- በጠዋት ምን የሚያስቅ ነገር አግኝተሽ ነው?
- ውይ ገብተዋል እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ምንድነው እንደዚያ ሲያፍለቀልቅሽ የነበረው?
- ወድጄ አይደለም ክቡር ሚኒስትር።
- እንዴት?
- ወዶ አይስቁ ሆኖብኝ ነው።
- በምን ምክንያት?
- ፌስቡክ ላይ የሚቀለደውን አይቼ …ነው ክቡር ሚኒስትር።
- ምን ተቀልዶ ነው?
- አይ… ይቅርብዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ለምን?
- ቢቀርብዎት ይሻላል ክቡር ሚኒስትር?
- ለምን? ጉዳዩ እኔን የሚመለከት ነው እንዴ?
- ኧረ በጭራሽ። እርስዎን በቀጥታ አይመለከትም። ቢሆንም ግን…
- ቢሆንም ምን?
- ብዙ አይርቅም?
- ማለት?
- ስለ አማካሪዎት ነው እየተቀለደ ያለው?
- እንዴት? በምን ምክንያት?
- ለሚዲያ በሰጡት ኢንተርቪው ነው ክቡር ሚኒስትር።
- ምን ብሎ ነው?
- የኑሮ ውድነትን ለማቅለል መንግሥት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን በተመለከተ በሰጡት ሐሳብ ነው።
- ምን ዓይነት ሐሳብ ነው የሰጠው?
- ክቡር ሚኒስትር እንዲያው ቢቀርብዎት ይሻላል ብዬ እኮ ነው?
- ለምን አትነግሪኝም?
- ካሉ እነግሮታለሁ።
- ንገሪኝ ምንድነው ያለው?
- አንደኛ የተናገሩት መንግሥት የኑሮ ውድነትን ለማቅለል በማሰብ ማጋራት ጀምሯል አሉ።
- ምንድነው የሚያጋራው?
- ማዕድ!
- እሺ ሌላስ ምን አለ?
- ሌላው ደግሞ ገበያ እንዲጀመር አድርጓል ነው ያለው።
- የምን ገበያ?
- የእሑድ ገበያ!
[ክቡር ሚኒስትር ከባለቤታቸው ጋር በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ፕሮግራም እየተከታተሉ ነው]
- ምንድነው?
- አይ… ገርሞኝ ነው?
- ምኑ?
- አለቃህ የሚሉትን አትሰማም እንዴ?
- አገርን ስለሚጠቅም የባህር ወደብ ጉዳይ እንጂ የሚያስቅ ነገር ሲናገሩ አልሰማሁም።
- ጉዳዩማ ጠቃሚ ነው።
- ታዲያ ምንድነው ያሳቀሽ?
- አስፈላጊ ነው ብለው የሚያወሩትን ጉዳይ የገዥው ፓርቲም አቋም አይደለም ማለታቸው ነዋ።
- እንደዚያ ብለዋል?
- እንደዚያ ብቻ እይደለም ያሉት።
- ሌላ ምን አሉ?
- ሐሳቡን የማቀርበው እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ እንጂ እንደ መንግሥት አይደለም።
- አይሉም!
- ታዲያ እኔ ከየት አመጣዋለሁ?
- የት እንደሰማሽው እኔ ምን አውቄ?
- እንዲሁ ሳስበው ብቻ መሸከም አቅቷችሁ ወደ ሕዝቡ እያቀበላችሁት ነው የሚመስለው።
- ምንድነው መሸከም ያቃተን?
- ምን እንደሆነ አላውቅም ግን…
- ግን ምን?
- አንድ ትኩስ ድንች ሳይገጥማችሁ አልቀረም።
- ቆይ የቀይ ባህር ጉዳይ ጠቃሚ አይደለም እያልሽ ነው?
- አላልኩም።
- እና ምን እያልሽ ነው?
- ከቀይ ባህር በፊት የማኅበረሰቡን የዕለት ችግር ፍቱ፣ ቢያንስ ሽንኩርት አቅርቡ እያልኩ ነው።
- የምን ሽንኩርት?
- ቀይ ሽንኩርት።
- እየቀለድሽ ነው?
- በፍጹም። ማኅበረሰቡ ከጦርነት ሳያገግም በኑሮ ውድነት ይሰቃያል። በየአካባቢው የብሔር ግጭት ተንሰራፍቷል። መጀመሪያ ይህንን ነው መፍታት።
- እና ወደብ አያስፈልገንም እያልሽ ነው?
- እላልኩም።
- እና ምን እያልሽ ነው?
- እያልኩ ያለሁት?
- እ…?
- አሁን የሚያስፈልገን ወደብ ሳይሆን ሌላ ነገር ነው፡፡
- ምን?
- አደብ!