Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለመድኃኒት አቅራቢዎች ብቻ ታክስ መቀነስ የሚያስችል የጉምሩክ ማኑዋል ሊዘጋጅ መሆኑ ተሰማ

ለመድኃኒት አቅራቢዎች ብቻ ታክስ መቀነስ የሚያስችል የጉምሩክ ማኑዋል ሊዘጋጅ መሆኑ ተሰማ

ቀን:

ለአገር ውስጥ መድኃኒት አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያገለግሉ ከውጭ የሚገቡ የተለያዩ ዕቃዎች ላይ የሚጣለው ከፍተኛ ታክስ በመሆኑ፣ ለመድኃኒት አቅራቢዎች ብቻ መፍቀድ የሚያስችል የጉምሩክ ማኑዋል ሊዘጋጅ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራች ኢንዱስትሪዎች ዘርፍ ማኅበር አስታወቀ።

ማኅበሩ ከጉምሩክ ኮሚሽንና ከአርማወር ሀንሰን ሪሰርች ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ በመሆን እያዘጋጀ ያለው የጉምሩክ ማኑዋል፣ የጤና ሚኒስትር እያዘጋጀ ባለው የ‹‹ኢኮ ሲስተም አሰስመንት›› ሥር የሚገኝ ነው ሲሉ የማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ ዳንኤል ዋቅቶላ ለሪፖርተር ተናግረዋል።

በጤና ሚኒስቴርና በኢንስቲትዩቱ እየተሠራ ያለው ‹‹አሰስመንት›› ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የሚያግዝ መሆኑን፣ ማኅበሩ እያዘጋጀ ያለው ማኑዋል የጤና ሚኒስቴር ከሚሠራው አንደኛውን ክፍል ማለትም በጉምሩክ በኩል ያሉትን ችግሮች መፍታት የሚያስችል እንደሆነ ሊቀመንበሩ አስረድተዋል።

የጉምሩክ ማኑዋል መዘጋጀቱ በብሔራዊ ባንክ በኩል ያለውንና አሁንም ድረስ ለኢንዱስትሪው ማነቆ የሆነውን መመርያ እንዲሻሻል ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።

በሌሎች አገሮች የተመረተ መድኃኒት ከውጭ ሲገባ በሚጓጓዝበት ወቅት ያለው ጥራትና ቶሎ የመድረስ ሁኔታ፣ ከፍተኛ ችግር ሲፈጥር ቆይቷል ሲሉ አቶ ዳንኤል ተናግረዋል።

ለማዘጋጀት የታሰበው ማኑዋል የመድኃኒት አቅራቢ ድርጅቶች ለሚያስመጡዋቸው ዕቃዎች በሙሉ የታክስ ወጪ እንዲቀንስላቸው ድጋፍ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ዕቃዎቹ ከገቡ በኋላ በትክክል የመድኃኒት አምራቾች እየተጠሙቀባቸው መሆኑን የጤና ሚኒስቴር፣ የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ እንዲሁም የዓለም የጤና ድርጅት ቁጥጥር የሚያደርጉበት አሠራር እንዲፈጠር፣ በማኑዋሉ ውስጥ ለማካተት መታሰቡን አቶ ዳንኤል ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራች ኢንዱስትሪዎች ዘርፍ ማኅበር 22 አባላት ያሉት ሲሆን፣ ሰኞ መስከረም 21 ቀን 2016 ዓ.ም. የ20ኛ ዓመት ጠቅላላ ጉባዔውን አካሂዷል። በጉባዔው ላይ ከተገኙት ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮችና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት፣ ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ሐሳቦች ተነስተዋል።

በጉባዔው ከተገኙት አመራሮች መካከል የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር)፣ የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል፣ የኢትዮጵያ ሾፒንግና ሎጂስቲክ ኢንተርፕራይዝ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሲራጅ አብደላ፣ የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ወ/ሮ ዓለምፀሐይ ጳውሎስና ሌሎችም ተገኝተዋል፡፡

የመንግሥትና የግል ድርጅቶች በጋራ በርካታ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚችሉ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታው እዮብ (ዶ/ር) በውይይቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡

መንግሥት በጀመረው ሪፎርም የግሉ ሴክተር ከ80 በመቶ በላይ የብድር አገልግሎት የሚያገኝ መሆኑን፣ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ወ/ሮ ዓለምፀሐይ አስረድተዋል።

‹‹የመድኃኒት አቅራቢ ድርጅቶች ከውጭ ለሚያስመጧቸው ማናቸውም ዕቃዎች በሎጂስቲክ በኩል የሚፈጠሩ ችግሮችን ከተቋማቱ ጋር በጋራ በመሆን ለመፍታት ዝግጁ ነን፤›› ሲሉ የኢትዮጵያ ሾፒንግና ሎጂስቲክ ኢንተርፕራይዝ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሲራጅ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የመድኃኒት አቅራቢ ድርጅቶች፣ ለኅብረተሰቡ የሚያቀርቡት 41 በመቶ ብቻ መሆኑን፣ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት እስከ 70 በመቶ የሚሆነውን መድኃኒት ለማቅረብ ዕቅድ መያዙ በጉባዔው ላይ ተገልጿል።

ዘርፉ እንዳያድግ የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ ችግር እንደነበር፣ ሐምሌ 2015 ዓ.ም. በገንዘብ ሚኒስቴር የተወሰነው 55 በመቶ የመድኃኒት መሥሪያ ጥሬ ዕቃ ግብዓቶችን ለማስመጣት መንግሥት የውጭ ምንዛሪን በቀጥታ እንዲፈቅድ የተደረሰበት ውሳኔ ችግሩን እያቃለለ እንደሆነ፣ በጉባዔው የተሳተፉ የግል መድኃኒት አቅራቢ ድርጅቶች ገልጸዋል።

የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የሚችሉ አስመጪ ድርጅቶች የመድኃኒት ጥሬ ዕቃ እያስገቡ፣ ለአገር ውስጥ ፍላጎት ያልተቋረጠ አግልግሎት መስጠት አለባቸው ሲሉ የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...