በኢትዮጵያ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ አረጋውያን፣ ሕፃናትና እናቶች ጎዳና ወጥተው ምፅዋት ሲጠይቁ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ የኑሮ ውድነት እንዲሁም በአገሪቱ የሚስተዋው አጠቃላይ ችግር ጎዳና ወጥተው ምፅዋት የሚጠይቁ ወገኖች በርካታ እንዲሆኑ ምክንያት መሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ እነዚህን ምፅዋት የሚጠይቁ ወገኖች ከጎዳና ለማንሳት መንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እየሠሩ ቢሆንም፣ ችግሩ ግን አሁንም አልተፈታም፡፡ ችግሩን ለመፍታት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ በጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል በርቶሎሚዎስ በጎ አድራጎት ድርጅት ይገኝበታል፡፡ አቶ ገዛኸኝ ሲሳይ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ የድርጅቱን ሥራ በተመለከተ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በርቶሎሚዎስ የበጎ አድራጎት ድርጅት መቼ ተመሠረተ?
አቶ ገዛኸኝ፡- በርቶሎሚዎስ የበጎ አድራጎት ድርጅት የተፀነሰው በ2011 ዓ.ም. ሲሆን፣ ሕጋዊ ፈቃድ ያገኘው በ2014 ዓ.ም. ነው፡፡ ሕጋዊ ፈቃድ ካገኘን ቅርብ ዓመት ቢሆንም፣ ከዚያ በፊት ግን በርካታ ሥራዎችን መሥራት ችለናል፡፡ ድርጅቱ ለሕፃናትና ለአረጋውያን የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡ የምግብ አቅርቦት፣ አስቤዛ፣ አልባሳትንና ሌሎች ነገሮችን ለ150 አረጋውያንና ሕፃናት ድጋፍ ሲያደረግ ቆይቷል፡፡ በሌላ በኩል በሱስ የተጠመዱ ወጣቶች ከሱሳቸው እንዲያገግሙ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ይሠራል፡፡ በበጎ አድራጎቱ ሥር በሚገኙ አባላት ምክንያት በኪነ ጥበብ ዙሪያ የተለያዩ ሥልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል፡፡ በርቶሎሚዎስ የበጎ አድራጎት ድርጅት ቋሚ የገቢ ምንጭ ስለሌለው አሁን ላይ ለጊዜው የሚሰጠውን ድጋፍ አቋርጧል፡፡ ድርጅቱ ከዚህ በፊት ለአረጋውያንና ለሕፃናት ድጋፍ ያደረገው ስፖንሰር በመፈለግና የኪነ ጥበበ ሥራዎች በመሥራት በሚያገኘው ገቢ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ ከዚህ በፊት ከስፖንሰር የሚያገኘው ገቢ ሙሉ ለሙሉ መቋረጡ ሥራችን ላይ እንቅፋት ሆኖብናል፡፡ ተቋሙም አሮጌ ጫማዎችንና አልባሳትን ሰብስቦ የምሳ ፕሮራግራም በማዘጋጀት ለተቸገሩ ወገኖች የሰበሰበውን አልባሳትና ጫማ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ ቤት ለቤት በመሄድ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ ችሏል፡፡ ከዚህ ባለፈም ቸግሮናል ላሉ ወገኖች የቤት ኪራይ ወጪ፣ የአስቤዛና ሌሎች ድጋፎችንም ይሰጣል፡፡
ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ከተመሠረተ በኋላ በሥራችሁ ምን ዓይነት ችግር ገጥሟችኋል?
አቶ ገዛኸኝ፡- ድርጅቱ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ችግሮች ገጥሞታል፡፡ በተለይ አሮጌ ጫማና አልባሳት፣ እንዲሁም ትኬቶችን በምንሸጥበት ወቅት ወረዳዎች ላይ የሚገኙ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ሥራ እንዳንሠራ አድርገውናል፡፡ በሌላ በኩል እዚያው አካባቢ የሚገኙ ወረዳዎች ስፖንሰር የምንፈልግበትን የድጋፍ ወረቀት እንዲጽፉልን ስንጠይቅ ምላሻቸው ዕንቢታ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ከዚህ አካባቢ ከሚገኙ የበጎ ፈቃድ ወጣቶች ጋር ተጣልተን እስከመታሰር ደረጃ ደርሰን ነበር፡፡ ወደ በርካታ ተቋማት በመሄድ ስፖንሰር እንዲያደርጉን ጥያቄ ብናቀርብም፣ ተቀባይነትን አላገኘንም፡፡ ሌላው ደግሞ ድርጅቱ የራሱ ቢሮም ሆነ ቦታ ስለሌለው ሥራችን ላይ ጫና ፈጥሮብናል፡፡ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት መቀመጫውን በወጣት ማዕከል ውስጥ አድርጎ እየሠራ ቢሆንም፣ የተሻለ ሥራ ለመሥራት የቦታ ይዞታ እየፈለገ ይገኛል፡፡ በተለይም ከአንድም ሁለት ጊዜ የቦታ ይዞታ እንዲሰጠን አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ለመጠየቅ ስንሄድ ከበር መልሰውናል፡፡ ተቋሙ ሕጋዊ ፈቃድ ቢኖረውም፣ እስካሁን ግን የራሱ የሆነ ንብረት ስለሌለው መሥራት የሚጠበቅበትን ያህል ሳይሠራ ቀርቷል፡፡ ትልልቅ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በመሄድ ጥቃቅን የሚባሉ ድጋፎች እንዲያደርጉልን ብንጠይቅም አሻፈረኝ ብለውናል፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አቅማቸው ከፍተኛ ስለሆነ የቆዩ ኮምፒዩተሮችንና ሌሎች ድጋፎችን ቢያደርጉልን የተሻለ ሥራ መሥራት እንችል ነበር፡፡ ከየተቋማት ተርፈው የተመለሱ አልባሳትና አሮጌ ጫማዎች ለእኛ ተቋም እንዲሰጥ ጥያቄ ብናቀርብም፣ መልስ ልናገኝ አልቻልንም፡፡ በተለይ መንግሥት የቦታ ይዞታ ችግር ቢቀርፍልን በሥራችን ለውጥ ማምጣት እንችላለን፡፡
ሪፖርተር፡-መንግሥት ምን ዓይነት ድጋፍ አድርጎላችኋል?
አቶ ገዛኸኝ፡- መንግሥት እስካሁን ምንም ዓይነት ድጋፍ አላደረገልንም፡፡ ፈቃድ ካገኘን ጀምሮ ለሲቪል ማኅበረሰብ ኤጀንሲ የተሠሩ ሥራዎችን በየዓመቱ ሪፖርት እያደረግን እንገኛለን፡፡ ነገር ግን ለእያንዳንዱ በጎ አድራጎት ድርጅት በሲቪል ማኅበረሰብ ኤጀንሲ በኩል ከውጭ የሚመጣው ፈንድ አለ፡፡ እሱም ፈንድ ለእኛ ተቋም አንድም ጊዜ ተሰጥቶ ስለማያውቅ ሥራችን ላይ ችግር ፈጥሮብናል፡፡ በተለይ ፕሮፖዛል ነድፈን መንግሥት ቦታ እንዲሰጠን ብንጠይቅም፣ ከበር ስለመለሱን ሥራችንን በአግባቡ እንዳንሠራ አድርጎናል፡፡ ሌላው ደግሞ በአካባቢው የሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ ያለው የአሠራር ክፍተት ሥራችን ላይ ጫና ፈጥሮብናል፡፡ እነዚህንም ችግሮች ለማለፍ እንዲሁም ለድጋፍ የሚሆኑ ግብዓቶችን ለማግኘት ተቋሙ ሰፊ ሥራ የሚሠራ ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ ከሌሎች ተቋማት ጋር ቅንጅት ፈጥሮ እየሠራ ይገኛል፡፡ በሥራችሁ ምን ዓይነት ለውጥ አምጥታችኋል?
አቶ ገዛኸኝ፡- ተቋሙ የተለያዩ ወረዳዎች ጋር በመሄድ መረጃ በመሰብሰብ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ አረጋውያንም ሆኑ ሕፃናት ድጋፍ እንዲያገኙ እያደረገ ይገኛል፡፡ በዚህም ወረዳዎች የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ድርጅታችን ከዘ አርት ኢንተርቴይመንት ጋር በመሆን ጥቅምት 4 ቀን 2016 ዓ.ም. በሀገር ፍቅር ቴአትር የኪነ ጥበብ ሥራዎችን በማቅረብ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር አከናውኗል፡፡ ይህም የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በርካታ ሕፃናትና አረጋውያን ያሉባቸውን ችግሮች የሚቀርፍ ይሆናል፡፡ ወረዳዎቹ ላይ ከሚገኙ ጤና ጣቢያዎች ጋር በመሆን የኤችአይቪ ኤድስ ምርመራን ሰዎች እንዲያደርጉ ማድረግ ችለናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአባላዘር በሽታ ኮርስ መስጠት ችለናል፡፡ በክረምት በተቋሙ ሥር በሚገኙ አባላት ምክንያት በነፃ የኪነ ጥበብ ሥልጠና መስጠት ችለናል፡፡ በቀጣይም እነዚህን እንቅስቃሴዎች ከፍ በማድረግ የተሻለ ሥራ ለመሥራት አቅደናል፡፡
ሪፖርተር፡- በቀጣይ ምን ለመሥራት አስባችኋል?
አቶ ገዛኸኝ፡- ድርጅቱ በቀጣይ ቋሚ የሆነ የገቢ ምንጭ እንዲኖረው የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት ዕቅድ ይዟል፡፡ ለሕፃናትና ለአረጋውያንም በቋሚነት ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለመፍጠር ለመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት ፕሮፖዛል በማስገባት ገቢ የሚያገኙበት አማራጭ እንዲፈጠር እየሠራን ነው፡፡ በተለይ መንግሥት ቦታ እንዲሰጠን የምንወተውት ይሆናል፡፡ መንግሥትም ያሰብነውን ቦታ ከሰጠን አረጋውያንንና ሕፃናትን በቋሚነት ለመደገፍ ይረዳናል፡፡ አንድ ተቋምም ስፖንሰር የሚያደርገው ተቋሙ የሠራው ሥራ ምን ይመስላል? የሚለውን በማወቅ ስለሆነ የሚታይ ሥራ ለመሥራት ዕቅድ ይዘናል፡፡ በሌላ በኩል ተቋሙ የራሱ የሆነ የማገገሚያ ማዕከል በማቋቋም በጎዳና ተዳዳሪነት የሚኖሩ ሕፃናትን የሚታደግ ይሆናል፡፡ ዕቅዱን ዘንድሮ ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን የምንሠራ ይሆናል፡፡ በተለይ ሰዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ስንጠይቅ የኑሮ ውድነቱ ነው መሰለኝ ምላሻቸው ጥሩ የሚባል አይደለም፡፡ ነገር ግን እነዚህን ሁለ ችግሮች ለማለፍና ወጥ የሆነ ድጋፍ ለማድረግ ድርጅታችን ሰፊ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ይሆናል፡፡