Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የዋጋ ግሽበቱ እንደ አቅማችን እንዳናበድርና ተበዳሪዎችም እንዳይከፍሉ እያደረገ ነው›› አቶ ፍጹም አብረሃ፣ የአሚጎስ የቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ

አሚጎስ የቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበር፣ በተቋም ደረጃ ለመመሥረቱ መነሻው ጓደኛሞች በየወሩ በቁጠባ መልክ የሚቆርጡት ተቀማጭ ገንዘብ ነው፡፡ በ20 ሺሕ ብር ካፒታል በ20 ጓደኛሞች በ2005 ዓ.ም. የተቋቋመው ማኅበሩ፣ አሁን ላይ ከ6000 በላይ አባላትን ይዟል፡፡ የሀብት መጠኑን ሁለት ቢሊዮን ማድረስ ችሏል፡፡ በመጪው አምስት ወራት ደግሞ የሀብት መጠኑን አምስት ቢሊዮን ብር ለማድረስ የሚያስችል አቅም መፍጠሩም ይነገራል፡፡ አቶ ፍፁም አብርሃ የኅብረት ሥራ ማኅበሩ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ዳዊት ቶሎሳ አነጋግሯቸዋል፡፡

‹‹የዋጋ ግሽበቱ እንደ አቅማችን እንዳናበድርና ተበዳሪዎችም እንዳይከፍሉ እያደረገ ነው›› አቶ ፍጹም አብረሃ፣ የአሚጎስ የቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ሪፖርተር፡- አሚጎስ የቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበር የተመሠረተበት ግብ ምንድነው?

አቶ ፍፁም፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ የኅብረት ሥራ ማኅበር በ1870ዎቹ በጀርመን እንዲሁም በእንግሊዝ ውስጥ እንደተጀመረ ይነገራል፡፡ እኛ አገር ዕድርና ዕቁብ ተብሎ እንደሚታወቀው በማኅበረሰብ ውስጥ የተጀመረ የፋይናንስ አገልግሎት ነው፡፡ ኅብረት ሥራ ማኅበራት በሌላው ዓለም ትልቅ ደረጃ ደርሰዋል፡፡ በአንፃሩ በኢትዮጵያ ብዙም ስላልተሠራ ወደተፈለገው ደረጃ ደርሰናል ማለት አይቻልም፡፡ በአሚጎስ በኩል በኢትዮጵያ ትልቅ የኅብረት ሥራ የፋይናንስ ተቋም እንዲሁም ባንክ የማቋቋም ዓላማን አንግበን እየሠራን ነው፡፡ ዋናውና ትልቁ ዓላማ ግን ሰዎች የቁጠባ ባህላቸውን በደንብ እንዲያሳድጉና እንዲያዳብሩ ማድረግ ነው፡፡ ብድር እየወሰዱ በተለያዩ ሥራዎች እንዲሰማሩ ማድረግ የሥራችን አንዱ ክፍል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሚጎስ ከተመሳሳይ የብድር ተቋማት ወይም ከባንኮች በምን ይለያል?

አቶ ፍፁም፡- ለምሳሌ ሰው በባንክ ስለቆጠበ ብቻ ብድር መውሰድ አይችልም፡፡ በአንፃሩ እኛ ለቆጠበ ሰው በአራት ወይም በሦስት ዕጥፍ ብድር እንሰጣለን፡፡ በሌላ በኩል ባንኮች አብዛኛውን ጊዜ ለባለሀብቶችና ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ላላቸው ብቻ ነው የሚያበድሩት፡፡ ከዝቅተኛው ማኅበረሰብ ክፍል ገንዘብ ከሰበሰቡ በኋላ ግዙፍ የኢኮኖሚ አቅም ለፈጠሩ ብቻም ያበድራሉ፡፡ እኛ ለቆጠበ ግለሰብ እናበድራለን፡፡ ለሚቆጥቡ ከ50 ሺሕ ብር እስከ አሥር ሚሊዮን ብር ብድር እንሰጣለን፡፡ ከዚህም ባሻገር ከብድርና ቁጠባ ውጪ የመድን አገልግሎት አለን፡፡ በሥራ ፈጠራ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሥልጠናና የማማከር አገልግሎትም እንሰጣለን፡፡ የቢዝነስ፣ የአካውንቲንግና የፋይናንስ አስተዳደር ሥልጠና ለአባላት እንሰጣለን፡፡ ጥሩ ለቆጠበ ሽልማትና የምሥጋና መርሐ ግብርም አለን፡፡

ሪፖርተር፡- የአሚጎስ አባል ለመሆን የሚያስፈልገው መሠረታዊ መሥፈርትና የአገልግሎት ሒደቱ ምን ይመስላል?

አቶ ፍፁም፡- አንድ ሰው ሲመዘገብ አክሲዮን ይገዛል፡፡ በየወሩ አንድ ሺሕ ብር ይቆጥባል፡፡ ማንኛውም ዕድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነ አባል የአሥር ሺሕ ብር አክሲዮን መግዛት አለበት፡፡ ይኼ ዝቅተኛው የአክሲዮን መጠን ሲሆን ከፍተኛው እስከ ሦስት ሚሊዮን ድረስ መግዛት ይችላል፡፡ እስካሁን ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ለአባላት ብድር የሰጠን ሲሆን፣ ከ3‚000 ሺሕ በላይ አባላት የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ለመኪና፣ ለቤት፣ ለቤት ዕቃ ግዥ፣ ለግብርና እንዲሁም ለሥራ ፈጠራ አገልግሎት ብድር ማመቻቸት ችለናል፡፡ ለምሳሌ አሚጎስ ሥራ ሲጀምር 14 ሺሕ ብር የተበደረ አባል ዛሬ ካፒታሉ ከአሥር ሚሊዮን በላይ ደርሷል፡፡ ሌላም አባል የሚስማር ፋብሪካ ገንብቶ ካፒታሉን 20 ሚሊዮን ማድረስ ችሏል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከ65 በመቶ በላይ የሚሆኑት ለመኪና ግዥ ተበድረው በትራንስፖርት አገልግሎት ተሰማርተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አብዛኛው የአገሪቱ የብድር አሰጣጥ ሒደት ከሦስት ወራት በላይ ይፈጃል፡፡ እናንተ በስንት ቀናት ውስጥ ብድር ትሰጣላችሁ?

አቶ ፍፁም፡- አሚጎስ የሚለይበት አሠራር ብድር የሚሰጥበት ጊዜ ነው፡፡ የአሚጎስ አባል ሆኖ ንብረት ማፍራት የሚፈልግ ሰው፣ አባል በሆነበት በአንድ ወር ጊዜና በሁለት ወር የሚሰጥ ብድር አለን፡፡ በዚህም መሠረት ለምሳሌ እስከ 2.5 ሚሊዮን ብር ድረስ በአንድ ወር ውስጥ መውሰድ የሚችሉበት አሠራር አለን፡፡ አንድ ሰው 200 ሺሕ ብር በፍጥነት ፈልጎ አንድ አራተኛውን ቆጥቦ ወይም 50 ሺሕ በማስቀመጥ መውሰድ ይቻላል፡፡ ብድሩ እየጨመረ ሲሄድ ለምሳሌ አንድ ሚሊዮን ብድር የሚፈልግ 30 በመቶ ቆጥቦ ብድሩን ማግኘት ይቻላል፡፡ ይህ ማለት በአንድ ወር ውስጥ መውሰድ ለሚፈልግ ነው፡፡ መውሰድ የሚፈልግበት የጊዜ ገደብ በጨመረ ቁጥር መቆጠብ የሚጠበቅበት መቶኛ እየጨመረ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ ዝቅተኛ የጊዜ ቆይታ ሦስት ወር ሲሆን፣ ክፍያው እስከ አሥር ዓመት ጊዜ ገደብ አለው፡፡ የወለዳችን ከፍተኛ መጠንም 15 በመቶ ነው፡፡ ይኼም በየወሩ አባሉ በከፈለ ቁጥር እየቀነሰ የሚሄድ ነው፡፡ ሌላው ከደመወዝ ዋስትና ጀምሮ ብድር እናመቻቻለን፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩን እየፈተነ የሚገኘው ምንድነው?

አቶ ፍፁም፡- ማኅበሩ በአሥር ዓመት የሥራ እንቅስቃሴው ውስጥ ያጋጠሙ ችግሮች አሉ፡፡ አሁን ያለው የዋጋ ግሽበት ማኅበሩን በእጅጉ እየፈተነው ነው፡፡ ግሽበቱ ማኅበሩ ባቀደው ልክ ብድር እንዳይሰጥና አባላትም ብድራቸውን እንዳይመልሱ እያደረገ ነው፡፡ በየጊዜው የሚጨምረው የኑሮ ውድነት የሺዎችን የመግዛት አቅም እያዳከመና የማኅበሩን የማበደር አቅምም እየወሰነው ነው፡፡ የሰላምና የፀጥታ እጦትም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ተፅዕኖ ፈጥረዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ቀጣይ ዕቅዳችሁ ምንድነው?

አቶ ፍፁም፡- በኢትዮጵያ በኅብረት ሥራ ማኅበር ባንክ መመሥረት እስካሁን አልተፈቀደም፡፡ በመጪው አምስት ዓመታት ያለን ዕቅድ ካፒታላችንን አምስት ቢሊዮን ብር የማድረስ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር የአገሪቷ ፖሊሲዎች ከተስተካከሉ የኅብረት ሥራ ባንክ መመሥረትና መካከለኛ ገቢ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የብድርና የቁጠባ አቅም በከተማ ለሚገኙ የላዳ ታክሲዎችና ማኅበሮች የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ከአስመጪዎች ጋር ተነጋግረናል፡፡ አባላትን የቤት ባለቤት ለማድረግ የቤት ግንባታ እያከናወንን ነው፡፡ አያት አካባቢ በ705 ካሬ ሜትር መሬት 12 ወለል ያለው የመኖሪያ ቤት እየገነባን ነው፡፡ ሕንፃው ከመኖሪያ ቤት ባሻገር የንግድ ሱቆች ያሉት ሲሆን፣ 300 ሚሊዮን ብር ድረስ ወጪ ይጠይቃል፡፡ ግንባታው ተጀምሮ ሦስተኛ ወለል ላይ የደረሰ ሲሆን፣ በሁለት ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይገመታል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...

‹‹የኤድስ በሽታ ከ10 እስከ 24 ዕድሜ ክልል ባሉ ልጆች በሁለት እጥፍ እየጨመረ ነው›› ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ ኤድስ ዘርፍ...

የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት ከቦታ ቦታ ቢለያይም እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ አዲስ አበባም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዷ ናት፡፡ ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በአዲስ አበባ ጤና...

‹‹ለአዕምሮ ሕሙማን አስተማማኝ የመድኃኒት አቅርቦት እንዲኖር እንፈልጋለን››

ወ/ሮ እሌኒ ምሥጋናው ተወልደው ያደጉትና የመጀመርያና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በአዲስ አበባ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የመጀመርያ፣ በሶሲዮሎጂ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በሥራ...