Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ግብርና ሚኒስቴር ሥጋ ላኪዎችን አስጠነቀቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሥጋና በእንስሳት ውጤቶች ማቀነባበርና ላኪነት የተሰማሩ አቅማቸውን ገንብተው ከዘርፉ መገኘት ያለበትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማስገኘት ካልቻሉ፣ የግብርና ሚኒስቴር ትኩረት እንደማያደርግላቸው አስታወቀ፡፡

የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ከአሥር በላይ ሥጋ ላኪዎች፣ ከዕርድ ተረፈ ምርት ላኪዎች፣ ከማር ላኪዎች፣ እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ውይይት ሲያደርግ ነው የግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ይህንን ያስታወቁት፡፡

የሥጋ ኤክፖርት ያላደገበት ዋነኛ ምክንያት አገር ውስጥ ያሉ ላኪዎች በጤናማ መንገድ ከመወዳደር ይልቅ እርስ በርስ ለመበላለጥ በሚያደርጉት ፉክክርና በቀላሉ መፍታት በሚቻል ሐሳብ ላይ በመጨቃጨቃቸው መሆኑን የተናገሩት ሶፊያ (ዶ/ር)፣ በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ በኮንትሮባንድ በሚወጡ የቁም እንስሳት ሌሎች አገሮች ኤክስፖርታቸውን እያሳደጉ ነው ብለዋል፡፡

ላኪዎች በተገለጸው መንገድ አቅማቸውን በማሳደግ ኤክስፖርትን የማያጠናክሩ ከሆነ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ውስጥ ትልቅ ውጤት ያስመዘገቡት ብቻ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው፣ ነገር ግን ከዘርፉ ለሚገኘው 100 ሚሊዮን ዶላር ለማይሞላ ገቢ ትኩረት እንደማይደረግ ሶፊያ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

‹‹የእንስሳት አቅራቢዎች ገበያ አለማግኘታቸውና ላኪዎች ምርት የማጣታቸው ምክንያቱ ሥርዓት ያለው ገበያ ባለመፈጠሩ ነው፡፡ በመሆኑም ላኪዎች መሥራት በሚችሉት መጠን በመሥራት፣ እርስ በርስ በመግባባትና አቅም በመፍጠር፣ እንዲሁም በዘርፉ ያሉትን ችግሮች በተደራጀ መንገድ በማኅበራቸው በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ እንዲገኝ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፤›› ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ትኩረት በመስጠት ከላኪዎች ጋር ውይይት የሚያደርገው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ሲቀንስ መሆኑን፣ የኤክስፖርት አፈጻጸም የሚቀንስባቸውን ምክንያቶች ማለትም ‹‹የክልሎች ተደጋጋሚ ቀረጥ፣ የኮቴ ክፍያ፣ እንዲሁም በዞንና በወረዳ የሚስተዋል ቸልተኝነትን ቀድሞ እንዲፈታ ሲጠየቅ በዝምታ አልፎ ከቆየ በኋላ ነው፤›› ሲሉ የግሪን ፌስ ትሬዲንግ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጆኒ ግርማ ችግር ያሉትን በውይይቱ ወቅት አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም የአገር ውስጥ ምርትን በርካሽ በመሸጥ ከውጭ ውድ ዕቃ ማስገባት የሚለው የኤክስፖርት መቀነስን በኢምፖርት ማካካስ አሠራር አዋጭ እንዳልሆነ አቶ ጆኒ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ባለሙያ አቶ ዓለማየሁ ከበደ፣ በዘርፉ ያለው ከፍተኛ ችግር በእንስሳት አቅራቢዎችና በላኪዎች መካከል ሕጋዊ የውል ስምምነት አለመኖር ነው ብለዋል፡፡

የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሕጋዊ ተቋማት ቢሆኑም ከሚያቀርቡለት ድርጅት ጋር የሚዋዋሉበት ሕጋዊ ውል ያለው የግብይት ሥርዓት ባለመኖሩ፣ በአፋር ክልል ሁለት የኅብረት ሥራ ማኅበራት በአጠቃላይ የ2.1 ሚሊዮን ብር ክፍያ ስላልተፈጸመላቸው ኪሳራ ውስጥ ገብተዋል ሲሉ አቶ ዓለማየሁ ገልጸዋል፡፡

የሥጋ አምራች ላኪዎች ማኅበር የአመራር ለውጥ በማድረግ መንግሥትን መገዳደር እንዲችል ማድረግ አለበት ሲሉ ሶፊያ (ዶ/ር) አሳስበዋል፡፡

በዚህም መሠረት በ1996 ዓ.ም. በሲቪል ማኅበራት ድርጅት ምዝገባ ያደረገው የሥጋ አምራች ላኪዎች ማኅበር፣ ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም. በ11 አባላቱ ጠቅላላ ጉባዔ አድርጓል፡፡

በጉባዔው ላይ በባለሀብቶች መካከል ያለውን አላስፈላጊ ውድድር በማቆም እንደ አገር መወዳደር እንደሚገባ በመገንዘብና የቀድሞ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት በመቀየር ማኅበሩ ለውጥ ማድረጉን፣ የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ አበባው መኮንን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በለውጡ መሠረትም የቀድሞውን ፕሬዚዳንት የኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ የቀድሞ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ሐጎስን በመቀየር የአክሸከር ኢትዮጵያ ኬዚንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና የአላና ግሩፕ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ከሊፋ ሁሴን ፕሬዚዳንት፣ እንዲሁም የሞጆ ሞደርን ኤክስፖርት ቄራ ስራ አስኪጅ መንግሥተ አብ አኔቦን (ዶ/ር) ምክትል ፕሬዚዳንት ተደርገው መመረጣቸውን አቶ አበባው ገልጸዋል፡፡

በአዋጅ ቁጥር 1263/2014 በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 506/2014 ሁለት ኢንስቲትዩቶች፣ ማለትም የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትና ብሔራዊ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ኢንስቲትዩት ተዋህደው የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት መቋቋሙ ይታወሳል፡፡

የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት የ2015 ዓ.ም. የእንስሳት ምርት ማቀነባበርና ወጪ ንግድ ዕቅድ አፈጻጸምና የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ውይይት፣ ወጪ ምርቶችን 50 በመቶ በማሳደግ 33,415 ቶን ማድረስ፣ የወጪ ንግድ ገቢ በ48 በመቶ በማሳደግ 140 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘት መታቀዱን የኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሳህሉ ሙሉ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በቁም እንስሳት የሚታየውን ሕገወጥ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ ለመቀነስ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሠራል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም አርብቶ አደሩን ቀጥታ ከኤክስፖርት ቄራዎች ጋር ለማስተሳሰር፣ የኮንትራት ዕርባታ አሠራር ተግባራዊ ይደረጋል ሲሉ ሳህሉ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

ምርት ወደ ውጭ መላክ ያቆሙ የዘርፉ ማቀነባበሪያ ድርጅቶች ወደ ሥራ እንዲመለሱ መደገፍ፣ የማምረት አቅምና አጠቃቀምን መሠረት ያደረገ የማበረታቻ ሥርዓት ይዘረጋል ብለዋል፡፡   

በኢትዮጵያ የሚገኙ የኤክስፖርት ቄራ ድርጅቶች ማለትም ሉና፣ ሞጆ ሞደርን፣ ሀላል፣ አክሸክር/አላና፣ አቢሲኒያ፣ ኦርጋኒክ፣ ኢትዮሚት፣ አልጁም፣ ማዕረግ ኤክስፖርት ቄራ ድርጅቶችና ኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ የሚያመርቱዋቸውን የሥጋ ምርቶች ወደ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኳታር፣ እንዲሁም በቅርቡ የተጀመረው አዲስ የገበያ መዳረሻ ካምቦዲያ በመላክ በ2015 ዓ.ም. 92 ሚሊየን ዶላር ማስገኘታቸው ታውቋል፡፡

የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አሥራት ጤራ (ዶ/ር) የ2015 የእንስሳት ምርት ማቀነባበርና ወጪ ንግድ ዕቅድ አፈጻጸምንና የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድን በመገምገም በዘርፉ ያሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ፣ የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያደርግ የውይይት መድረክ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

በ2015 በጀት ዓመት የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ የእንስሳት ውጤቶች ላኪዎች ዕውቅናና ሽልማት ተሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች