በኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ መብቶችና ሕጎች በተገቢ ሁኔታ እየተተገበሩም ሆነ ዕውቅና እየተሰጣቸው አይደለም ሲል፣ የአካባቢ ጥበቃ መብት ላይ የሚሠራው የሥርዓተ ምኅዳር ፍትሕ ኢትዮጵያ (ECO Justice Ethiopia) አስታወቀ፡፡
ይህ የተገለጸው ቁም ለአካባቢና የሥርዓተ ምኅዳር ፍትሕ ኢትዮጵያ በጋራ በመሆን፣ ‹‹አካባቢያዊ መብቶችና የሕዝብን ጥቅም ለማስከበር የሚደረግ ሙግት፣ ጽንሰ ሐሳብ፣ የሕግ ማዕቀፍና ተጨባጭ ፈተናዎቹ በኢትዮጵያ፤›› በሚል ጥቅምት 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ዓውደ ጥናት ባዘጋጁበት ወቅት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ሰዎች ንፁህና ጤናማነቱ በተጠበቀ አካባቢ መኖር እንዳለባቸው ቢጠቅስም፣ ብዙ ጊዜ የአካባቢ ብክለት ሲደርስ፣ በአካባቢያዊ ተፅዕኖ ማኅበረሰቡ ጉዳት ሲደርስበት ከመብት ጥሰት ጋር በማያያዝ የሚጠይቅ የለም ሲሉ፣ የሥርዓተ ምኅዳር ፍትሕ ኢትዮጵያ መሥራች አቶ እስከዳር አውግቸው ተናግረዋል፡፡
የአካባቢያዊ መብት ምን እንደሆነ የሚገነዘብም ሆነ መብቱንም የሚጠይቅ ኅብረተሰብ፣ እንዲሁም ለዚህ የመብት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ የመንግሥት አካልም ሆነ የፍርድ ቤት ክርክሮች የሉም ብለዋል፡፡
ከአካባቢያዊ መብቶች አጠባበቅ አንፃር በአገሪቱ በርካታ የሕግና የአተገባበር ችግሮች የሚታዩ በመሆናቸው፣ በእነዚህ ላይ ውይይት በማድረግ፣ የመፍትሔ ሐሳቦችን በማመንጨት፣ ሁሉም የሚመለከተውን ኃላፊነት በመወጣት፣ የመብቶቹ አተገባበር እንዲፈጠር፣ እንዲሁም ከአካባቢያዊ መብቶች ጋር በተገናኘ በብሔራዊና በዓለም አቀፍ የተገኙ ግኝቶች የተገለጸበት ውይይት ተደርጓል፡፡
በዓውደ ጥናቱም ከአካባቢያዊ መብቶች ጋር በተገናኘ ከተለዩት ችግሮች ውስጥ የአካባቢያዊ ሕጎች በተሟላ ሁኔታ ያለ መኖር፣ የአስፈጻሚ አካላት ተገቢውን ቁጥጥር በማድረግ የሚጠበቅባቸውን ያህል ዕርምጃ ያለ መውሰድ፣ አግባብነት ያለው የአቅም ማጎልበቻና የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሮች ያለ መተግበራቸውና በዚያ ሊገኝ የነበረው ውጤት ያለ መመዝገቡና የተወሰኑ የመንግሥት ተቋማትን ጨምሮ የበካዮች ለአካባቢያዊ ሕጎች አተገባበር እንቅፋት መሆናቸው በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡
የሥርዓተ ምኅዳር ፍትሕ ኢትዮጵያ (ECO Justice Ethiopia) በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተመዝግቦ ከመስከረም 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሕጋዊ መንገድ በአካባቢ ጥበቃና በአየር ንብረት ለውጥ ፍትሕ ላይ እየሠራ የሚገኝ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡
ድርጅቱ በአካባቢ ጥበቃና በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ዙሪያ ኢትዮጵያ የአካባቢና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤን በተመለከተ ጠቃሚ የሆኑ ዓለም አቀፍ ሕጎችንና ስምምነቶችን እንድትፈርምና ቀደም ሲል የፈረመቻቸውንም በአግባቡ እንዲተገበሩ ማገዝ፣ በብሔራዊ ደረጃ የፕላስቲክ ብክለትን የተመለከቱ አዎንታዊ ሕጎች እንዲወጡና እንዲተገበሩ ተፅዕኖ መፍጠር፣ የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ በሚደረጉ ዓለም አቀፍ ድርድሮች ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉና ሌሎች ከፍተኛ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ አገራዊ መድረኮችን ማዘጋጀት ከሚያከናውናቸው ሥራዎች መካከል ተጠቃሽ እንደሆኑ አቶ እስከዳር አስረድተዋል፡፡