን ነህና ነው የምሰጥህን ምፅዋት ተመን የምታወጣለት…›› ስለው በቁጣ፣ ‹‹ጋሼ አትቆጣ እንጂ፣ በየደረስክበት የተጠየቅከውን እየከፈልክ አይደለም እንዴ ሳታንገራግር የምትወስደው፡፡ የእኔ እኮ በፈጣሪ ስም የቀረበልህ ልመና ነው…›› ብሎኝ ሲስቅብኝ፣ ‹‹መስከረም የሚባል ፈጣሪ የለም…›› ብዬው ጥዬው ተፈተለኩ፡፡ ፖለቲከኛውም የእኔ ቢጤውም ከአንድ ኮሌጅ ነው እንዴ የሚመረቁት ያሰኛል እኮ፡፡ ጉድ በሉ!
ካነሳሁት አይቀር ስለገንዘብና አያያዙ ብዙ እንድንጫወት ፈልጌያለሁ። እኛና ገንዘብ እንዲሁ አሁን አሁን ዓይጥና ድመት ከመሆናችን በፊት እንዲያው ማን ይሙት የሠራነው ግፍ አይቆጠርም። በአጭሩ ‹ጢባ ጢቤ ተጫወትንበት› በተባለው ዓይነት ብንይዘው ይቀላል። ሌላ ገላጭ የለውም። ዛሬ እሱ በተራው ይኼው ያንቀረቅበናል። እኛም አያያዙን አንችልበት እሱም አንጠባጠቡን አብዝቶት፣ አዳሜ አግኝቶ በማጣት ተውኔት ሰማይ ነክቶ ሲፈርጥ የአልፎ ሂያጅ መሳቂያ ሆኗል። ከአወዳደቅ መማር ለእኛ አልተፈጠረምና የሳቅንም በዓመቱ ሊሳቅብን ተራ እንይዛለን። ኧረ አጀብ ነው። አጀብ ብለን ጀምረን ሳንጨርስ ደግሞ መስከረም ጠብቶ ዕዳ ያሸክመናል። ሌላ አጀብ አትሉም። ታዲያ ምን ሆነ መሰላችሁ? ያንን የቦሌ ቡልቡላ ቤት አሻሽጨ ኮሚሽኔን ተቀበልኩና ባሻዬ አስጠርተውኝ ወደ እሳቸው ሄድኩ። እሳቸው ለአንድ ጉዳይ ፈልገውኝ ስለነበር ስደርስ ከአንድ አዛውንት ጋር ጠላ እየጠጡ ያወራሉ፡፡ ወሬያቸው ደግሞ ከዛሬ ሃምሳ ዓመት በፊት ስላለፉበት ሕይወት ነው፡፡ እኔ ደግሞ ያለፈውን ዘመን ታሪክ ማዳመጥ ብወድም የብዙዎቹ ታሪክ ተናጋሪዎች ግነት ብግን ያደርገኛል፡፡ እውነቴን እኮ ነው!
እንግዳው አዛውንት ከቀረበላቸው ጠላ ማግ እያደረጉ፣ ‹‹… ባሻዬ ይኸውልህ እኛ የኮንጎ ዘማቾች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተፈቀደልን አበል አልተከፈለንም ብለን የጀመርነው አመፅ አብዮት ቢያስነሳም፣ አብዮቱ በእነዚያ መልቲ መኮንኖችና ከአሜሪካና ከአውሮፓ በተሰባሰቡ ጎረምሳ ፖለቲከኞች ተጠልፎ እንዳይሆኑ ሆነ ቀረ እልሃለሁ…›› እያሉ አዲስ ታሪክ መጻፍ ሲጀምሩ ደነገጥኩ፡፡ አዛውንቱ ባሻዬ በትዝብት እያዩዋቸው፣ ‹‹ሃምሳ አለቃ ተው እንጂ፣ የኮንጎ ዘማቾች ጥያቄ መቅረብ የጀመረው እኮ አብዮቱ የንጉሠ ነገሥቱን ዙፋን ከነቀነቀ በኋላ ነው፡፡ ጭራሽ እኛ አዛውንቶች ከዚህ ምድር በመሰናበቻችን ጊዜ ዋሽተን ካስዋሸንማ ታሪክ ይቅር አይለንም…›› ብለው ሲያርሟቸው ቀለብላባ ምላሴ ወደ አፎቷ ተመለሰች፡፡ ባሻዬ በይሉኝታ ዝም ቢሉ ኖሮ የአዲሱ ታሪክ ፈብራኪ ከእኔ የነገር ሚሳይሎች አንዱን ይቀምሱ ነበር፡፡ አብዮቱ ሃምሳ ዓመት ሊሞላው አምስት ወራት ያህል እየቀሩት ታሪካችንማ አይዛባም፡፡ መረን የተለቀቁት ጥራዝ ነጠቅ ፖለቲከኞችን እንዲህ ነበር እጅ ከፍንጁ መያዝ፡፡ አጭበርባሪ ሁሉ!
በሉ እንሰነባበት። ማለቱን እንላለን እንጂ መኖሩን ከተውን ቆይተናል። ንግግር የበዛው ለምን መሰላችሁ ታዲያ? እውነቴን ነው። ሰሞኑን ታዲያ እኔና ምሁሩ የባሻዬ ልጅ በጊዜ ተገናኝተን በጊዜ ተጎንጭተን በጊዜ ወደ ቤታችን መሯሯጥ ይዘናል። የባሻዬ ልጅ በችኮላ ወጥተን በችኮላ ስንገባ፣ ‹‹አወይ ኃላፊነትን መዘንጋት?›› ይላል። ‹‹የምን ኃላፊነት?›› ስለው፣ ‹‹አታይም እንዴ እያንዳንዳችን የገዛ ኃላፊነታችንን እየረሳን በሰላማችን፣ በህልውናችን ላይ የመጣውን ችግር። ‹ሳይቃጠል በቅጠሉን› ረስተን ይኼው እንደ ፖንፔ ሕዝብ ገሞራው ከፈንዳ በኋላ የሞት የሽረት ጨዋታ ስንጫወት…›› ሲለኝ ግራ ገብቶኝ ዝም አልኩ። እኔ እምልህ አልኩት ቀስ ብዬ። ‹‹አንተ የምትለኝ…›› አለኝ። ‹‹ፖንፔ ማን ናት?›› ስለው ከት ብሎ ስቆ፣ ‹‹አይ አንበርብር አረጀህ እኮ?›› ብሎ ይስቅብኛል። እሱ የዓለምን ታሪክ ጠጥቶታልና እኔ ማስታወስ ሲያቅተኝ አረጀህ እባላለሁ። ‹‹ወይ ዘንድሮ…›› አለ ዘፋኙ። እናላችሁ ምሁሩ በየባሻዬ ልጅ በትንሹ ያጫወተኝ የፖንፔ ታሪክ መሰጠኝ። የፖንፔ ሕዝብ በአሁኒቷ ጣሊያን ግዛት ከዛሬ 2,000 ዓመት በፊት ይኖር ነበር። ማሲቩየስ የሚባል ታላቅ ተተራ አጠገቡ አለ። ይኼ ተራራ ያልበረደ የእሳት ውኃ ውስጡ እያራገበ ከቀን ቀን ቅራኔው ሲጨምር የፖንፔ ሕዝብ ይበላ፣ ይጠጣ፣ ይዘፍንና ይዳራ ነበር። ልክ እንደ ነነዌ በሉት!
አንድ ቀን አገር አማን ብሎ ሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮውን ሲያከናውን ያ እሳተ ጎሞራ ወጥቶ ፈሰሰበት ነው ታሪኩ። ወደ እኛ ፖንፔ ስንመለስ ደግሞ እኔና የባሻዬ ልጅ ጥቂት እንደተያየን፣ ለአፍታ አንገቴን ባዞር ከየት መጣ ያላልኩት ጠርሙስ በግንባሬ ትይዩ ይምዘገዘጋል። እንዴት እንደሳተኝ አምላክ ያውቃል። ግሮሰሪው በአንድ እግሩ ቆመ። ስድብና ቡጢ እንደ ሆያ ሆዬ ተዛዝለው አበዱ። ምንም በማናውቀው ነገር በተቀመጥንበት ተቸክለን ቀረን። ፖሊስ መጣ፣ ታፍሰን ፖሊስ ጣቢያ። ማንጠግቦሽ ስትሰማ አሉ ጨርቋን ጥላ ልታብድ ምንም አልቀራት። መርማሪው ፀበኛውንና ሰላማዊውን ከለየ በኋላ የፀቡ መነሻ ሲጣራ ስም ሆኖ አረፈው። ስም እንዴት ያጣላል የምትሉ ጠይቁና ድረሱበት። እኮ ከዚህ በላይ ምን እሳተ ጎሞራ አለ ጎበዝ? ኧረ ‹ሳይቃጠል በቅጠል?› ብለን ብለን በስም እንጣላ? ዋ ‹ይኼም ቀን ያልፍና…› አለ ዘፋኙ። እስኪ ልብ እንግዛ። ሌላ ምን ይባላል ታዲያ!
በመስከረም ማገባደጃ ሰሞን ላይ ሆነን ድድ ማስጫችን ወጋችንን እየጠረቅን የደንበኞቻችንን ስልክ ስንጠባበቅ ሳለ፣ አንድ በቅርቡ የደላላውን ቡድን በነፃ ዝውውር የተቀላቀለ ወጣት ደላላ ስልኩ ጮኸ፡፡ አንስቶ መነጋገር ሲጀምር ቢዝነሱ ከበድ ያለ ይመስላል፡፡ ‹‹ይዞታውን እኮ ከእነ ብሉ ፕሪንቱና ኢሜጁ በዋትስአፕ ልኬላችኋለሁ፣ እኔም ከሰዓት በኋላ በተባባልነው መሠረት እደርሳለሁ…›› እያለ ሲነጋገር ዘ ልማዳውያን በመገረምና በድንጋጤ ስሜት ተያዩ፡፡ ቀደም ብለን መተግበሪያዎችን መጠቀም የጀመርነው ግን እንደ ወትሮው ሁሉ ወሬያችንን ቀጠልን፡፡ በወሬያችን መሀል ግን ከዘመናዊነት ራቅ ያሉት የመከፋት ስሜት ሲሰማቸው እያየሁ ነበር፡፡ ለብቻቸው ፈንጠር ብለው ሲያወሩ ግን አልመችህ አለኝ፡፡ ጎበዝ እንዴት ነው ነገሩ? ወደ ሥልጣኔው ጎራ መቀላቀል ወይስ ተገፍቶ መንገዋለል ይሻላል? ይህን ጊዜ ነበር ወጣቱ ደላላ፣ ‹‹እኔማ በዘመነ ፌስቡክና ቲክቶክ ወረቀት ብተና ተጀመረ ሲባል ነው ነገር ዓለሙ የበቃኝ…›› እያለ ሲስቅ ከጀማው ተለይቼ ወደ ካፌ አመራሁ፡፡ ሥልጣኔ እጅ ከፍንጅ እስኪይዘንማ እጅ አንስጥ እንጂ፡፡ መልካም ሰንበት!