Sunday, February 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በየሳምንቱ የሚያዘው የኮንትሮባንድ ምርት የመጨረሻ አድራሻም ሊታወቅ ይገባል!

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በእጅጉ እየጎዱ ካሉ ሕገወጥ ድርጊቶች መካከል አንዱ ኮንትሮባንድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ልካ ከምታገኛቸው የውጭ ምንዛሪ ይልቅ፣ በሦስትና በአራት እጥፍ የሚበልጥ ገቢ ሊገኝበት የሚችለው የወጪ ንግድ ምርት በኮንትሮባንድ ይወጣል ይባላል፡፡ 

አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቅሱት፣ ኢትዮጵያ በኮንትሮባንድ በዓመት እስከ 20 ቢሊዮን ብር የሚገመት የውጭ ምንዛሪ ታጣለች፡፡ ኮንትሮባንድ ምን ያህል ሥር እንደሰደደ ለማሳየት የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን በተከታታይ የሚያወጧቸው መረጃዎችም ይህንኑ ያመለከታል፡፡

ለምሳሌ በ2015 በጀት ዓመት ብቻ ከ11.6 ቢሊዮን ብር በላይ የገቢና የወጪ ኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ገልጿል፡፡ ከዚህ መረጃ ጎን ለጎንም በቅንጅት በተሠራ ቁጥጥር አገር ልታጣ የነበረውን ከ84 ቢሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉንም ያመለክታል፡፡ ከበጀት ዓመቱ መጠናቀቅ በኋላ በየሳምንቱ በአማካይ ከሩብ ቢሊዮን ብር በላይ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ስለመያዛቸው የእነዚሁ ተቋማት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ 

ይህ ኮንትሮባንድ በወጪ ንግድ ገቢ ላይ የሚያሳርፈው ተፅዕኖን በትንሹ ሊያመላክት ይችላል፡፡ በሕጋዊ መንገድ ለዓለም ገበያ መቅረብ ሲገባቸው፣ በሁሉም የአገሪቱ ጠረፎች በሕገወጥ መንገድ የሚሻገሩት ምርቶቻችን የአገሪቱን የኢኮኖሚ ስብራት አብሰውታል፡፡ ወርቅ፣ ቡና፣ የቀንድ ከብት፣ ጫት፣ የቅባት እህሎች፣ መዋቢያዎች፣ ነዳጅ፣ የከበሩ ማዕድናት ሌሎች የወጪ ንግድ ምርቶች፣ ሌሎች የወጪ ንግድ ምርቶች በሕገወጥ መንገድ እንደ ልብ ሲሻገሩ ቆይተዋል፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ድርጊቱ እንደተባባሰ ይነገራል፡፡ መረጃዎችም ይህንኑ ያሳያሉ፡፡ የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ ገቢ እዚያው ባለበት እንዲራመድ አድርጎታል፡፡ አሳዛኙ ነገር ይህ ችግር እየባሰ መምጣቱ ነው፡፡ 

ለችግሩ መባባስ ድንበር ተሻግረው የሚወጡ ምርቶች ‹‹የማርያም መንገድ›› የተበጀላቸው እስከመምሰል ድረስ መለቀቃቸው ነው በቀዳሚነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡

 ይህ ደግሞ የችግሩን አሳሳቢነትና ጉዳት ተገንዝቦ ወደ ውጭ የሚወጡ የኢትዮጵያ ሀብቶች ላይ ቁጥጥሩ እጅግ የላላ መሆኑ ሊያመላክት ይችላል፡፡ ምክንያቱም ሕግ አስከባሪዎች ወይም ጉምሩክና ገቢዎቸ በኮንትሮባንድ ወደ ውጭ ሲወጣ ተያዘ የሚባለው የወጪ ንግድ ምርት ዜና አንሰማም፡፡ ከኮንትሮባንድ ቁጥጥር ሥራ ጋር በተያያዘ ደጋግመን የምንሰማው ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ስለመያዛቸው ነው፡፡ 

ስለዚህ በሕገወጥ መንገድ የሚወጡ የወጪ ንግድ ምርቶቻችን በገፍ እየወጡ ከሆነ፣ ቢያንስ እንደገቢ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ቁጥጥር የማይደረግባቸው ለምንድነው? የሚለው ጉዳይ በደንብ መፈተሽ አለበት፡፡ 

ከዚህ ባሻገር ግን በአሁኑ ወቅት በእጅጉ የተንሰራፋና መጠኑ እየጨመረ ያለው ከውጭ ወደ አገር ውስጥ በሕገወጥ መንገድ የሚገቡ ምርቶች ከኅብረተሰቡ ደኅንነት አንፃር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳቸው ብዙ ሊያነጋግረን ይገባል፡፡ ከጥቂት ወራት ወዲህ በተከታታይ ከተለቀቁ መረጃዎች መገንዘብ እንደሚቻለው በኮንትሮባንድ የሚገቡ ዕቃዎች መውጣታቸውን ነው፡፡ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ ግምታቸው ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ የሆኑ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር በተከታታይ ካወጣቸው መረጃዎች መመልከት ይቻላል፡፡ 

እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን ተያዙ ከተባለበት የኮንትሮባንክድ ዕቃዎች ውጪ፣ ሾልከው የሚገቡትና ገበያ ውስጥ የሚቸበቸቡበት ተያዙ ከተባሉት በእጅጉ የሚበዙ መሆናቸውን ነው፡፡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች አደገኝነት በአጠቃላይ የአገር ኢኮኖሚውን ከመጉዷት ባለፈ፣ እነዚህ ዕቃዎች ደረጃቸውና ትክክለኛነታቸው የማይታወቅ በመሆኑ ከሸማች ላይ የሚያሳርፉት ጉዳት እግጅ አደገኛ መሆኑ አይቀርም፡፡ 

በተለይ በኮንትሮባንድ የሚገቡ ምግብ ነክ ምርቶችና መድኃኒቶች ስንቶችን ጤና እያወኩና ምናልባትም ለስንቶች ለሕይወት መጥፋት ምክንያት እንደሆኑ ቤት ይቁጠረው፡፡ ሾልከው የሚገቡ በኮንትሮባንድ የሚገቡ መድኃኒቶችና የታሸጉ ምግቦች ለሸማቹ የሚቀርቡት በሕጋዊ መደብሮች ጭምር በመሆኑ፣ ሸማቹ በኮንትሮባንድ ይግባ፣ አይግባ የሚያውቅበት መንገድ ስለሌለ በእምነት የሚጠቀምባቸው ናቸው፡፡ ይህ የሚያሳየን ጉዳታቸው የአገር ኢኮኖሚንና ሕጋዊ የግብይት ሒደትን ከማወክ ባለፈ፣ ለሰው ሕይወት ጠንቅ መሆናቸውን ነው፡፡  

ትልቁ ችግርም በየአቅጣጫው ሾልከው የሚገቡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ያለ ችግር ሕጋዊ የንግድ ፈቃድ ባላቸው መደብር ሼልፎች ላይ የሚደረደሩ በመሆኑ፣ ሸማቹ ትክክለኛ ምርት ነው ብሎ የሚገዛባቸው ምርቶች በሥውር እየገደሉት ነው፡፡ ብዙዎችን ኮንትሮባንድ ምርቶች ደረጃቸውን የጠበቁ እንደማይሆኑ ይታመናል፡፡ ቢሆኑ እንኳን የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፉ ምርቶች በኮንትሮባንድ የሚገቡበት ዕድል የሰፋ ስለሆነ፣ በየትኛውም መንገድ አደገኝነታቸው ጎልቶ ይታያል፡፡ እነዚህ ምርቶች የሚጓጓዙትም በሕገወጥ መንገድ በመሆኑ፣ በየቦታው የሚፈራረቅባቸው የአየር ፀባይ በራሱ አገልግሎታቸውን የሚያጓድል ነው፡፡ 

የመዋቢያ ዕቃዎች ተብለው ለገበያ የሚቀርቡ አንዳንድ ምርቶች ሳይቀሩ፣ በኮንትሮባንድ ከሚገቡ ተመሳሳይ ምርቶች ጋር ተደባልቀው የሚሸጡበት አገር ላይ ነንና ብዙዎች እየተጎዱበት መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ በኮንትሮባንድ የሚገቡ ምርቶች በየብስ ጠረፍ ሰብረው የሚገቡ ብቻ ያለመሆናቸውም ልብ ይሏል፡፡ 

በአየር ተጓጉዘው የሚገቡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ሌላ ራስ ምታት እየሆነ መምጣቱ ይታመናል፡፡ ኮንትሮባንድን የሚቆጣጠሩ አካላት በአየር ትራንስፖርት የሚገባ ኮንትሮባንድ አሳሳቢ ስለመሆኑ እየገለጹ ነው፡፡ በቅርቡ በተደረገ የጋራ ምክክር ላይ ‹‹በየብስ ከሚደረገው የኮንትሮባንድ ዝውውር በተጨማሪ በአየር መንገድ በኩል የሚከናወነው የኮንትሮባንድ ዝውውር ችግሩን የበለጠ አሳሳቢና ውስብሰብ አድርጎታል፤›› መባሉ በአስረጅነት ይቀርባል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም የአየር ላይ የኮንትሮባንድ ንግዱ ስለመጧጧፉ በቂ መረጃ የሚሆነው 2015 በጀት ዓመት በኮንትሮባንድ ከተያዙ የገቢና የወጪ ዕቃዎች ውስጥ 2.8 ቢሊዮን ብር የሚሆነው በኤርፖርት ጉምሩክ የተያዘ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ኮንትሮባንድ መግቢያ ቀዳዳዎች እየሰፉ ስለመሆኑ ጠቋሚ ነው፡፡ መረጃው ሕገወጥ ተግባራት ምን ያህል እንደተንሠራፉ ጭምር የሚነግር ነው፡፡ 

በሌላ በኩል ደግሞ ተያዙ በሚባሉ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ‹‹በቁጥጥር ሥር›› ከዋሉ በኋላ፣ ‹‹ምን ይደረጋሉ?›› የሚለው ጥያቄ ብዙ የሚያነጋግር መሆኑ አልቀረም፡፡ በቢሊዮን ብር የሚገመቱ ምርቶች ውስጥ ምን ያህሉ ትክክለኛ ምርቶች ናቸው የሚለው ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በገበያ ውስጥ ቢገቡ ለሸማቹና ለተገልጋዩ አደገኛ ናቸው የተባሉ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ሲያዙ በአግባቡ መወገዳቸው ካልታወቀ፣ መልሰው ወደ ገበያ ያለመግባታቸው እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል?፡፡ 

በቁጥጥር ሥር የዋለ አደገኛ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በአንዳንድ ‹‹ሕግ አስከባሪዎች›› ተባባሪነት አምልጠው ከኅብረተሰቡ ላለመቀላቀላቸውስ ማረጋገጫው ምንድነው?  

በኮንትሮባንድ የሚገቡና የሚወጡ ምርቶች መጠን መጨመሩ ራሱ አደጋ ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ብሎ መፍትሔ ማፈላለግንም ይጠይቃል፡፡ ለችግሩ መባባስ ብዙ ምክንያቶች ሊደረደሩ ቢችሉም፣ ሕግ እንዲያስከብሩ ኃላፊነት የተሰጣቸው አንዳንድ ብልሹ ግለሰቦች የሚያደርጉት ትበብር መኖሩ ግን የሚካድ አይደለም፡፡ እንዳላዩ ሆነው የሕገወጥ ሥራው ተባባሪ የሆኑም አሉ፡፡ ለማንኛውም እየተያዙ ናቸው የሚባሉ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ብዛት የተሻለ ቁጥጥር እየተተገበረ መሆኑን ቢያመለክትም፣  በኮንትሮባንድ የተያዙ ምርቶች ሕገወጥ ከሆኑ የኮንትሮባንድ ዕቃ ተያዙ ከሚለው ዜና ጎን ለጎንም ስለአወጋገዳቸው መረጃ ሊሰጥ ይገባል፡፡ 

ምክንያቱም ሕገወጥ የተባለውን ምርት መልሶ ወደ ገበያ ለመላክ የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው ግለሰቦች ስለማይጠፋ ነው፡፡ ሕግ አስከበርን ተብሎ በሌላ መንገድ ሕገወጥ መንገድ መከፈት ስለሌለበት በዚህን ያህል ደረጃ የተያዘ ኮንትሮባንድ የመጨረሻ አድራሻውም ሊታወቅ ይገባል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት