Sunday, April 14, 2024

የሕወሓትና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሽኩቻ የፈጠረው ሥጋት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከጥቅምት 3 እስከ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. የሚዘልቅ ክልላዊ ብሔራዊ የሐዘን ቀን በማወጅ ነበር ጥቅምት ወርን የተቀበለው፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሕይወታቸውን ላጡ የትግራይ ወጣቶች ቤተሰቦች መርዶ በማርዳት ዕርማቸውን እንዲያወጡ መደረጉ፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርን ከግራም ከቀኝም የተለያዩ ዓይነት ምላሾች ሲያሰጠው ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጂ የልጆቻቸውን ሞት የተረዱ የትግራይ እናቶች ያፈሰሱት ዕንባ ገና ሳይደርቅ ሌላ ዙር ሥጋት በትግራይ መቀስቀሱ እየተነገረ ነው፡፡ በጦርነቱ ለሞቱ ሰዎች የተጣሉ ድንኳኖች ሳይፈርሱና ዕርም የማውጣቱ ሥነ ሥርዓት ሳያበቃ፣ አዲስ መቆራቆስ በትግራይ የፖለቲካ ልሂቃን መካከል መፈጠሩ ግራ መጋባት ፈጥሯል፡፡

ከሰሞኑ ተከሰተ የተባለው በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርና በሕወሓት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ክልሉን ወደ ቀውስ እንዳይከት እየተሠጋ ነው፡፡ ውዝግቡ ገንፍሎ ወጥቶ ከትግራይ ክልል አልፎ አገር አቀፍ አደጋ እንዳይፈጥር እየተፈራ ነው፡፡ የሕወሓትና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አለመግባባት ከክልላዊና አገራዊ ቀውስነት አልፎ፣ እንደ ሱዳንና ኤርትራ ያሉ የቀጣናው አገሮችንም እንዳያዳርስ አንዳንዶች ሥጋታቸውን በመግለጹ ላይ ናቸው፡፡

ሕወሓት ሐሙስ ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም. ቅዳሜና እሑድ በመቀሌ ከተማ በሚካሄደው ስብሰባ ላይ በክልሉ ያሉ ካድሬዎቹ እንዲገኙ ጥሪ አቅርቦ ነበር፡፡ በማግሥቱ ዓርብ ጥቅምት 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ግን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ መገናኛ ብዙኃንን ጠርተው፣ ሕወሓት የጠራው ስብሰባ ሕግን ያልተከተለ ስለመሆኑ መግለጫ ሰጡ፡፡

በስብሰባው መጠራት ጉዳይ ላይ በሕወሓትና በጊዜያዊ አስተዳደሩ መካከል ልዩነቱ ለምን ተፈጠረ ለሚለው ሁለቱ ወገኖች የተለያዩ ዓይነት ምላሾችን በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ አንዱ ሌላውን ‹‹ሕግና አሠራርን ያልተከተለ›› በሚል ሲከሱ ቢደመጥም፣ ጉዳዩ ከስብሰባ ጭቅጭቅ የዘለለ እንዳይሆን ሲያሠጋ ሰንብቷል፡፡

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት በተላለፈ ጥሪ ሕወሓት ካድሬዎቹን ለስብሰባ ስለመጥራቱ ገልጿል፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የፓርቲው ስብሰባ እንዲካሄድ አስቀድሞ ከስምምነት የተደረሰበት ቢሆንም፣ የስብሰባው መካሄጃ ቀን ግን አልተቆረጠም ነበር ብሏል፡፡ በድንገትና አላግባብ የተጠራው ስብሰባ እንዳይካሄድ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከሕወሓት አመራሮች ጋር ንግግር በማድረግ ከመግባባት መድረሱን በዋዜማው አሳውቆ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ጊዜያዊ አስተዳደሩ አግባብነት የሌለው ያለውን ይህን ስብሰባ ሕወሓት በጠራው መሠረት መቀሌ ከተማ ከማድረግ አልተቆጠበም፡፡ ሕወሓት ጊዜያዊ አስተዳደሩን በመቃወም ባደረገው በዚህ ስብሰባ ደግሞ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ስድስት ካድሬዎችን ማባረሩን የሚቃወም አቋም በመያዝ ነበር የተለያየው፡፡ ይህ ሁሉ አለመግባባት በሁለቱ ወገኖች መካከል እንዴት ሊፈጠር ቻለ የሚለው ጉዳይ አሁን በሰፊው እያነጋገረ ነው፡፡

የትግራይ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ረዳዒ ሃለፎም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ስብሰባውን የተቃወመው በክልል ደረጃ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው መሠራት ያለባቸው አሳሳቢ ጉዳዮች በመኖራቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ተሰብሳቢዎቹ የፓርቲ አመራሮች ብቻ ሳይሆኑ በየደረጃው ባሉ እርከኖች የቢሮ ኃላፊዎችና መንግሥታዊ ሥራ የሚሠሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ክልሉ አሁን ቅድሚያ የሰጣቸውና መሠራት የሚገባቸው፣ ጊዜውን ባልጠበቀ ዝናብ ሰብል ሳይበላሽ ምርት የመሰብሰብ፣ አንበጣ የመከላከልና የመሳሰሉ አጀንዳዎች በመሆናቸው ነው፤›› በማለት ነበር የስብሰባው መጠራት ጊዜውን ያልጠበቀ መሆኑን የተናገሩት፡፡

ስብሰባው በጊዜያዊ አስተዳደሩ ተቃውሞ ቢገጥመውም ሕወሓት ግን 600 ካድሬዎችን ቅዳሜና እሑድ ጠርቶ መሰብሰቡ ታውቋል፡፡ በፓርቲው ላይ ባጠሉ አደጋዎች ላይ መምከሩን ከስብሰባው በኋላ ይፋ ያደረገው ሕወሓት፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ስድስት ካድሬዎችን ከሥራ ማሰናበቱ ተቋማዊ አሠራርን ያልተከተለ ዕርምጃ ነው ብሎታል፡፡

የሕወሓት ስብሰባ ከመካሄዱ አስቀድሞ፣ ‹‹የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥራ የማደናቀፍ አካሄድ ነው፤›› ሲል የጠራው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ግን ስብሰባው፣ ‹‹የትግራይ ሕዝብ ከገባበት ችግር ለማውጣት የምናደርገውን ጥረትም አያግዝም፤›› ሲል ነበር የተቃወመው፡፡

አቶ ረዳዒ፣ ‹‹ከኃላፊነት የተነሱት ካድሬዎች እኮ ወደ ኃላፊነት የተመደቡት በስብሰባ አይደለም፡፡ የክልሉ መንግሥት የሚወስነውን ውሳኔ የሆነ አካል እየተነሳ አግባብነት የለውም ቢል ተገቢ አይደለም፡፡ ሰዎቹ ከኃላፊነት የተነሱትም በስብሰባ አይደለም፡፡ በስብሰባ እገሌን መድቡት እገሌን አቆዩት ማለት አግባብነት የለውም፡፡ ሹመት በሚያስፈልግበት ቦታ አግባብነት ያለው ኃላፊ ይመደባል፡፡ ከሥራ መነሳት የሚገባቸው ካሉም ይነሳሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ጉዳይ ስክነት የጎደለው ነው፤›› በማለት ነበር ምላሽ የሰጡት፡፡

ይህ ሰሞነኛ የሕወሓት ፓርቲ አመራሮችና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ኃላፊዎች የመግለጫ ውዝግብ ደግሞ፣ በትግራይ ፖለቲካ ላይ በርካታ ሙግቶችን እያስነሳ ነው፡፡ አንዳንዶች ሕወሓት በፌዴራል መንግሥቱ በአዋጅ የተቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳደር ለመገልበጥ እያሴረ ነው የሚል ጠንካራ ሙግት እያነሱ ነው፡፡ ሌሎች በበኩላቸው ሕወሓት አሁንም በትግራይ ፖለቲካ ውስጥ ተፅዕኖ እንዳለው ራሱን ለማሳየት የተጠቀመበት ነው እያሉ ናቸው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ነባሩ የሕወሓት አመራር ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ተገልሎ መቆየቱ ቆጭቶት በክልላዊ ፖለቲካ ራሱን ወደ ውሳኔ ሰጪነት ሚና ለማምጣት እየተከተለው ያለ አዲስ የትግል ስትራቴጂ ነው ያሉት አሉ፡፡ ይህ ሁሉ ያልተዋጣላቸው አንዳንድ ወገኖች ግን ሁኔታውን የተለመደ የሕወሓት የፖለቲካ ሴራ ነው በማለት ሊበይኑት ሲሞክሩ ተደምጠዋል፡፡

መቀመጫውን መቀሌ ያደረገው በግሉ የሚሠራው ጋዜጠኛ መሐሪ ሰለሞን በበኩሉ፣ ሁኔታው ከምን እንደመነጨ ለመናገር አስቸጋሪ መሆኑን ይናገራል፡፡ ‹‹በትክክል ምን እየተደረገ ነው? ምን ዓይነት አሠላለፍ ነው ያለው? ማን ምን ዓይነት ሚና ነው ያለው? ከውጭም ሆነ ከውስጥ ምን እየተካሄደ ነው? የሚለውን ጉዳይ በትክክል ለማወቅ ይከብዳል፡፡ አጠቃላይ እንቅስቃሴውን በቅርበት ሆነንም ለመረዳት ይከብዳል፤›› ነው ያለው፡፡

የሕወሓትና የጊዜያዊ አስተዳደሩ በየሚዲያው የሚካሄድ ሰሞነኛ የመግለጫ ውዝግብ ከበስተጀርባው ያሉ መነሻ ምክንያቶች ጥርት ብለው አለመታወቃቸው፣ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ጎኖች ያሉት መሆኑን ጋዜጠኛ መሐሪ ይጠቅሳል፡፡

‹‹ጉዳዩ ጥርት ብሎ ቢገለጽ ለችግሩ መፍትሔ በማፈላለግ ሊረዱ የሚችሉ ወገኖች ዕገዛ ማድረግ ይችላሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ችግሩን በማባባስ በትግራይ ፖለቲካ ቁርሾ የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር የሚሹ ኃይሎች ክፍተቱን አሉታዊ ሚና ለመጫወት ሊያውሉት ይችላሉ፤›› በማለት ነው የተናገረው፡፡ በሁለቱም መንገድ ጉዳዩ ሊኖረው የሚችለው አፀፋ ታይቶ መረጃዎች እንዲታፈኑ መደረጉ የሚጠበቅ እንደሆነ ነው ጋዜጠኛው ያስረዳው፡፡

የሕወሓት መሥራችና የቀድሞ ከፍተኛ አመራር አሁን ግን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) መሪ አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር)፣ ችግሩ የመነጨው ከሕወሓት መሠረታዊ ባህሪ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

‹‹በመሠረቱ የሕወሓት አመራር የዴሞክራሲ አሠራር ባህል የለውም፡፡ በሽኩቻና በሴራ የሚኖር ድርጅት ነው፡፡ አመራሩ ሁሌም የሚኖረው የግል ጥቅሞችን በማሳደድ እንጂ ለሕዝብ ጥቅም የቆመ አይደለም፡፡ ለሕዝብ ችግር መፈታት ደንታ ያለው ቢሆን ኖሮ ይህ ሁሉ ሕዝብ ባላለቀ ነበር፤›› በማለት አረጋዊ (ዶ/ር) የሕወሓት መሠረታዊ ባህሪ ያሉትን አስረድተዋል፡፡

የሰሞነኛው ችግርም ሆነ በክልሉና በመላው አገሪቱ ላይ የደረሰው ቀውስ ምንጭ የሕወሓት አመራሮች ያልተገራ የፖለቲካ ጥቅም ፈላጊነት መሆኑን የገለጹት አንጋፋው ፖለቲከኛ፣ የአሁኑ ችግርም በዚሁ አንደማያበቃ ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡

ሕወሓት የሥልጣን ሽኩቻ በመፍጠር ላይ መጠመዱን ያመለከቱት አረጋዊ (ዶ/ር)፣ ‹‹ይህንን ሽኩቻም ወደ እርስ በርስ ግጭት በመውሰድ በየዞኑና በየሠፈሩ የጎበዝ አለቆች እንዲፈጠሩ ሊያደርግ ይችላል፤›› በማለት ግምታቸውን አክለዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ሕወሓት በትግራይ ፖለቲካ ውስጥ ብቸኛ አዛዥና ሁሉንም አድራጊ ኃይል ሆኖ መቀጠል የሚችልበት ሁኔታ አለ ወይ የሚል ጥያቁ የቀረበላቸው ፖለቲከኛው፣ የሕወሓት ፍላጎት ይህ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ‹‹ጊዜያዊ አስተዳደሩ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ነው የተቋቋመው፡፡ በስምምነቱ አንቀጽ አሥር መሠረት ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶችና ሲቪክ ማኅበራት በተውጣጡ አካላት ይመሠረታል ነው የተባለው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ በተግባር ላይ አልዋለም፡፡ በዚህ የተነሳ ሕወሓት በበላይነት አስተዳደሩን ጠቅልሎ ይዞታል፡፡ ይህ በመሆኑ ደግሞ ሕወሓት በክልሉ የምፈልገው ነገር ካልተፈጸመ በሚል የበላይነት ስሜት ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ሽኩቻ እየፈጠረ ነው፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

በእሳቸው እምነት የፕሪቶሪያው ስምምነት በትክክል በተግባር ባለመተርጎሙና ጊዜያዊ አስተዳደሩን ሕወሓት እንዲጠቀልል በመፈቀዱ ነው ይህ ሁሉ ችግር የተፈጠረው፡፡ ‹‹በዚህ የተነሳ ወደ ሰላም ስምምነቱ መመለስ አለብን፤›› የሚሉት ፖለቲከኛው፣ ሁሉንም ወገን ያቀፈ ጠንካራ ጊዜያዊ አስተዳደር ካልተፈጠረ በስተቀር ሕወሓት እንዳሻኝ ልሁን ማለቱ ይቀጥላል በማለትም ተናግረዋል፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ አሁን በሕወሓት ሕገወጥ እንቅስቃሴ አደጋ ገጥሞታል ብለዋል፡፡

አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉት የትግራይ ክልል ፖለቲካን የሚከታተሉ አስተያየት ሰጪ ሰሞነኛውን ሁኔታ፣ ‹‹የውስጣዊ ዴሞክራሲ ትግል›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡ በእሳቸው እምነት ጊዜያዊ አስተዳደሩ የፓርቲውን ፍላጎት ማስፈጸም ያለበት አካል እንጂ፣ ፓርቲውን ለምን ብሎ መቃወም አይኖርበትም፡፡

‹‹በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ባይቶናና ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ቢኖሩም ሕወሓት ግን 51 በመቶ አብላጫ ድምፅ የያዘ ነው፡፡ የጊዜያዊ አስተዳደሩ መሪ አቶ ጌታቸው ረዳም ቢሆኑ የሕወሓት አባል ናቸው፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሳይሆን ካድሬዎቹን የመሰብሰብ፣ የመሾምና የመሻር መብት ያለው ራሱ ፓርቲው ነው፤›› ሲሉ የተፈጠሩ የውዝግብ ነጥቦችን ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡

እኚሁ አስተያየት ሰጪ እንደሚናገሩት፣ የፓርቲውና የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሽኩቻ የሕዝብ ጥያቄና የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት አተገባበር ጉዳይ ጭምር የፈጠረው ነው፡፡ ‹‹የክልሉ ሕዝብ የሰላም ስምምነቱ በአግባቡ በተግባር እንዲተገበር ይፈልጋል፡፡ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱና መደበኛ ሕይወት ወደ ቀደመው ሁኔታ እንዲመለስ ይፈልጋል፡፡ ፓርቲው ይህን የሕዝብ ፍላጎትና ጫና ጊዜያዊ አስተዳደሩ በኃላፊነት ወስዶ እንዲያስፈጽም ይፈልጋል፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ግን ሁኔታውን እንደ አላስፈላጊ ጫናና ጣልቃ ገብነት የቆጠረው ነው የሚመስለው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

የሕወሓት ሰሞነኛ እንቅስቃሴ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይ የማሴር ነው ብለው የሚገምቱ ሌሎች ወገኖች ግን፣ ሕወሓት ያለፈበት የትግል ታሪክን መልሶ መፈተሸ እንደሚያስፈልግ ነው የሚጠቁሙት፡፡ በየጊዜው በየተወሰነ ወቅት ሕወሓት ያለፈበት የትግል ጉዞ ወደ ውስጥና ወደ ውጭ የመገንፈል ባህሪ ያለው መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ፓርቲው እነዚህን አጋጣሚዎች ውስጣዊ የዴሞክራሲ ትግል ብሎ ቢጠራቸውም፣ ይሁን እንጂ አጋጣሚዎቹ ክልላዊና አገራዊ ቀውሶችን የፈጠሩ ስለመሆናቸው ያስረዳሉ፡፡

ወደ 50 ዓመታት ዕድሜው እየተሻገረ ያለው ሕወሓት በኢሕአዴግ ውስጥ በነበረበት ወቅት ብቻ ሳይሆን፣ ኢሕአዴግ ከመሆኑ በፊትም ውስጣዊ ሽኩቻ እንዳጋጠሙት መሥራች ታጋዮቹ ጭምር መመስከራቸው ይታወቃል፡፡ በመጀመሪያው ዙር ‹ህንፍሽፍሽ› ወይም የ1977 ዓ.ም. የሕወሓት ሽኩቻ ወቅት ለዴሞክራሲ፣ ለፍትሕና ለእኩልነት ሕይወታቸውን ሊሰው የወጡ የሕዝብ ልጆችና የነፃነት ታጋዮች በረቀቀ አሻጥር በሞትም በመባረርም ከድርጅቱ እንዲገለሉ መደረጉን ያስታውሳሉ፡፡

በደርግ ውድቀት ማግሥት ኢሕአዴግን እየመራ አገር የተቆጣጠረው ሕወሓት በትግሉ ሒደት ብዙ መስዋዕት ሲከፍሉ የቆዩ ነባር ታጋዮችን ያለ ክብርና ያለ ካሳ ከድርጅቱ ማግለሉን ሌላኛው ‹ህንፍሽፍሽ› ይሉታል፡፡

በሌላ በኩል በ1993 ዓ.ም. በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ማግሥት የተፈጠረውን ሁኔታ የሚያነሱት እነዚህ ወገኖች፣ ‹ቦናፓርቲዝም› እና ‹አንጃ› በሚሉ ተቀፅላዎች ነባር ታጋዮች እርስ በርስ መበላታቸውን ይናገራሉ፡፡ በኪራይ ሰብሳቢነትና በፀረ ሙስና የትግል ታፔላዎች የመጣው የጊዜው የፖለቲካ ሽኩቻ ሕወሓትን፣ ብሎም ሕወሓት መራሹን ኢሕአዴግ ግለሰባዊ አምባገነንነት የሰፈነበት ድርጅት እንዳደረገው ይገልጹታል፡፡

የ1997 ዓ.ም. ምርጫ ውጤት እንዲሁም በ2010 ዓ.ም. የተፈጠረው የፖለቲካ ለውጥ የሕወሓትን ቅርፅና የፖለቲካ ማንነት እንደቀየሩት ያስረዳሉ፡፡ አሁን ደግሞ በሰሜኑ ጦርነት ማግሥት ሕወሓት ሌላ ዙር የውስጥ ሽኩቻ እያስተናገደ ይገኛል ይላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ፓርቲው ሰሞኑን ከጊዜያዊ ጋር አስተዳደሩ በከፈተው ሽኩቻ እየተገለጠ ነው ሲሉም በምሳሌነት ያነሳሉ፡፡

በሚኒስትሮች ምክር ቤት በፀደቀውና የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ደንብ ቁጥር 533/2015 ላይ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመሠራረት ሒደት ብቻ ሳይሆን ሥልጣንና ኃላፊነትም በዝርዝር ሰፍሮ ይገኛል፡፡

ይህንኑ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ያጣቀሱ ወገኖች ጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉ ያሉ ቢሮዎችን የማደራጀትና የቢሮ ኃላፊዎችን የመሾምና የመሻር ሙሉ ሥልጣን እንዳለው ይከራከራሉ፡፡

ይህ ደንብ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉ ቢሮዎችን የማደራጀትና ኃላፊዎችን የመሾምና የመሻር ሙሉ ሥልጣን ያለው መሆኑ ብቻም ሳይሆን፣ ከደንቡ ጋር የሚቃረን ማንኛውም የፌዴራልም ሆነ የክልል ደንብ፣ መመርያም ሆነ አሠራር ተፈጻሚነት እንደሌላቸው በግልጽ ማስቀመጡን ያክላሉ፡፡

ይህ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ማቋቋሚያ ሕጋዊ ሥልጣንና ኃላፊነት ሳይሻርና በሥራ ላይ እያለ ሕወሓት በምን አግባብ ነው በክልሉ ጉዳዮች ያገባኛል የሚለው ሲሉ እነዚህ ወገኖች ይጠይቃሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -