Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበጎንደር ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች ለረሃብና ለበሽታ መጋለጣቸው ተገለጸ

በጎንደር ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች ለረሃብና ለበሽታ መጋለጣቸው ተገለጸ

ቀን:

በዳንኤል ንጉሤ

በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ለተፈናቃዮች  ምግብ ማድረስ ባለመቻሉ ለከፋ ረሃብና ለበሽታ እየተጋለጡ መሆናቸውን፣ የጎንደር ከተማ አስተዳደር የተፈናቃዮች አስተባባሪ አቶ መላኩ ገብሬ ለሪፖርተር ገለጹ።

‹‹በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት የከተማው መግቢያና መውጫ መንገዶች ዝግ ሆነዋል፤›› ያሉት አቶ መላኩ፣ የተለያዩ የዓለም አቀፍ ዕርዳታ ድርጅቶች፣ የፌዴራልም ሆነ የክልል የምግብ ዋስትና ተቋማት ለተፈናቃዮቹ ምንም ዓይነት ዕርዳታ በነፃነት ማቅረብ አልቻሉም ብለዋል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹የፌዴራል መንግሥት ከክልሉ መንግሥት ጋር ተነጋግሮ ከወረታ ወደ ጎንደር ቀበሮ ሜዳ መጠለያ 840 ኩንታል እህል እንደሚሠራጭና እንደሚሰጣቸው በደብዳቤ አረጋግጦልናል፤›› ብለው፣ ነገር ግን በጎንደር ከተማ በተለይ ‹‹ባዘዘው›› በሚባለው አካባቢ የሚገኘው ኮማንድ ፖስት፣ የጭነት ተሽከርከሪዎች ለግዳጅ ስለሚጠቀምባቸው  በርካታ ተፈናቃዮች ለረሃብ መዳረጋቸውን ገልጸዋል። 

ለክልሉ ምግብ ዋስትና፣ ለክልሉ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ እንዲሁም ተሽከርካሪዎቹን ለሚጠቀምባቸው አካል ማለትም በአካባቢው ለሚገኘው መከላከያ ችግሩን በተደጋጋሚ አሳውቀናል ያሉት አስተባባሪው፣ ሆኖም  እስካሁን ምንም ዓይነት ምላሽም ሆነ መፍትሔ እንዳልተሰጣቸው ጠቁመዋል፡፡

‹‹በጎንደር ከተማ ልደታ በተባለ አካባቢ የክልሉ እህል መጋዘን ውስጥ በቂ ስንዴ አለ፤›› ያሉት አቶ መላኩ፣ መንግሥት የማጓጓዝ ችግር ካጋጠመው ከኮማንድ ፖስቱ፣ እንዲሁም ከክልሉ መንግሥት ጋር በመነጋገር ከዚህ ሥፍራ ማስመጣት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

‹‹የተፈናቃዮቹን ችግር መፍታት አለብን ብለን ለክልሉ አስተዳደር፣ እንዲሁም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በደብዳቤ አሳውቀናል፤›› ያሉት አስተባባሪው፣ ሰዎች ለከፋ ረሃብ መጋለጣቸው ከቀጠለ ሕይወት ሊጠፋ ስለሚችል መንግሥት ችግሩን እንዲፈታላቸው አሳስበዋል።

‹‹ሰላሳ ሁለት ሰዎች በረሃብ ምክንያት ታመው ሆስፒታል ገብተዋል፤›› ያሉት አቶ መላኩ፣ ከተፈናቃዮቹም መካከል የስኳር፣ የደም ግፊት፣ እንዲሁም ኤችአይቪ ያለባቸው ሰዎች ምግብ ባለማግኘታቸው ከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ጎንደር ቀበሮ ሜዳ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በድንበር ዘለልና በአገር ውስጥ መፈናቀሎች ምክንያት ተፈናቃዮች እንዳሉ የገለጹት አቶ መላኩ፣ በተለይም ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ በትግራይ ክልል ጦርነት ሳቢያ በቦታው ይኖሩ የነበሩ 2,703 ዜጎች ጎንደር ከተማ እንደገቡ አስታውሰዋል፡፡ አስካሁን ድረስ በፌዴራል፣ በክልልና በከተማ አስተዳደሩ እየተረዱ መቆየታቸውንም ገልጸዋል።

በተያያዘም በሱዳን ጦርነት ምክንያት 5,100 ትውልደ ኢትዮጵያውያን  ጎንደር ከተማ እንደሚገኙ አክለዋል፡፡

‹‹እነዚህ ሰዎች  በጦርነት እንደ መፈናቀላቸው መጠን ወደ ቀዬአቸው መመለስ፣ ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀል፣ ካልተቻለም በሠፈራ ፕሮግራም ማደራጀት የመንግሥት ተግባር ነው፤›› ያሉት አቶ መላኩ፣ በካምፓላ ኮንቬንሽን መሠረት አንድ ሰው መጠለያ ጣቢያ ውስጥ መቆየት ያለበት ለስድስት ወራት ቢሆንም፣ በአገሪቱ አንፃራዊ ሰላም ባለመኖሩ ምክንያት ወደ ቦታቸው መመለስ  አልተቻለም ብለዋል።

‹‹የእነዚህን ዜጎች መብት ማስጠበቅ ያለበት መንግሥት ነው፤›› ያሉት አስተባባሪው፣ ከተፈናቃዮቹ መካከል ሕፃናት፣ አጥቢ እናቶችና አረጋውያንን ጨምሮ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ስለሚገኙ የሚመለከተው አካል መፍትሔ እንዲሰጥ አሳስበዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...