Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የመከፋት ስሜት!

ከቤላ ወደ ጊዮርጊስ ልንጓዝ ነው፡፡ መውሊድና መስቀልን በተከታታይ ቀናት ያከበርን እኛ ኢትዮጵያውያን፣ ዛሬ ደግሞ ጎዳናው አገናኝቶን ወደ ጉዳያችን ለማምራት ታክሲ ተራ ተገናኝተናል። ኅብራዊው ሕይወታችን እዚህች ምድር ላይ እንዳገናኘን ጎዳናውም በየዕለቱ ያስተናግደናል። በወርኃ መስከረም መገባደጃ አካባቢ መጣሁ ሄድኩ በሚለው ዶፍ ዝናብ ውሎው እንዳይበላሽና ሐሳባቸው እንዳይስተጓጎል ሥጋት የገባቸው ጥቂት አይደሉም። በፈጣሪ ቁጥጥር ሥር እስካለን ድረስ ያደረገንን ሆነን ባስቀመጠን ተገኝተን ከመኖር ሌላ ምን ምርጫ አለን? በአንፃሩ ጊዜን የሚቀድም የሚመስለው ከደመናው በላይ የማትጠፋውን የማትበራ ፀሐይ ባለችበት ሊያቆይ የሚሻው፣ በትከሻው ሌላውን መንገደኛ እየገጨ ያዝግማል። ‹‹ቀስ አትልም እንዴ?›› አንዱ ትከሻዋን አውልቋት ሲሄድ አንዲት ሞንዳላ ጮኸች፣ አላስተረፋትም መሰል፡፡ ‹‹ዘመናይ መንገዱን በሊዝ ገዛሁት እንዳትይ ብቻ፡፡ ዘንድሮ በሊዝ የሚሸጠውን መሬት በጉልበት የሚሻማውን አልቻልነውም…›› ብሏት መንገዱን ይቀጥላል። ትከሻዋን እያሸች ቦርሳዋን አጥብቃ ይዛ ንጭንጯን ሳታባርድ ታክሲ ፍለጋ ትቃብዝ ጀመር። ይህም የጎዳናው አካል ነው!

ከረጅም ሠልፍ ጥበቃ በኋላ አሮጌ ሚኒ ባስ ታክሲ መጥቶ ተሳፍረናል፣ ‹‹ደግ መቼ ይበረክታል?›› እያለ አንድ ክልስ የሚመስል ፊት ያለው ጎልማሳ ከጎኑ አብሮት ከተቀመጠ ሰው ጋር ወግ ጀመረ። ‹‹ተወኝ እስኪ…›› ይላል የወዲያኛው። ወያላው ክርኗ ተቀዳ የተጣፈች ሹራቡን እየደረበ፣ ‹‹የሚለብሰው የሌለው የሚከናነበውን እየሸመተ ባለባት አገር፣ እኔ ሳልቫጅ መቀየር ያቅተኝ? ወይኔ የሰውዬው ልጅ…›› እያለ ብሶቱን ለሾፌሩ ያካፍላል። ‹‹ፈጣሪ ሰው አያሳጣህ አቦ፣ ልብስ ቢደራረብ ያለ ሰው መቼ ይሞቃል?›› ይለዋል ሾፌራችን። ጋቢና የተሰየመ ወጣት ደግሞ፣ ‹‹የዘመኑን ሰው እኮ ገንዘብ ይዞት ጠፋ…›› እያለ የገዛ ሕይወቱን ውጣ ውረድ ሳይጠይቀው ለሾፌሩ ይነግረዋል። ሾፌሩ ራሱን እየነቀነቀ አንዴ መንገዱን አንዴ የተራኪውን ዓይኖች እያየ ይዘውራል። ‹ደግ አይበረክትም› ባዩ ጎልማሳ ክልስ መሳይ ወዳጁን ዘወር ብሎ፣ ‹‹ኧረ ለመሆኑ ያ ማነው ስሙ ደህና ነው?›› ሲል ስሙን የረሳውን ሰው ያነሳል። ‹‹ምን ይሆናል እሱ? ያችን ልጅ እንዳትሆን አድርጎ ተጫውቶባት ካበቃ በኋላ በዓመቱ ባለፈው ወር መሰለኝ ሠርግ ደገሰ…›› እያለ ይነግረዋል። ‹‹ወይ ድፍረት? እንኳንም ኢየሱስ ክርስቶስ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አልመጣ…›› ይላል። ‹‹እንዴት?›› ይጠይቀዋል ግርምት በተቀላቀለበት የድምፅ ቃና። ‹‹እህ ያኔ አንድ ሰው ነው አሳልፎ የሰጠው። አሁን ቢሆን ኖሮ አሥራ ሁለቱም አሳልፈው አይሰጡትም ብለህ ነው?›› ይላል ያኛው። ገጻችን በፈገግታ ተሳስቦ ቢወጠርም ውስጣችን ግን ደንግጧል። ስለራስ ዋጋ የለሽነትና ፅናተ ቢስ የኑሮ ልማድ እንዲህ በአደባባይ ዕውቅና እየሰጡ እንደ መጨዋወት ታዲያ ሌላ ምን የሚያም ነገር ይኖራል? ምንም!

‹‹ማን ስለሆነ? ምኑ ይሰረቃል ደግሞ እሱ? ኤሎን መስክ፣ ቢል ጌትስ ወይስ ዋረን ቡፌት ነው?›› ድንገት የአንዲት ወጣት ድምፅ በጥያቄ አስገመገመ። ‹‹ኧረ ዝም በይውማ እሠራለታለሁ…›› ትላለች አጠገቧ የተቀመጠች ወዳጇ። ‹‹እንዴ ሌላው ሰው በቃ ምንም የለውም? እንዲህ የዓለማችንን ታላላቅ ቱጃሮች እየጠራችሁ በሞራላችን የምትረማመዱት?›› አላት አጠገቤ የተመቀጠ ወጣት ተንጠራርቶ። ሴቶቹ እርስ በርሳቸው ተያይተው ሲያበቁ፣ ‹‹ከእኛዎቹማ ብዙዎቹ ወይ ጤና የላቸው ወይ ሰላም የላቸው፡፡ ምንጩ የማይታወቅ ሀብት አግበስብሰው ሲቃዡ የሚያድሩ ምስኪኖች ናቸው…›› አለችው አንደኛዋ። ታክሲያችን በሆታ ሳቅ ተናጋች። ‹‹አንቺ? ያውም በዚህ ወጣት ባለሀብቶች በበዙበት ዘመን እንዲህ ይባላል?›› አላት ወጣቱ መልሶ። ‹‹ሀብታቸው በዓለም እንዳያሳውቃቸው አመጣጡ አይታወቅም እባክህ። ‹ፓስወርዱ› የማይታወቅ ሀብት አይሠራም…›› አለች ሌላኛዋ። ‹‹ወይ ታክሲ ስንቱን ያሰማናል?›› ትላለች ጠና ያለች ወይዘሮ ከመጨረሻ ወንበር። ‹‹ሲያዩሽ የኑሮ ‹ፓስወርድ› የገባሽ ይመስላል። ለመሆኑ ይህ ያንቺው የሚስጥር ቁጥር በሙስናና በሽብር የሚያስጠረጥር ነው ወይስ ሰላማዊ ነው?›› ስትላት ሳቁ ቀጠለ፡፡  ከለቅሶ መሳቅ ይሻላል!

ሴቶቹ ቆንጅዬዎች ናቸው። መቼም ዘንድሮ መንገዱ በቆንጆዎች የተወረሰ ነው የሚመስለው እኮ፡፡ ‹‹አንተ ፋራ ነህ መሰል? በዲጂታል ዘመን እያደግክ መስሎኝ? የግለሰብ ‹ፓስወርድ› ይጠየቃል እንዴ?›› አለችው አንደኛዋ። ‹‹ምን ችግር አለው? ኃያላን መንግሥታትና የመረጃ ቀበኞች ሳያንኳኩ ከፈለጉ በቴሌግራም፣ ከፈለጉ በዋትስአፕ ሰብረው ይገቡ የለ። እንዲያውም እኔ በፀባይ ነው ጠየቅኩሽ…›› አላት። ወጣቶቹ መድረኩን እንደ ተቆጣጠሩት ዘለቁ። ልጁ ያሻውን የኑሮ ሚስጥር ቁጥር ግን እንዳሰበው አላገኘውም። ‹‹ለአንዱ የቀናው መንገድ ለሌላው ይቀና መሰለው እንዴ ይኼ? አቦ ተፋታቸው…›› መጨረሻ ወንበር ከወይዘሮዋ ጋር የተቀመጠ ጎረምሳ ሲናገር አጠገቤ የተቀመጠው ወጣት አልሰማውም። ‹‹ባልተሄደበት መንገድ መሄድ ባልተመነጠረ ጥሻ ውስጥ መጓዝ፣ ለእኛ ሰው የሚሞከር ነገር እንዳልሆነ አመጣጣችን ብዙ ይናገራል። ለዚህም ይሆናል በሰው ቁስል እንጨት ስንሰድ፣ በሰው ገበታ ጣታችንን ስናስገባ፣ የሰው ድስት ስናማስል የእኛ የምንለው የሌለን ሆነን ያረፍነው። ዝንት ዓለም ከሰረቀው ጋር ስንሰርቅ ከሸፈተው ጋር ስንሸፍት የማይሰለቸን…›› ይላል አንድ ጎልማሳ በምሬት። መጥኔ!

ጉዟችን እንደ ቀጠለ ነው። መጨረሻ ወንበር የተቀመጡት ጎረምሶች ተማሪዎች ናቸው። ወቅታዊና መሳጭ ጭውውት ይዘዋል። ‹‹በመጪው ዓመት ልትመረቅ ነዋ?›› ይሉታል አንደኛውን ጓደኛቸውን። ‹‹ዕድሜ ለበለጬ ይኼው እዚህ ደረስን…›› አላቸው እየሳቀ። ‹‹እንዲህ ብለህ ባልሆነ ፎቶ ተነስተህ የምረቃ መጽሔታችሁ ላይ የወጣኸው?›› አለው አንዱ። ‹‹እዚያ ላይማ ሥራ አጥነት መጣንልሽ ብያለሁ፣ አይደለም እንዴ?›› በማለት ይመልሳል። ‹‹ብራቮ… ብራቮ…›› ትከሻውን እየቸመቸሙ ያደንቁታል። ‹‹ቆይ ልውረድና እፈርምላችኋለሁ…›› ቢላቸው፣ ‹‹ግድ የለም የፊርማውን ነገር ከመጪው ዓመት በኋላ። ለጊዜው እንፈልግሃለን። ከእነ ጋዋንህ ደግሞ ወህኒ ወርደህ…›› እያለ አንዱ ያሾፋል። እርስ በርስ በክፉም በደጉ የሚተዋወቁ የሚመስሉት እነዚህ ወጣቶች ወጋቸው አይጨበጥም። ዘንድሮ ተመራቂ የሆነው ተማሪ ደግሞ በተራው ከተጠያቂነት ወደ አቀንቃኝ ተጫዋችነት ተገልብጧል። መሆን አለበት!

‹‹እከሌን ታስታውሱታላችሁ?›› አላቸው። ሊያስታውሰው ብዙም ሳይደክም አንዱ፣ ‹‹ምን ሆነ ደግሞ?›› አለው። ‹‹ምን ይሆናል አሁንማ የሆነውን አንዴ ሆኗል። ያን የመሰለ ብሩህ ቀለሜ የምግብ መመረዝ ሥር ሰዶበት ታሞ ባያቋርጥ ኖሮ አብሮን ይመረቅ ነበር…›› እያለ ከንፈሩን ይመጣል። ‹‹በኑሮ መመጣጠን አቅቶን በተመጣጠነ አመጋገብ አለመኖራችን ሳያንስ፣ ጭራሽ ዘንድሮማ አየሩም ተበክሏል ይሉናል…›› የሚለኝ አጠገቤ የተቀመጠው ወጣት ነው። ‹‹ታዲያ ላይታመም ኖሯል፣ በፊውዳሉ ጊዜ ንጉሡ ራሳቸው ሙዝና ብርቱካን ይዘው የሚጠይቁት፣ በጥራት ተመግቦ በጥራት የተማረ የነበረው ዛሬም በስተርጅና አገር የሚያተራምሰው ትውልድ፣ ‹የለም ከጥራት በብዛት አምናለሁ› እያለ መስሎን የትምህርት ጥራትን ገድሎ  ጉድ የሚሠራን…›› ሲል አንደኛው ይመልሳል። ወዲያው ደግሞ በሩቅ ያለ ጓደኛቸውን አንስተው (የሚታማው በትምህርቱ ቸልተኛና ግድየለሽ እንደሆ ካነጋገራቸው ያሳብቃል) ‹‹የምረቃ መጽሔቱ ላይ ምን ሊል ተዘጋጅቷል?›› ሲለው ከዚያ በኩል ዘንድሮ የሚመረቀው ወጣት ሳቅ እየቀደመው፣ ‹‹ከትልቁ ሾላ ከዛፉ ደርሼ፣ ያለ ዕድል አይበሉ መጣሁ ተመልሼ ካላልኩ እያለ ነው…›› ብሏቸው ከት ብለው ሳቁ። የሳቁ ኃያልነት ብዙም አልገባን። ትውልዱ ከአገሪቱ የትምህርት ፖሊሲ እስከ ገዛ ስንፍናው በመሳለቅ ፖለቲካውን እያሾረ እንደሆነ ግን አረጋገጥን። ይገርማል!

ወደ መዳረሻችን ነን። ‹‹እናንተ ይኼ የአውሮፓ እግር ኳስ እንዴት አድርጎ ይዞን ኖሯል ለካ?›› ሲል በግርምት ጎልማሳው እያወራ ነው። አብራራው ተባለ። ‹‹ይኼው አሁን ተጀምሮልን ፈታ አልን እንጂ በክረምቱ ጭር ብሎብን የምንሰማው ዜና ሁሉ የትርምስና የጦርነት ነበር። ከሰሜኑ የአገራችን ክፍል የጀመረው እስከ ሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ድረስ ስንቱን ሆረር ሰማነው?›› ከማለቱ ወያላው ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹መርጠን እያየንና እየሰማን እንጂ አሁንስ ቢሆን ብሶብን የለም እንዴ?›› ሲል፣ ‹‹እግዚኦ፣ ለዘመናት ክፉና ደጉን ያየን እኛ በመናኛ ፖለቲካ እየተላለቅን አገራችንን የመርገምት ምድር አደረግናት፡፡ ወግና ጨዋነት በማይጠበቅ ጭካኔ፣ ማጭበርበር፣ ማታለልና ስርቆት፣ አስገድዶ መድፈርና መሰል የወንጀል ድርጊቶች ዓለም ጭምር ሲከሰን ምን ያልሰማነው አለ? እንዲያው ሰምቶ እንዳልሰማ ዓይቶ እንዳላየ መሆን ቢቻል እንዴት ደግ ነበር በፈጣሪ፡፡ ግን የአገር ጉዳይ እንዴት ችላ ተብሎ ይታለፋል… በዚያ ላይ በዚህ አልላቀቅ ባለን ግጭትና ጦርነት ምክንያት የምንሰማቸው ጉዶች አያሳብዱም ወይ…›› አለች። ታክሲያችን መቆሚያ ሥፍራ ፈልጋ ስታቀዘቅዝ ወያላው በሩን ከፍቶ ‹‹መጨረሻ!›› ሲል፣ ወይዘሮዋ ለራሷ እያጉረመረመች ወርዳ የእግር መንገዷን ስትይዝ፣ የዚህ አላባራ ያለ ጦርነት ጉዳይ ሁላችንንም በመከፋት ስሜት ሰቅሶ የያዘን ይመስል ነበር። መልካም ጉዞ!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት