Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የፎቶ ጠቢባንን በጥበብ መናኸሪያ

አንድ ግልጽም ሆነ ውስብሰብ ሐሳብን በምሥል በማንፀባረቅ በብዙ አቅጣጫ ትርጉም እንዲኖረው ከሚያደርጉ መካከል የፎቶግራፍ ባለሙያዎች ይገኙበታል፡፡ ፎቶግራፍ የበርካታ ሰዎችን ቀልብ ከመሳብ በተጨማሪ፣ የተለያዩ ሁኔታዎችን የሚፈጥር ድንቅ ትዕይንት ሲሆን፣ ከሺሕ ቃላት በላይ ዋጋ እንዳለው ጭምር  ይወሳል፡፡ ይህንን ትዕይንተ ጥበብ ለማዳበር ግራር የጠቢባን መናኸሪያ ድርጅት እየሠራ ይገኛል፡፡ ድርጅቱ በተለያዩ የሕይወት መስመሮች ያለፉ የሚገናኙበት፣ የሚመካከሩበት፣ ዕውቀትና መረጃ የሚለዋወጡበት፣ እንዲሁም የገበያ ዕድል የሚያገኙበት ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ላይ እንደሚገኝ ይናገራል፡፡ አቶ ሰሚናስ ሃደራ የድርጅቱ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ድርጅቱ የሚሠራውን ሥራ በተመለከተ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ግራር የጠቢባን መናኸሪያ ድርጅት ዓላማው ምንድነው?

አቶ ሰሚናስ፡- ግራር የጠቢባን መናኸሪያ ዋና ዓላማው በጥበብ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ዕውቅና እንዲያገኙ፣ እንዲሁም የሥራ ዕድል እንዲመቻችላቸው ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ተቋሙም የተፀነሰው የዛሬ ስድስት ዓመታት ገደማ ቢሆንም፣ ሕጋዊ ፈቃድ ካገኘ ግን አንድ ዓመት ከስድስት ወራት ሆኖታል፡፡ በተለይም በጥበብ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ እንዲያገኙ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ከኅብረተሰቡ ጋር የሚገናኙበትና ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት መድረክ ከአዲስ አበባ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች ማኅበር ጋር በመሆን፣ ‹‹የዘወትሯ ኢትዮጵያ›› የተሰኘ የፎቶ ዓውደ ርዕይ ከጥቅምት 2 እስከ ጥቅምት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ለማካሄድ ችሏል፡፡ በዚህም ዓውደ ርዕይ በርካታ ፎቶግራፈሮች መሳተፍ ችለዋል፡፡ የፎቶ ዓውደ ርዕዩም ከዩኤስኤይድ በተገኘ ድጋፍ የተከናወን ሲሆን፣ ከ80 በላይ የሆኑት ፎቶግራፎቹም ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና ሌሎች ይዘቶች ያሏቸው ናቸው፡፡ ዓውደ ርዕዩ የኢትዮጵያን አስደማሚና ምሉዕ ገጽታ በማውጣት አንድነትንና ትስስርን ያጎላ ገጽታ ነበረው፡፡ ዓውደ ርዕዩ ወጣቶች በፈጠራ ሥራዎች በኩል ለሰላም ግንባታ እንዲተጉ የሚያሳይ ሆኗል፡፡ በዓውደ ርዕዩ ላይም በተመልካቾች ዘንድ አሳታፊና ገንቢ የሆነ ውይይትን ፈጥሯል፡፡

ሪፖርተር፡- በሥራችሁ ምን ዓይነት ለውጥ ማምጣት ችላችኋል?

አቶ ሰሚናስ፡- ተቋማችን ከአዲስ አበባ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች ማኅበርና ከዩኤስ ኤይድ ጋር በመሆን፣ የኢትዮጵያን ባህላዊ እሴቶች በጠበቀ መልኩ የፎቶ ዓውደ ርዕዩን ለሁለተኛ ጊዜ አካሂዷል፡፡ የመጀመርያው ዓውደ ርዕይ ‹‹ፎቶግራፍ ለሰላም›› በሚል የተዘጋጀ ሲሆን፣ በወቅቱም አርባ ፎቶዎች ለዕይታ ቀርበዋል፡፡ መሠረተ ሐሳቡም የኢትዮጵያ ወጣቶች እንዴት አድርገው የሰላም ውይይት መፍጠር ይቻላሉ? የኢትዮጵያ ገጽታ በምን ዓይነት መልክ ቢቀርብ የተሻለ ይሆናል? የሚለውን ያንፀባረቀ ነው፡፡ በወቅቱም ከ200 በላይ ሰዎች የፎቶግራፍ አነሳስ ጥበብ ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡ በፎቶግራፍ ባለሙያ በሚካኤል ፀጋዬ አማካይነት በተዘጋጀው የዘወትር ኢትዮጵያ የፎቶግራፍ ዓውደ ርዕይ የአሥራ አምስት አንጋፋና ጀማሪ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች ሥራዎች በአዲስ አበባ፣ በባህር ዳር፣ በሐዋሳና በድሬዳዋ ሊታይ ችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋማችሁ ምን ዓይነት ችግር ገጥሞታል?

አቶ ሰሚናስ፡- ተቋሙ እንደ ትልቅ ችግር የሚያየው የጥበብ ዘርፉ እንደ አንድ ኢንዱስትሪ ዕውቅና አግኝቶ እየተንቀሳቀሰ ባለመሆኑ ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል፡፡ በተለይ በትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች እንደ ሥዕልና ሙዚቃ የፎቶግራፍ ትምህርት በአግባቡ ቢሰጥ፣ በዘርፉ የተሻለ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ ይህ በራሱ ባለመሆኑ የተነሳ የጥበብ ዘርፍ አንድ ዕርምጃ እንዳይሻገር ያደርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የፎቶግራፍ ባለሙያዎች ሥራቸው ላይ የተሻለ ዕድገት እንዲያመጡ ተቋማችሁ ምን ዓይነት ድጋፍ ያደርጋል?

አቶ ሰሚናስ፡- ግራር የጠቢባን መናኸሪያ የፎቶግራፍ ባለሙያዎችን ወደ አንድ ጠረጴዛ በማምጣት፣ ውይይት እንዲያደርጉ መድረኮችን ይፈጥራል፣ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ የጥበብ ባለሙያዎች ማኅበር እንዲያቋቁሙ የበኩሉን ድርሻ ይወጣል፡፡ በተለይ የፊልም፣ የሙዚቃ፣ የሥዕል፣ የደራስያንና ሌሎች ማኅበሮች ተዋቅረው የተሻለ ሥራ እየሠሩ ይገኛል፡፡ ይህንን በማየት በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች ማኅበር ሊቋቋም ችሏል፡፡ ማኅበሩም በዋናነት አዲስ አበባ ላይ የተቋቋመበት ዋነኛ ምክንያት የፎቶግራፍ ሥራዎች በተጠናከረ መልኩ እንዲታይ ለማድረግና ክልሎች ድረስ ለመሄድ እንዲቻል በማሰብ ነው፡፡ ግራር የጠቢባን ማኅበርም እንደ እነዚህ ዓይነት ማኅበሮች ሲፈጠሩ ምን ማድረግ እንዳለበትና እንዴት መምራት ይቻላል? የሚለውን እንደ ኃላፊነት በመውሰድ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል፡፡ በተለይ ማኅበሮች ላይ ጠንካራ የሆነ ትስስር መፍጠር ከተቻለ የገበያ ትስስሩም የተሻለ እንዲሆን ያደረግላቸዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- ከታች ለሚገኙ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች የምትሰጡት የክህሎት ሥልጠና አለ?

አቶ ሰሚናስ፡- የፎቶግራፍ ሙያ ገና እያደገ ያለ ሙያ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ከታች ለሚገኙ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች ቴክኒካል ብቃታቸውን እንዲያሳድጉ ተቋሙ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ይህንንም ለማድረግ ሥልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል፡፡ በተለይ አሁን ላይ ስማርት ስልኮችን በመጠቀም በቀላሉ ፎቶዎችን አንስቶ የተለያዩ የሶሻል ሚዲያዎች ላይ በመልቀቅ ዕውቀታቸውን ማዳበር የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል፡፡ ይህም የፎቶግራፍ ሙያን ለማሳደግም ሆነ ባለሙያውን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ትልቅ አማራጭ መሆን ችሏል፡፡ ይህንንም ማድረግ ከተቻለ በዘርፉ ያለውን መሠረታዊ ችግር እንዲቀረፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋማችሁ በቀጣይ ምን ለመሥራት አስቧል?

አቶ ሰሚናስ፡- ተቋማችን በቀጣይ የተለያዩ ሥራዎች ለመሥራት ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በተለይ በፎቶግራፍ ዘርፍ ላይ ያለው አደረጃጀት ውጤታማ ሆኖ ስላገኘነው ወደ ሌሎች ዘርፎችም ገብቶ ለመሥራት ዕቅድ ይዘናል፡፡ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ፊልም፣ ቴአትር፣ ሙዚቃና ሥዕሎች ላይ ይህንን አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በፊልም ላይ ለሚታዩ ባለሙያዎች የሦስት ወራት ሥልጠና በመስጠትና ለዘጠኝ ወራት ያህል የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ለማድረግ ፕሮግራም ቀርፀን እየሠራን እንገኛለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሴት ሠዓሊያን ላይ ያተኮረ ፕሮጀክት ቀርፀን እየሠራን ነው፡፡ በዚህም ፕሮጀክት ሃያ ሴት ሠዓሊያንን እንዲሳተፉ በማድረግ፣ ሥራዎቻቸውን ለዓለም አቀፍ ገበያ እንዲያበቁ የምናደርግ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የማስታወቂያ ሥራዎች ላይ ለሚሠሩ ባለሙያዎችም ተገቢ ሥልጠና እንዲያገኙ የምንጥር ይሆናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ሠራተኛ ስቀጥር ካለመሠልጠናቸውም በላይ ስንት ይከፈለኛል ብለው ሲጠይቁ እደነግጥ ነበር›› ወ/ሮ ቅድስት ጌታቸው፣ የሶጋ ትሬዲንግና ፖላር ፕላስ ኤክሰለንስ ሀብ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ

በኢትዮጵያ የሚገኙ ቀጣሪ ድርጅቶች የሚፈልጉት የሠለጠነ የሰው ኃይልና የሥራ ፈላጊው ብቃት በብዛት አይጣጣምም፡፡ በዚህም ቀጣሪዎች ብቁ የሰው ኃይል አለማግኘታቸውን፣ ሠራተኞችም የሚፈልጉትን የሥራ ዓይነት አጥተው...

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞችን መደገፍ የግድ እንደሚል ይታመናል፡፡ መንግሥት ሊያደርግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ ደግሞ የውጭ...

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...