Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከ300 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሚሰቃዩበት ድባቴ

ከ300 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሚሰቃዩበት ድባቴ

ቀን:

ድብርት ወይም ድባቴ የአዕምሮ በሽታ ሲሆን፣ በስሜት መረበሽና ለነገሮች ፍላጎት በማጣት የሚፈጠር መሆኑን የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

የመንፈስ ጭንቀት የተለመደና ከባድ ሕክምና የሚያስፈልገው ሕመም ሲሆን፣ ሰዎች በሚሰማቸው ስሜት፣ በአስተሳሰብ እንዲሁም በድርጊታቸው አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ይነገራል፡፡

ሰዎችም በአንድ ወቅት በወደዷቸው እንቅስቃሴዎች ላይ ፍላጎት ማጣት ሲታይባቸውና የሐዘን ስሜት ውስጥ ሲዋጡ የችግሩ ሰላባ እንደሚሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ድብርት ለተለያዩ ስሜታዊና አካላዊ ችግር ሊዳርግ እንደሚችል የሚነገር ሲሆን፣ ሕመሙ ያለባቸው ሰዎች በሥራ ቦታ እንዲሁም በቤት ውስጥ የመሥራት ችሎታቸው ይቀንሳል፡፡

ድብርት ከተለመደው የስሜት መለዋወጥ ለአጭር ጊዜ ለሚቆይ ስሜታዊ ምላሾችና በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ለሚፈጠሩ ተግዳሮቶች ምክንያት መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ይገልጻል፡፡

በተለይም ችግሩ በተደጋጋሚ በሚከሰትበት ጊዜ መካከለኛ ወይም ከባድ የጤና ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህም የተጎዳ ሰው በከፍተኛ ሁኔታ እንዲሰቃይና በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት እንዲሁም በቤተሰብ ውስጥ በደንብ እንዳይሠራ ሊዳረግ የሚችልበት አጋጣሚም በጣም ሰፊ እንደሆነ ይታመናል፡፡

አማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተመላላሽ ሕክምና ክፍል ኃላፊና የሥነ አዕምሮ ፕሮፌሽናል ስፔሻሊስት አቶ ሳሙኤል ቶሎሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ደረጃ ተዘጋጅቶላቸው በባለሙያ የሚለዩ ከ300 በላይ የአዕምሮ በሽታዎች አሉ፡፡

ከእነዚህ በሽታዎች ውስጥ አንዱ የድባቴ እንደሚጠቀስ የተናገሩት ኃላፊው፣ በበሽታው በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ተጠቂ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የድባቴ በሽታ ሕፃናትን፣ ወጣቶችን፣ አዋቂዎችን፣ እንዲሁም አረጋውያንን የሚያጠቃ ሲሆን፣ የዚህን በሽታ ሳይንሱ እንደ መነሻ የሚያስቀምጠው ‹‹ባዮ ሳይኮ ሶሻል ፖፑሌሽን›› ውስጥ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሠረት በተለምዶ የአዕምሮ ተብለው የሚጠሩ ሥነ ልቦናዊ፣ ማኅበራዊና አዕምሯዊ ምክንያት እንዳለው ገልጸው፣ አንድ ሰው ተደጋጋሚ የማዘን ስሜት ሲሰማውና ለተከታታይ ጊዜያት ሲጨነቅ የድባቴ በሽታ ተጠቂ እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡

አንድ ሰው በየሆነ ነገር ተበሳጭቶም ሆነ አዝኖ ደብሮኛል ወይም ከፍቶኛል ሲል ይህንን ብቻ በማሰብ የድባቴ በሽታ ተይዟል ማለት እንደማይቻልና ቢያንስ ለሁለት ወር ያህል ተደጋጋሚ ዓይነት ስሜት ሲታይበት የዚህ ችግር ሰላባ መሆኑን ማወቅ እንደሚቻል ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡  

በዓለም ላይ ከ300 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በድባቴ በሽታ ተጠቂ መሆናቸውን፣ በየዓመቱም ከ700 ሺሕ በላይ ሰዎች ራሳቸውን እንደሚያጠፉ አስታውሰዋል፡፡፡

በተለይ አንድ ሰው ከዚህ በፊት ያስደስተው የነበረው ነገር ሳያስደስተው ሲቀር፣ ለሁለት ሳምንት ያህል የምግብ ፍላጎቱ ሲጠፋ እንዲሁም የስሜት መለዋወጦች ሲታይበት ድባቴ በሽታ ምልክቶች እንዳሉበት ያሳያል ብለዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ የሥነ አዕምሮ ሕክምና በብዙ ተቋማት እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም በዚህ ችግር ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በፈለጉት የሕክምና ተቋማት በመሄድ አገልግሎቱን የሚያገኙበት ሁኔታ ሰፊ እንዳደረገው፣ ኃላፊው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየተከሰተ ባለው ግጭትም ሆነ ተከስቶ በነበረበት ወቅት ምክንያት በርካታ ሰዎች የሥነ አዕምሮ እንዲሁም የድባቴ በሽታ ተጠቂ መሆናቸውን የተናገሩት ኃላፊው፣ እነዚህ ሰዎች የሕክምና አገልግሎት በፍጥነት ካላገኙ ለተለያዩ በሽዎች ተጋላጭ እንደሚሆኑ አብራርተዋል፡፡

