Wednesday, December 6, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ሁሉም አገራዊ ጉዳዮች ግልጽ ንግግር ይሻሉ!

ሰሞኑን አዲሱ የአገር መነጋገሪያ አጀንዳ እንዲሆን የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲክስ ጉዳይ  ወደ አደባባይ ብቅ ብሏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሌሎች በዓባይ ጉዳይ እንደፈለጉ ሲነጋገሩ፣ የቀይ ባህር ነገር በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለምን አይነኬና አይጠጌ (Taboo) ይሆናል በማለት ነበር በይፋ የመነጋገሪያ አጀንዳ እንዲሆን ያቀረቡት፡፡ ለኢትዮጵያውያን የቀይ ባህርና የወደብ ጉዳይ አዲስ አይደለም፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ ከራስ ካሳር እስከ ራስ ዱሜራ የነበራትን የቀይ ባህር ባለቤትነት በኤርትራ ነፃ መውጣት ማግሥት ብታጣም፣ በቸልተኝነት ወይም ሆን ተብሎ በተቀነባበረ ሴራ ወደብ አልባ ሆኗ መቅረቷ ብዙዎችን ሲያበሳጭ የነበረ የታሪክ ክስተት ነበር፡፡ አሁን ጉዳዩ አፍጦና አግጦ ሲመጣ ግን አገሪቱ ካለችበት ጥልቅ የሆነ የፖለቲካ መከፋፈል አኳያ ልዩ ልዩ ትርጓሜዎችና አንድምታዎች እየቀረቡ፣ ለዘመናት ከኢትዮጵያውያን ሐሳብ ውስጥ የማይጠፋው የወደብ ተጠቃሚነት ወይም ባለቤትነት ጥያቄ ሌላ መነታረኪያ እየሆነ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከልዩነት ይልቅ በአንድነት ለመቆም የሚረዱ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ ውስጣዊ ክፍፍሉ መተማመንን እያጠፋ መራራቅን እያበዛ ነው፡፡

በዚህ በሰሞነኛው የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲክስ ጉዳይ አንዱ ወገን ታሪካዊ ዳራዎችን እያጣቀሰ መነጋገሪያ መሆኑን ሲደግፍ፣ ሌላው ወገን ደግሞ የትኩረት አቅጣጫን ለማስቀየር ሲባል የቀረበ ማደናገሪያ ነው በማለት ያጣጥለዋል፡፡ በአንድ በኩል እርስ በርስም ሆነ ከጎረቤት አገሮችና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በጉዳዩ ላይ በግልጽ የመነጋገርን አስፈላጊነት የሚያስረዱ ሲኖሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጉዳዩ ውስብስብና በውዝግቦች የተሞላ በመሆኑ ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን የመጠቀም አማራጭን የሚጠቁሙ አሉ፡፡ ይህ ጉዳይ አሁን ለምን ሊነሳ ቻለ የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፣ አሁን ካልተነሳ መቼ ሊነሳ ነው የሚሉም መኖራቸው ይስተዋላል፡፡ ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጋር ያላትን ታሪካዊ ትስስርና ብሔራዊ ጥቅም በማውሳት የሚሞግቱ ሲኖሩ፣ ውስጣዊ መረጋጋት በመፍጠር በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ አቀራረብ ካልሆነ ሌላ መዘዝ ያመጣል የሚሉም ይደመጣሉ፡፡ ውስጣዊ ችግርን ሳይፈቱ ወደ ውጭ ማማተር አደገኛ መሆኑን በማሳሰብ፣ ለጋራ ተጠቃሚነትና ለክፍለ አኅጉራዊ ትብብር የሚያግዝ ቅን ዓላማ ማንገብን ይጠይቃሉ፡፡ ከፍጥጫ ይልቅ ትብብር ላይ ይተኮር ይላሉ፡፡

ከላይ የተነሱ በተለያዩ ዓውዶች የሚንፀባረቁ ሐሳቦች እንዳሉ ሁሉ ሌሎች ጽንፍ የረገጡ ምልከታዎችም ይሰማሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ዕይታዎች በአንድ አገር ውስጥ ሲንሸራሸሩ ቆም ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚኖርባት ትልቅ አገር ናት፡፡ በአካባቢው በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በዲፕሎማሲና በተለያዩ መስኮች የገዘፈ ተፅዕኖ የመፍጠር ዕምቅ አቅም አላት፡፡ እንኳንስ ከጎረቤት አገሮች ጋር በጋራ ለመልማት የሚያስችሉ ጉዳዮችን ቀርቶ፣ ችግሮች ሲያጋጥሙ በሰላማዊ መንገድ በመፍታት የተረጋጋ ምኅዳር ለመፍጠር ትችላለች፡፡ ለዚህ ግን ቅድመ ሁኔታ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ቅድመ ሁኔታ ውስጣዊ አለመግባባቶችን በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ በመፍታት አንድነት ለመፍጠር ጥረት የማድረግ ፍላጎት ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ብልፅግና የሚመራው መንግሥት በመላ አገሪቱ ሰላም ለማስፈን የሚረዳ ፍኖተ ካርታ ያስፈልገዋል፡፡ ግጭት የሚያነሳሱ አደገኛ ትርክቶች ቆመው በሰላማዊ መንገድ ለመነጋገር የሚያስችሉ የጋራ መድረኮች ያሻሉ፡፡ በየቦታው የተለኮሱ ግጭቶች ቆመው ሰላምና ፀጥታ መስፈን ይኖርበታል፡፡ በሕዝብ ላይ እንግልት የሚፈጥሩ ብልሹ አሠራሮች መወገድ አለባቸው፡፡

በአሁኗ ኢትዮጵያ በሕዝብና በመንግሥት፣ በገዥው ፓርቲና በተፎካካሪዎቹ፣ እንዲሁም በተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል መተማማን እየጠፋ ነው፡፡ መተማመን በመጥፋቱ ለአገር የሚጠቅሙ የጋራ ብሔራዊ ጉዳዮች እየመከኑ ነው፡፡ በመንግሥትም ሆነ በሌላ አካል አንድ ሐሳብ ሲቀርብ መተማመን ስለሌለ ለሴራ ትንተና ይጋለጣል፡፡ መንግሥት አሠራሩ በሕግ እንደተደነገገው በግልጽነት፣ በኃላፊነትና በተጠያቂነት መርህ ቢመራ መተማመን አይቸግርም ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ የፖለቲካ ልዩነቱ ከመጠን በላይ በመጦዙ ምክንያት ለአገር የሚበጅ ሐሳብ ይዞ ቢቀርብ እንኳ፣ ለሴራ ፖለቲካ እየተጋለጠ በቅጡ ከሚያዳምጡት ይልቅ የሚያብጠለጥሉት ይበረክታሉ፡፡ ልዩነት መኖሩ ተፈጥሯዊ ቢሆንም ቅራኔው በጣም መሠረታዊ ሲሆን፣ አንድ አገራዊ ጉዳይ ቅቡልነት የሚያገኘው ወይም የሚያጣው ካለው ጠቀሜታ አኳያ አይደለም፡፡ ይልቁንም የፖለቲካ ጎራ አሠላለፉ እየወሰነው ለአገር የሚጠቅም ጉዳይ ከንቱ ሆኖ ይቀራል፡፡ የሰሞኑ የቀይ ባህር መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ እየተንሸራሸረ ያለው ልክ እንደ አመጣጡ በድንገቴ ድጋፍና ተቃውሞ ነው፡፡

በፖለቲካው ዓለም አንድ የሚታወቅ አባባል አለ፡፡ እሱም በዓለም ላይ ውዱ ነገር ዩራኒየም፣ አልማዝ፣ ወርቅ፣ ነዳጅ ወይም ሌላ የማዕድን ውጤት ሳይሆን መተማመን ነው ይባላል፡፡ በዓለም ዙሪያ በሁለትዮሽም ሆነ በባለ ብዙ ወገን ግንኙነት ዲፕሎማሲው የሚቀላጠፈው በመተማመን መንፈስ ነው፡፡ አንዱ በሌላው አካል ላይ ጥርጣሬ ቢኖረው እንኳ፣ የውስጡን በውስጡ ይዞ ለገባው ቃል ወይም ለፈረመው ስምምነት ታማኝነቱን ያሳያል፡፡ በአገር ደረጃም ቢሆን ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎችንም ሆነ ዜጎችን የሚገዛው ሕግ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት በሚከበርበት አገር ውስጥ ሁሉም ዜጎች ከሕግ በታች ናቸው፡፡ ሕግና ሥርዓት ሲኖር አንዱ በዳይ ሌላው ተበዳይ አይሆኑም፡፡ ሕግ ሳይከበር ሲቀር ግን ከልካይ የሌለባቸው ጉልበተኞች አገር ያተራምሳሉ፡፡ ሕገወጦች ገነው ሕግ አክባሪዎች ሲረገጡ መተማመን ይጠፋል፡፡ ጥቂቶች እንዳሻቸው እየፈነጩ ብዙኃን ጥጋቸውን ሲይዙ ቅራኔው ይጋጋማል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንኳንስ አንድነት መፍጠር አብሮ መኖርም አይቻልም፡፡ ለዚህም ነው በአገር ደረጃ መተማመን እንዲኖር ፍኖተ ካርታው መነደፍ ያለበት፡፡

የመተማመን ፍኖተ ካርታው ተነድፎ በእኩልነት ለመነጋገር የሚያስችል ምኅዳር ሲፈጠር፣ በሁሉም የአገር የጋራ ጉዳዮች ላይ ልዩነትን ይዞ መመካከር ይቻላል፡፡ መተማመን በሌለበት ግን ጠቃሚ አገራዊ ሐሳቦች እየመከኑ ልዩነቱ እየሰፋ ይሄዳል፡፡ በቀና መንፈስ የታሰቡ አገር ጠቃሚ አጀንዳዎች ተመልካች አጥተው በየጎራው መናከሱ ይቀጥላል፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ አዙሪት ውስጥ በፍጥነት በመውጣት አገራዊ የጋራ መደላድል መፍጠር የግድ መሆን አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከቂም በቀል፣ ከጥላቻ፣ ከሐሜት፣ ከአሉባልታና ከሴራ ተላቆ የአገር ህልውናን ማስቀጠል ይጠበቅበታል፡፡ በፖለቲካው ምኅዳር ውስጥ ያሉ ተዋንያን በሙሉ የባህሪ ለውጥ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በተለይ ደግሞ የአገረ መንግሥቱን ሥልጣን የያዘው ብልፅግና ፓርቲ አመራሮችም ሆኑ አባላት፣ ችግሮችን አባባሽ ከመሆን ተቆጥበው መፍትሔ አፍላቂ ይሁኑ፡፡ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮችም ሆኑ አባላት ከአሉታዊ አስተሳሰቦች ተላቀው ለአገር አሳቢ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ትጥቅ አንግበው የሚፋለሙ አካላትም እንዲሁ፡፡ ለግልጽነት፣ ለተጠያቂነትና ለኃላፊነት መርህ መገዛት ሲለመድ ተቀምጦ መነጋገር አያቅትም፡፡ ሁሉም አገራዊ ጉዳዮች ግልጽ ንግግር እንደሚሹ ግንዛቤ ይኑር! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...