ሰላም! ሰላም! እንግዲህ በመልካም ምኞቶች ልውውጥ የጀመርነው አዲሱ ዓመት መስከረም ወር እየተጠናቀቀ ነው፡፡ በተስፋ ጀምረን አንድ ወር ሳይታወቅ ፉት ሲል ድንቅ ይላል፡፡ ጊዜ እንደ ጅረት ጥሎን እብስ ሲል የዘመን መለዋወጥ ትርጉሙ የሚገባን በትውልዶች መተካካት ነው፡፡ በዚህ ዓለም ተጀምሮ የማያልቅ ተወጥሮም የማይላላ ምንም ነገር የለም። አያያዛችን በዚህ ከቀጠለ የእኔና የማንጠግቦሽ ትዳር በዩኔስኮ ሳይመዘገብ አይቀርም። ሰው ወካይ የሆኑት የማይዳሰሱ ቅርሶቻችን የዓለም ሀብት ሆነው ሲመዘገቡ፣ የእኛም ትዳር የአገር ሀብት መሆን አለበት እላለሁ፡፡ አዳሜ በዝነኞች የትዳር ዝና ብዙ ሲሰማ ኖሮ፣ ቆይተው ሲፋቱ አመዱ ቡን የሚለው ለምንድነው ግን? እንዲያው ሸንበቆ መመርኮዝ የምንወደው ለምን ይሆን? እኔማ ወትሮም ‘ይኼ ምኑ ይወራል’ ብዬ ትቼው ነበር። የዘንድሮ ሰው ግን እንኳን ትታችሁለት ወጥራችሁለትም አርፎ አይቀመጥም። በሰው ትዳርና በሰው ወርቅ የሚደምቁ በዝተዋል። ሁሉም ግን ሸንበቆ እንደ መደገፍ እንደሆነ ይኼው መሰንበት ያሳየናል። ‹‹ድሮም በሰው ፍቅርና ትዳር መመካት መጨረሻው ይኼ ነው…›› እያልኩ ስጀነን ማንጠግቦሽ የዝነኛ ተብዬዎችን ጉድ ሰምታ ኖሮ፣ ‹‹እስኪ የእኔና የአንተ የ30 ዓመታት የትዳር ጉዞ ይገምገም…›› ብላ ይኼው ሥራ ፈትቻለሁ። ያውም በወርኃ መስከረም መጨረሻ በጥቅምት መጀመሪያ ሰሞን፡፡ ‹‹በጥቅምት አንድ አጥንት›› እየተባለ ገቢን በየአቅጣጫው ማሳለጥ በሚያስፈልግበት ጊዜ ግምገማ መቀመጥ ይደንቃል፡፡ ያስደንቃልም!
የእኛ አገር ግምገማ ታውቁት የለ ቋቅ ነው የሚለው፡፡ ለማስመሰል ብቻ መገማገም ይደብራል እኮ። የሆነ ሰዓት ላይ ሰለቸኛ፣ አልቻልኩም። ‹‹ማንጠግቦሽ…›› አልኳት። ‹‹… ያልተኖረ ልጅነትና ያመለጠ ዕድል አንድ ነው። እስካሁን አብረን ኖረናል። ከዚያ በፊት የነበረው ደግሞ አምልጦናል። ከስም በስተቀር ግምገማ ምንድነው ትርፉ?›› ስላት። በጣም ታዝባ አየችኝ። ይኼም የግምገማው አካል ሆኖ ቀረበ። አብዛኛውን የግምገማ ሰዓት ለማነሳቸው ጥያቄዎች መልስ ከመስጠት ይልቅ፣ ‘እሱን በጥናት የምናየው ይሆናል’ እያለች አሰለቸችኝ፡፡ መጨረሻ ላይ እሷ ራሷ ሲመራት፣ ‹‹ሂድ እንዳሻህ…›› ብላ ለቀቀችኝ። እኔ ደግሞ ያመለጠኝን የሥራ ሰዓት ላካክስ መራወጥ ጀመርኩ። አገሬ ደግሞ እንደምታዩዋት የሚሠራ ሳይሆን የሚጨቃጨቅና የሚፋለም ሞልቶባት በየሄድኩበት፣ ባልተረጋገጠ ወሬ ሥራ ፈቶ ነገር የሚሰነጥቅ ይከበኝ ጀመር። አቤት እኛ። አፍራሽ ነገርና ፍቺ ስንሰማ የምንቅበጠበጠው ግን ምን ለክፎን ነው? ወይ ከመጀመሪያው ምሳሌ የሚሆንን አርዓያ ማድረግ። ካልሆነ ዝም ማንን ገደለ? ዳይ ወደ ሥራ ማለትስ አሁን ነው!
እናማ ፍቅር እስከ መቃብር የኢትዮጵያ ድርሰት ሆኖ ሊቀር ነው አሉ። ሰሞኑን እኔና ማንጠግቦሽ የሆሊውድን ጥንዶች ማስናቅ ጀምረናል። ደስ ይላል። ቢያንስ እንዲህ ሰዎች በሥልጣን ብቻ ሳይሆን በፍቅርም ዘለግ ያለ ዘመን ሲኖሩ ደስ ይላል። ማንጠግቦሽ ይኼ የሰሞኑን ‘አበጃችሁ አበጃችሁ’ መባል ትንሽ ሞቅ እያደረጋት በአለፈች በአገደመች ቁጥር ‘የትዳራችን ፅናት መሠረቱ የግምገማ ውጤት ነው’ እያለች ሳትጠየቅ ጋዜጣዊ መግለጫ እየሰጠች አስቸግራኛለች። ‹‹ምን ላድርጋት?›› ብዬ ምሁሩን የባሻዬን ልጅ ሳማክረው፣ ‹‹አጅሬው በዚህ መጣህ እንዴ? የመናገር ነፃነቷን እቃወማለሁ ብለህ አንድ ነገር ብትናገራት መጣላታችን ነው…›› ብሎ አስደነገጠኝ። ‘ቀን ሲከፋ በግም ይነክሳል’ ነው የሚባለው? ወዳጄ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጭምር ከተነሳብኝማ ምን አደርጋለሁ ብዬ ዝም አልኩ። ጭጭ ምጭጭ!
ብቻ ዘንድሮ ለሰላም፣ ለፍቅርና ለዘመናት ወዳጅነት የምንከፍለው ዋጋ አልተመጣጠነም። ደግሞ እናንተም እንደ ማንጠግቦሽ ‘ጥናት እስኪመልሰው ታገስʼ እንዳትሉኝ አደራ። አንድ በረጋበት የፀና ቀንደኛ የገዥው ፓርቲ ደጋፊ ወዳጅ አለኝ። ‹‹ዕድሜ ለአገር በቀል የመደመር ዕሳቤያችን የሃይማኖትና የፖለቲካ አቋም የግል መሆኑን ተቀብለን፣ ይኼው እያደር የመቻቻልና የመደማመጥ ባህላችንን እያዳበርን ነው…›› ሲለኝ ይኼ ፖለቲካ ድራማ ነው እንዴ አሰኝቶኝ ነበር። ምንም ቢባል እንኳ ከት ብሎ የመሳቅም ሆነ የማልቅስ መብታችን ተፈጥሯዊ ቢሆንም፣ ለጊዜው አልፈቅድም። ቂ…ቂ…ቂ… ይቅርታ አምልጦኝ ነው። እና ምን ነበር ልላችሁ የነበረው? አዎ፣ ይኼ ወዳጄ እንደማጫውታችሁ ትክት ሲያደርገኝ የሰነበተውን የዝነኞች ፍቺ ሰማ አሉ። ምን ቢል ጥሩ ነው? ‘እስኪ ቆይ በግምገማ ይረጋገጥና አምናለሁ’ አይል መሰላችሁ? ዓይንና ጆሮ የማይታመኑበት ዘመን ይሏችኋል እንዲህ ነው!
ጨዋታን ጨዋታ ወንዝን ወንዝ ያስባለው ፍሰት ነውና ከጥናትና ከምርምር ጋር አያይዤ አንድ ጨዋታ ላጫውታችሁ። መቼም ዘንድሮ እንደምታዩትና እንደምትሰሙት መነሻና መድረሻ የጠፋበት ነገር በዝቷል፣ ፍሰት ጠፍቷል። ‹‹ዓባይን ገድበን ኤሌክትሪክ እናመንጭ ስንል የሐሳብና የጨዋታ ፍሰትን ጭምር አብረን መገደብ ጀምረን ይሆን እንዴ አንበርብር?›› ብለው የሚጠይቁኝ አዛውንቱ ባሻዬ ናቸው። ሰሞኑን ታዲያ ከአባታቸው በውርስ ያገኙትን መኖሪያ ቤት ከአሥር ዓመት ክርክር በኋላ ባለመብትነታቸውን አስጠብቀው ሊሸጡት ከተነሱ አዛውንት ጋር ገጥሜ ነበር። ግለ ታሪካቸውን በተለይ አሥር ዓመት ሙሉ ባረባ ጉዳይ ከወዳጅ ዘመድ ተናክሰው ፍርድ ቤት መመላለሳቸውን ሲያወሩኝ አንጀት ይበላሉ። እኔም ሕጋዊ ወራሽነታቸውን ለማስከበር አሥር ዓመት እንደተንከራተቱት ለሽያጩም እንዳይጓተቱ ሁነኛ ገዥ ፈልጌ አገናኘኋቸውና ተሳካ። መልካም ዕድል!
ኮሚሽኔን ሊሰጡኝ በተቃጠርንበት ቀን ስንገናኝ ልባቸው አርፎ ፊታቸው ወዝቶ መረቁኝ። ‹‹ዓለምና ፍርዷ መቼስ የምታውቀው ነው…›› አሉኝና አንድ ታሪክ አጫወቱኝ። አሜሪካ አገር ነው አሉ። ‹‹አንድ መንደር ውስጥ የሚኖር ወጣት ነበር። ልዩ መታወቂያው የሠፈር አውደልዳይነትና ዕፅ ተጠቃሚነት ነበር። አንድ ቀን እዚያው የሚኖርበት አካባቢ የምትኖር የቤት እመቤት ሞታ ትገኛለች። ፖሊስ አሟሟቷ የግድያ ወንጀል እንደሆነ ያረጋግጣል። ከመሞቷ በፊት ፆታዊ ጥቃት እንደደረሰባትም ማስረጃ ያገኛል። ከእመቤቲቱ ብቻ ሳይሆን ከገዳዩም የደም ናሙናውን ይገኛል። ወዲያው ያንን ወጣት ጠርጥሮ ያስረዋል። ፖሊስ ድርጊቱን ከእሱ ሌላ የፈጸመ እንደሌለ ያጠናቀርኩት ማስረጃና ምርመራ አረጋግጧል ብሎ ክስ ይመሠርትና የሞት ፍርድ ተፈርዶበት የሚገደልበት ቀን ሳይወሰን እስር ቤት ይገባል። ወጣቱ ʻእኔ ነፃ ነኝʼ ቢል ሰሚ ያጣል። ከሃያ ዓመት በኋል በድንገት ስለዲኤንኤ ሳይንስ ይሰማና እሪ ብሎ በስንት ውጣ ውረድ ያ የተወሰደው ደም ከያኔው ወጣት ከአሁኑ ጎልማሳ ጋር እንዲተያይለት ይጠይቃል። ሲጣራ ፍርደኛው ሟቿ በደረሰችበት አለመድረሱ ተረጋገጠ፡፡ ይህችና ናት ዓለምህ ይህች ናት ዓለሜ…›› ብለው ቆዘሙ። የዕድሜ አሳር በዕድሜ ልክ ላይፈታ ትርፉ ስብራት ብቻ፡፡ መጥኔ!
ይኼንን ታሪክ ከሰማሁ በኋላ እንዲያው እንደ ምናምን አድርጎኝ ልሞት። ዕንባ ዕንባ ይለኛል ዕንባዬ ጠብ አይልም። ‘ወይ ጉድ’ እልና ሳቅ ሳቅም ይለኛል፡፡ ደግሞ መልሶ ጥርሴ በሰቀቀን ሲፋጭ መልሼ ለራሴው አዳምጣለሁ። አዛውንቱ ባሻዬ፣ ‹‹ምን ነክቶሃል አንተ ሰሞኑን?›› እያሉ ይከታተሉኛል። ‹‹ኧረ ባሻዬ የሰሞኑ የምሽት ቅዝቃዜ እንጃልኝ…›› ስላቸው፣ ‹‹ታዲያ በአንተ ብቻ አልመጣ? ብርድና ባለጌ ፊት ከሰጡት አይቻልም። እቱቱ እያልክ አታባብሰው…›› ይሉኛል አምነውኝ። በኋላ አሁንም አሁንም ሲጠይቁኝ የሰማሁትን ቅስም የሚሰብር ታሪክ አጫወትኳቸው። እትቱዬ ወደ እሳቸው ተጋባ። ጠያቂ እኔ ተጠያቂ እሳቸው ሆኑ። ‹‹ምነው ባሻዬ?›› ስላቸው፣ ‹‹ቅዝቃዜው አጥንቴ ድረስ ዘልቆ እየገባ አልቻልኩትም…›› ሲሉኝ፣ ‹‹አይዞዎት በእርስዎ ብቻ አልመጣም…›› እላቸዋለሁ። ለየብቻ ሲሆን ሸክም ለመካሪ ይቀላል አሉ!
ባሻዬን እንዲህ ስላቸው ግን ፈገግ ብለው፣ ‹‹የሰው ልጅ አይችለው የለም። አይ ሰው… አይ ሰው…›› ይላሉ። ከአብሮነታችን ባይነዋርነታችን፣ ከሳቃችን ዕንባችን በሚልቅባት ወደ እዚህች ዓለም እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ከመጣሁበት ቀን አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ሰው ያለ ኃጥያቱና ያለ በደሉ ሲኮነን፣ ሲወገዝ እንዳየሁት ሌላ ተገዳዳሪ ኢፍትሐዊ ነገር አጋጥሞኝ አያውቅም። ታዲያ ቀስ በቀስ የእኔ ቅዝቃዜ ወደ ባሻዬ እንደተጋባው፣ ከባሻዬ ወደ ምሁሩ ልጃቸው፣ ደግሞ ከእኔ ወደ ውዷ ማንጠግቦሽ ተጋባና ይኼው አሁን ሠፈሩ በሞላ ቁርጥማት ታሟል አሉ። ʻእውነት ትቀጥናለች እንጂ አትበጠስምʼ ያሉትን አስታውሰን እትቱ እትቱ እያልን ነው። ፍትሕም እንደ ብርድ እቱቱ ያስብላል ግን? ወይ አንቺ ዓለም!
በሉ እንሰነባበት። ‘ዓለም አታላይ’ን እያፏጨሁላችሁ ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር የለመድኳትን ልቀማምስ ወደ ግሮሰሪ አመራሁ። የባሻዬ ልጅ ያወራኛል። እኔ አልሰማውም፣ አፏጫለሁ። ‹‹ደግሞ ከመቼ ወዲህ ነው ፉጨት?›› አለኝ። ‹‹አንዳንዴ ግድ ይላል…›› ስለው በዘመኑ አነጋገር፣ ‹‹ማን ከማን ያንሳል?›› ብሎ እሱም ፉጨት ጀመረ። ሲል ሲል መላ ግሮሰሪው በፉጨት አበደ። ኋላ አንዱ ተነስቶ፣ ‹‹ፉጨትና ንፋስ አልወድም። ንፋስ ትንቢት ሳይኖረው እንደማይነፍስ ሰው ሳይከፋው አያፏጭም…›› ብሎ ሒሳብ ጠየቀ። ‹‹ታዲያ አንተ መሸሽህ ነው አሁን?›› ሲለው አንዱ፣ ‹‹ተው… ተው… እኔ ደግሞ ምን ድምፅ ኖሮኝ? የቱን ቀልድ ቀልጄ ሕዝብ ስቆልኝ? ወይስ የትኛው ድራማ ላይ ተውኜ ስሜ ገኖ ተጠርቶ እሸሻለሁ? መሸሽ እንዲህ ቀላል አደረጋችሁት እንዴ? ዝና ይጠይቃል እኮ…›› ሲል የግሮሰሪው ታዳሚዎች በሳቅ ፈረሱ። ይሳቅ እንጂ!
‹‹ዋ አንቺ ኢትዮጵያ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ… እስከ መቼ ግን?›› ሲል ሌላው፣ ‹‹በምግብ ዋስትና ራሳችንን የቻልንበት ዘመን እየደረሰ ነው እየተባለ ለምንድነው ምግብ ማግኘት እንደ መንግሥት ሰማያት የራቀው?›› አለው አንዱ ሞቅ ያለው፡፡ ሳቅ አሁንም። ‹‹የሚያበላ ሳይኖር የሚበላ እንዴት ይኖራል?›› ይላል መልሶ ያ። ‹‹ኧረ እናንተ ሰዎች ምድራዊው ምግብ ላይ ስታተኩሩ ሰማያዊው ምግብ ሊያመልጣችሁ ይችላልና አርፋችሁ ጠጡ…›› ሲል ከወዲያ ማዶ ጥጉን ይዞ የተቀመጠው፣ ‹‹ምድር ላይ ደልቶህ ሳትበላ ነው እንዴ ስለሰማያዊ ምግብ የምታስበው?›› ይላል ሰካራሙ። ሳቅ በሳቅ። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ሹክ ይለኛል። ‹‹አንበርብር እኔ መሄዴ ነው። ሰው ሳቁ ሳይመጣበት ደጋግሞ ሲስቅ አልወድም…›› ሲለኝ እኔም ከመቀመጫዬ እየተነሳሁ፣ ‹‹ማን ይወድና?›› አልኩታ። የጠጣነውን ብንከፍልም የሳቁን ግን ማንም አላስከፈለንም። ማን በሳቀው ማን ይከፍላል? ማን ባለቀሰውስ ማን ይስቃል? ኧረ ባልተከፈለበት የሚስቁ በዙ!
በዚህ መሀል አንዱ የሠፈር ለቅሶ ሊያስተዛዝን መሸት ሲል ይሄዳል ብሎ ወግ ጀመረ፡፡ ቀደም ብሎ ግን ቀማምሶ ሞቅ ብሎታል፡፡ ለቅሶው ቤት ደርሶ ገና ከመቀመጡ አንዱ በነገር፣ ‹‹ዛሬ እንዴት በጊዜ ተገኘህ?›› በማለት ወጋ ያደርገዋል፡፡ ሞቅ ያለው ሰውዬም፣ ‹‹ለነገሩ በጊዜ መገኘት ጥሩ ነበር፡፡ ነገር ግን ቀን በነገር ስታቆስሉን እየዋላችሁ እንዴት በጊዜ ቤታችን እንግባ? ቁስላችን እንዲሽር እኮ ነው አልኮል የምንጋተው…›› ሲለው የለቅሶው ድንኳን በሳቅ ውካታ ተርገበገበ፡፡ ነገሩ እየከፋንም ቢሆን እንሳቅ ነው፡፡ ጥግ ላይ የተቀመጡ ከዕድሜውም ከዕውቀቱም ገፋ ያደረጉ ጉምቱ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፣ ‹‹እስቲ እንደማመጥ…›› ሲሉ ትኩረታችንን አገኙ፡፡ ፈገግ እያሉ፣ ‹‹መነጋገር መልካም ነው፡፡ ሐሳብ መለዋወጥም እንዲሁ…›› ብለው፣ ‹‹መመካከርን የመሰለ ነገር የለም፡፡ ከብልህ የተማከረ ደግሞ ጥቅሙ ከፍ ያለ ነው፡፡ እርስ በርስ ስንገናኝ እንመካከር፡፡ ወጉም በምክር ይውዛ፡፡ ምክር የማይሰሙ ናቸው ካሰቡበት የማይደርሱት፡፡ አገርም ሆነ ቤተሰብ የሚያስተዳድር ጥሩ መካሪ ያሻዋል፡፡ መካር የሌለው መከራ ይመክረዋል፡፡ ለዚህም ነው አዝማሪው ‹ሰሚ የለም እንጂ ሰሚማ ቢኖር መካሪ ነበር› ያለው…›› ብለው አገር ከገባችበት ጦርነት ውስጥ ወጥታ ሰላም እንዲሰፍን ተመኝተውልን ተሰናበቱን፡፡ መልካም ሰንበት!