Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየአሜሪካዊ-አይሁዳውያን ‹‹ፍትሕ ለፍልስጤማውያን›› ውትወታ

የአሜሪካዊ-አይሁዳውያን ‹‹ፍትሕ ለፍልስጤማውያን›› ውትወታ

ቀን:

አሜሪካዊ-አይሁዳውያን ለፍልስጤማውያን ፍትሕ እንዲሰፍንና በአጠቃላይም በቀጣናው ሰላም እንዲመጣ ‹‹የተኩስ አቁም ስምምነት ይደረግ›› ሲሉ በአሜሪካ ተቃውሞ ሠልፍ የወጡት ባሳለፍነው ሳምንት ነው፡፡

በአሜሪካ አብዛኞቹ ግዛቶች የሚገኙ አሜሪካዊ አይሁዳውያን የሰላም ወትዋቾች (አክቲቪስቶች) እና የእነሱ ሐሳብ ደጋፊዎች ‹‹ጦርነቱ በእኛ ስም አሁን›› ሲሉም እስራኤል በጋዛ ንፁኃን ላይ እየወሰደች ያለችውን የአየር ድብደባ እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡

መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የ‹‹ጂዊሽ ቮይስ ፎር ፒስ›› የራቢኒካል (የአይሁዳውያን ሕግ ወይም አስተምህሮ) ምክር ቤት አባል ራቢ አሊሳ ዋይዝ ለሲኤንኤን እንዳሉት፣ በእያንዳንዱ ንጋት እስራኤል በጋዛ ንፁኃን ላይ እየወሰደች ያለውን ወታደራዊ ዕርምጃ ሲሰሙ ዓይናቸው በዕንባ ይሞላል፣ ልባቸውም ይደልቃል፡፡ ሃማስ በእስራኤል ላይ የወሰደውን ድንገተኛ ጥቃት ሲያስታውሱም ተመሳሳይ ሐዘንና ሰቀቀን ውስጥ ይገባሉ፡፡

የአሜሪካዊ-አይሁዳውያን ‹‹ፍትሕ ለፍልስጤማውያን›› ውትወታ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ይህን ስሜታቸውን አምቀው መቀመጥ ያልቻሉት ዋይዝ፣ የአሜሪካ-አይሁድ አባላትን ባቀፉት በ‹‹ጂዊሽ ቮይስ ፎር ፒስ›› እና በ‹‹ኢፍ ኖት ናው›› በካፒቶልሂል በተዘጋጀው የተቃውሞ መድረክ በመገኘት፣ የእስራኤልና ፍልስጤም ግጭት ሰላማዊ መፍትሔ እንዲያገኝ፣ አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲደረግና፣ በንፁህ ፍልስጤማውያን ላይ የሚደረግ ጭፍጨፋ እንዲቆም ወትውተዋል፡፡

አሜሪካ ለእስራኤል የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ እንድታቆም የጠየቁት አሜሪካዊ-አይሁዳውያን ወትዋቾች የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንና ሌሎች ባለሥልጣናት እስራኤል እየወሰደች ላለችው ወታደራዊ ዕርምጃ ልጓም እንድታበጅ እንዲያደርጉና በርካታ ንፁኃን ሰዎችን መግደል ሃማስ እየፈጸመ ላለው ጥቃት ምላሽ እንደማይሆን አሳስበዋል፡፡

የእስራኤል ከፍተኛ ባለሥልጣናት ወደ ዘር ማጥፋት ወንጀል የሚያመሩ ፀያፍ ንግግሮችን ከማድረግ እንዲቆጠቡ፣ የአይሁዶች ቅድመ አያቶች በሆሎከስት የገጠማቸው ዓይነት ጭፍጨፋ በሌሎች ላይ እንዲደርስ እንደማይፈልጉም  የ‹‹ኢፍ ኖት ናው›› የፖለቲካ ዳይሬክተር ኢቫ ቦርጋዋርት ገልጸዋል፡፡

በሺዎች የሚቆጠሩ አሜሪካ-አይሁዳውያንና አጋሮቻቸው ሰላም እንዲሰፍን የሚወተውቱ መፈክሮችን ይዘው ተቃውሞ ሲወጡ፣ 355 ያህል ወትዋቾች ታስረውም ነበር፡፡ ከእነዚህ አንዷ የነበሩት ዋይዝ፣ ከእስር ከተለቀቁ በኋላ የቅርብ ፍልስጤማዊ ጓደኛቸው ሙሉ ቤተሰብ እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ማለቃቸውን መስማታቸውንና የእነሱም ተቃውሞ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ሰከን እንዲል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ የአይሁድ ማኅበረሰብ በማንኛውም ሠልፍ ወቅት የሚጠቀሙበት ‹‹መቼም እንዳይደገም፣ ለማንም ቢሆን መቼም እንዳይደገም፤›› (ኔቬር አጌን፣ ኔቨር አጌን ፎር ኤኒዋን) የሚለውን መፈክር፣ አሜሪካዊ-አይሁዳውያን የሚያጎሉበት ጊዜ ነውም ብለዋል፡፡

ቦርጋዋርት፣ ጦርነት ማስቆም የሕይወት ዘመናቸው ትልቁ ፈተና እንደሆነ ገልጸው፣ እስራኤላውያን፣ አይሁዶችና ፍልስጤማውያን ፍትሕ አግኝተው በእኩልነት እንዲኖሩ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡

እስራኤል በጋዛ ውስጥ እየፈጸመች ያለው የአየር ጥቃት ይቆምና ፍትሕ ይሰፍን ዘንድ በአሜሪካ ለተቃውሞ የወጡ አሜሪካዊ-አይሁዳውያን፣ የእስራኤል ደጋፊ በሆኑ ቡድኖች ነቀፋ ተሰንዝሮባቸዋ፡፡

የአንቲዲፋሜሽን ሊግ ብሔራዊ ዳይሬክተር ጆናታን ግሪንብላት፣ ለተቃውሞ የወጡት አሜሪካዊ-አይሁዳውያን ሐሳባቸውን በነፃነት የመግለጽ መብት ቢኖራቸውም፣ ግልጸኝነት ይጎላቸዋል፣ እስራኤል ሳትሆን ሃማስ በጋዛ ለሚሞቱት ንፁኃን ተጠያቂ ነው ብለዋል፡፡ እስራኤልን የሚቃወሙት ፀረ ፂዮናዊ ስለሆኑም እንደሆነ አክለዋል፡፡

ዋይዝ ግን ይህን አይስማሙበትም፡፡ ‹‹እኔ አይሁዳዊ ነኝ፡፡ እስራኤል አይሁድ አይደለችም፡፡ እስራኤል አገር ነች፤›› ይላሉ፡፡ ፍልስጤማውያን ነፃ እንዲሆኑ፣ የሁሉም ደኅንነትና ነፃነት እንዲጠበቅ ጦርነትን ማቆም ወሳኝ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡

ሲኤን ኤን እንደሚለው፣ ሃማስ በእስራኤል ድንገተኛ ጥቃት ማድረጉን ተከትሎ  እስራኤል ባለፉት 17 ቀናት በጋዛ በፈጸመችው የአየር ድብደባ 4‚600 ፍልስጤማውያን ተገድለዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 2‚000 ሕፃናት እንደሆኑ ተገምቷል፡፡ 14 ሺሕ የተጎዱ ሲሆን፣ 1.4 ሚሊዮን ደግሞ ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡

በእስራኤል በኩል 1‚400 የተገደሉ ሲሆን፣ ከ200 በላይ በሃማስ መታገታቸው በእስራኤል ባለሥልጣናት ተነግሯል፡፡ 5‚431 እስራኤላውያንም ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ይህ ጦርነት ዋጋ እያስከፈለ ያለው ንፁኃንን መሆኑን የሰላም አቀንቃኞች እየገለጹ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...