Sunday, February 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የኢትዮጵያ የግብይት ሥርዓትን ለማረም ጠንካራ የሸማቾች ተሟጋች ተቋማትን ማደራጀት ያሻል!

በአሁኑ ወቅት በአገራችን ብቻ ሳይሆን በአብዛኛው የዓለማችን አገሮች የዋጋ ንረት ከፍተኛ ተግዳሮት መሆኑ ይታመናል፡፡ 

በእያንዳንዱ አገር ያለው የዋጋ ንረት መጠኑና ይዘቱ ይለያይ እንጂ የሸማቾችና የተገልጋዮች ምሬት ምንጭ መሆኑ አልቀረም፡፡ 

በተለያዩ ቦታዎች የተቀሰቀሱት ጦርነቶች በተለይ ከኮቪድ ወረርሽኝ መከሰት ወዲህ የዓለም ኢኮኖሚ የገጠመው ችግር አሁንም ድረስ ባለመሻሩ ዓለም ለገጠማት የዋጋ ንረት አንድ ምክንያት መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ 

በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ያስከተለው ጉዳት ሳያንስ የሩስያና የዩክሬን ጦርነት መቀስቀስ በቅርቡም በመካከለኛው ምሥራቅ መቀስቀስ ደግሞ እንደገና ለዓለም ኢኮኖሚ እንዳይረጋግ የዋጋ ንረቱም እንዳይወርድ አድርጓል፡፡ ለዚህም ነው የአገራችን የዋጋ ንረት ችግር ምንጭ ውጫዊና ውስጣዊ እንደሆኑ የሚገለጸው፡፡ አሁን ከዚህ አዙሪት ለመውጣት አስቻይ ሁኔታዎችም አይታዩም፡፡ 

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ግጭቶች አሉ፡፡ ለሌሎች የዋጋ ንረቱን ሊያባብሱ የሚችሉ ችግሮቻችንም አልቀረፍንም፡፡ በግብይት ሥርዓት ውስጥ ያሉ ብልሹ አሠራሮችን ለማስተካከል የሚያስችል ተጨባጭ ዕርምጃዎች እየታዩ አይደለም፡፡ ለዋጋ ንረት መባባስ በምክንያትነት የሚጠቀሰው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪም ከሌላው ጊዜ በተለይ ዋጋው መሰቀሉ የአገራችንን ዋጋ ንረቱን ለመቀነስ የሚደረጉ ጥረቶች ወደ መፍትሔው ለመዳረስ አላስቻሉም፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች የዋጋ ንረቱን ለመቅረፍ የሚደረጉ ጥረቶችን ሁሉ እየተፈታተኑ በመዝለቃቸው በቀላሉ ከገባንበት የዋጋ ንረት ለመውጣት እጅግ ከባድ ሆኗል፡፡ እንደ ተዓምር ዱብ ሊል የሚችል መፍትሔ ካልመጣ በቀር ችግሩ አብሮን ይቆያል የሚለውን ሥጋት በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ በአጭሩ አሁን ካለንበት ነባራዊ ሁኔታ የዋጋ ንረቱን ለማቃለል ቀላል ባለመሆኑ ቢያንስ ከዚህም በላይ እንዳያሻቅብ ሁነኛ መፍትሔ የማፈላለጉን ጉዳይ በአንድ በመንግሥት ላይ ብቻ መጣል ፈጽሞ የሚያዋጣ አይሆንም፡፡ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ኑሮ ተወደደ ዋጋ ጨመረ ከሚለው ሮሮ ባሻገር እንዴት የመፍትሔው አካል እችላለሁ የሚለውን የግድ ሊያስብና በተግባርም ማሳየት የግድ እያለ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ እያደገ የመጣውን ፍላጎት ለመሙላት ቢያንስ ደፋር ባለሀብቶች በተይ በግብርናው ዘርፍ እንዲሰማሩ ማድረግ የውዴታ ግዴታ ሊሆን ይችላል፡፡

አሁን ባለንበት ሁኔታ ግን የሚቀርበውን ምርት በአግባቡ ለመጠቀም ብሎም ያልተገባ የዋጋ ጭማሪዎችን ለመከላከል በቅድሚያ መታሰብ ካለባቸው ጉዳዮች አንዱ ሸማቾችን የሚወክሉ የሸማቾች ተቆርቋሪዎችና ተሟጋች ተቋማትን ማፍራት ነው፡፡ 

በዓለም ላይ በተለያዩ አገሮች ያሉ የዋጋ ንረትን ለመከላከል ያልተገባ የግብይት ሥርዓትን ለመቆጣጠር የሸማቾች ተቆርቋሪ ተቋማት ብዙ ሥራ እየሠሩ ነው፡፡ የሸማቾች ጨዋነትም ታክሎበት ችግሩ እንዳይባባስ ዕገዛ እያደረጉ ነው፡፡ 

ከዚህ ጉዳይ አንፃር በተለይ በዚህ ወቅት በብዛትና በጥራት ሊኖሩን የሚገቡ የሸማቾች ተቆርቋሪ ማኅበራት መጥፋት በእጅጉ ጎድቶናል፡፡ አንድ ሰሞን ብቅ ብቅ ብለው የነበሩ የሸማቾች ተቆርቋሪ ማኅበራት ዛሬ ላይ ጭራሽ ድምጻቸው አይሰማም፡፡ ሸማቾች ስለእነርሱ ብሎ የሚሟገት ተቋማት የላቸውም፡፡ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ያሉ ችግሮችን አይቶ ችግሩን ምንም ለይቶ መፍትሔ የሚሆኑ ሐሳቦችን አካቶ ለመፍትሔ የሚቀርብ እከሌ የሚባል ተቋም መጥፋቱ በራሱ ብዙ ነገር አጉሏል፡፡ ሸማቾች በዋጋ ብቻ ሳይሆን ከአገልግሎት አሰጣጥ ግድፈትና መሰል ችግሮችን በማየት እዚህ አካባቢ ይህ ችግር አለ ብሎ የሚሞግት የሸማች ተቆርቋሪ ማጣት ሸማቾች ሊኖራቸው የሚገቡ መብቶች ተሸርሽረዋል፡፡ በእጅጉ እንዲሸረሸር አድርጓል፡፡ በቀላሉ ሊታረም የሚችሉ ችግሮች እንዲሰፋ አድርጓልም ማለት ይቻላል፡፡ በዘፈቀደ የሚደረጉ ያልተገቡ የዋጋ ጭማሪዎች ሸማቹን የጎዱ መሆኑ እየታወቀ ይህንን ለመሞገት የሚችል ተቆርቋሪ በመጥፋቱ ነገሩ ሁሉ በምሬት እየታለፈ ነው፡፡ 

ስለዚህ እጅግ ብዙ ችግሮች ያሉበትን የግብይት ሥርዓት ለማረም ከዚህ አገር ተያይዞ የሚከሰተውን የዋጋ ንረት ለመከላከል ጠንካራ ሸማቾችን የሚታደግ በሕግ የተሰጣቸውን መብት እንዲጠቀሙበት ለማስቻል ለማስቻል የሸማች ተቆርቋሪ ማኅበራት የግድ ያስፈልጉናል፡፡ 

አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ መንግሥት የዋጋ ንረትን ለመቀነስ እሠራዋለሁ ብሎ የሚያስባትን ሥራዎች ሁሉ ከግብ ለማድረስም ቢሆን እነዚህ አካላት ሊኖር አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ መግባት የለበትም፡፡ 

ተቋማቱ ታች የሚታየውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋትም ሆነ ባልተገባ መንገድ የሚካሄድን ግብይት ከሥር መሠረቱ በመልዕክት ለመንግሥት በማቅረብ ጭምር ዕርምት እንዲደረግ የሚያግዙ መሆናቸወ መሳት የለበትም፡፡ 

ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ሸማቹም የራሱን መብት አውቆ እንዲገበያይ ጥራት ያለው ምርት እንዲቀርብ፣ ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶች ገበያ ውስጥ መሮራቸውን ለማጋለጥ መንግሥት አካላት ብቻ የሚወጡት ባለመሆኑ የሸማች ተሟጋቾች መኖር ጠቀሜታውን ዘርፍ ብዙ ያደርገዋል፡፡ ከሌብነት የፀዳ አገልግሎት የማግኘት መብት እንዲጎናጸፍም በሸማች ተቋማት በኩል የሚሰጡ ግንዛቤ ማስጨበጫዎች ብዙ ነገር እንደሚቀይር ይታመናል፡፡ 

ስለዚህ በኢትዮጵያ የግብይት ሥርዓት ውስጥ በግድ ሊኖሩ የሚገቡትን የሸማች ተሟጋች ተቋማትን ኅብረተሰቡ ሊፈጥር ይገባል፡፡ መንግሥትም የተቋማቱን መኖር አስፈላጊነት በማመን ፕሮፌሽናል የሸማች ተሟጋች ተቋማት በየዘርፉ እንዲፈጠሩ ማድረግ እየናረ የመጣውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር አንድ አስቻይ መንገድ ከመሆንም በላይ በግብይትና በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ሁሉ በተደራጀ መንገድ በማቅረብ መፍትሔ እንዲያገኝ አቅም ስለሚሆን መንግሥት እነዚህ ተቋማት በየዘርፉ እንዲቋቋም ዕገዛ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት