- ሁሉም ከፍተኛ አመራር በሥልጠናው ይሳተፋል ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ከፍተኛ አመራሩ ብቻ ሳይሆን አስከታች ያለው በየደረጃው እየተሳተፈ ነው።
- ሥልጠናው ምን ላይ ያተኮረ ነው?
- ሰሞኑን ቴሌቪዥን አላየህም ማለት ነው?
- ኧረ በየዕለቱ ነው ቴሌቪዥን የምከታተለው።
- ታዲያ ከዕዳ ወደ ምንዳ የሚል ሥልጠና እየተሰጠ እንደሆነ አልማህም?
- እሱ ነው እንዴ?
- አዎ።
- አሱንማ መስማት ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ውጤቱን በጉጉት እየጠበቅን ነው።
- በጉጉት?
- አዎ ክቡር ሚኒስትር ሁሉም ሠራተኛ የሚያወራው ስለዚህ ሥልጠና እኮ ነው።
- ለምን?
- ያው ሁላችንም በኑሮ ውድነቱ እየተሰቃየን ነዋ ክቡር ሚኒስትር።
- ታዲያ ከዚህ ሥልጠና ጋር ምን አገናኘው?
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር? ሥልጠናው ሲያልቅ ትወስናላችሁ ብለን ነዋ፡፡
- ምንድን?
- ጭማሪውን።
- የምን ጭማሪ?
- የደመወዝ ጭማሪ ነዋ፡፡
- ስለደመወዝ ጭማሪ መቼ ተወያየን እኛ?
- ውይይቱ ከዕዳ ወደ ምንዳ አይደል እንዴ?
- አዎ።
- ታዲያ መጨረሻ ላይ አይወሰንም?
- ምን?
- ደመወዝ ነዋ፣ ምንዳ?
- ከዕዳ ወደ ምንዳ ስንል ደመወዝ ማለታችን እኮ አይደለም።
- ምን ማለታችሁ ነው ታዲያ?
- ካለፈው ሥርዓት የተወረሱ ዕዳዎችን ወደ ምንዳ መቀየር አለብን ማለታችን ነው።
- እንጂ ስለደመወዝ አይደለም?
- እንደዚያ ከሆነ የሥልጠናውን ርዕስ ብትቀይሩት ይሻል ነበር።
- ምን ብንለው ይሻል ነበር?
- በዕዳ ላይ ዕዳ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ቢገቡም ጸሐፊያቸው ዛሬም በሰዓቱ ቢሮ አልተገኘችም። በነገሩ መደጋገም ተናደው ቢሮ ውስጥ እየተንጎራደዱ ሳለ ጸሐፊዋ እየጣደፈች ወደ ቢሮ ገባች]
- ውይ ክቡር ሚኒስትር ዛሬም ቀደሙኝ?
- እኔ ቀድሜሽ አይደለም።
- እህ… ነው እንጂ ይኸው ቢሮ ቀድመውኝ ገብተው?
- ቀድሜሽ ሳይሆን የሥራ ሰዓት እያከበርሽ ባለመሆኑ ነው።
- ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር ዛሬስ አርፍጄያለሁ።
- ዛሬ ብቻ አይደለም። ታስተካክያለሽ ብዬ ዝም ብልሽም ከመደጋገም አልፎ በዛ፡፡
- ምን ላድርግ ክቡር ሚኒስትር …ወድጄ አይደለም እኮ፡፡
- ስንት ዓመት እዚህ ቢሮ ስትሠሪ ያለየሁብሽን ባህሪ ነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያየሁ ያለሁት። የሆንሽው ነገር አለ?
- በፊት መኖሪያ ቤቴ መሀል ከተማ ውስጥ ስለነበረ ትራንስፖርት አልቸገርም ነበር ራመድ ብዬም መድረስ እችል ነበር። አሁን ግን….
- አሁን ግን ምን?
- የመኖሪያ ቤት ኪራይ መክፈል ሲከብደኝ ከመሀል ከተማ ራቅ ብዬ ተከራየሁ።
- እሺ?
- እዚያም ብዙ መቆየት አልቻልኩም።
- ለምን?
- ዋጋ ጨመሩብኝ።
- እና?
- የጠየቁኝን ዋጋ መክፈል ስለማልችል ለቅቄ ራቅ ወዳለ አካባቢ ተከራየሁ።
- እሺ?
- እዚያም ዋጋው አልቻልኩትም።
- ስለዚህ?
- ከዛም ለቅቄ አሁን የከተማው መውጫ ጫፍ ላይ ነው የምኖረው።
- ከመሀል ከተማ ወደ ጫፍ ሄድሽ?
- ምን ላድርግ ክቡር ሚኒስትር። ለነገሩ እኔ ብቻ አይደለሁም።
- እህ…?
- አብዛኛው ነባር የከተማዋ ነዋሪ እኮ እንዲሁ የቤት ኪራይ ዋጋውን አልችል ብሎ ከመሀል ከተማ ቀስ እያለ ወደ ከተማው ጫፍ ወጥቷል።
- ያሳዝናል፡፡
- ይህ አይደለም የሚያሳዝነው፡፡
- ታዲያ ምንድነው የሚሳዝነው?
- የከተማ አስተዳደሩ ያወጣው አዲስ ታሪፍ ነው የሚያሳዝነው።
- የምን ታሪፍ?
- የትራንስፖርት ታሪፍ?
- እንዴት?
- ለታክሲ 52 ብር እንድንከፍል ወሰነ።
- ለምን?
- ወደ መሀል ከተማ ለመግባት።
- ወይ ጉድ?
- ስለዚህ ክቡር ሚኒስትር አንድ ነገር ያድርጉልኝ?
- ምን ላድርግልሽ?
- መሀል ከተማ ላይ ኮንዶሚኒየም ቤት ያሰጡኝ?
- እንዴት አድርጌ?
- አንድ መላ ፈልገው ቤት ያሰጡኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ምን ዓይነት መላ ላቀርብ እችላለሁ?
- የእርሶ ጸሐፊና የእንትን ልጅ መሆኔን ከገለጹ በአንድ ጊዜ ሊያሰጡኝ ይችላሉ ክቡር ሚኒስትር።
- የምን ልጅ?
- የአርሶ አደር ልጅ!