Sunday, February 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የባከኑ ሐሳቦች!

ሰላም! ሰላም! ባርኔጣዬን አውልቄ የአክብሮት ሰላምታዬን ሳቀርብላችሁ በከፍተኛ ወገናዊ ፍቅር ነው። ወገናዊ ስል ለሰብዓዊ ፍጡራን በሙሉ መሆኑንም ተገንዘቡልኝ፡፡ አንዳንድ ነገረኞች የማልፈልገው መቧደን ውስጥ ከተውኝ፣ ‹አንበርብር ምንተስኖት ድለላ አልሳካ ሲለው የእነ እከሌን ቡድን ተቀላቀለ› ብለው የአፍ ማሟሻቸው እንዳያደርጉኝ ሥጋት ይዞኝ ነው ይህንን ማሳሰቢያ የማቀርበው፡፡ እኔ አንበርብር ምንተስኖት ፈጣሪ በአምሳሉ ለፈጠራቸው ሰብዓዊ ፍጡራን ብቻ ሳይሆን፣ ለእንስሳትና ለዕፅዋት በሙሉ ልዩ ፍቅር እንዳለኝም ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ግን የእዚህ ዘመን ነገረኞች ምን ሆነን ነው የሆነ ቡድን ውስጥ መለጠፍ የምንወደው? እኔ ነፍስ ካወቅኩበት ጊዜ ጀምሮ ኳስ ወይም ሩጫ ወይም የደቦ እርሻ እንጂ ሰውነት የቡድን ሥራ አይፈልግም፡፡ ይፈልጋል እንዴ? እኔ እኮ ግራ ገባኝ እናንተ? ‹‹በሸንጎ ቢረታ ሚስቱን ገብቶ መታ…›› አሉኝ አዛውንቱ ባሻዬ በቀደም ዕለት፡፡ ‹‹ማን ነው እሱ?›› ስላቸው፣ ‹‹ማንነቱ ምን ይሠራልሃል? ዝም ብለህ ከምሳሌው ተማር። ምነው አንተም በማንነት ስም የሚቀነቀን የእኔነት አባዜ አለብህ እንዴ?›› ብለው ቆጣ አሉ። ‹‹ለነገሩ እያንዳንዱ ጥቃቅን ነገር ሳይቀር ፖለቲካዊ አጀንዳ የመያዙ ሚስጥር እኮ በቡድንተኝነት ፖለቲካ መቀፍደዱ ነው…›› የሚለኝ ምሁሩ ልጃቸው ነው፡፡ ይገርማል!

ምን ልበላችሁ በቃ አንዲት እርግብ ከትናንት ወዲያ ተመርቆ ከተከፈተው የእከሌ ሕንፃ መስታወት ጋር ተጋጭታ ሕይወቷ አለፈ ብሎ አንዱ ሲያወራው ሌላው ተቀብሎ፣ ‹‹የሰው አልበቃ ብሏችሁ ደግሞ ምንም የማያውቁትን እንስሳት መግደል ጀመራችሁ?›› ብሎ ኮሜንት ይሰጣል። ያዝ እንግዲህ ይባልልኛል። አንዱ በቀደደው መንቆርቆር ነው፣ ግር ብለን እንነዳዳለን። ‹የእከሌ ትርፍ አንጀት ፈንድቶ ወደ ሕክምና ጣቢያ ሳይደርስ ሕይወቱ አለፈ ሲባል፣ ሰላሳ ምናምን ዓመታት ሙሉ ገዝታችሁ በአቅራቢያችን በፍጥነት የምንደርስበት አንድ የረባ ክሊኒክ ወይም መናኛ ሆስፒታል የለም…›› ብሎ መጀመር ብቻ ነው የሚጠበቅበት። ሌሎቻችን መግተልተል ነው። ‹ደላላው አንበርብር ምንተስኖት በመረጃ ላይ ተመሥርተን ማሰብ ትተን በስማ በለው ማሰብ ጀምረናል አለ…› ቢባል፣ ለምሳሌ ስንት ምሁር ባለባት አገር በማይም ደላላ እንመከር ማለት ብቻ ነው የሚጠበቅባችሁ። ቡድን አደራጁ እንጂ ተከታዩ ሺሕ ነው!

እናላችሁ የሰሞነኛው የባህር በር የማግኘት ጉዳይ ላይ ተደርቦ ይኼ በተነዱበት መነዳትና ያለ ምክንያት ማሰብ በየአቅጣጫው ሲወረኝ፣ እውነቴን ነው የምላችሁ ነገር ሁሉ ይሰለቸኝ ጀምሯል። ለምን የሚሉት ጥያቄ ጠፍቷል፣ ተሰዶብናል። የት? እንዴት? መቼ? ለምን? ቀብረናቸዋል። አስቡት እስኪ እንደ ‹ደንባራ በቅሎ ቃጭል አንጠልጥሎ› ስንሆን። እናማ ተማርኩ፣ በቃሁ፣ አወቅኩ የሚለው ደግሞ ባሰ። በቀደም ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር አንድ ካፌ ውስጥ ማኪያቶ ስንጠጣ አንዱ ድንገት ደርሶ ገና ሳይቀመጥ፣ ‹‹ጎበዝ እንዴት ነው ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መልስ በየቦታው ግጭት ተባብሶ እያለ፣ ይህንን ሁሉ ታንክና ሮኬት ይዘን ወደ ቀይ ባህርና ህንድ ውቅያኖስ ልንዘምት ነው እንዴ?›› ብሎ ጀመረላችኋ። እንኳን ይህችን የዝንብ ጠንጋራ ቀርቶ የዝንብ ወፈፌም እናውቃለን አልኩና በልቤ፣ ‹‹ቢል ታመጣልን?›› አልኩት አስተናጋጁን። ‹‹እስኪ ይህንን ሰውዬ ወሬውን እናስጨርሰው…›› ሲለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ሰውዬው ፋታ ሳይሰጠን፣ ‹‹አዬ እንደ ዘንድሮ አያያዛችን ከሆነ ለማንም የምንመለስም አይመስልም…›› ብሎ ብቻውን ሳቀ። አሳሳቁ ታዲያ ቲፎዞ ፍለጋ ስለሚመስል ነገረ ሥራው አላማረኝም፡፡ ድንቅ ነው!

‹‹የበላችው ያስመልሳታል በላይ በላዩ ያጎርሳታል…›› የሚለው አባባል ትዝ ብሎኝ ፈገግ ስል ለእሱ የሳቅኩለት መስሎት፣ ‹‹ግድ የለም ዛሬ እኔ የማኪያቶውን ሒሳብ ልዝጋላችሁ…›› አለን። ይኼውላችሁ እንግዲህ ገና ለገና ጥርስ ለጥርስ ተለካካን ብለን፣ በአጋጣሚምም በስህተትም ብርጭቋችን ተጋጨ ተብሎ እዚህ ደረጃ ደርሰናል። የሰውዬውን ሁኔታ መልሼ መላልሼ ሳስበው ስለተበሳጨሁ፣ ‹‹እኔ አሁን ሥራ ስላለብኝ እቸኩላለሁ…›› ብዬ ለመሄድ ስነሳ ምሁሩ የባሻዬ ልጅም አብሮኝ ተነሳ፡፡ ሰውዬው ግን ወሬው ስለተቋረጠበት ተበሳጭቶ ነው መሰል፣ ‹‹እኔ እኮ ስንትና ስንት የተጣራ መረጃ ልነግራችሁ ስል ነው የምትጣደፉት…›› እያለ ሊያግባባን ሲሞክር ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹የአንተ ወሬ የተጣራ መሆን አለመሆኑ እንዳለ ሆኖ ግርድፉን ስንሰማው ግን በጣም ጥሬ ነው…›› ብሎት ተለያየን፡፡ ይሻላል!

