Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአላዋቂዎች ሊሞክሩት የማይገባው የባህል ሕክምና

አላዋቂዎች ሊሞክሩት የማይገባው የባህል ሕክምና

ቀን:

የባህል ሕክምና በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይ በቻይና፣ በህንድ፣ በተለያዩ የላቲን አሜሪካና የአፍሪካ አገሮች በሰፊው ይሰጣል፡፡ አሰጣጡ ደግሞ በዘፈቀደ ሳይሆን ዕውቀትን መሠረት ማድረግ እንደሚገባው፣ በባህል ሕክምና ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

የባህል ሕክምና ከዘመናዊ ሕክምና የተለየ ጥበብ የሚፈልግም ነው፡፡ በዘመናዊ ሕክምና ማንኛውም የሕክምና ባለሙያ በፈለገው ጊዜ ‹‹አገልግሎቱን እሰጣለሁ›› ማለት እንደማይቻለው ሁሉ፣ የባህል ሕክምናንም ማንም እንደፈለገ የሚሞክረው አይደለም፡፡

የሕክምና አገልግሎቱ ከበፊት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ቢሆንም፣ እንደ ዘመናዊው ትኩረት እያገኘ አይደለም፡፡ ይህም ጥቂት ዕውቀት ወይም ምንም ዕውቀት የሌላቸው በድፍረት እንዲሠሩበት ዕድል ፈጥሯል፡፡

በዘርፉ ተሰማርተናል የሚሉ ሰዎች አገልግሎቱን እንዳሻቸው እንዲሰጡ አስችሏል፡፡ በኢትዮጵያም በተሽከርካሪዎች፣ በመብራት ፖሎች፣ በአጥር እንዲሁም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ማስታወቂያ በመለጠፍ ‹‹የባህል ሕክምና አገልግሎት እንሰጣለን›› የሚሉ በዝተዋል፡፡ 

‹‹በኢትዮጵያ በባህል ሕክምና ዘርፍ ከሚሠሩ ተቋማት አንዳንዶቹ ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸው ሲሆኑ፣ አብዛኛዎቹ ግን ሕጋዊነት የሌላቸው ናቸው፤›› ሲሉ፣ የኢትዮጵያ የባህል መድኃኒት አዋቂዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ሐጂ ሼክ ዓሊ አደም ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ10 ሺሕ የሚበልጡ ባህላዊ የሕክምና ተቋሞች ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸው ናቸው፡፡

የባህል ሕክምና ከበፊት ጀምሮ በተለምዶ የሚሰጥ ሲሆን፣ በዘርፉ ላይ የሚሠሩ አብዛኞቹ ባለሙያዎችም ከቅድመ አያቶቻቸው በወረሱት ልምድ መሠረት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ የባህል ሕክምና ተጠቃሚ እንደሆነ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ትክክለኛና ወጥ የሆነ አሠራር ዘርፉ ላይ ስለማይታይ ሕገወጥ የባህል ሕክምና እንዲስፋፋ፣ የዜጎች የጤና ደኅንነት አደጋ ላይ እንዲወድቅና በመስኩ የሠለጠነ የሰው ኃይል እንዳይኖር አድርጎታል ብለዋል፡፡

የኪንታሮት፣ የስንፈተ ወሲብ፣ የአባላዘር፣ የቆዳና ሌሎች የበሽታ ዓይነቶችን የሕክምና አገልግሎቶች በሚሰጡ ተቋማት የሚሠሩ ባለሙያዎች፣ ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ የሆኑና በሥራቸው በቂ የሆነ ልምድ ያላቸው ሊሆኑ እንደሚገባም አክለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ገንዘብ ሰጥተው፣ ፈቃድ አውጥተው የሚሠሩ ተቋማት እንዳሉ ጠቅሰው፣ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ባለሙያዎች ማንነታቸው እንኳን የማይታወቅ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የባህል ሕክምና ትልቅ ደረጃ እንዲደርስ መንግሥት ፖሊሲዎችን መከለስ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የባህል ሕክምና እንደ ዘመናዊ ሕክምና ትምህርት ቤት ውስጥ የሚሰጥ አለመሆኑን ገልጸው፣ እንደ በሽታው ዓይነት የሕክምና ባለሙያዎችም የሚሰጡት አገልግሎት የተለያየ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ስመ ጥር የሚባሉ የባህል ሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት አሉ የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፣ እነዚህ ተቋማት የተሻለ ሕክምና ለማኅበረሰቡ ተደራሽ በማድረግ የበኩላቸውን ኃላፊነት እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ ትክክለኛ መሥፈርት አሟልተው የባህል ሕክምና አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት 300 መሆናቸውን ገልጸው፣ የመንግሥት ሠራተኛ ሆነው በዘፈቀደ ‹የባህል ሕክምና አገልግሎት እንሰጣለን› እያሉ በሕገወጥ መንገድ የተሰማሩ አካላት እንዳሉ አመልክተዋል፡፡

አብዛኛው የባህል ሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት የራሳቸው አሠራር እንዳላቸውና ለሕክምናው አገልግሎት የሚጠቀሙትን ግብዓት የተለያዩ ገጠራማ አካባቢዎች ሄደው በመልቀም መድኃኒት እንደሚቀምሙ አብራርተዋል፡፡

ለባህል ሕክምና መድኃኒትነት የሚያገለግሉ ግብዓቶች ከሦስት ዓይነት ነገሮች የሚዘጋጁ ሲሆን፣ መድኃኒቱንም የሚያዘጋጀው አካል ራሱ ባለሙያው ብቻ መሆን እንዳለበት ሆኖም በዘፈቀደ የሚሠሩና ኅብረተሰቡን ለአደጋ የሚያጋልጡ መኖራቸውን አክለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን የጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ቁጥጥር ዳይሬክተር ሲስተር በድሪያ ሁሴን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በከተማዋ እስካሁን 80 የሚሆኑ የባህላዊ ሕክምና ተቋማት ተመዝግበው አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡

በከተማዋ የባህላዊ ሕክምና አገልግቱን ለማስፋፋት ባለሥልጣኑ በማኅበር እንዲደራጁ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፣ እስካሁን ሕጋዊ ሰውነት የሌላቸው ተቋማት እንዳላጋጠሙ አስረድተዋል፡፡

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የጤና ተቋማት ባለሙያዎች ቁጥጥር ዳይሬክተር እመቤት አማዶ በበኩላቸው፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በኩል ሕጋዊ ፈቃድ አግኝተው አገልግሎት የሚሰጡ ስድስት ባህላዊ የሕክምና ተቋማት አሉ፣ የባህል ሕክምናውን የሚሰጡ ተቋማትም በዓመት ሁለት ጊዜ ‹‹ምን ዓይነት ሥራ እየሠሩ ነው?›› በሚል ክትትል ይደረግባቸዋል ብለዋል፡፡

እነዚህም ስድስት ተቋማት በየትኛውም ጊዜ በሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ስህተት ከሠሩ ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው ገልጸው፣ በዘርፉ የሚሠሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመድኃኒትና ምግብ ቁጥጥር ባለሥልጣን ባስቀመጠው መሥፈርት መሠረተ የሚገመገሙ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

በከተማዋ በርካታ ባህላዊ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት እንዳሉና በክፍለ ከተማ ደረጃ ቁጥጥር የሚደረግባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ተቋማቱን ለመቆጣጠር በሚኬድበት ጊዜ በራቸውን ዘግተው እንደሚጠፉ፣ ይህም የሚሆንበት ምክንያት ለአንድ ሳምንት ያህል ለመድኃኒትነት የሚያገለግሉ ግብዓቶች ለመልቀም ወደ ገጠራማ ሥፍራዎች ስለሚሄዱ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በተቋማት ደረጃ እስካሁን ምንም ዓይነት ቅሬታ እንዳልደረሳቸው የተናገሩት ዳይሬክተሯ፣ የባህል ሕክምና መድኃኒት የሚያዘጋጀው ባለሙያ እዚያው ክፍለ ከተማ ላይ በመሥፈርቱ መሠረት የተመዘገበ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

የባህል ሕክምና አገልግሎት ከዘመናዊ የሕክምና ሥርዓት የተለየ በመሆኑ፣ የባህል ሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች አገልግሎቱን ለመስጠት ‹‹መሥፈርቱን ያሟላሉ ወይ?›› የሚለውን የሚገመግም መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት በመቀመጫው አካባቢ ኪንታሮት ወጥቶበት ወደ ባህል ሕክምና ሄዶ አገልግሎት ያገኘው አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ወጣት፣ ዘመናዊ የተባሉ ሆስፒታሎች ሄዶ የሕክምና አገልግሎት ቢያገኝም፣ መልሶ እዚያው ቦታ ላይ እንደ አዲስ እየወጣበት ሲሰቃይ መክረሙን ይናገራል፡፡፡

በኪንታሮት በሽታ ከአንድ ዓመት በላይ መሰቃየቱን የሚናገረው ወጣቱ፣ አንድ የባህል ሕክምና አገልግሎት የሚሰጥ ተቋማት ጋር ሄዶ በመታከም ሙሉ ለሙሉ ከበሽታው ማገገም መቻሉን ለሪፖርተር ያስረዳል፡፡

የባህል ሕክምናውን ሲወስድ ለአንድ ወር ያህል መሰቃየቱን፣ ነገር ግን ከብዙ ስቃይ በኋላ መዳን እንደቻለ ገልጾ፣ መንግሥት የባህል ሕክምና ላይ በተገቢው መንገድ በመሥራት የሕክምና ዘርፉ ላይ ለውጥ ማምጣት ይችላል ይላል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃም የተለያዩ ታዋቂ የሆኑ የባህል ሕክምና ተቋማት እንዳሉ፣ እነዚህም ተቋማት ከአንዳንድ ዘመናዊ ከሚባሉ የሕክምና ተቋማት የተሻሉ መሆናቸውን ይናገራል፡፡

ሕገወጥ በሆነ መንገድ የባህል ሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት መኖራቸውን፣ እነዚህ ተቋማት በመስፋፋታቸው ብቻ በባህላዊ ሕክምና አገልግሎት ማግኘት የማይፈልጉ ሰዎች መኖራቸውን ያስታውሳል፡፡

የባህል ሕክምና ከዘመናዊ ሕክምና አንፃር ሲታይ በጣም ጥንቃቄ የሚያስፈልገው እንደሆነ ገልጾ፣ አብዛኛውን ጊዜም የጥንቃቄ ጉድለት ስለሚታይ፣ በርካታ ተቋማት ችግር ውስጥ ሊገቡ መቻላቸውን ያስረዳል፡፡

በተመሳሳይ በስኳር በሽታ ለረዥም ጊዜ እየተሰቃየ የሚገኝ አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ወጣት ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ ከስኳር በሽታ ለማገገምና ጤናማ ለመሆን ዘመናዊም ሆነ ባህላዊ ሕክምና እየተጠቀመ ነው፡፡

በአንድ ወቅት አንድ ባህላዊ የሕክምና ተቋማት በመሄድ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ ለአንድ ሳምንት ያህል የሕክምና አገልግሎቱን ወስዶ ብዙም ክትትል ሳያደርግ መቅረቱን ይናገራል፡፡

ወደ ባህላዊ ሕክምና ለመሄድ ዋነኛ ምክንያት ጓደኛው መሆኑን የሚገልጸው ይህ ወጣት፣ ከዚህ በፊት ጓደኛው በኪንታሮት በሽታ ታክሞ መዳኑን ያስታውሳል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ከዓለም 88 በመቶ ያህሉ ሕዝብ የባህል ሕክምናን በአማራጭነት እንደሚጠቀም ያሳያል፡፡ ከ194 የድርጅቱ አባል አገሮች 170ው የባህል ሕክምናን በአማራጭነት የሚጠቀሙ መሆናቸውንም ለድርጅቱ ሪፖርት አድርገዋል፡፡

ድርጅቱ ለአማራጭ ሕክምናዎች ዕውቅና የሰጠ ሲሆን፣ የባህል ሕክምናን ከዘመናዊው አቀናጅተው መሥራት ለሚፈልጉም ድጋፍ ያደርጋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2014 – 2023 የሚቆይ የባህል ሕክምና ስትራቴጂ ማውጣቱም ይታወሳል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...