Sunday, February 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መደበቂያ እንዳይጠፋ!

ከስታዲየም ወደ ቦሌ ልንጓዝ ነው። ከረጅም ሠልፍ ጥበቃ በኋላ የተገኘ አንድ አሮጌ ሚኒባስ ላይ ተሳፍረናል፡፡ ‹‹መጓዝ ወዲያ ማዶ መራቅ የትናየት አንድም ለመታወስ አንድም ለመረሳት፣ አንድም ለመወደድ አንድም ለመጠላት። ‹ሾፌር ሞተሩን አስነሳው እንጂ…›› ይላል እንደ ጩልሌ ዓይኖቹ እዚህም እዚያም እየቃበዙ ጋቢና የተቀመጠ ሾፌሩን ዕረፍት የሚነሳ ተሳፋሪ። ‹‹ሞት ይጥራህና ከተሠለፉት ውስጥ አንድ ሰባቱን ጠርተህ አስገባና እንሂድበት…›› ሾፌሩ ወያላው ላይ አንባረቀ። ወያላው ሞትም ሕይወትም ሳይጠሩት መሀል ላይ ነው መሰል፣ ‹‹አንተ ሰውዬ ዛሬ በግራ ጎንህ ነው መሰል የተነሳኸው፡፡ አጠገብህ የትራፊክ ፖሊስ ተገትሮ ትርፍ ጫን ስትለኝ አታፍርም እንዴ…›› ሲለው፣ ‹‹እንኳንስ ለማይሞላ የታክሲ ኑሮ ትርፍ መጫን ገና ምን አይተህ ቀይ ባህርንና ህንድ ውቅያኖስን እንዋኝባቸዋለን…›› ብሎ ሾፌሩ ያልታሰበ የጂኦ ፖለቲካ ወሬ ደንቀር ሲያደርግ ወያላው በዚያ ተናዳፊ መሳይ ምላሱ፣ ‹‹ለማንኛውም መንገድ ላይ እንጂ ከመነሻ ትርፍ ለመጫን እንደማይቻል በአክብሮት እየነገርኩህ፣ ቀይ ባህርና ህንድ ውቅያኖስ ላይ የምታሽከረክረውን ዘመናዊ ጀልባ ስትይዝ ያልከውን ጉዳይ በሚገባ እንነጋገርበታለን…›› እያለ ሲስቅ፣ ‹‹አንዳንዱ ሰው ያለቦታው ሲገኝ ግን አይገርምም? ምናለበት ሾፌርነትና ወያላነትን ትተው የፖለቲካ ተንታኝ ቢሆኑ እነዚህ ሰዎች?›› ይላል ቀጠን ረዘም ያለ መሀል ወንበር የተቀመጠ ወጣት። ያስብላል!

ጉዟችን ተጀምሯል። ‹‹እንዴት ነው በጠዋት አንድ ሁለት ጃንቦ ቸልሳችሁ ነው እንዴ ቀኑን የጀመራችሁት…›› ሲል አንድ ጎረምሳ ሾፌራችን ፊት ነስቶ ዝም እንደማስባል፣ ‹‹ጃንቦ ጄት እንዴት ያለ ነው?›› እያለ አዲስ ወግ ያስጀምራል። ‹‹ጃንቦ ጄት አታውቅም? ‹ኦ ማይ ጋድ› እውነትም የትምህርት ጥራት ወርዷል። መንግሥት ግን ምን እንደሚሠራ ይታወቀዋል?›› እያለች አንዷ ዘመናይ ማብራሪያ ስትጀምር ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠች ቆንጆ ወጣት፣ ‹‹የባሰ አታምጣ ስንለው አይሰማም እንዴ?›› ብላ ከጎኗ ወደ ተቀመጠው ጎልማሳ ፊቷን አዞረች። ‹‹ዌል ጃንቦ ጄት ምን መሰለሽ? ‹‹ጃንቦ… ጃንቦ…›› እያለ ጎልማሳው ሲወዛገብ፣ መጨረሻ ወንበር የተቀመጡ ወጣቶች ወያላውን ጠሩት። ወያላው ምን ፈልገው ነው በሚል ስሜት. ‹‹አቤት?›› ሲላቸው፣ ‹‹እስኪ ቀስ ብለህ አጣራ ሰውዬው ዕድሜውን ድራፍት ቤት ነው ወይስ ዩኒቨርሲቲ ነው የጨረሰው?›› አለ አንደኛው። ወያላው እንደተምታታበት ፊቱን አዞረባቸው። መሀላቸው የተሰየሙ አዛውንት ፈገግ ይላሉ። ሦስተኛው ረድፍ ላይ ጥቁር የለበሰች ወይዘሮ አርፎ አልቀመጥ ያላትን ብላቴና ልጇን እየገሰፀች፣ ‹‹ዘንድሮ ከድራፍት ቤትና ከዩኒቨርሲቲ መመረቅ ይነጣጠላሉ እንዴ?›› ብላ አጉተመተመች። ምን ታድርግ!

ወያላው ሒሳብ መቀበል ጀምሯል። ከጋቢና አንስቶ መጨረሻ ወንበር ወደ ተቀመጡት ወጣቶች እስኪደርስ ታክሲው ውስጥ ፀጥታ ሰፍሮ ነበር። ወያላውም ሒሳቡን ሰብስቦ ከጨረሰ በኋላ፣ ‹‹ለካ በደንብ እየሸቀልክ ነው በዘናጭ ልብስና ጫማ ያሸበረቅከው…›› ብሎ አንዱ ወያላውን ሲያሞጋግሰው፣ ‹‹እንዲህ ሽክ የሚለው እኮ በሰልቫጅ ነው፣ ዕድሜ ለቦንዳ እያለ ሲመርቅ ነው የሚውለው…›› እያለ ሾፌሩ ሲስቅ፣ ‹‹ገና ምን አይተህ ቀይ ባህርና ህንድ ውቅያኖስ ላይ የውኃ ታክሲ አገልግሎት መስጠት ስንጀምር፣ ከፓሪስና ከለንደን ዘመናዊ ብራንድ ሱቆች እየገዛን እንለብሳለን…›› ብሎ መለሰለት፡፡ የሾፌርና የወያላ ተሳፋሪዎችን ወደ ፖለቲካው ሠፈር የመጎተት አባዜ ያሳሰባቸው አንድ አዛውንት፣ ‹‹እንዴት ነው ነገሩ የተማረም ያልተማረም ፖለቲካውን እንደ ጭቃ እያቦካ ወዴት ነው መዳረሻችን የሚሆነው…›› እያሉ ዙሪያ ገባውን ሲቃኙ፣ ‹‹መዳረሻችን ተነገረን እኮ፣ ከቦሌ መልስ ወደ ቀይ ባህር…›› ብሎ ሾፌሩ ሲስቅ ሁላችንም ሳንወድ በግድ ሳቅን፡፡ ይሻላል!

‹‹ታክሲ ውስጥ የወደቀ ዕቃ ባለቤት እንደሌለው ተቆጥሮ ይወረሳል የሚል ማስታወሻ ተጽፎ ሊለጠፍልን ይገባል። አለበለዚያ እኮ ስናምናቸው የጣሉንን እያሰብን ጨርቃችንን ጥለን የምናብደው ታክሲ ውስጥ መሆኑ የማይቀር ነው…›› ይላል አንዱ በድንገት። ወዲያ ደግሞ ባለባርኔጣው፣ ‹‹ሥልጣን ብይዝ መጀመሪያ የማቋቁመው የምግብ ሚኒስቴር ነበር…›› እያለ ሌላው ሌላ ነገር አመጣ። ‹‹ምን ልታደርግበት?›› አለች ቆንጂት በመገረም እያየችው። ‹‹በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት በሚመጣ መቀንጨር አዕምሮአችን በትክክል ማሰብ ለማቆሙ አንዱ ማሳያ፣ በራሳችን ህሊና ማብሰልሰል ትተን የሚነገረንን ሁሉ የዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ መሰንቀር መውደዳችን ነው…›› ሲል ተሳፋሪዎች ተንጫጩበት። ‹‹ምነው ወንድሜ ምን አድርገንህ ነው ሁላችንንም አንድ ሙቀጫ ውስጥ ከተህ የምትወቅጠን?›› ብላ ወይዘሮዋ ስትቆጣ፣ ‹‹አዕምሮአችንን ማሠራት ብንችል ኖሮ ሌብነት፣ አድርባይነትና አስመሳይነት እየተጫወቱብን በድህነታችን ማንም እየቀለደብን አንኖርም ነበር፡፡ አሁንም እንደምታይው ምግብ የለም እኮ? ምግብ የሌለበት ደሃ አገር አጉል ሲንጠራራ ግርም ይላል…›› እያላት ባርኔጣውን አስተካከለ፡፡ ጉድ እኮ ነው!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። አዛውንቱ በአንዱ ጥግ ከአንዱ ጋር ያወጋሉ። ወጣቶቹ ልብ ብለው ያደምጣሉ። ‹‹አንድ ሰውዬ በግ ሊገዛ ገበያ ወጣ…›› ያቋርጣቸዋል ባርኔጣ የደፋው ወጣት። ‹‹መቼም በዛሬ ገበያ ባልሆነ?›› ሲላቸው፣ ‹‹ቆይ ትደርስበታለህ፣ ምናለበት ለነገር ከምትቸኩሉ ጨዋታ ብታስጨርሱ?›› አዛውንቱ ወሬያቸውን ስላቁዋረጡዋቸው ደህና እንዳልተግባቡዋቸው  ወጣቶቹን ማማረር ጀመሩ። አጠገቤ የተቀመጠ ላጤ መሳይ፣ ‹‹መጨረስ ምንድነው? ያስጨረሰንስ ማን ነው? የጨረሰን እንጂ የጨረሰልንስ አለ እንዴ?›› ሲለኝ ለካ ሰምተውታል። ‹‹እሱንስ ስታጨርሰኝ ታገኘው መስሎኝ? የልጅ ነገር አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ አሉ…›› ተረቱ አዛውንቱ። ‹‹ተቀይሯል አባት፣ ለዛሬዎቹ አይሠራም…›› አለቻቸው ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመችው ሴት። ‹‹እኮ ምን ተተረተባቸው?›› አዛውንቱ ሳያስቡት መስመራቸውን ሳቱ። ‹‹እነ ማን ላይ?›› ወይዘሮዋ ጠየቀች። ‹‹ስለእነ ማን ነው የምናወራው? ስለዛሬ ልጆች ነዋ…›› ቁጣ ቁጣ አላቸው። ወይዘሮዋ፣ ‹‹ዛሬ ደግሞ ምን ልጅ አለ? ገና ሳይወለዱ እየሸበቱ…›› ማባዘት ወደ ፈለገችው ነገር ስትንደረደር አዛውንቱ፣ ‹‹በይ ተይው…›› ብለው ወደ በግ ገበያቸው ተመለሱ። ምን ያድርጉ!

‹‹እና ምን እያልኳችሁ ነበር? አዎ ሰውየው በግ ሊገዛ ገበያ ሄደ። አንዱን የሰባ ያለተለተ በግ ዓይቶ ወደ ባለበጉ ጠጋ አለና ‹ስንት ነው?› አለው። ‹60 ብር› ሲለው ነጋዴው፣ ‹60 ብር? በ20 ብር አህያ አልገዛም እንዴ?› እያለ ተነጫነጨበት። ታዲያ በግ ነጋዴው ምን አለው መሰላችሁ? ‹የሚጣፍጥህን አንተ ታውቃለህ›…›› ብለው ሲያሳርጉ ጥልቅ ዝምታ ሰፈነ። ወያላው አንገቱን ደፍቶ በቀስታ ሲስቅ ወጣቶቹ አዛውንቱ ያመጡት ምሳሌ አንድምታ ሰፍቶባቸው ያወጣሉ፣ ያወርዳሉ። ወይዘሮዋ አንዴ ያንን ተራቢ ጎልማሳ አንዴ ወጣቶቹን እያየች ታገነግናለች። ‹‹እኔ እኮ እዚህ አገር የማይገባኝ ነገር፣ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ትልቁ የመንግሥት ቢሮ ድረስ በሥርዓት ተነጋግሮ ለመግባባት ሙከራ ማድረግ የከበደበት ሚስጥር ነው…›› ብሎ ኮስታራ መሳይ ጎልማሳ መናገር ሲጀምር፣ ‹‹ዌል እንግዲህ… የትምህርት ደረጃህና ዕውቀትህ ሳይመጣጠን ሲቀር የሚያጋጥም ችግር ነው፡፡ ‹ኢማጂን ያልተማረ የበዛበት አገር ውስጥ ለመግባባት ስትሞክር የሚጠፋው ጊዜና ‹ኢነርጂ›..›› ብላ ያቺ ዘመናይ መልስ ስትሰጥ፣ ‹‹ድንቄም ትምህርት፣ ድንቄም ዕውቀት… ዕድሜ ለማትሪክ አየነው እኮ በአካፋ እየተዛቀ ሲታደል የነበረው ዲግሪ ‹ፌክ› መሆኑን…›› ብላ ወይዘሮዋ ስትናገር ክው አልን፡፡ ያስደነግጣል!

መውረጃችን ደርሶ ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ብሎ በሩን ሲከፍተው አዛውንቱ ወደ ወጣቶቹ ዞረው፣ ‹‹የዛሬን አያድርገውና ይህች አገር ስንት ባለቅኔ፣ ስንት ነገር ፈቺ፣ ተፈጥሮን መርማሪ እንዳላመጠች የእኔ ትንሽዬ ምሳሌ ቋጥኝ ትሁንባችሁ?›› ብለው እያዘኑ ለመውረድ ከወንበራቸው ተነሱ። ‹‹በአንድ በኩል አልፈርድባችሁም፡፡ ጥፋቱ የእናንተ ሳይሆን የእኛ ትልቅ ተብዬዎች ነው፡፡ ገና ከመሠረቱ የትምህርቱን ነገር አጥብቀን ብንይዘው ኖሮ እናንተም ፈተና በመጣ ቁጥር አትሳቀቁም ነበር፡፡ እኛም በሠራነው ሥራ እያፈርን መደበቂያ አናጣም ነበር፡፡ እርግጥ ነው ይህ የአገር ችግር የማያሳስባቸው፣ አሳስቦናል ካሉም የእንጀራ መብያ የሆነላቸው ግን ደንታቸውም አይመስለኝም፡፡ ለማንኛውም ለሁሉም ነገር ቅደም ተከተሉን እያስተካከልን አብረን ለመሥራት ፈቃደኛነት ብናሳይ፣ ይህ ሁሉ የመከራ ዶፍ አገራችን ላይ አይዘንብም ነበር…›› እያሉ ወርደው ሲሰናበቱን፣ አሰስ ገሰሱን ከመስማት እንዲህ ዓይነቱን በዕድሜ የታሸ ምርጥ አስተያየት መርጦ የመስማት ስሜት ሁላችንም ውስጥ የተጋባ ይመስል ነበር፡፡ በኃፍረት መደበቂያ ላለማጣት ሲባል ይህ ስሜት ሁሉም ዘንድ ቢጋባ መልካም ነበር፡፡ መልካም ጉዞ!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት