Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ፕሬዝዳንቷ ፓርላማውን ሲከፍቱ የሸማችን ልብ ያሞቀ ንግግር ማድረጋቸውን መዝግበናል!

የሁለቱ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች መክፈቻ ፕሮግራም ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ በበጀት ዓመቱ መንግሥት ትኩረት ያደርግባቸዋል ያሏቸውን የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጠቅሰዋል፡፡ በመንግሥት በትኩረት ይሠራባቸዋል ብለው ካመለከቷቸው ጉዳዮች አንዱ የንግድና የግብይት ሥርዓቱን ማሻሻል ነው። 

ከዚህ ቀደም የመንግሥትን የትኩረት አቅጣጫ የሚያመለክቱ የመክፈቻ ንግግሮች ላይ ይህ ጉዳይ እምብዛም ሲጠቀስ አልተሰማም፡፡ ዘንድሮ ግን ኢኮኖሚ ጉዳዮችን ከተመለከቱ የመንግሥት አቅጣጫዎችና ተግባራት መካከል የግብይት ሥርዓቱን ለማሻሻል የሚሠራ መሆኑን በግልጽ መቀመጡ መልካም ነው፡፡ 

በእርግጥም የአገራችን የንግድ ወይም አጠቃላይ የሥርዓት ምናልባም ለኢኮኖሚ ስብራታችን አንዱ ምክንያት ተደርጎ የሚወሰድ በመሆኑ፣ በዚህ ዙሪያ ያለውን ሥር የሰደደ ችግር መፍታት ብዙ ሸክም ያቃልላል፡፡ በመሆኑም የአገራችንን የተበለሻሸ የንግድና የግብይት ሥርዓት መስመር ለማስያዝ መንግሥት በተያዘው ዓመት ልሠራባቸው ካቀድኳቸው ኢኮኖሚያዊ ክዋኔዎች መካከል አንዱ ይኼው የንግድ ሥርዓትና ጥራት ጉዳይ ከሆነ ደግሞ ጉዳዩ በጥልቀት ሊሠራበት ይገባል፡፡    

ዛሬ ለተዘፈቅንበት የዋጋ ንረትና ለኑሮ መወደድ የተበለሻሸው የግብይት ሥርዓታችን ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ እንዳለው በመገንዘብ፣ አጠቃላይ የንግድ ሥርዓቱ በሕግና በደንብ እንዲገዛ ማስቻል በእርግጥም ልዩ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ 

የግብይት ሥርዓትን ጤናማነት ለማስጠበቅ ገበያ ለማረጋጋት፣ ጊዜን የዋጀ አሠራር ስለሚያስፈልግ እስካሁን ሥራ ላይ አሉ የሚባሉ የመቆጣጠሪያ ሥልቶችና አሠራሮችን ይዞ መሆን እንደሌለበትም ሊሰመርበት ይገባል፡፡ 

ገበያውን ለማረጋጋት ያልተገባ የዋጋ ዕድገቱን ለመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጣቸው መንግሥታዊ ተቋማት የእስካሁኑ ጉዟቸው የሚሳየን የግብይት ሥርዓቱን ለማዘመንም ሆነ ገበያ መር የሆነ አሠራር እንዲኖር በአግባቡ ያለመሥራታቸው ነው፡፡ ይህም በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ የገዘፈ ሥርዓት አልበኝነት እንዲጋነን ማድረጉን በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡

መንግሥት ሁሌም እሳት ማጥፋት ተግባር ላይ የተጠመደ በመሆኑ፣ አሠራሩ ያዝ ለቀቅ እያለ የዘለቀ ነበር። ይህም ገበያው ምክንያታዊ ባልሆነ የዋጋ ንረት እንዲናጥ አድርጎታል። በሁሉም ቢዝነስ ዘርፎች ያሉ ብልሽቶች ሕጋዊ አሠራሮችን ተላልፈው ሕገወጦች የሚከብሩበት መንገድ የተከፈተው የንግድ ሥርዓታችንን በወጉ ያልተያዘ በመሆኑ ጭምር ነው፡፡   

በአንድ ጀምበር ‹‹እከሌ ቢዝነስ ዘጋ፣ እከሌ እኮ ሚሊዮነር ሆነ›› የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ በሕጋዊነት ሽፋን ብዙዎች በሙስና ተጨመላልቀው፣ ሕጋዊ አሠራሮች ተጨፍልቀው ነውና የግብይት ሥርዓታችን ይስተካከል ካልን፣ በአንድ ጀምበር ሚሊዮነር የሚሆኑትን መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን በሕጋዊ መንገድ ለመጓዝ ተጠያቂ የሚያደርግ መሆኑን ማመላከት ያስፈልጋል፡፡  

የንግድ ሥርዓቱ ሊስተካከል ይገባል ሲባል፣ አጠቃላይ የታመመውን ኢኮኖሚያችንንም መድኃኒት ልናገኝለት ይገባል ማለት ነው፡፡ አንደኛው ታክስ እየከፈለ ሲሠራ ሌላው ደግሞ ያለ ንግድ ፈቃድ ተመሳሳይ ሥራ እንዳይሠራ በሕግ መገደብ ማለት ነው፡፡

የአገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት አንዱ መገለጫው ገበያ መር በሆነ መንገድ የሚካሄድ ግብይትን ማጎልበት፣ ከሌብነት የፀደ አገልግሎት መስጠትን ሁሉ የሚያጠቃላል በመሆኑ፣ በሙስና የተጨማለቁ እጆች እንዲሰበሰቡ ቁርጥ ውሳኔ ሊወሰድ ካልቻለ የንግድ ሥርዓቱ አይስተካከልም፡፡

ሕጋዊ የሆነ የግብይት ሥርዓት በሌለበት ዓውድ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አይጠበቅምና ከታች ጀምሮ ትክክኛ የትርፍ ህዳግ ይዞ የሚሠራ የንግድ ኅብረተሰብ መፍጠር ካልተቻለም ጤናማ ግብይት አይኖርም፡፡  ለዚህም ነው የግብይት ሥርዓታችን በሕግና በሥነ ምግባር ይመራ የምለው፡፡ 

አምራቾች ጥረውና ግረው ያመረቱትን ምርት የንግድ ፈቃድ እንኳን የሌላቸው ደላሎች ዋጋ እየወሰኑለት፣ እነሱ በትርፍ እየተንበሸበሹ በቃችሁ ካልተባሉ ከገባንበት አዙሪት አንወጣም፡፡ ስለዚህ ግብይቱን በሕግና በሥርዓት ለመምራት ከታሰበ ከታች ከአምራቹ ማሳ ጀምሮ ሸማቹ ዘንድ እስኪደርስ ድረስ በየመሃል ዋጋን የሚያጦዙ በአካፋ ትርፍ እያፈሱ፣ ለአምራቹ በማንኪያ የሚቆነጥሩ ደላሎች ሥርዓት እንዲይዙ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በገበያ ሥርዓት ውስጥ አቀባባይ ነጋዴዎች መኖራቸው ግድ ሊሆን ቢችልም፣ ይህ ቁልፍ ተግባር ግን በደላሎች ሳይሆን ሕግ በሚያውቃቸው ነጋዴዎች እንዲሸፈን ማድረግን የንግድ ሥርዓቱ ማሻሻያ አንድ አካል መሆን አለበት፡፡ 

በአጠቃላይ የግብይት ሥርዓቱን እናስተካክላለን ሲባል መፈተሽ ያለባቸው እጅግ ብዙ ጉዳዮች ስላሉ የእንዳንዱን ዘርፍ ችግሮች በመፈተሽ ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግ ይጠይቃል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት እየከሰሩ ምርት የሚልኩና ገበያውን የሚያበለሻሹ  ሁሉ የግብይት ሥርዓታችንን ብልሽት አንዱ መገለጫ ነው፡፡ ‹‹አንደር ኢንቮይስ›› እና ‹‹ኦቨር ኢንቮይስ›› በማድረግ የሚደረግ ማጭበርበርም ገበያው ውስጥ ያልተገባ ውድድር እንዲናኝ ብዙ ነገር አበላሽቷል፣ አሁንም እያበላሸ ነው፡፡ 

ከውጭ የሚመጡ ምርቶች የሚገዛባቸውና እዚህ የሚሸጥባቸው ዋጋ እጅግ የተጋነነ በመሆኑ ትክክለኛ የትርፍ ምጣኔ እንዲዛባ አድርገዋል፡፡ የግብይት ሥርዓቱ ይሻሻላል ሲባል፣ እንዲህ ላሉ ብልሽቶች ሁሉ ትክክለኛ መፍትሔ የሚሰጥ አሠራር ሊኖረን ይገባል ማለት ነው፡፡   

መንግሥት የግብይት ሥርዓቱ ላይ ያለውን ችግር ለማስተካከል ሲነሳም የማስተካከያ ዕርምጃዎቹ በተወሰኑ ዘርፎች ብቻ መሆን የለበትም የሚባለው በሁሉም ቦታ ችግር ስላለ ነው፡፡ ለአንዱ መፍትሔ በመፈለግ ሌላውን ማቆየት ወይም መዘንጋት የሚፈለገውን ውጤት አያመጣም፡፡ ዛሬ በሁሉም የቢዝነስ ዘርፎች ላይ ያሉ ችግሮች ሁሉ የገበያ ሥርዓትን ጠብቆ ያለመነገድና በአመዛኙ በአቋራጭ ለመበልፀግ ብርቱ ፍላጎት ያለበት በመሆኑ፣ ይህንን አደገኛ አካሄድ መቀልበስ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ለማድረግ  ሁሉም ተጠያቂ ሊሆንበት የሚያስችል አሠራር መዝጋት ነው፡፡ 

የገበያ ሥርዓቱ ጤናማ እንዲሆን በተለይ አብዛኛውን ኅብረተሰብ የሚገለገልባቸው መሠረታዊ ምርቶችን ከምርቱ መነሻ ጀምሮ ሸማቹ እጅ እስኪገቡ ድረስ ያለውን ረዥም ሰንሰለት ማሳጠር መሥራትንም ይጠይቃል፡፡ ሌላው ቀርቶ አንዳንድ ምርቶችን የዋጋ ገደብ እንዲኖራቸው ማድረግ የግብይት ሥርዓቱን ለማስተካከል መነሳት ማለት ጭምር መሆኑን ተገንዝቦ፣ አጠቃላይ የንግድ ሥርዓቱ በሕግ እንዲመራ ማድረግ ኢኮኖሚውን ለመደገፍ ሸማቹንም ለመታደግ ያግዛል፡፡  

ከሰሞኑ የፓርላማ የመክፈቻ ፕሮግራም ላይ ፕሬዚዳንቷ ዝቅተኛ የኅበረተሰብ ክፍሎችን እየፈተነ ያለውን ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ለመቀነስ ጥብቅ የፊዚካልና የገንዘብ ፖሊሲ እንደሚተገበር ገልጸዋል፡፡ 

አያይዘውም፣ ‹‹ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከምርት አቅርቦት እጥረት የሚመነጭ የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ይሠራል፤›› በማለት መንግሥት ያሰበውን ተያያዥ ዕቅድ አመላክተዋል። ይህንን ለማሳካትም ቢሆን መሠረታዊው ጉዳይ የንግድ ሥርዓቱን በሥነ ምግባር እንዲመራ ማድረግ ነው፣ ተጠያቂነትን ማስፈን ነው፡፡ 

በነገራችን ላይ የግብይት ሥርዓቱን ለማስተካከል ግን ኃላፊነቱን ሁሉ ለአንድ መንግሥት ብቻ የሚተው መሆን የለበትም፡፡ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ አሠራር መዘርጋትና የመፍትሔ ሐሳቦችን የሚያቀርቡ አካላትን ሁሉ ማሳተፍ ይገባል፡፡ ስለዚህ የግብይትን ሥርዓቱን ለመቆጣጠርና እንዲዘምን ለማድረግ መንግሥት ቁርጠኛ ከሆነ፣ ይህንን ሥራውን በተለመደው አሠራር ሳይሆን አዲስ አሠራር መቅረፅ ወደ ሥራ ይግባ፣ የግብይት ሥርዓቱን ለማስተካከል በይፋ የገባውንም ቃል ያክብር፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት