ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ መስኮች የተለያዩ ምናባዊ መረጃዎች ሲወጡ ብዙ ጊዜ የተዓማኒነት ጥያቄ ይነሳባቸዋል፡፡ የተዓማኒነት ጥያቄ የሚነሳባቸው በርካታ ምናባዊ መረጃዎችም አሳማኝ ምላሽ አያገኙም፡፡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ ለሌሎች አካላት የሚቀርቡ ብዙዎቹ ሪፖርቶች ላይ የተዓማኒነት ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ ሪፖርት አቅራቢ የካቢኔ አባል የሆኑ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችም ሆኑ የእነሱ ተጠሪ የሆኑ ተቋማት፣ በተደጋጋሚ በፓርላማ ቋሚ ኮሚቴዎች ሳይቀር ጥያቄዎች ሲቀርቡላቸው ከእውነታው ጋር የሚቀራረቡ ምላሾች ለመስጠት ሲቸገሩ ተስተውለዋል፡፡ በዘመነ ኢሕአዴግም ሆነ በዘመነ ብልፅግና በተቋማት በሚቀርቡ ሪፖርቶች ላይ ጥያቄዎች ተነስተው አጥጋቢ ምላሾች ሲጠፉ የግልጽነት፣ የተጠያቂነትና የኃላፊነት መርህ አለመከበርን በሚገባ ያሳያሉ፡፡ ያልተሠራን እንደተሠራ አድርጎ ማቅረብ የረዥም ጊዜ ልማድ በመሆኑ፣ ብዙዎቹ ሪፖርቶች ውስጥ የሚታጨቁት ሐሰተኛ ቁጥራዊ መረጃዎች መሬት ላይ የሚታየውን እውነት ለማድበስበስ ይሞክራሉ፡፡ ነገር ግን ሐሰተኛ መረጃዎቹ እውነታውን የመደበቅ አቅም እያነሳቸው ተቋማቱንና አመራሮቻቸውን ያጋልጣሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ድርጊት በፍጥነት መገታት አለበት፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች የልማት ሥራዎች መከናወናቸው አዲስ አይደለም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ካሏት ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችና አቅም አኳያ ሲታዩ ግን እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም፡፡ ለዚህም ዋነኛው ማስረጃ ሥር በሰደደ ድህነት ምክንያት በምግብ ራስን መቻል ዛሬም ከባድ ፈተና መሆኑ ነው፡፡ በግብርናው ዘርፍ ሊታረስ ከሚችለው 60 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ ሩቡን መሸፈን አለመቻሉ ነው በባለሙያዎች የሚነገረው፡፡ እዚህ ላይ በመስኖ ሊለማ የሚችለው የመሬት መጠን ሲጨመርበት ደግሞ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ለሥራ የሚያነሳሳ በጥናት ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ ቢኖር፣ ኢትዮጵያውያን እንኳንስ ምግብ ሊቸገሩ ቀርቶ ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም ገበያ መትረፍ ይችሉ እንደነበር ባለሙያዎች በተለያዩ መድረኮች በቁጭት የሚያወሱት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በቁም እንስሳት ሀብት ከአፍሪካ አንደኛ፣ እንዲሁም ከዓለም ግንባር ቀደም አገሮች ተርታ ብትሠለፍም፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግን የእንስሳት ተዋፅኦ ውጤቶች እንደ አልማዝና ወርቅ ብርቅ ሆነውበታል፡፡ ሪፖርቶች ተቀሽረው ሲወጡ ግን ከእውነታው ብዙ ርቀት ላይ ናቸው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ስሟ በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት ሲጠራ ይሰማል፡፡ ባለፈው ሰሞን የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አኪንውሚ አዴሲና (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2018 በቆላማ ቦታዎች ከአምስት ሺሕ ሔክታር በታች የነበረው የስንዴ እርሻ እ.ኤ.አ. በ2022 እና በ2023 ወደ 1.4 ሚሊዮን ሔክታር ማደጉን በአድናቆት ተናግረው፣ እ.ኤ.አ. በ2023 ተጨማሪ 1.6 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ መመረቱንና ኢትዮጵያም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በስንዴ ምርት ራሷን መቻሏን አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም ለጎረቤት አገሮች ስንዴ መላክ መጀመሯን አክለዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ምስክርነት በትልቅ ዓለም አቀፋዊ መድረክ ላይ ሲሰጥ ደስ ማለቱ አይቀሬ ነው፡፡ ከደስታው ባሻገር ደግሞ የተለያዩ ጥያቄዎችም ይነሳሉ፡፡ ለምሳሌ በተባለው መጠን የተገኘውን ምርት ወደ ገበያ ማድረስ ያስቸገረበት ምክንያት፣ ዋጋን ለማረጋጋት ለምን እንዳቃተ፣ ኤክስፖርት ተደርጎ ያስገኘው የውጭ ምንዛሪ መጠንና ሌሎች ጥያቄዎች ይቀርባሉ፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በስንዴ ምርት ራሷን በመቻል ታዋቂ ከሆነች፣ ዳቦ መጠኑ እያነሰ ዋጋው ለምን ተወደደ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መስጠት የግድ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ሙስናን በተመለከተ የተለያዩ መረጃዎች ይወጣሉ፡፡ በትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል እ.ኤ.አ. የ2022 የሙስና ኢንዴክስ መሠረት ከ100 ያገኘችው 38 ነጥብ ነው፡፡ ከ194 አገሮችም ደረጃዋ 94ኛ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ከአማካዩ በታች ላይ እንደምትገኝ ነው፡፡ መንግሥት በፊትም ሆነ አሁን ሁኔታው ከፋ ሲል ሙስናን ለመታገል በማለት፣ ጠንከር ያሉ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ እንቅስቃሴዎችን ሲጀምር ይታያል፡፡ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ ሚዲያዎችም አድርገው የማያውቁትን የፀረ ሙስና ፕሮግራሞች በስፋት አዘጋጅተው ያቀርባሉ፡፡ ከፍርድ በፊት ውሳኔ የሚመስሉ ዳኝነቶችን በፕሮግራሞቻቸው ሲያሰጡም በተደጋጋሚ ተደምጠዋል፡፡ በዘመቻ መልክ ከመንግሥት ባለሥልጣናትም ሆነ ከንግዱ ማኅበረሰብ ውስጥ የተወሰኑት በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ ይጀመራል፣ ምርመራው አለቀ ተብሎም ፍርድ ቤት ክርክር ይቀጥላል፣ ትንሽ ቆየት ብሎ ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ታሳሪዎች ይፈታሉ፡፡ ይህ ሁሉ ወጀብ ካለፈ በኋላ ኢትዮጵያ በሙስና አሁንም በመልካም ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ የሚጠቃቅሱ አድራሻቸው የማይታወቅ መረጃዎች እየተለቀቁ ግራ መጋባት ይፈጠራል፡፡
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ መሬትና መሬት ነክ ጉዳዮች ሙስናን ተቋማዊ እንዲመስል እንዳደረጉ ብዙ ተብሎበታል፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው ተብሎ በግልጽ የተደነገገ ቢሆንም፣ በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እንዳሉት የሌቦችና የደላሎች ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ኢንቨስተሮች መሬት ተረክበው ለልማት ለማዘጋጀት የሚያልፉበት የቢሮክራሲ መረብ ዋነኛው የሙስና መደላድል መሆኑን ማንም የሚያውቀው ነው፡፡ በወረዳዎችና በክፍላተ ከተሞች በመሬትና ላዩ ላይ ያለ ይዞታን በተመለከተ ጉዳይ ያላቸው ዜጎች፣ በገዛ ንብረታቸው የሙሰኞች መጫወቻ መሆናቸውም እንደ አዲስ የሚነገር ጉዳይ አይደለም፡፡ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች ከመሬት ጋር በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ መጠን ጉቦ መጠየቃቸው የተለመደ ነው፡፡ የሙስናው ስፋት በዜጎች መካከል ያለውን የኑሮ ልዩነት ማስፋቱ፣ ለመሠረተ ልማቶች ግንባታ የሚውል ሀብት መብላቱና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ላይ አደጋ መደቀኑ ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ›› እንጂ፣ በሐሰተኛ ሪፖርት የሚስተባበል አይደለም፡፡ እንደ ሰጎን ጭንቅላትን አሸዋ ውስጥ በመቅበርም ‹‹አላየሁም ነበር›› ማለት አይቻልም፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም በየቀኑ የሚፈጠሩና ከበፊት ጀምሮ ሲንከባለሉ የመጡ በርካታ ችግሮች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ የሚያማምሩትን ብቻ የበለጠ እያሰማመሩ ወደ አደባባይ ማውጣት ላይ ትኩረት ሲደረግ፣ የማያምሩት ወይም እውነተኛውን ነባራዊ ሁኔታ የሚያጋልጡት ሲደበቁ የበለጠ ችግር ያስከትላሉ፡፡ መሬቱ ታርሶ የተትረፈረፈ ምርት ሲገኝ ዜጎች ደስተኛ የሚሆኑት፣ እንደ እሳት ከሚያንገበግባቸው የኑሮ ውድነት ፋታ ሲሰጣቸው ነው፡፡ ዘወትር ኢትዮጵያ እኮ በእንስሳት ሀብት ከአፍሪካ አንደኛ ናት እየተባለ ከሚነገራቸው ይልቅ ሥጋ፣ ዕንቁላል፣ ዶሮ፣ ወተት፣ ቅቤ፣ ዓይብና መሰል ተዋፅኦዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት ቢችሉ ይመርጣሉ፡፡ የአገሪቱ የእንስሳት ሀብት፣ ቡና፣ ወርቅና ሌሎች ምርቶች በኮንትሮባንድ ወደ ውጭ እየወጡ ብርቱ ችግሮች ማጋጠማቸው እየተሰማ ነው፡፡ ነገር ግን የችግሮቹ ስፋትና ጥልቀት እየታወቀ አጉል የማበረታቻ ፕሮፓጋንዳ ለማንም ምንም አይፈይድም፡፡ ይልቁንም የአገሪቱን ፀጋዎች በጋራ አልምቶ ለመጠቀም የሚያስችሉ ፖሊሲዎች ቢታሰብባቸው ይሻላል፡፡ ከምናባዊ መረጃዎች ይልቅ ለሚታዩ እውነታዎች ትኩረት ይሰጥ!