አንድ አባት ዝንጀሮ ‘‘እኔ ከዚህ ሁሉ የዝንጀሮ መንጋ ጋር አብሬ ስንጋጋ በወንጭፍ ድንጋይ ዓይኖቼን ማጣት አልፈልግም፤’’ ብሎ ለብቻ መሰማራት ጀመረ፡፡ ነገር ግን ጾሙን ወደ ዋሻው ገብቶ ተቀመጠ፡፡ እናት ዝንጀሮ ደግሞ ከመንጋው ሳትለይ በተሰማራችበት ቦታ ሁሉ ጥሩ ዕድል አጋጥሟት ታላቅ ክምር ስትዘነጥል ውላ ተመለሰች፡፡ አባት ዝንጀሮን ‘‘እንዴት ዋልክ! ስተለው ዝም አላት፡፡ ‘‘ምነው ምን ሆነሃል? ደህና አይደለህም ወይ?’’ ብትለው መልስ መስጠት አልቻለም፡፡
ልጆቹም ‘ሰላም’ ሲሉት ዝም አለ፡፡ እናት ዝንጀሮ ትንሽ ቡጫሊት የሆነች ልጅዋን እጭኗ ላይ አድርጋ ስታስጨፍር ‘‘በሞኝ ክምር ዝንጀሮ ልጅዋን ትድር ‘እንዲሉ ዛሬም በልተናል ለነገም ክምር አይተናል’’ ስትል ሰምቶ አባት ዝንጀሮ ነቃ አለና ‘‘የት ነው እባክሽ?’’ አለ ይባላል፡፡ ታዲያ ይህ የራስ ወዳድነት ጸባይ ግን በአባት ዝንጀሮ ተመካኘ እንጂ የሰውን ራስ ወዳድነት ባህርይ አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡
መጋቤ አዕላፍ መክብብ አጥናው ‹‹ሁለገብ የአእምሮ ማዝናኛ›› (2005)