Thursday, December 7, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በሰላምና በምግብ ዕጦት ለሚፈተኑ ወገኖች መፍትሔ ይፈለግ!

ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የወቅቱ ከባዱ ችግር የሰላምና የምግብ ዕጦት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ዜጎች ሰላም አጥተው በየቦታው በነፃነት መንቀሳቀስም ሆነ መሥራት ሲቸግራቸው በስፋት ይስተዋላል፡፡ በትግራይ ክልል ውስጥ ተጀምሮ ለሁለት ዓመታት ያህል የዘለቀው ጦርነት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ቢገታም፣ በትግራይ ብቻ ሳይሆን በአማራና በአፋር ክልሎች ላይ ያደረሰው ዕልቂትና ውድመት አይዘነጋም፡፡ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት አንፃራዊ ሰላም ሊሰፍን ነው ተብሎ በተስፋ ሲጠበቅ፣ በአማራ ክልል ሁሉም አካባቢዎች የተጀመረው ግጭት መቋጫ አጥቶ የንፁኃን ሕይወት እየተቀጠፈ የአገር ሀብት እየወደመ ነው፡፡ በኦሮሚያና በሌሎች አካባቢዎችም በታጣቂዎች በሚፈጸሙ ጥቃቶች ሳቢያ የዜጎች ሕይወት ለአደጋ እንደተጋለጠ ነው፡፡ ሰላም በመጥፋቱ ምክንያት ብቻ የግብርና ምርቶችን ከቦታ ወደ ቦታ ማንቀሳቀስ ከማስቸገሩም በላይ፣ በሚፈለገው መጠን ማምረት ባለመቻሉ የምግብ ዋጋ ከዜጎች አቅም በላይ እየሆነ ነው፡፡ እንደ ጤፍና ጥራጥሬ ምርቶችና ሌሎች የምግብ ግብዓቶች ዋጋ ንረት በየቀኑ እያሻቀበ ኑሮ ከአቅም በላይ እየከበደ ነው፡፡

ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በማስቆም ሰላም ማስፈን ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር መሆን አለበት፡፡ እንደ ሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት ወደ ፕሪቶሪያ ወይም ሌላ ቦታ የሚወስዱ የውጭ ገላጋዮችን ከመፈለግ ይልቅ፣ በአገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች የተካኑ የአገር ውስጥ አሸማጋዮችን ይዞ ሰላም ማውረድ ተገቢ ነው፡፡ ግጭት ቀስቅሶ ከመፋጀት በተሻለ በርካታ የሰላም አማራጮች እንዳሉ በመገንዘብ፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ አሸናፊ ሊኖርበት የማይችል መተላለቅ እንዲቆም ድምፅን ማሰማት ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ግጭትን በዘላቂነት ለማስቆም የሚያስችሉ በቂ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሰው በእኩልነት ለመቀራረብ፣ ለመነጋገርና ለመደራደር ፈቃደኛ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ፈቃደኝነቱ የሚመነጨውም በመከባበር ስሜት በጋራ አገርን ለማስቀጠል ከሚኖር ፍላጎት ነው፡፡ ይህ ፍላጎት መመሥረት ያለበት ከምንም ዓይነት ዓላማ በላይ አገርን ማስቀደም ነው፡፡ በዚህ መሠረት ግጭቶችን በሙሉ በማስቆም በአገር ግንባታ ማዕቀፍ ውስጥ ተነጋግሮ ችግርን መፍታት ይቻላል፡፡

ከዚህ ቀደም በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያና በደቡብ የተለያዩ አካባቢዎች በግጭቶች ምክንያት ሕይወታቸውን ካጡ በርካታ ዜጎች በተጨማሪ ሚሊዮኖች መፈናቀላቸው ይታወሳል፡፡ በግጭቶች ሳቢያ ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣቢያዎችና ማኅበረሰቦች ውስጥ ከተጠለሉ በተጨማሪ፣ በድርቅ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች አሁንም የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ጠባቂዎች ናቸው፡፡ እንደ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) እና የተመድ የዓለም የምግብ ፕሮግራም የመሳሰሉ ለጋሾች በዝርፊያ ምክንያት ዕርዳታ በማቋረጣቸው፣ 32 ሚሊዮን ያህል ወገኖች የምግብ ያለህ እያሉ በየአቅጣጫው እየጮሁ ነው፡፡ ግጭት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች በተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሰዓት ዕላፊ ገደብ፣ በኔትወርክና በስልክ መቋረጥና በምርቶች መንቀሳቀስ አለመቻል ሳቢያ የብዙዎች ሕይወት እየተመሰቃቀለ ነው፡፡ ገንዘብ ባንክ ውስጥ ያላቸው ሰዎች አውጥተው መጠቀም ካለመቻላቸውም በላይ፣ ብዙዎቹ የመንግሥትና የግል ድርጅት ተቀጣሪዎችና መምህራን ሳይቀሩ ደመወዝ ማግኘት አቅቷቸው ለከፋ ችግር ተዳርገዋል፡፡ የመማር ማስተማር ሒደቱንም በአግባቡ መምራት አልተቻለም፡፡

በአሁኑ ጊዜ የምግብ ዋጋ ለብዙዎች ከአቅም በላይ እየሆነ ነው፡፡ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ አገልግሎት ከሚያወጣው ወርኃዊ የሸቀጦች ዋጋ ኢንዴክስ ለመገንዘብ እንደሚቻለው፣ የምግብ ዋጋን ለማረጋጋት የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ዓላማቸውን ማሳካት እንዳልቻሉ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በምሳሌነት የሚጠቀሱ ማሳያዎች አሉ፡፡ በአብዛኛው ከኢትዮጵያውያን ገበታ ላይ የማይጠፋው የጤፍ ዋጋ በአጭር ጊዜ ውስጥ በእጥፍ መጨመሩ የሚጠቀስ ሲሆን፣ የሌሎች ምግቦችና ምግብ ነክ ምርቶች ዋጋ ማሻቀብም ከዚህ ጋር የሚታይ ነው፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከተሜዎች ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ሕይወታቸው ላይ መፈጠራቸውን የሚያስረግማቸው የዋጋ ንረት ሲከሰት፣ መንግሥት በተቻለው መጠን በጥናት ላይ የተመሠረቱ የዋጋ ንረት ማረጋጊያዎችን መተግበር ይጠበቅበታል፡፡ መካከለኛ ገቢ አላቸው የሚባሉ ሳይቀሩ ከቤት ኪራይና ከምግብ ወጪ የማይተርፍ ኑሮ የሚመሩበት ደረጃ ላይ መድረሳቸው፣ የኑሮ ውድነቱ ፈተና የቅድሚያ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ተግባራት መካከል መመደብ እንዳለበት አመላካች ነው፡፡ መንግሥት ዜጎች በኑሮ ውድነቱ ምክንያት ሕይወታቸው ተመሰቃቅሎ ቀውስ ከመፈጠሩ በፊት፣ የምግብ ዋጋ እንዲረጋጋና ገበያውም በምርቶች እጥረት እንዳይቸገር የሚፈለግበትን ኃላፊነት ይወጣ፡፡

ከዘንድሮ የመኸር ምርት የሚሰበሰበው ከበፊቱ በጣም ሊያንስ እንደሚችል እየተካሄዱ ያሉ ግጭቶችን ዋቢ በማድረግ የሚያስጠነቅቁ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ዓምና የማዳበሪያ ግብዓት በወቅቱና በሚፈለገው መጠን ባለመቅረቡ ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች አርሶ አደሮች በሰላማዊ ሠልፍ ጭምር ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ በሃምሳ በመቶ የማዳበሪያ ግብዓት የሚፈለገውን ያህል ምርት ማግኘት እንደሚቸግር እየተነገረ ሲሆን፣ ትርፍ አምራች የሚባሉ የአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ዓውደ ውጊያ ውስጥ መሆናቸው የሥጋቱን መጠን ያባብሰዋል፡፡ አርሶ አደሮች በግጭቶችና በግብዓቶች እጥረት ተቸግረው ምን ያህሉን አምርተው ወደ ገበያ ያወጣሉ የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ፣ ግጭቶች ተባብሰው የሚቀጥሉ ከሆነ የዜጎችም ሆነ የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት በመረዳት ከወዲሁ ለመፍትሔ ፍለጋ መተባበር ካልተቻለ የብዙዎች ተስፋ እንደ ጉም ይበናል፡፡ በግጭትና በድርቅ የተፈናቀሉትን መልሶ በማቋቋም ወደ አምራችነት መመለስ፣ እንዲሁም በሰላም ዕጦት ምክንያት እየተስጓጎለ ያለውን የልማት ሥራ ማስቀጠል ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ትልቅ አደራ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡

እውነቱን እንነጋገር ቢባል እኮ ኢትዮጵያ ውስጥ ወገን ከወገኑ ጎራ አለያይቶ በጭካኔ የሚያፋጅ መሠረታዊ የሚባል ቅራኔ የለም፡፡ አለ ቢባል እንኳ በንግግርና በድርደር ሊፈታ የሚችል መለስተኛ ቅራኔ ነው፡፡ መለስተኛ ቅራኔን በአግባቡ ይዞ በሥርዓት ለመነጋገር የሚያስችል ዓውድ መፍጠር ባለመቻሉ፣ ከሥልጣንና ከሚያስገኘው ጥቅም የሚልቁ በርካታ የጋራ እሴቶች ተዘንግተው መፋጀት በጣም ያሳዝናል፡፡ ሌላው ቀርቶ በቅርቡ ከተካሄደውና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እጅግ ዘግናኙ ዕልቂት ብሎ ከፈረጀው የሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት ባለመማር፣ ሌላ ዙር ፍጅት ውስጥ እንደገና ስንገኝ ምንድነው የነካን ብሎ በአገር አቀፍ ደረጃ ለመነጋገር ሙከራ አለማድረግ ከማሳዘን አልፎ ያሳፍራል፡፡ ወንድም በወንድሙ ላይ ዘምቶ ግዳይ ከማስቆጠርና ምርኮ ከማሳየት በላይ ሌላ የሚያሳፍር ነገር ይኖራል ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመጠን በላይ የሰለቹት ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ አንደኛው ዕድሜ ልኩን ሰላም አጥቶ መኖር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የሚበላው ጠፍቶ ምፅዋት ጠባቂ መሆኑ ነው፡፡ ይህንን ኩሩ ሕዝብ ሰላም መንሳትም ሆነ ማስራብ በታሪክ ያስጠይቃል፡፡ ለዚህም ነው በሰላምና በምግብ ዕጦት ለሚፈተኑ ወገኖች መፍትሔ ይፈለግ የሚባለው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...