መቼስ አንዳንዴ ስሜታዊ እየሆንኩ ጨዋታዬ እንደ ዘመኑ ተቃዋሚዎችና ደጋፊዎች ድርቅ ይላል አይደል። ምንላድርግ ቀልድ ጠፋ። ማለቴ ቀልዱ ሁሉ ያው እንደምታዩት የምር የምኖረው ኑሮ ሆኗል። ቀልድ አሯሯጫችን መሆኑ ቀርቷል። እንደ ሳይንስ ፊክሽን ማለቴ ነው። የዛሬን አያድርገውና በቀደሙት ዘመናት አሁን በእጃችን የጨበጥናቸውና ኪሳችን የከተትናቸው፣ ቆፍረን የቀበርናቸው ቴክኖሎጂዎችና የጦር መሣሪያዎች ትናንት ተረት ተረት ነበሩ። ቀልድና ሳይንስ ፊክሽን የሚያመሳስላቸው ይኼው ነው። ትናንት ቀልድና ስላቅ እንደ ዛሬው እያንዳንዳችን የሚያጋጥመን የምኖረው ሀቅ አልነበረም። በአብዛኛው ነው የምላችሁ። ዘመኑ የመረጃና የማስረጃ ነውና ማስረጃዬን ላቅርብ። በቀደም አንድ ቪላ ቤት እያሻሻጥኩ ነበር። ገዥኛ ሻጭ ስለዋጋ መናር ሲጨቃጨቁ አንደኛው በንዴት፣ ‹‹አንተ አሁን እየሸጥክልኝ ያለኸው ዋጋ መሬት ላይ ያለውን እውነታ አያሳይም…›› ሲለው፣ ‹‹አንተስ ብትሆን የግንባታ ማቴሪያሎችን ስትሸጥልኝ የነበረው ከእውነታው ጋር እየተጋጨህ አልነበር እንዴ…›› ብሎ ሲስቅበት ፀጥታ ሰፈነ። ‹ዕባብ ለዕባብ ይተያያል ካብ ለካብ› አትሉም ታዲያ!

ታዲያላችሁ ሰዎቹ ተቀላልደው ግብይቱን ፈጽመው ኮሚሽኔን በአካውንቴ ተቀባብዬ ወደ ቤቴ ስጣደፍ ብሄድ፣ ማንጠግቦሽ ቤቱ እንደተዝረከረከ ለጥ ብላ ተኝታለች። ሰዓቴን ሳይ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ይላል። እንግዲህ ተመልከቱ ይኼን እያየ እየሰማ ራሱ የኢትዮጵያን ዕድገት የሚጠራጠር አለ? ለነገሩ የእኛ እንቅልፍ በዕድገት የሚረዝም በረሃብ የሚያጥር አይደለም፡፡ እሱ በጥበቡ ሲሠራን በተፈጥሯችን ተኙ ብሎ ፈጥሮናል። ባሻዬ ይኼን አስተሳሰቤን ስለሚጋሩኝ፣ ‹‹የእኛ ጠላታችን ከድህነት ጎን ለጎን የሚቀሰቅሰን ብቻ ነው…›› ይሉኛል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ቀስቃሽ በአየቅጣጫው የዘመተበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ‹‹…ያለበት ሁኔታ ነው ያለው…›› የሚለው የካድሬዎችና የቴሌቪዥን ጣቢያው ካድሬ አከል ጋዜጠኞች አባባል ትዝ ሲለኝ ነው ሁኔታን ሰንቀር ያደረግኩት፡፡ የካድሬና የካድሬ አከል ጋዜጠኞች አነጋገርና የዘንድሮ ኑሮ ግራ ያጋባን የለ? እኔም አንዳንዴ ስወዛገብ ወሬዬ ሁሉ እንዲያ ለመሆን እየቃጣው፣ ‹‹አንበርብር ዛሬ የት ነው የዋልከው…›› የሚል ጥያቄ መስማት ልማዴ ነው፡፡ ክፉ ልማድ!

የአዋዋልን ነገር ካነሳን እኔ ያው እንደምታውቁት ይህ የድለላ ሥራዬ የማያደርሰኝ ቦታ የለም፡፡ አሁን ሳሪስ ነው ተብዬ ወዲያው መርካቶ ብገኝ አይገርምም፡፡ ፈረንሣይ ለጋሲዮን ታይቼ ከዚያ ካዛንቺስ ስታይ የሚገረሙ ቢኖሩም እኔ ግን አይደንቀኝም፡፡ መቼ ዕለት ነው አንዱ፣ ‹‹አንበርብር በቀደም ዕለት ለቡ ሙዚቃ ሠፈር ዓይቼህ ትንሽ ቆይቶ ሲኤምሲ ከች ስትል ተደንቄ ነበር…›› እያለ ሲያደራ እየነዳው የነበረውን ዘመናዊ ‹ኢንቪንሲብል› በምን ፍጥነት እንዳስከነዳሁበት በገደምዳሜ እየነገረኝ ነበር፡፡ እሱ ትናንት ከሚኒ ባስ ወደ ሚኒባስ እየተገላበጠ ያካለለውን ከተማ ዛሬ በንፋስ አመጣሽ ሀብት በዘመናዊ መኪና ሲርመሰመስበት፣ እኔም ለፈጣሪዬ ክብርና ምሥጋና ይግባውና በሌላ ሀብታም ዘመናዊ ቪኤይት መንፈላሰሴ ነበር ያናደደው፡፡ ለነገሩ ቅና ያለው በምን ይቀናል እንዲሉ ሆኖ እንጂ፣ እኔና እሱ እኮ አሁን ካለበት ደረጃ አንፃር የሚያፎካክረንም ሆነ የሚያወዳድረን ነገር አልነበረም፡፡ እዚህ ላይ ግን ለፍተው ጥረው ያገኙ ባለፀጋዎችንና በአቋራጭ የከበሩ ንፋስ አመጣሾችን እኩል እንዳናይ አደራ እላለሁ፡፡ ለማንኛውም መንገር ስለነበረብኝ፣ ‹‹በአንድ አዳር የመጣ ገንዘብም ያልቅና ያስተዛዝበናል ይኼ ቀን ያልፍና…›› ብዬው እያፏጨሁ በቆመበት ጥዬው ሄድኩ፡፡ ንገሩኝ ባይ!

በሉ ልንሰነባበት ነው። ብቻ ይህ ሳይሠሩ የሚከበርበት ነውረኛ ጊዜ ነገር ግርም እያለኝ፣ ‹‹ሰው ከሰውነት ወደ እንስሳነት ተቀይሯል እንዴ? ለምን ይሆን ግን እኛስ ብንሆን በዕውቀቱና በጉልበቱ ከሚማስነው ይልቅ ጊዜ ላነሳው ምድረ ወረበላ የምናሸረግደው?›› ብዬ ሳልጨርስ ማንጠግቦሽ ትዝ አለችኝ። አስተኛኘቷ ደስ አላለኝም። ከመጮኼ በፊት አንዴ ልሞክራት ብዬ ነካ አደርጋታለሁ፣ ‹‹የቀሰቀሷቸው ደንበኛ አሁን መነሳት አይችሉም። እባክዎ ከሰዓታት በኋላ እንደገና ይሞክሩ…›› ብለኝ ተገላብጣ ተኛች። ደህና ከሆንሽስ ብዬ ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር ተያይዘን ወደ ግሮሰሪያችን አመራን። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ የማንጠግቦሽን ኩመካ ሰምቶ ሲያበቃ፣ ‹‹አንዳንዱ እንቅልፍ እኮ ለበጎ ነው አንበርብር። ባንነቃ ባንቀሰቀስ የሚሻለን ጊዜ  አለ ሰሚ የለም እንጂ..›› ሲለኝ፣ ‹‹አንዳንዴ ሳምንቱ ቅጣቱ ሲከብድ፣ ምንም አይሳካም ከእሑድ እስከ እሑድ…›› ብሎ አንዱ በአንድ ወቅት ያጨደው መከራ ትዝ አለኝ። ምነው የዘንድሮ ባሰ አልኩ። መነካት በማይገባን ጎናችን እየተነካን፣ መቀስቀስ በሌለብን ሰዓት እየቀሰቀሱን እኛም አቤት እያልን ከእሑድ እስከ እሑድ ከትውልድ እስከ ትውልድ፣ ከዓመት እስከ ዓመት ከሚሊኒየም እስከ ሚሊኒየም፣ እንዲሁም እስከ ዛሬ የተባላነው አይበቃም ጎበዝ? እስከ መቼ በእንቅልፍ ላይ እንቅልፍ? እስከ መቼ? እስከ መቼ? ከዓመት እስከ ዓመት፣ ከእሑድ እስከ እሑድ መና ይቀራል? ሌላው ቢቀር ለዕድሜ እንዘን፡፡ ሺሕ ዓመት ላይኖር ራሳችንንም አገራችንንም አናሰቃይ፡፡ አይሻልም እንዴ!

እኔና ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ግሮሰሪያችን ስንደርስ ጢም ብላ ሞልታለች፡፡ በጮሌው አስተናጋጅ እየተመራን ጥግ ላይ ቦታ ተገኝቶልን ተቀመጥን፡፡ የወርኃ ጥቅምት መገባደጃ አካባቢ የምሽት ቅዝቃዜ ነው መሰል የግሮሰሪ ደንበኞች ከበረንዳው ይልቅ ውስጥ መከማቸታቸው የገባኝ ከተቀመጥን በኋላ ነበር፡፡ ያዘዝነው ቢራችን መጥቶልን ጎንጨት ማድረግ ስንጀምር፣ ‹‹አዳሜ መሸታ ቤት ተጎልተህ አረቄ ስታንቃርር ላይህ ላይ ታሪክ እየተሠራ ነው…›› የሚል ድምፅ ከውጭ ተሰማን፡፡ ተናጋሪውም ታዋቂው የሠፈራችን የጠጅ ቤት ደንበኛ አንድ አምስቱን ልፎ እንደሚለፈልፍ የታወቀ ነበር፡፡ ራሱን ከጨዋታው አስወጥቶ እኛን በነገር ሲወጋን፣ ‹‹አንተስ ከዝንቦች ፏፏቴ ጠጅ ቤት አንቡላህን ልፈህ አይደል እንዴ የመጣኸው…›› የሚል ሌላ ድምፅ ተከተለ፡፡ ይህንንም እናውቀዋለን፣ ማዶ ሠፈር የአንበሳ ማሰሪያ አረቄ ቤት የዘወትር ታዳሚ ነው፡፡ ‹‹እነሱስ ጠጅና አረቄያቸውን አስገብተው ነው የሚተራረቡት፣ እኛስ ቢራና ጅን የምንለጋው ምን ልንባል ይሆን…›› የሚለው ደግሞ የግሮሰሪያችን የዘወትር የሞቅታ መድረክ መሪ ነው፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ፖለቲከኞቻችንም እንዲህ በሠለጠነ መንገድ ቢተራረቡ እኮ ስንትና ስንት ለአገር የሚጠቅሙ ሐሳቦች አይባክኑም ነበር…›› እያለኝ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጀምሮ እስከ ሰሞኑ የቀይ ባህር ጂኢ ፖለቲክስ ጉዳይ ሲተነትንልኝ የባከኑ ሐሳቦቻችን እያስቆጩኝ ነበር፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት