Wednesday, December 6, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ከንግግርና ከድርድር ውጪ ያለ አማራጭ መዘዙ የከፋ ነው!

የፖለቲካው ምኅዳር ጤና አጥቶ በየቦታው አለመግባትና ግጭት ሲባባስ፣ ኢኮኖሚውም ከሕመሙ ማገገም አቅቶት የሕዝቡን ኑሮ ከድጡ ወደ ማጡ ያደርገዋል፡፡ በአገራዊ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ መግባባት ጠፍቶ ልዩነት ወደ ጦር መሣሪያ ትግል ሲያመራ፣ ለአገር ተስፋ የሚሆኑ የልማት ትሩፋቶች መና ሆነው እየቀሩ ሕዝብ የድህነትና የድንቁርና መጫወቻ ይሆናል፡፡ ዓለም በየቦታው በሚለኮሱ ጦርነቶችና ግጭቶች ሰላም አጥቶ ችግሮች እየተባባሱ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ ውስጥም ከአንድ ጦርነት ወደ ሌላ ጦርነት እንደ ዋዛ እየተገባ ዙሪያው ገደል እየሆነ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ በታደለቻቸው ፀጋዎች ተጠቅማ ለአፍሪካና ለዓለም ገበያ መትረፍ ሲገባት፣ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን ፈር ማስያዝ አቅቶ ሕዝባችን በምግብ እጥረትና በሰላም ዕጦት እየተሰቃየ ነው፡፡ በምግብ ምርቶች፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በእንስሳት ሀብት ውጤቶች፣ በማዕድናት፣ በቱሪዝም፣ በውኃ፣ ክረምት ከበጋ ምርት በሚሰጡ የአየር ጠባዮችና በመሳሰሉት የታደለች የወጣቶች አገር ሰላም አጥታ በርካታ ሚሊዮኖች ዕርዳታ ሲለመንላቸው ያሳዝናል፡፡ በሠለጠነ ዘመን እንደ ዘመነ መሣፍንት መፋጀት ያሳፍራል፡፡

የአሁኑን ዘመን ትውልድ የታሪክ ድርሳናት የሚያገላብጠው መጪው ትውልድ፣ ዓለም በቴክኖሎጂ ተራቆ ሕይወትን ባቀለለበት ጊዜ ለምን ባለፉ የታሪክ ትርክቶች ላይ ተሰንቅሮ መፋጀትን መረጠ ብሎ መታዘቡ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ቴክኖሎጂው ተራቆ የሰው ልጅ በጣም መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶችን አሟልቶ ለመጪው ትውልድ የሚጠቅም አስተዋጽኦ ሲያበረክት፣ እዚህ ግን ለነገው ትውልድ ቂምና ቁርሾ ለማውረስ የሚያስችሉ አስከፊ ድርጊቶችን መፈጸም ነው የተያዘው፡፡ ለወጣቶች ጥራት ያለው ትምህርት ከመስጠት ይልቅ፣ የብሔርና የእምነት ማንነቶች ላይ በመቸንከር ጠመንጃ አንጋቢ ማድረግ ነው የተመረጠው፡፡ የትምህርት ጥራቱ እጅግ በጣም የወረደ ከመሆኑ የተነሳ ባለፉት ሁለት ዓመታት በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የተገኘው ውጤት ሌላው የታሪክ ቅሌት ነው፡፡ ከጠቅላላ ተፈታኞች 97 በመቶ ያህሉ የመውደቃቸው መርዶ ሲነገር፣ ጥፋቱን በተማሪዎች ስንፍና በማሳበብና ጣትን ሌሎች ወገኖች ላይ በመቀሰር ማምለጥ አይቻልም፡፡ ታሪክም ሆነ መጪው ትውልድ አምርረው የሚኮንኑት የዚህን ትውልድ አባላት በሙሉ ነው፡፡ የግልና የወል ተጠያቂነት እንደሚኖር አይዘንጋ፡፡

ከላይ እስከ ታች የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ በየተዋረዱ ሥልጣን የጨበጡ፣ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎችና አደረጃጀቶችን የሚመሩና የሚሳተፉ፣ የእምነት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሙያና የጥቅም ማኅበራት መሪዎችና ወኪሎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አመራሮች፣ የንግዱ ማኅበረሰብ ማኅበራት፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች በሙሉ ኢትዮጵያ ለምን ከግጭትና ከድህነት አዙሪት ውስጥ መውጣት አቃታት የሚለውን መሠረታዊ ጉዳይ በጋራ ባለመምከራቸው ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ አንደኛው ወገን ሥልጣኑን ለማጠናከርና ተገዳዳሪውን ለማዳከም፣ ሌላው ደግሞ በአገኘው አጋጣሚ ሥልጣኑን ነጥቆ መንበሩን ለማደላደል በሚያደርጉት መራኮት አገር እየደማች ሕዝብ ፍዳውን እያየ ነው፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ ከአገር ህልውና በፊት የራሳቸውን ጥቅም የሚያስቀድሙ ከንቱዎች መለያቸውን እየለዋወጡ፣ ሥልጣን ከያዘውና ለሥልጣን ከሚተናነቀው ተገዳዳሪ ጋር ወቅት እያዩ እየተለጠፉ የአገርንና የሕዝብን መከራ እያበዙ ነው፡፡ በአድባርይነትና በአስመሳይነት በተካኑ ማፊያዎች አገር ሰላም ስታጣ፣ ለብሔራዊ መግባባት የሚበጅ ምክረ ሐሳብ ማቅረብ ለምን እንደሚያቅት ይደንቃል፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በውጭ ኃይሎች ግፊት በፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት እንዲገታ እንደተደረገው ሁሉ፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች እየተካሄዱ ያሉ መጠነ ሰፊ ግጭቶች በአገር በቀል ሽምግልናም ሆነ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ማስቆም እንዴት ያቅታል? በአራቱም የአገሪቱ ማዕዘናት ለብዙ ሺሕ ዓመታት ያገለገሉና በየማኅበረሰቦች ትልቅ ክብር የሚሰጣቸው የግጭት መፍቻ ዘዴዎች፣ እንኳንስ ለውስጣዊ ችግሮች ድንበር ተሻግረው ለሌሎች አገሮች መትረፍ ይችሉ እንደነበር አይጠረጠርም፡፡ የገዳይና የሟች ቤተሰቦችን ሸምግለው ሰላምና ዕርቅ ከማውረድ አልፈው በጋብቻ በማስተሳሰር ዝምድና መፍጠር የሚችሉ የተከበሩ አዛውንቶች ባሉባት ኢትዮጵያ፣ በሰላማዊ ንግግር መፈታት የሚችሉ መለስተኛ ቅራኔዎች ለመቶ ሺዎች ንፁኃን ዕልቂትና ለሚሊዮኖች መፈናቀል ምክንያት ሲሆኑ ከማየት የበለጠ ምን የሚያሳፍር ነገር አለ? የሚያጋጥሙ ችግሮችን ሰብሰብ ብሎ በሽምግልና መፍታት የተከበረ ባህል በሆነባት ኢትዮጵያ ውስጥ፣ በሰበብ በአስባቡ ጠመንጃ እያነገቱ ከመተላለቅ የተገኘው ጥቅም ምንድነው? ከትናንት ስህተቶች በመማር ነገን ማሳመር ሲቻል የስህተት አረንቋ ውስጥ መዳከር በጣም ያስንቃል፡፡

እጅግ በጣም ቅርብ ከሚባለው የሰሜን ኢትዮጵያ ዕልቂትና ውድመት ለመማር ሳይፈለግ ቀርቶ፣ አሁን የተገባበት አደገኛ የጥፋት መንገድ በፍጥነት በንግግርና በድርድር መላ ካልተፈለገለት ይህ ትውልድ አንገቱን የሚያስደፋው የታሪክ ጠባሳ ጥሎ ያልፋል፡፡ ይህ ጠባሳ አገርን የማፍረስና ሕዝብን የመበተን ጦስ ስለሚኖረው ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ሁሉንም ነገር ለፖለቲከኞችና ጠመንጃ ወልውለው ጥራኝ ዱሩ ለሚሉት መተው ያተረፈው ነገር ቢኖር፣ አገርን እያደር ወደ ሰላም አልባነት እንዲሁም ሕዝብን ለመረረ ድህነትና ተመፅዋችነት መዳረግ ነው፡፡ ብዙኃኑ ሕዝብ በአገሩ ዕጣ ፈንታ ላይ ወሳኝ መሆን ሲገባው፣ ጥቂቶች የፕሮፓጋንዳ ማሽኑን ተቆጣጥረው ሕይወቱ እየተመሰቃቀለ ነው፡፡ ሕግ አለ ተብሎ በሚታሰብበት አገር በየቦታው ወረበሎች ዜጎችን እያገቱ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለማስለቀቂያ ሲጠይቁ መስማት ይዘገንናል፡፡ የወረበሎቹ ዕገታ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ጭምር መከናወን ተጀምሯል ሲባል ያስደነግጣል፡፡ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ በሥርዓት ተቀምጦ መነጋገር ሲያቅት፣ አገር የሥርዓተ አልበኞች መፈንጫ እንደምትሆን ነጋሪ የሚያሻው ጉዳይ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ጊዜ የሚያስፈልጋት ዋነኛው አንገብጋቢ ጉዳይ ዘለቄታዊ ሰላም ሊያስገኝ የሚችል ብሔራዊ ንግግር ነው፡፡ ብሔራዊ ንግግርን ወደ ጎን በመግፋት በጉልበት ዓላማን ማሳካት ይቻላል የሚሉ ካሉ ጤነኝነታቸው ያጠራጥራል፡፡ ከዚህ በፊትም ሆነ ትናንት የተካሄደው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሊገታ የቻለው በሰላም ድርድር እንጂ፣ በአንድ ወገን አሸናፊነት እንዳልነበረ በገሃድ የታየ እውነት ነው፡፡ በጦርነት ምናልባት ጊዜያዊ ድል ሊገኝ ይችል እንደሆነ እንጂ፣ ዘለቄታዊ የበላይነት መጎናፀፍ እንደማይቻል በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ትናንት ያለ የሌለ ኃይላቸውን አሠልፈው በምድርና በሰማይ ሲፋለሙ የነበሩ ዛሬ ሰላም አውርደው ከአንድ ገበታ ማዕድ ሲቋደሱ፣ በፀፀትና በቁጭት ውስጥ ሆነው በከንቱ ሕይወታቸው ያለፈ ንፁኃንን እያሰቡ እንደሆነ ማንም አያስተባብልም፡፡ ለልዩነቶች ዕውቅና ተሰጣጥቶ በጠረጴዛ ዙሪያ በመነጋገር በቀላሉ መፍትሔ መፈለግ እየተቻለ፣ ከተፋላሚዎች በተጨማሪ በርካታ ንፁኃንን እሳት ውስጥ መማገድ ደረጃ አይደረስም ነበር፡፡ አሁንም በግራና በቀኝ ሆነው ‹ግፋ በለው› የሚሉም ሆነ አጃቢዎቻቸው ልብ ሊሉት የሚገባ ቁምነገር፣ በሥርዓት ተቀምጦ ከመነጋገርና ከመደራደር ውጪ ያለ አማራጭ መዘዙ የከፋ መሆኑን ነው!   

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...