Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትከአገር በቀል ይልቅ በውጭ ተጫዋቾች ግዥ የተጠመዱት የኢትዮጵያ ክለቦች

ከአገር በቀል ይልቅ በውጭ ተጫዋቾች ግዥ የተጠመዱት የኢትዮጵያ ክለቦች

ቀን:

የቀድሞ የእንግሊዝ እግር ኳስ ማኅበር ሊቀመንበር ግሬግ ዳይክ፣ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሚጫወቱ የውጭ አገር ተጫዋቾች ቁጥር በሕግ እንዲገደብ አጥብቆ ይፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ትውልደ እንግሊዛውያን ተጫዋቾች ዕድል እንዲያገኙና የዓለም ዋንጫን ለማሸነፍ የናፈቃት እንግሊዝ፣ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ይዛ እንድትቀርብ በመሻት ነው፡፡

በአውሮፓ ከሚከናወኑ የእግር ኳስ ውድድሮች ተወዳጅነትን ባተረፈው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሕግ መሠረት፣ አንድ ክለብ እንግሊዛዊ ያልሆኑ 17 ተጫዋቾችን በቡድን ውስጥ ማካተት እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ ይህ ማለት አንድ ክለብ መያዝ ከሚችላቸው ከ25 ተጫዋቾች ውስጥ በጥቂቱ 8 ተጫዋቾች ትውልደ እንግሊዛዊ መሆን እንደሚገባቸው ያስቀምጣል፡፡

የቀድሞው የእግር ኳስ ሊቀመንበሩ ግሬግ፣ ‹‹የውጭ አገር ተጫዋቾች ቁጥሩ አሁንም መቀነስ ይገባዋል፤›› የሚል የጠነከረ ሐሳብ አለው፡፡ በዚህም መሠረት በፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፉ ክለቦች በቡድናቸው ማካተት የሚገባቸው ትውልደ እንግሊዛዊ ተጫዋቾች ቁጥር ከስምንት ወደ 12 ከፍ ማለት እንደሚገባውና ሁለት ተጫዋቾች ከታዳጊ ቡድን  ማደግ እንደሚገባቸው ያስረዳል፡፡

በዚህም ስሌት መሠረት የትውልደ እንግሊዛውያን ተጫዋቾችን ቁጥር መጨመር እንደሚቻልና የውጭ አገር ተወላጅ ተጫዋቾችን ቁጥር መቀነስ እንደሚቻል ያመለክታል፡፡

ታዳጊ ተጫዋቾች በእንግሊዝ ክለብ ከ15ዓመታቸውጀምሮእንዲቀላቀሉደንብ መኖሩን ያስታወሰው ግሬግ፣ አገር በቀል ተጫዋቾች ቢያንስ በ18ዓመት ዕድሜያቸውበዋናው ቡድን ውስጥ መካተትእንደሚገባቸውያምናል፡፡ በዚህም ስሌት መሠረት የውጭ አገር ተጫዋቾች አገራቸውን ጥለው በሌላ አገር ሊግ የመጫወት ዕድላቸውእንደሚቀንስያመለክታል።

ይህም በእንግሊዝ ያሉ ታዳጊ ተጫዋቾች ከልጅነታቸው ጀምሮ በክለብ አካዴሚዎች ታንፀው እንዲሠለጥኑና ብሔራዊ ቡድናቸውም በዓለም ዋንጫ፣ እንዲሁም በተለያዩ የእግር ኳስ ውድድሮች ላይ ስኬታማ መሆን እንደሚያስችላቸው ያብራራል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2017 በርካታ የውጭ አገር ተጫዋቾች ከልጅነታቸው ጀምሮ በእንግሊዝ በሚገኙ አካዴሚዎች ሠልጥነው፣ በፕሪሚየር ሊግ ግልጋሎት ከመስጠትም አልፈው፣ የዓለም እግር ኳስን መቆጣጠር መቻላቸው እንደ ምሳሌ ያነሳል፡፡

ለምሳሌ ስፔናዊው ሲኤስ ፋብሪጋስ፣ ናይጄሪያዊ ቪክቶር ሞስስ፣ ትውልደ ፈረንሣዊው በማንቺስተር ዩናትድ አካዴሚ ያደገው ፖል ፓግባ፣ የቤልጂየሙ ሮሜሎ ሉካኮ፣ እንዲሁም ለአርሰናል ሲጫወት የነበረው ስፔናዊው ሄክቶር ቤላሪን ይጠቅሳሉ፡፡

አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ዕድሜያቸው 20 ዓመትን ከተሻገረ በኋላ፣ የእንግሊዝ ክለቦችን በመቀላቀላቸው፣ የአገሪቱ ታዳጊዎች ላይ ተፅዕኖ መፍጠራቸው አልቀረም፡፡ ቁጥሩም ማሻሻያ ተደርጎበት እንግሊዝ ለአገር በቀል ተጫዋቾች የበለጠ ዕድል መስጠት እንደሚገባት በርካታ የእግር ኳስ ባለሙያዎች የሚያነሱት ጉዳይ ነው፡፡

በአንፃሩ ከዓመት ዓመት መሻሻል እንዳላሳየ የሚተቸው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ፣ የተጫዋቾች ዝውውር ‹‹የግብር ይውጣ›› ይመስል ዘንድሮም ቀጥሏል፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እየተሳተፉ የሚገኙት 16 ክለቦች በተለያዩ ችግሮች ታጥረው የውጭ አገር ተጫዋቾች ግዥ ላይ መጠመዳቸው እየተነሳ ይገኛል፡፡

ዘንድሮ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እየተሳተፉ የሚገኙ ክለቦች አብዛኛዎቹ፣ በጥቂቱ አንድ እና ከአንድ በላይ የውጭ አገር ተጫዋቾችን በቡድናቸው ውስጥ አካትተው ይገኛሉ፡፡ ከዓመታት በፊት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አምስት የውጭ አገር ተጫዋቾችን ማስፈረም የሚያስችለውን ሕግ ወደ ሦስት ዝቅ ቢያደርገውም፣ ክለቦች ታዳጊዎች ከማፍራት ይልቅ የውጭ አገር ተጫዋቾችን ማስፈረሙን ተያይዘውታል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በፕሪሚየር ሊጉ እየተሳተፉ የሚገኙ ሁሉም ክለቦች ሁለትና ሦስት የውጭ አገር ዜጋ ያላቸውን ተጫዋቾችን ማስፈረማቸውን ያመለክታሉ፡፡

በተለይ ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ክለቦች የውጭ አገር ግብ ጠባቂዎችን ማስፈረማቸው ጠቅሰዋል፡፡

በአንፃሩ እንደ ባለሙያዎች አስተያየት ከሆነ፣ ክለቦች መሠረታዊ የመዋቅር፣ የበጀት፣ እንዲሁም ታዳጊዎችን ማፍራቱ ላይ ችግሮች እያለባቸው ቅጥ ባጣ መልኩ፣ በውጭ አገር ተጫዋቾች ግዥ  መጠመዳቸው የአገሪቱ እግር ኳስ ‹‹ከድጡ ወደ ማጡ›› እንዲያመራ እያደረገው እንደሚገኝ ያነሳሉ፡፡

ባለሙያዎቹ ለዚህም ማሳያነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) በአፍሪካ መድረክ በሚያደርገው ተሳትፎ፣ በተለይ በግብ ጠባቂና በአጥቂ ዕጦት መመታቱን ያነሳሉ፡፡ ዋሊያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫና በዓለም ዋንጫ ማጣሪያዎች ላይ በግብ ጠባቂ ስህተት ተረተው ከውድድር ውጪ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ ይህም በአገር ውስጥ ሊጎች የሚሳተፉ ክለቦች በተተኪዎች ላይ ያለ መሥራታቸው እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡

‹‹አብዛኛዎቹ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚካፈሉ ክለቦች የውጭ አገር ግብ ጠባቂዎችንና አጥቂዎችን ማስፈረም ልምድ አድርገውታል፡፡ ይህም ከታች የሚመጡ ታዳጊዎች ላይ እንቅፋት ሆኗል፤›› በማለት የሶከር ኢትዮጵያ ጋዜጠኛው ቴዎድሮስ ታከለ ለሪፖርተር አስተያየቱን ይሰጣል፡፡

ብሔራዊ ቡድኑ በግብ ጠባቂ ዕጦት ተመትቶ፣ ክለቦች የውጪ አገር ተጫዋቾች ግዥ ላይ ተጠምደው፣ ተስፋ ሰንቀው በክለብ ውስጥ የሚገኙ ተጫዋቾች የተጠባባቂ ወንበር ገፈት ቀማሽ ከመሆናቸው በላይ፣ እግር ኳስ ሕልማቸውን እያጨለመ እንደሚገኝ ያስረዳል፡፡

ከዚህም በላይ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦችን የሚቀላቀሉ የውጭ አገር ተጫዋቾች አብዛኞቹ የተሻለ እንቅስቃሴ ወይም ክህሎት አለማሳየታቸውንም ይተቻል፡፡

‹‹ዓምና ቅዱስ ጊዮርጊስና ድሬዳዋ ካስፈረሟቸው የውጭ አገር ተጫዋቾች በስተቀር ሌሎቹ የተሻለና ክለብን የሚጠቅም አበርክቶ አድርገዋል ለማለት ያዳግታል፤›› ሲል ቴዎድሮስ ትዝብቱን ለሪፖርተር ይናገራል፡፡  

ዘንድሮ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ያደጉት ሀምበሪቾ ዱራሜ አንድ የውጭ ዜጋ ተጫዋች፣ ንግድ ባንክ ሦስት ተጫዋቾችን፣ እንዲሁም ሻሸመኔ ከተማ ሦስት የውጭ አገር ተጫዋቾችን ማስፈረማቸው ታውቋል፡፡

ምንም እንኳን በአንድ አገር የፕሪሚየር ሊግ በአገር በቀል ተጫዋቾች ብቻ መከናወን አለበት የሚለው ድምዳሜ ውኃ አያነሳም፡፡ ሆኖም በዕድሜ ጠገብ ችግሮች ተተብትቦ የሚከናወነው ሊጉ በታዳጊዎች ላይ መሥራት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ መሠረት እንደሚሆን ብዙኃን የሚስማሙበት መሆኑ ይነሳል፡፡

ይህም በፕሪሚየም ሊግ ከሚሳተፉ 16 ክለቦች ከሁለቱ በስተቀር፣ በመንግሥት ካዝና እየተዳደሩ እግር ኳሱ ወዴት እያመራ ነው? የሚለውን ጥያቄ ያጭራል፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ ፊርማቸውን ካኖሩ የውጭ አገር ተጫዋቾች መካከል የሴኔጋል፣ ማሊ፣ ዑጋንዳ፣ ጋና፣ ማሊ፣ አይቮሪኮስት፣ ኤርትራ፣ ናይጄሪያና የዩናይትድ ስቴት ተጫዋቾች ይገኙበታል፡፡

ከፍተኛ ተጫዋቾች የዝውውር ገንዘብ የሚወጣበት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ፣ የክልል ክለቦች በወር 630 ሺሕ ብር ለአንድ ተጫዋቾች መክፈል ጀምረዋል፡፡ በዚህም ስሌት አንድ ተጫዋች ለሁለት ዓመት 15.1 ሚሊዮን ብር ይከፈለዋል ነው፡፡

ከዚህም በላይ በመንግሥት በጀት የሚተዳደሩትን ክለቦች ጨምሮ፣ ክለቦቹ ለአንድ ውድድር ዘመን እስከ 130 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚያደርጉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በተለያዩ ከተሞች እየተዘዋወሩ የሚጫወቱ ክለቦች ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረጉ እንደሚገኙ ሲገልጹ ከርመዋል፡፡ ሆኖም አሁንም ካልተገባ ወጪ ራሳቸውን እንዳልቆጠቡና ይልቁንም እምብዛም ለውጥ እያመጣ ለማይገኘው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ‹‹በእንቅርት ላይ…›› ሆኖ መቀጠሉ ይነሳል፡፡

ከሳምንታት በፊት አምስተኛው መደበኛ ሦስተኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔውን ያከናወነው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር፣ በሊጉ ክለቦች የእግር ኳስ ክህሎትን ከማሳደግ ይልቅ፣ ማጭበርበሮች ከፍተኛ መሆናቸው መገለጹን የአክሲዮን ማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ ተናግረዋል።

ማኅበሩም ማጭበርበሮች እንዲታረሙ የሁሉንም ክለቦች አሠልጣኞችንና ቡድን መሪዎችን ጠርቶ ድርጊቱ ዳግም እንዳይከሰት ማሳሰቢያ መስጠቱ ተገልጿል፡፡ ከዚህም ባሻር በሊጉ የተጋነነ የተጫዋቾች ደመወዝ ክፍያ እየተከናወነ መሆኑን፣ ከኳሱ ላይ ግን የሚታየው ዕድገት ሰማይና ምድር ነው በማለት የአክሲዮን ማኅበሩ ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በድንግዝግዝ እየተጓዘ የሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከእንቅልፉ የሚነቃበት ጊዜን ሁሉም የእግር ኳስ አፍቃሪ የሚያጓጓው ሆኗል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...