Saturday, July 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የህንዱ ሥጋ ላኪ ኩባንያ የአስመጪነት ፈቃድ ካልተሰጠው ሥራውን ሙሉ በሙሉ እንደሚያቆም አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ሁለት ድርጅቶችን የሚያንቀሳቅሰው የህንዱ ግዙፍ ሥጋ አምራች የሆነው አላና ግሩፕ፣ ሥጋ ወደ ውጭ ልኮ በሚያገኘው የውጭ ምንዛሪ የአስመጪነት (ኢምፖርት) ሥራ ለማከናወን የሚያስችለውን ፈቃድ ካላገኘ ሥራውን ሙሉ ለሙሉ እንደሚያቆም አስታወቀ፡፡

የግሩፑ አካል የሆነው አክሸከር ኢትዮጵያ ኬዚንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሐምሌ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ለእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት በጻፈው ደብዳቤ፣ ኢንስቲትዩቱ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር ተወያይቶ ማስመጣት እንዲችል እንዲያስፈቅድ መጠየቁን አስታውሰው፣ አሁን እያጋጠመ ባለው ኪሳራ ከቀጠለ በየቀኑ የሚልክውን የሥጋ ምርት እንደሚያቆም፣ የአላና ግሩፕ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ከሊፋ ሁሴን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ ለግብርና ሚኒስቴር፣ ለግብርና ባለሥልጣን፣ ለኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ለገቢዎች ሚኒስቴር፣ ለገንዘብ ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ለብሔራዊ ባንክ በግልባጭ መላኩን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ደብዳቤውን ተቀብሎ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ማስገባቱን አቶ ከሊፋ ተናግረዋል፡፡

ከሁለት ወራት በፊት የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ባዘጋጀውና የንግድ ሚኒስቴር፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የግብርና ሚኒስቴር ኃላፊዎች የተገኙበት የውይይት መድረክ ላይ የሚመለከታቸው የንግድ ማኅበረሰቡ አባላት ባሉበት በደብዳቤ የተገለጸው ጥያቄ ተነስቶ እንደነበር አቶ ከሊፋ አስረድተዋል፡፡

ከስብሰባው በኋላ ብሔራዊ ባንክ የወሰነው አስመጪዎች ከኤክስፖርት የሚያገኙትን የዶላር መጠን ከ20 በመቶ ወደ 40 በመቶ ከፍ ማድረጉ ኤክስፖርት አድርገው የምርት ግብዓት ከውጭ ለሚያስመጡ ድርጅቶች ብቻ የሚጠቅም መሆኑንና እንደ ሥጋ፣ ቡናና ሰሊጥ ላኪ ድርጅቶች ግብዓት ከውጭ የማያስመጡ ስለሆነ ውሳኔው ጥቅም እንደማይሰጣቸው አቶ ከሊፋ ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለኢምፖርት ንግዳቸው የውጭ ምንዛሪ የሚፈልጉ የኤክስፖርት ቄራዎችና ቄራ ተከራይተው የሚልኩ ኩባንያዎች የእንስሳት መግዣ ዋጋ በመናሩ፣  ከጊዜ ወደ ጊዜ ኪሳራው እየበዛ ኩባንያቸው ወደ ኪሳራ እየገባ መሆኑን አቶ ከሊፋ ተናግረዋል፡፡

የአገር ውስጥ ቄራዎችም ሆኑ ግለሰብ ላኪዎች በኢምፖርት ንግድ የሚያካክሱ ሲሆን፣ የህንዱ ድርጅት ግን የውጭ ባለሀብቶች ንብረት በመሆኑና በኢምፖርት ንግድ ላይ መሰማራት እንደማይችል በኢንቨስትመንት አዋጅ የተከለከለ ስለሆነ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው ወደ ውጭ ለሚልከው ሥጋ አንድ የቁም እንስሳት በኪሎ የሚገዛው በ420 ብር ወይም 7.4 ዶላር እንደሆነ፣ የወቅቱ ሥጋ ወደ ውጭ የመላኪያ ዋጋ 6.6 ዶላር መሆኑን፣  ይህ ማለት የማምረቻ ወጪ ሳይጨምር በአንድ ኪሎ ግራም 44 ብር ወይም 0.8 ዶላር ኪሳራ አለው ብለዋል፡፡

አላና ግሩፕ በወር አንድ ሚሊዮን ዶላር የሚያስገኙ የሥጋ ምርቶች ወደ ውጭ የሚልክ በመሆኑና በአንድ ወር ውስጥ የእንስሳት መግዣ ዋጋ ከዚህ በላይ እየጨመረ ስለሆነ፣ ኩባንያው ኪሳራ ውስጥ እንዳይገባ ምርቱን በመቀነስ ከዚህ በፊት በአማካይ በቀን አሥር ሜትሪክ ቶን ሥጋ እያመረተ ሲልክ ከነበረበት በአሁኑ ወቅት በቀን ሦስት ሜትሪክ ቶን ብቻ እየላከ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት ከኢትዮጵያ በቀን 60 ሜትሪክ ቶን ሥጋ ይላክ የነበረው በአሁኑ ወቅት በቀን ከ20 ሜትሪክ ቶን በታች እየተላከ መሆኑም ጠቁመዋል፡፡  

በ2015 በጀት ዓመት 14,500 ቶን ሥጋ ተልኮ 89 ሚሊዮን ዶላር የተገኘ መሆኑን፣ ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ ድርጅቱም ሆነ አጠቃላይ የሥጋ ኤክስፖርት ከፍተኛ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል በደብዳቤው ተገልጿል፡፡

ኪሳራውን ለመቀነስ የኤክስፖርት መሸጫ ዋጋ እንዳይጨምር እንደ ኬንያ ያሉ ተወዳዳሪ አገሮች ተመሳሳይ ጥራት ያለው የሥጋ ምርት በወቅቱ ካለው የኢትዮጵያ የሥጋ መሸጫ ዋጋ በታች እየሸጡ ስለሚገኙ፣ የአገር ውስጥ ሥጋ አምራቾች ለረዥም ጊዜ ከተገነባው የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ገበያ በተለይም ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ገበያ እየወጡ ነው ብለዋል፡፡

ኩባንያው የውጭ ባለሀብት በመሆኑ በዚሁ ሁኔታ መሥራትና መወዳደር ባለመቻሉ በገጠመው ኪሳራ ምክንያት፣ እ.ኤ.አ. ከ2019 ጀምሮ ለሁለት ዓመታት ሙሉ ለሙሉ ሥራ አቁሞ የነበረ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ መንግሥት የኩባንያውን ችግሮች ለመፍታት ሌሎች የኤክስፖርት ቄራዎች እንስሳትን በከፍተኛ ዋጋ በመግዛት በኪሳራ ልከው በኢምፖርት ንግድ የሚካሱበት አሠራር መሠረት፣ የውድድር ሜዳው ፍትሐዊ እንደሚደረግ ቃል መግባቱን አቶ ከሊፋ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታትም ኩባንያው የምርት ወጪን በመቀነስ የኤክስፖርት ምርቱን በከፍተኛ መጠን በመጨመር፣ የተረፈ ምርት አጠቃቀሙን በማሳደግ፣ እንዲሁም የተሻለ ዋጋ የሚከፍሉ የሥጋ መዳረሻ ገበያ አገሮች ገበያ የማስፋት ሥራ ሲያከናውን እንደቆየ አውስተዋል፡፡

ኩባንያው በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሞጆ ከተማ ባለው ኤክስፖርት ቄራ ባለፉት ዓመታት ሥጋና የሥጋ ተረፈ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ፣ በዓመት ከ20 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ሲያገኝ ነበር ብለዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ሥጋ ወደ ውጭ በመላክ ከ40 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማስገኘቱን፣ አላና ግሩፕ ሥር የሚገኙት ሁለት ድርጅቶች በግል ባለሀብት የተገነቡት ሞጆ የሚገኘው ‹‹አክሰከር ኢትዮጵያ›› እና ዝዋይ አዳሚ ቱሉ የሚገኘው ‹‹ፍሪጎሪፊክ ቦራን ፉድስ›› ኩባንያዎች መሆናቸውን አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ እ.ኤ.አ. የ2021 መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ 42 ሚሊዮን በጎች፣ 52.5 ሚሊዮን ፍየሎች፣ 70.2 ሚሊዮን የቀንድ ከብቶች፣ 58 ሚሊዮን ዶሮዎች፣ እንዲሁም ስምንት ሚሊዮን ግመሎች አሏት፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች