በዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ (ዶ/ር)
ኢሬቻ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ እንደ ቅዱስ በዓል ይከበራል። የኢሬቻ በዓል ለዋቃ ጉራቻ ምስጋና የሚሰጥበት ቀን ነው። የመልካም ነገሮች ሁሉ ምንጭ ዋቃዮ ነው። ሕዝቡ ለዚህ መልካም ስጦታ ከልብ የመነጨ ምስጋና ለአምላኩ የሚያቀርብበትና ‹‹የዋቃዮ ስጦታ ተመልሶ ለዋቃዮ የሚሰጥበት ቅዱስ በዓል ነው›› ብለው ከልብ ያምንበታል። ስለዚህ ኢሬቻ ማለት ‹‹ስጦታ›› ማለት ነው።
በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ለምለም ሳር የሰላምና የብልፅግና ምልክት በመሆኑ፣ በኢሬቻ በዓል ላይ የሚሳተፈው እያንዳንዱ ግለሰብ፣ ይህንን ለምለም ሳር በሁለት እጆቹ በመያዝ አምላኩን ያመሰግናል። ከሁሉም በላይ ክረምቱን ከበረዶ፣ ከከባድ ነፋስ፣ ከጎርፍና ከውርጭ የታደጋቸውን ታላቅና ቅዱስ አምላካቸውን አንድ ላይ ሆነው ያመሠግናሉ። መኸሩንና አዝመራውን ደግሞ እንዲባርክላቸው ወደ ፈጣሪ ይጸልያሉ። ስለዚህ የኢሬቻ በዓል ከጨለማ ወደ ብርሃን ላሻገረ አምላክ የሚሰጥ የክብር ዋጋ ነው።
አገር በቀል የሆኑ የእምነት በዓላትን የመገንዘብና የማብራራት ችግር ያለባቸው ኢትዮሮፒያንስ (Westernized Ethiopians) ግን፣ የኢሬቻ በዓልን በተሳሳተ መንገድ ሲረዱና ሲተረጉሙ ይታያሉ። ለምሳሌ በበዓሉ ላይ የሚደረገውን የአምልኮ ሥነ ሥርዓት በመመልከት፣ ሕዝቡ ዋቃዮን ሳይሆን ውኃውን አሊያም ሰይጣንን “እንደሚያመልክ” አድርገው ይረዳሉ። ኦድላይ ሶቴቪንስን “በአቶሚክ ቦንብ ውስጥ ሰይጣን የለም፣ በሰዎች ልቦና እንጂ” እንዳለ ሁሉ፣ ሰይጣን በእነዚህ ሰዎች አዕምሮ ውስጥ እንጂ በውኃ ውስጥ አይኖርም። ሰይጣን ዳክዬ ወይም ጉማሬ አይደለም፡፡ ካልጠፋ ቦታ ውኃ ውስጥ አሁን ምን ይሠራል! ባይሆን የሰይጣን ትክክለኛ አድራሻና ማደሪያ የሰው ልቦና ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮሮፒያንስ ሰይጣንን ልቦናቸው ውስጥ ይፈልጉት!
በተቃራኒው ውኃ የሕይወት ምልክት ነው። ለዚህም ነው ውኃና ልምላሜ እንደ ዋቃዮ ስጦታ የሚታዩት። ያለ ውኃ ሕይወት ቀጣይነት የለውም። ውኃ ዋቃዮ ለፈጠራቸው ልጆቹ የሰጠው ፀጋ ነው። ድሪቢ ደምሴ ቦኩ እንዳለው፣ “ኦሮሞ ወንዝ፣ ጫካና ተራራ ይወዳል፣ የተፈጠረበትና ፍቅር ያገኘበት ስለሆነ በየዓመቱ ለምለም ሳርና የአደይ አበባ ይዞ ለኢሬቻ ወንዝ ውኃ ዳርቻ በመሄድ፣ ተራራ ላይ በመውጣት፣ ለፈጣሪው ምስጋና ያቀርባል። በጤና፣ በሰላም፣ ለሰውና ለከብት ዕርባታ እንዲሰጠውም ይጸልያል።”
ኢሬቻ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ነው። ለምሳሌ ፋሲካ፣ አረፋ፣ ጥምቀት፣ ገና…፣ ወዘተ ሃይማኖታዊ በዓሎች ናቸው እንጂ፣ በራሳቸው ሃይማኖት አይደሉም፡፡ የኦሮሞ አገር በቀል ሃይማኖት ዋቄፋና ተብሎ ይጠራል። Waaqa ማለት እግዚአብሔር ማለት ሲሆን፣ Faana ማለት ደግሞ መከተል ማለት ነው። ትርጉሙም ፈጣሪን/እግዚአብሔርን መከተል ማለት ነው። ለኦሮሞ ሕዝብ ዋቃ የሁሉ ነገር አስገኝ፣ የማይጠፋ፣ የማይለወጥ፣ ቋሚና ዘለዓለማዊ ነው። የሁሉም ነገር ምንጭ ዋቃ ነው። ዋቃ ምሉዕ በኩለሄ (omniscient)፣ ሁሉን ቻይ (ominipresent)፣ ዘላለማዊ (eternal)፣ ፍፁም (absoulute)፣ እና ገደብ የሌለው (infinite) ነው።
የኢሬቻ ቅዱስ በዓል ጸሎት
ሀዬ! ሀዬ! ሀዬ! (አሜን አሜን አሜን)
ሀዬ! የእውነትና የሰላም አምላክ!
ሀዬ! ጥቁሩና ሆደ ሰፊው ቻይ አምላክ!
በሰላም ያሳደርከን በሰላም አውለን!
ከስህተትና ከክፉ ነገሮች ጠብቀን!
ለምድራችን ሰላም ስጥ!
ለወንዞቻችን ሰላም ስጥ!
ከጎረቤቶቻችን ጋር ሰላም ስጠን!
ለሰውም ለእንስሳቱም ሰላም ስጥ!
ከገዳ ባህላችን ከዋቄፋና እምነታችን ጋር አኑርልን!
አንድነታችንን አጠንክርልን!
ትናንሾቻችንን አኑርልን!
ጤነኛና ብልህ ልጆች ስጠን!
ወላድ በጤና ትገላገል!
የወለደችውን አሳድግላት!
ሕፃን በእናቱ እቅፍ ይደግ!
ለወላድ ጤናና ዕድሜ ስጣት!
ላልተማረው ዕውቀት ስጥልን!
ኦ አምላክ አደራጀን!
አደራጅተህ አታፍርሰን!
ተክለህ አትንቀልን!
ፈጥረህ አትዘንጋን!
ክፉውን ያዝልን!
ከወንጀልና ከወንጀለኛ አርቀን!
ምቀኛና ቀናተኛውን ያዝልን!
ከመጥፎ አየር ጠብቀን!
ንፁሕ ዝናብ አዘንብልን!
ያለአንተ ዝናብ የእናት ጡት ወተት አይሰጥምና!
ያለአንተ ዝናብ የላም ጡት ወተት አይሰጥምና!
ያለአንተ ዝናብ መልካው ውኃ አይሰጥምና!
ያለአንተ ዝናብ ምድሩ ቡቃያ አይሰጥምና!
ከእርግማን ሁሉ አርቀን!
በአባቱ ከተረገመ አርቀን!
በእናቷ ከተረገመች አርቀን!
እውነትን ትቶ ከሚዋሽ አርቀን!
ከረሃብ ሰውረን!
ከበሽታ ሰውረን!
ከጦርነት ሰውረን!
ልጄ እያሉ አልቅሶ ከመቅበር ሰውረን!
በጥቁር ፀጉር ከመሞት ሰውረን!
በነጭ ፀጉር ከመደህየት ሰውረን!
አርሶ ምርት ከማጣት ሰውረን!
ከሌላ ሰው ጦስ ሰውረን!
ከከፉ ነገር ሁሉ ሰውረን!
ገዳው የሰላም፣ የልምላሜና የድል ነው!
ሀዬ! ሀዬ! ሀዬ!
የኦሮሞ ባህልን ከወንጌል እሴቶች ጋር እንዲስማሙ አድርጎ ማስተማር
‹‹ኢሬቻ የባዕድ አምልኮ ነው!›› ለሚሉት ሰዎች መልስ ለመስጠት ውድ ጊዜያቹን በከንቱ ባታጠፉ መልካም ይመስለኛል! በኦሮሞ (አፍሪካ) ፍልስፍና ዙሪያ ምርምር እያደረግን ያለን ግለሰቦች፣ ከዚህ በፊት በቂ መልስ ሰጥተንበታል፣ ማድረግ ያለብህን ነገር የኦሮሞ ባህልን ከወንጌል እሴቶች (Gospel Values) ጋር እንዲስማሙ አድርጎ ማስተማር ነው። ኦሮሙማ –የፈጣሪ ስጦታ ነውና እንንከባከበው! የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ፣ ቋንቋና ማንነት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳንል እናስተምር፡፡ ከመማር አንቦዝን! ክርስቶስ ወደዚች ምድር ይዞ የመጣው ‹‹ወንጌል›› ፍቅር፣ ሰላምና አንድነትን እንጂ፣ ‹‹ለ… ነፍስ ዲያቆን መች አነሰው!›› የሚለው ወንጀል አይደለም!
ስለዚህ ራሳችንን ከህሊና ባርነት ነፃ እናውጣ! አንተ የፈጣሪ ውድ ልጅ ነህ! በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ያለን እንደሆነ፣ እንደ እነ አባ ላምበርት ባርለስ (Lambert Bartles)፣ አባ ጆሴፍ ሎ (Joseph Loo)፣ አባ ክላውድ ሳምነር (Claude Sumner)፣ ወዘተ. በኦሮሞ ሕዝብ ባህልና ፍልስፍና ላይ ጥልቅ ምርምር እናድርግ! በስፋት ተመራመሩበት! የሌሎችን ባህል፣ ቋንቋና ሃይማኖት አክብሩ! በፍፁም አታንቋሽሿቸው! ስለማንነትህ የገዛ ነፍስህን እንኳ ሳትሳሳ አሳልፈህ ለመስጠት ሁሌም ዝግጁ ሁን!፡፡
ቸር እንሰንብት፡፡
ከአዘጋጁ፡– ጸሐፊው የቢኤ፣ የማስተርስና የፒኤችዲ ዲግሪዎችን በፍልስፍና፣ በሳከርድ ቴኦሎጂ ቢ.ዲ ሲኖራቸው፣ በካፑቺን ፍራንቸስካና የፍልስፍናና የነገረ መለኮት ኢንስቲትዩት (CFIPT) የአፍሪካ ፍልስፍና መምህር ናቸው፡፡ ከምርምር ትኩረቶቻቸው መካከልም ሜታፊሎሶፊ፣ ኦሮሞ ፊሎሶፊ፣ ድኅረ ቅኝ ግዛት የአፍሪካ ፊሎሶፊ ይገኙባቸዋል፡፡ በኅትመት ደረጃ ‹‹የኢትዮሮፒያንስ አስተሳሰብ፤ ‹አበበ በሶ በላ› vs ‹ጫላ ጩቤ ጨበጠ›..››ን ጨምሮ ከኦሮሞ ፍልስፍና ጋር የተያያዙ መጻሕፍትንና የጥናት ውጤቶችን አሳትመዋል፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