- በዓመት የሚያገኘውን ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ያሳጣዋል
ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመዋዋል ከ25 ዓመታት በላይ የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከልንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የመስቀል አደባባይን ሲያስተዳድር የቆየው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ ከአስተዳደሩ ጋር የነበረው ውል መቋረጡ ተገለጸ፡፡
የኤግዚቢሽን ማዕከሉንና የመስቀል አደባባይን በማስተዳደር 50 በመቶ የትርፍ ድርሻ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር ሲጋራ የቆየው የንግድ ምክር ቤቱ፣ ውሉ እንዲቋረጥ የተደረገው በከተማ አስተዳደሩ በተቋቋመው ቦርድ ውሳኔ እንደሆነ ታውቋል፡፡
የኤግዚቢሽን ማዕከሉን እንዲመራ በከተማ አስተዳደሩ በቅርቡ የተሰየመው ቦርድ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው፣ በቦታው ላይ ከተማዋን የሚመጥን የኤግዚቢሽን ማዕከልና ኮንቬንሽን ሴንተር ለመገንባት በመወሰኑ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ቦርድ ለንግድ ምክር ቤቱ በጻፈው ዳብዳቤ፣ ማዕከሉ እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ልማት ያልተካሄደበት በመሆኑና በዚሁ ሁኔታ መቀጠል ስለሌለበት የነበረውን ውል ለማቋረጥ መገደዱን ማስታወቁ ተመልክቷል፡፡
በቦታው ላይ የታሰበውን ኢንቨስትመንት በጋራ ለማካሄድ አሁንም ቦርዱ ቅድሚያ ለንግድ ምክር ቤቱ መስጠቱን፣ በጋራ ማልማት የሚፈልግ ከሆነ ውሳኔውን በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንዲያሳውቅ የተገለጸለት መሆኑን ከምክር ቤቱ ምንጮች ማወቅ ተችሏል፡፡
የንግድ ምክር ቤቱ ከኤግዚቢሽን ማዕከሉ ቦርድ የተሰጠውን ውሳኔና በጋራ ለማልማት የተሰጠውን ዕድል እንዲያሳውቅ የተሰጠው ጊዜ እያበቃ ቢሆንም፣ እስካሁን ንግድ ምክር ቤቱ ምላሽ አለመስጠቱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የንግድ ምክር ቤቱ ቦርድ፣ የንግድ ምክር ቤቱ ከሰየማቸው አምባሳደሮች ጋር ሲመክርበት እንደነበር የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡ ነገር ግን በአስተዳደሩ ውሳኔ ላይ ንግድ ምክር ቤቱ ሊወስድ ያሰበውን ዕርምጃ በተመለከተ የንግድ ምክር ቤቱን ፕሬዚዳንትና ዋና ጸሐፊ ለማነጋገር የተደረጉ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ሊሳኩ አልቻሉም፡፡
በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር የኤግዚቢሽን ማዕከሉ ቦርድ ሰብሳቢና የንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢንያም ምክሩ፣ ውሳኔው ሊተላለፍ የቻለው በቦታው ላይ ከተማውን የሚመጥን ግንባታ ለማካሄድ ነው ብለዋል፡፡
ግንባታውን ለማካሄድ ምክር ቤቱ ቅድሚያ ዕድል እንደተሰጠው፣ ዕድሉን ተጠቅሞ የንግድ ኅብረተሰቡን በማስተባበር ከከተማው አስተዳደሩ ጋር በጋራ ለመገንባት በደብዳቤ ጭምር ጥያቄ እንደቀረበለት አክለዋል፡፡
የንግድ ምክር ቤቱ በዚህ ዕድል የማይጠቀም ከሆነ ግን ቦታውን ለማልማት ብዙ ጥያቄዎች እየቀረቡ ስለሆነ፣ ጥያቄ ካቀረቡ ባለሀብቶች ጋር በመሆን ማዕከሉን የከተማ አስተዳደሩ እንደሚያለማ ማስታወቁን ገልጸዋል፡፡
የአስተዳደሩን ውሳኔ ለመተግበር የግድ ቦታው ምንም ዓይነት ጥያቄ የማይነሳበት መሆን ስላለበትና የነበሩ ውሎችን ማቋረጥ ስለሚያስፈልግ፣ ውሳኔው ሊተላለፍ መቻሉንም አመልክተዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ከንግድ ምክር ቤቱ የቦርድ አባላት ጋር ሰፊ ምክክር የተደረገበት መሆኑን፣ የአስተዳደሩን ፍላጎት በተገቢው መንገድ ማስረዳታቸውንና በውሳኔው ላይ ንግድ ምክር ቤቱ በጋራ ማልማት ይችል ወይም አይችል እንደሆነ የሁለት ሳምንት ጊዜ የተሰጠው በመሆኑ ምላሽ እየተጠበቀ እንደሆነ አቶ ቢኒያም ገልጸዋል፡፡
የውሉ መቋረጥ የንግድ ምክር ቤትን ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ሊጎዳ እንደሚችል እየተገለጸ ነው፡፡
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከንግድ ምክር ቤቱ ዓመታዊ ገቢ ውስጥ ከኤግዚቢሽን ማዕከሉ ያገኝ የነበረው የተጣራ ገቢ ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህም ከዓመታዊ ጠቅላላ ገቢ ውስጥ ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚሆነውን የሚሸፍንለት እንደነበርም የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡ ከአስተዳደሩ በቀረበው ጥያቄ መሠረት ቦታውን በጋራ ለማልማት ሊቸግረው ይችላል የሚል አስተያየት የሚሰጡ አሉ፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት እያቀረቡ ያሉት ንግድ ምክር ቤቱ ከሰባት ዓመታት በፊት ዋና መሥሪያ ቤት እንዲገባበት ከአስተዳደሩ የተሰጠው ቦታ በፋይናንስ ችግር ባለመገንባቱ መነጠቁን ነው፡፡