አብዛኛው ሰዎች ድካም ሲሰማቸው፣ እንቅልፍ ሲያጡ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በሰውነታቸው ላይ ሲፈጠር ፍርኃት እንደሚያድርባቸውና ችግሩም የአዕምሮ በሽታ ነው ብለው እንደሚወስዱት አስረድተዋል፡፡

በአማኑኤል ሆስፒታል ውስጥ የተለያዩ የአዕምሮ በሽታ ተጠቂ ሰዎች የሕክምና አገልግሎት እያገኙ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ከዚህ በፊት ከተለያዩ ክልሎች መጥተው የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙ ሰዎች በሰላም መደፍረስ ምክንያት ቁጥራቸው ሊቀንስ መቻሉን አስታውሰዋል፡፡

በሆስፒታሉ ከ60 ሺሕ በላይ የተለያዩ የአዕምሮ በሽታ ተጠቂ የሆኑ ሰዎች የሕክምና አገልግሎት እያገኙ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ግን የድባቴ በሽታ ተጠቂ እንደሆኑ አክለው ገልጸዋል፡፡

በተለይ በሆስፒታሉ ለአንድ ሰው የአዕምሮ ሕክምና ሲሰጥ ረዥም ጊዜ እንደሚፈጅ፣ ይህንንም ለማድረግ አንድ ታማሚ በወር ውስጥ በአማካይ 600 ብር የሚከፍል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህ መሠረት የጤና መድኅንና ከጤና ጣቢያ ሪፈራል አጽፈው ለመጡ ሰዎች የሕክምና አገልግሎቱን በነፃ እንደሚያገኙ ገልጸው፣ ሕክምናውን በተመላላሽም ሆነ እዚያው በተቋሙ ውስጥ አልጋ በመያዝ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

በድባቴ የተያዘ ሰው ሙሉ ለሙሉ ከበሽታው እንዲላቀቅ ቢያንስ አንድ ዓመት ሊፈጅ እንደሚችል፣ ይህንን ለማድረግ የግል ሆስፒታሎች ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቁና በርካታ ሰዎችም በዚህ ችግር ውስጥ ማለፋቸውን አብራርተዋል፡፡

የሥነ አዕምሮ ሕክምና መድኃኒቶች የተለያዩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶች ርካሽ የሚባሉ እንደሆኑና በብዛትም ከውጭ አገር የሚመጣው መድኃኒት ተመራጭ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል በተደጋጋሚ ጊዜ ራሳቸውን ለማጥፋት የሚሞክሩ ሰዎች ወደ ተቋሙ መጥተው ሕክምናውን ለማግኘት ቢፈልጉ፣ የአገልግሎትና ሌሎች ወጪዎች ተደማምረው በወር ከፍተኛ ወጪ ሊያወጡ እንደሚችሉ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

አብዛኛውን ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ ታካሚዎች ለሕክምና የሚያወጡት ወጪ እንደሚቸገሩ ጠቀሰው፣ በዚህም የተነሳ አብዛኛው የአዕምሮ ሕመም ተጠቂ ሰዎች ወደ ሕክምና ተቋማት ሄደው አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡

በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የሥነ አዕምሮ በሽታን የሚከታተሉ ባለሙያዎች እጥረት መኖሩ ችግሩን እንዳባባሰው ገልጸው፣ በአጠቃይ የሕክምና አገልግሎቱ ይስፋፋ እንጂ በሚፈለገው ልክ እየተሰጠ አለመሆኑን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡   

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው፣ በዓለም ላይ 280 ሚሊዮን ሰዎች የድብርት (የድባቴ) ሕመም አለባችው፡፡ በዚህም በሽታ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች የበሽታው ተጠቂ ናቸው፡፡ ሕመሙ ሰዎች ሳይጠነቀቁ ቀርተው የሚይዝ በሽታ ባይሆንም፣ ብዙውን ጊዜ በአፍሪካ አገሮች ሕመሙን የመደበቅ ሁኔታ እንደሚታይ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

የመንፈስ ጭንቀት በዓለም ላይ የተለመደ በሽታ ሲሆን፣ ከጠቅላላ ሕዝብ 3.8 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች የሚጠቁ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በዓለም ዙሪያ በድብርት በሽታ ከሚጠቁ ሰዎች መካከል አምስት በመቶ በአዋቂዎችና 5.7 በመቶ ከ60 ዓመት በላይ ዕድሜ ባላቸው ሰዎች ላይ ይከሰታል፡፡

እንደ ድርጅቱ መረጃ፣ በዓለም ዙሪያ ከአራት ሰዎች አንዱ በአዕምሮ ጤና መታወክ ይሰቃያል፡፡ ነገር ግን 60 በመቶ ተጠቂዎች ሕመማቸውን በመደበቃቸው ምክንያት የሕክምና ዕርዳታ አያገኙም፡፡ በተለይ በየዓመቱ ከ700 ሺሕ በላይ ሰዎች ራሳቸውን የሚያጠፉ ሲሆን፣ ራስን ማጥፋት ከ15 እስከ 29 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚስተዋልና አራተኛው የሞት መንስዔ ናቸው፡፡

 የተለያዩ የስሜት መረበሽ ዓይነቶች እንዳሉ የሚገጸው ድርጅቱ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ የድብርት በሽታ በዓለም ላይ በ25 በመቶ እንደጨመረ ጠቁሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...