ሴቶች ከወንዶች እኩል ናቸው የሚለውን እውነታ ለመቀበል በርካቶች ብዙ ጊዜን ወስዶባቸዋል፡፡
በተለይ በቀደመው ዘመን ሴቶች ለወንዶች አገልጋይና ቤት ጠባቂ ከመሆን ውጭ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ውሳኔን የመወሰን፣ የማማከርም ሆነ ሐሳብ የመስጠት መብት የሌላቸው እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በቤት ውስጥ የሚሠሩት ሥራም ቢሆን በወንዶች ዘንድ ብዙ ትኩረት የማይሰጠውና የማያደክም ወይም ቀላል ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ምንም እንኳን ሴቶች ልጆችን ወልደው ከማሳደግ ጀምሮ በርካታ አድካሚ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ማከናወን፣ እንዲሁም በተለይ በገጠራማው አካባቢ ያሉ ሴቶች ከወንዶች ጋር ወደ ውጭ ወጥተው ከወንዶች ጋር እኩል ሥራዎችን ሲፈጽሙ ይስተዋላል፡፡
ከዚህ ባሻገር በተለይ በታዳጊ አገሮች በሴቶች ላይ ከሚደርሰው የሥራ ጫና በተጨማሪ ዘርፈ ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚደርስባቸው ይነገራል፡፡ አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ የተለያዩ ፆታዊ ጥቃቶች ይደርስባቸዋል፡፡
ጦርነት፣ ድርቅና የመሳሰሉት ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች በሚከሰቱበት ወቅት ቀድመው የጉዳቱ ሰለባ የሚሆኑት ሴቶችና ሕፃናት እንዲሁም አካል ጉዳተኞችና አቅመ ደካሞች እንደሆኑ በስፋት ይጠቀሳሉ፡፡
በዚህ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ሴቶች የአስገድዶ መደፈር፣ ለከፋ ረሃብ እንዲሁም ለሞት ያላቸው ተጋላጭነት ሰፊ ነው፡፡
ችግሩን የበለጠ አስከፊ የሚያደርገው ደግሞ ጥቃቱን የሚያደርሱት ተመጣጣኝ ቅጣት እንደማይፈጽምባቸው፣ ተጠቂዎችም ተገቢውን የሞራል ካሳ እንደማያገኙ የጥቃቱ ሰለባዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡
በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ከመድረሳቸው በፊት ለመከላከል፣ እንዲሁም ከደረሱ በኋላ የሚወሰዱት ዕርምጃዎች አጥጋቢ አይደሉም፡፡ ፖሊሲዎችና ሕጎችም ቢሆኑ አስተማሪና ችግሩን ከሥር መሠረቱ ለማስወገድ የሚያስችሉ እንዳልሆኑ ይነገራል፡፡
በ1986 ዓ.ም. የወጣው ብሔራዊ የሴቶች ጉዳይ ፖሊሲ ‹‹ከጥቃት ጋር በተያያዘ ብዙም የሚለው ነገር የለም፤›› የሚሉት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ወ/ሮ ፀሐይ ሽፈራው ናቸው፡፡
ፖሊሲው በወቅቱ ከነበረው ግንዛቤ አንፃር ጥሩ የሚባል ቢሆንም፣ ከዘመኑ ጋር አብሮ መሻሻል ዳግም መቀረፅ አለበት ሲባል መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ፖሊሲውን ዳግም በመቅረፅ ለሚመለከተው አካል የቀረበ ቢሆንም፣ ከመፅደቅ ጋር ተያይዞ ወደ ኋላ ቀርቷል ሲሉ የሚናገሩት ወ/ሮ ፀሐይ፣ ሌሎች ፖሊሲዎችና አዋጆች ለሕዝብ ተወካዮች ቀርበው የፀደቁ ቢሆንም፣ የሴቶች ጉዳይ ፖሊሲ ሳይሻሻል ግን ቆይቷል ብለዋል፡፡ አሁን ላይ መሻሻል እንዳለበትም ያምናሉ፡፡
በሥርዓተ ፆታና የሴቶች አቅም ግንባታ ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ ላይ አስፈላጊው ግብዓት መሰጠት እንዳለባቸውም አክለዋል፡፡
ግብዓቶቹም ፖሊሲውን የሚያዳብሩ በተለይ ሥርዓተ ፆታ ምንድነው ከሚለው ጀምሮ፣ የሴቶች አቅም ግንባታ ላይ ምን መሠራት አለበት የሚለውን መሠረት ያደርጋሉ፡፡ ሴቶች ወደ ውሳኔ ሰጭነት እንዲመጡ በምን በኩል ማገዝ ይጠበቅበታል የሚለውን ከተሞክሮ በመነሳት ግብዓት እንሰጣለን ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ሰው ሠራሽ በሆኑ ችግሮች ሳቢያ በሴቶችና ሕፃናት ላይ ጥቃቶች እየተፈጸሙ ይገኛሉ ያሉት ኃላፊዋ በተለይ ሴቶች እየተደፈሩ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ከሚፈጸምባቸው ጥቃት አንፃርም በጥቃት አድራሾች ላይ የሚወሰደው ዕርምጃ በሕጉ ሲታይ አስተማሪ አይደለም፣ ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ ሳይሆን ከመፈጸሙ በፊትም የሕግ ከለላ ሊደረግላቸው ይገባል ነው ያሉት፡፡
ቀደም ሲል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን የሚያስተዳድረው 621/2001 አዋጅ የሲቪል ማኅበረሰቡን ሊያሠራ አይችልም በሚል፣ በ2011 ዓ.ም. ተሻሽሎ በመቅረቡ፣ በሴቶች፣ በሕፃናት፣ በወጣቶችና በአጠቃላይ ድጋፍ በሚሹ የማኅበረሰብ ክፍሎች አተኩረው የሚሠሩ የማኅበረሰብ ድርጅቶች ነፃ ሆነው እንዲሠሩ ረድቷል ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የተወሰኑ ሥራዎችን ብቻ እንዲሠሩ የሚያስገድድ፣ ሴቶችን በሚመለከት በኢኮኖሚ ብቻ እንጂ ‹‹መብትን የሚመለከቱ ነገሮች እንዳንሠራ ታግደን ነበር፤›› የሚሉት የመሠረት በጎ አድራጎት ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ መሠረት አዘገ፣ አሁን ላይ በተሻሻለው አዋጅ በሴቶች መብት ጉዳዮች ላይም እንድንሠራ ተፈቅዶልናል ብለዋል፡፡
‹‹ልማትን ከመብት ውጭ መሥራት አደገኛ ነበር፤›› የሚሉት ወ/ሮ መሠረት፣ ከዚህ በፊት የሚሠሩ ሥራዎች በጣም ቁንፅል እንደነበሩ፣ አሁን ግን ሴቶች ከወንዶች እኩል መብት እንዳላቸው እያስተማሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ በልማቱና በመብት ማስከበሩ ላይም እየሠሩ እንደሚገኙም በመጠቆም፡፡